Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የዘገየው የመንግሥት ዕርምጃ ያለሚዲያው ተሳትፎ የትም አይደርስም!

  ሰሞኑን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ በተሠራ ጥናት ላይ ያደረጉት ውይይት በቴሌቪዥን ለሕዝብ ዕይታ በቅቷል፡፡ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከልና በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር የቀረበው ዳጎስ ያለ ጥናት ዝርዝሩ በስፋት ባይገለጽም፣ ለውይይት የቀረበው ማብራሪያ ግን በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ያሉ አሳሳቢ ችግሮችን የዳሰሰ ነው፡፡ በጥናቱ በቀጥታ የተሳተፉት አስረጂዎች የችግሩን መጠን ያሳዩበት አገላለጽ፣ በእርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዳሉት መንግሥትን የሚያስደነግጥ ነው፡፡ ችግሮችን መሬት ላይ ወርዶ ማየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበረም ያመላከተ ነው፡፡ ሚዲያው በዚህ ረገድ ሊያበረክተው የሚገባውን አስተዋጽኦ ያሳየ ነው፡፡ ሚዲያው በሕገ መንግሥቱ የሠፈረለት ነፃነት ይከበር፡፡  

  ጥናቱ በስፋት የተመለከታቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መሬት፣ ኢንቨስትመንት፣ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ ፍትሕ፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት፣ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንና የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ናቸው፡፡ በእነዚህ ከላይ በተገለጹት ዘርፎች ውስጥ የብቃትና የሥነ ምግባር ችግር፣ ሙስና፣ የአመራሮችና የሠራተኞች የአገልጋይነት መንፈስ ደካማ መሆን፣ የሕዝብ ቅሬታ አለመደመጥ፣ የተንዛዛ ስብሰባ፣ የማስፈጸሚያ ደንቦችና መመርያዎች አለመኖር ወይም በአስፈጻሚዎችና በፈጻሚዎች አለመታወቅ፣ የአመራሮችና የታችኛው ሠራተኛ አለመናበብ፣ ወዘተ. በስፋት ተተንትነዋል፡፡ ችግሩ ከመግዘፉ አንፃር በመንግሥት ከፍተኛ አስፈጻሚ አካላት ተገቢው ዕርምጃ እንዲወሰድም ጥሪ ቀርቧል፡፡ መንግሥት የሰማውን በልቡ አሳድሮ ለተግባራዊነቱ ካልተነሳ አደጋው የከፋ ነው፡፡ ሕገወጥነት በጊዜ ካልተገታ በኋላ አዳጋች ይሆናል፡፡ ሚዲያውም በሙሉ ኃይሉ እንዲገባበት ይደረግ፡፡

  በመሬት ላይ የታየው ችግር በራሱ ተነጥሎ እንኳ ሲታይ የከፋና የመረረ እንደሆነ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ መሬት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆኖ ደላላ የነገሠበት ሥርዓት ተፈጥሯል፡፡ በኔትወርክ የተደራጁ ኃይሎች የመሬት አቅርቦትና ፍትሐዊ ሥርጭትን በማዛበት፣ በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክልሎች ደላላ የሚፈነጭበት ሕገወጥ አሠራር ሰፍኗል ሲባል ከመንግሥት በላይ ማን ይደንግጥ? ከመሬት በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ሲገባ የመልካም አስተዳደር ጠንቅ የሆኑ አሠራሮችና የከፉ ሙስናዎች እየተፈጸሙ ነው፡፡ የሕዝብ ቅሬታዎችና ስሞታዎች አድማጭ በማጣታቸውና በአገልጋይነት መንፈስ ለአገራቸው የሚሠሩ ንፁኃን ዜጎች በመገፋታቸው፣ በጥቅማ ጥቅምና በብሔር ግንኙነት የተደራጁ ኃይሎች አገር እያጠፉ ነው፡፡ አሁን የችግሩ ምንጭ በግልጽ ከተነገረ ወደ መፍትሔው ነው ማማተር የሚሻለው፡፡ የሚዲያው ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሲረጋገጥ ለመፍትሔ የሚረዱ ግብዓቶች ይገኛሉ፡፡

  በውይይቱ ወቅት ከአጥኚዎቹ ቡድን ተወካይ እንደተሰማው፣ በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥታዊ ተቋማት ከታች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ ተብጠርጥረው ይፈተሹ፡፡ በየደረጃው ባሉ ተቋማት ውስጥ ጥፋት በመፈጸም ላይ የሚገኙ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ተገቢው ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰድ፡፡ የግሉም ሆነ የፐብሊክ ሚዲያው በነፃነት ሥራውን እንዲያከናውንና ተፅዕኖ እንዲፈጥር በሕገ መንግሥቱ የተሰጠው ዋስትና ተግባራዊ ይደረግ፡፡ ሕዝቡ በአገሩ ጉዳይ ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖረው ዕድሉ ይሰጠው፡፡ አገር ያሰለቸውና የተንዛዛው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስብሰባ ሥርዓት ይኑረው፡፡ ጥብቅ መመርያ ይውጣለት፡፡ ስብሰባና ሥልጠና ላይ ናቸው እየተባለ በሕዝብ ላይ መቀለድ ይቁም፡፡ ሚዲያውም እግር በእግር እየተከታተለ እንዲያጋልጥ ሕጋዊ ጥበቃ ይደረግለት፡፡  

  ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አንፃር በውይይቱ ላይ እንደተነሳው፣ እንደ ሰደድ እሳት በመቀጣጠል ላይ ያለውን አደገኛ አዝማሚያ ለማስቆም በጊዜያዊነት በዘመቻ መረባረብ ቢያስፈልግም፣ ለዘለቄታው ግን ተቋማዊ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስ ይመረጣል፡፡ አሁን ግን የችግሩን መሠረታዊ ምክንያት ነቅሶ በማውጣት ምሕረት የለሽ ሕጋዊ ዕርምጃ ካልተወሰደ ልፋቱ ሁሉ ቀልድ ይሆናል፡፡ ለዚህም በፅናት የሚቆሙ አገር ወዳድ ዜጎችን በልበ ሙሉነት በማሳተፍ፣ በኔትወርክ የተደራጁ ኃይሎችን ሴራ መበጣጠስ ጊዜው የማይሰጠው ተግባር መሆን አለበት፡፡ የችግሩ መጠን በውይይቱ ወቅት ከተነገረውም በላይ ስለሆነ ጊዜ ማባከን አያስፈልግም፡፡ ሚዲያውም የተዘጋጉ በሮች ተከፍተውለት በነፃነት ያጋልጥ፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡   

  በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉና ለሕግ የማይገዙ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚባለው መርህ የማይገባቸው፣ በአገር ሀብት እንደፈለጉ መፈንጨት መብታቸው የሚመስላቸው፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጨፈልቁ፣ ከአገር ይልቅ የራሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ፣ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይልቅ አምባገነናዊ ሥርዓት ለመፍጠር የሚፍጨረጨሩ፣ ወዘተ. በየቦታው ፈልተዋል፡፡ የእነሱ ጋሻ ጃግሬ የሆኑ አድርባዮችና አስመሳዮች በየተቋማቱ ተሰግስገው አገር እያጠፉ ነው፡፡ በስመ ድርጅት አባልነትና በመንደር ልጅነት የተሰባሰቡት እነዚህ ኃይሎች ሥርዓቱን ለደላላ አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ሕገወጥነት እንዲሰፍን ምኅዳሩን አመቻችተዋል፡፡ በመጀመሪያ የእነዚህን ከንቱዎች የቡድን ኔትወርክ መበጣጠስ ነው መቅደም ያለበት፡፡ በፍጥነት እነዚህ ኃይሎች በሚዲያው ሥራ ጣልቃ በመግባት፣ በማስፈራራት፣ በማንገላታት፣ በማሰርና በመቅጣት የሚዲያውን ነፃነት እያጠፉ ነው፡፡ አሁን ግን ርብርቡ ይህንን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ይሁን፡፡

  በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ እንዳልሆነ ማሳያ የሆነው አዲሱ ጥናት ከመውጣቱ በፊትም፣ ይኼ ጥልቅ ችግር ትኩረት እንዲሰጠው በተደጋጋሚ በዚህ ጋዜጣ ብዙ ተብሏል፡፡ ሕዝብ መንግሥት አለ ወይ? ፍትሕን በገንዘብ ለምን እንድገዛ እገደዳለሁ? መሬት በወረራ ቅርጫ ሲደረግ ለምን ዝም ይባላል? ሕገወጦች ከሕግ በላይ ሲሆኑ ለምን አይጠየቁም? በተሳሳቱ ሪፖርቶች እስከ መቼ ይቀለዳል? የፍትሕ ሥርዓቱ ችግሮች ለምን አይታዩም? የግብርና የታክስ ሥርዓቱ ፍትሐዊ እንዲሆን ዜጎች ያለአድልኦ የታክስ መረቡ ውስጥ ለምን አይገቡም? የጉምሩክ ኬላዎች አሠራር ለምን አይፈተሽም? ወዘተ. በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በወቅቱ የደነገጠም የተገረመም አልነበረም፡፡ ይልቁንም አንዳንዶቹ መንግሥታዊ ተቋማት ስማችን ለምን ተነሳ እያሉ በፈረደበት ሕግ ስም ያስፈራራሉ፡፡ አሁንስ? በቃ መባል አለበት፡፡

  መንግሥት በቁርጠኝነት ርብርብ በማድረግ ችግሩን የማስወገድ ተነሳሽነት ካለው፣ የሚዲያውን በነፃነት የመሥራት ሕገ መንግሥታዊ መብት ያክብር፣ ያስከብር፡፡ ሚዲያው በገለልተኝነት ሥራውን እንዲያከናውን ጣልቃ እንዳይገባበትና እንዳይዋከብ ይደረግ፡፡ በየሥርቻው ያሉ ‘የሹም ዶሮዎች’ ሚዲያውን መረጃ ከመከልከል አልፈው እያስፈራሩት ስለሆነ መንግሥት ያስታግሳቸው፡፡ ሚዲያው በነፃነትና በገለልተኝነት መርህ ኃላፊነቱን እንዲወጣና እገዛ እንዲያደርግ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን በተግባር ያሳይ፡፡ በሕዝቡ ውስጥ እምነት የሚፈጥር እንቅስቃሴ መጀመር የሚቻለው በብሔር፣ በዝምድና፣ በጥቅማ ጥቅምና በመሳሰሉት በኔትወርክ የተሳሰሩ ኃይሎችን ሴራ መበጣጠስ ሲቻል ነው፡፡ ይህ የሚሳካው ደግሞ የምርመራ ጋዜጠኝነት በተግባር ሥራ ላይ ሲውል ብቻ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የተለመደውንና አሰልቺውን ‘የሕዝብ ክንፍ’ አደረጃጀት እያሉ መንገታገት የሕዝብን ጥላቻ እንጂ አመኔታ አያመጣም፡፡ አሰልቺዎቹ አካሄዶች አገር የሚያጠፉ ከሆነ ለምልዓተ ሕዝቡ ተሳትፎ ዕድሉ ይመቻች፡፡ የሚዲያው ሕገ መንግሥታዊ ነፃነት ይከበር፡፡ ይህ ተግባራዊ ካልተደረገ ልፋቱ ከንቱ ይሆናል፡፡ የዘገየው የመንግሥት ዕርምጃ ያለሚዲያው ንቁ ተሳትፎ የትም አይደርስም!              

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  የትጥቅ  መፍታት ሒደትና የሰላም እንቅፋቶች

  የትግራይ ተራሮች ከጦር መሣሪያ ጩኸት የተገላገሉ ይመስላል፡፡ በየምሽጉ አድፍጠው...

  በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

  ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በክልሎችም ሊቋቋም ነው በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ...

  የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

  የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...