Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊነፃ ቀበሌ

ነፃ ቀበሌ

ቀን:

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ወደ ግምብቹ ወረዳ ለመጓዝ አዳማ ላይ የተሰባሰብነው ማልደን ነው፡፡ አዲሱን የቀለበት መንገድ ተያያዝነው፡፡ ከፊታችን 90 ኪሎ ሜትር ይጠብቀናል፡፡

ቢሾፍቱ ከተማን መሀል ለመሀል ቆርጠን ባቦ ጋያ ደረስን፡፡ ከዛም ወደ ወረዳው የሚዘልቀውን ቀጥ ያለ የአፈርና የጠጠር መንገድ ይዘን ወደ ውስጥ ገባን፡፡ አቧራው አውቶብስ ውስጥ ገብቶ ጢም አለ፡፡ እኩሉ አፉንና አፍንጫውን በጨርቅ ቢጤ ሲሸፍን ሌላው በኮፍያው መከላከል ጀመረ፡፡ ጠጠርማው መንገድ ደግሞ ተሳፋሪውን በተቀመጠበት ያርገፈግፈው ነበር፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን በግራና በቀኝ ባሉት የእርሻ ማሳዎች ቀልባችን መሳቡ አልቀረም፡፡ ሁሉም ፊቱን በየመስኮቱ አስጠግቶ የለመለመውን እርሻ በዓይኑ ማማተር ጀመረ፡፡ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የተልባና የሽምብራው እርሻ አካባቢውን አረንጓዴ አልብሶታል፡፡ ይህ የአቧራውንና የማርገፍገፉን ነገር እንድንረሳ አድርጎናል፡፡

- Advertisement -

በምንሄድበት ቀበሌ አንድ አርሶ አደር የአካባቢው ነዋሪ ሁሉ ይጠቅመኛል፣ ይበጀኛል ያለውን ‹‹እኔ አልቀበልም አሻፈረኝ›› ይላል፡፡ በብዙ መልኩ ለማስረዳትና ለማግባባት ቢሞከርም አርሶ አደሩ እሺ አላለም፡፡

ቀደም ሲል የአካባቢው ነዋሪ ሜዳ ላይ ነበር የሚፀዳዳው፡፡ ይህ ከፍተኛ የጤና ችግር እያስከተለ በመሆኑ፣ የአካባቢው ነዋሪ በቅጥር ግቢው ጉድጓድ እያስቆፈረ መፀዳጃ ቤት እንዲሠራ ማድረግ ተጀመረ፡፡ አርሶ አደሩ ይህን ነበር አልቀበልም ያለው፡፡ በጤናው ላይ ለመምከርና የአካባቢውን ጤና ለመጠበቅ በቡድን የተደራጀው የአካባቢው ነዋሪ መላ ያለው አርሶ አደሩና ቤተሰቡ የሚፀዳዱበትን ቦታ የዘወትር መሰብሰቢያ ማድረግን ነበር፡፡ በመጨረሻ አርሶ አደሩ በዚህ ሊረታ መቻሉን የቀበሌው አስተዳደር ኃላፊዎች ገልጸውልናል፡፡

አንድ የጤና ባለሙያ ጉዞው የሚደረው ‹‹ከአር ነፃ›› ወደ ሆነ ቀበሌ መሆኑን ተናገሩ፡፡ ምን ማለት ነው? የቃላት አጠቃቀሙስ ተገቢ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለባለሙያው ሰነዘርን፡፡ የባለሙያው መልስ ‹‹ልክ ነው መጠሪያው፣ ኦፕን ዲፌክሽን ፍሪ ነው፡፡ የሚያመለክተውም ክፍት ቦታ ወይም ሜዳ ላይ መፀዳዳትን ነው፡፡ እኛ ግን ይህን ላለማበረታታት፣ ኅብረተሰቡም ጭርስኑ እንዲጠየፈውና ከአድራጎቱም እንዲገታ በማሰብ አር የሚለውን ቃል መጠቀም ግድ ሆነ፤›› የሚል ነበር፡፡

ትንሽ እንደተጓዝን ከመኪና መንገድ ዳር ‹‹ከአር ነፃ የሆነ ቀበሌ›› የሚል ጠቋሚ ሰሌዳ (ታፔላ) ተመለከትን፡፡ ወበሪማንሱር ቀበሌ ክልል ገባን፡፡ ከሁለት ሺሕ በላይ የሚሆን ሕዝብ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ 1,127 ወንዶቸ ሲሆኑ፣ የቀሩት ሴቶ ናቸው፡፡ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና ጤና ኬላ አለው፡፡ ከአውቶቡስ እንደወረድን በቀጥታ ያመራነው ወደ አርሶ አደሮች መኖሪያ ቤቶች ነበር፡፡ አንዳንድ አባወራዎች ባለሦስት፣ ከፊሉ አባወራ ደግሞ እንደየአቅሙ ሁለት ክፍሎች ያሏቸው ቤቶች አላቸው፡፡

የየቤቶቹ ስፋትና ጥበት ይለያይ እንጂ አጥር ግቢያቸው ጭምር ንፁህ ናቸው፡፡ ከየቤቶቹ በስተጀርባ ኩሽናዎች፣ የከብት ማደሪያዎች (በረቶች) እና መፀዳጃ ቤቶች ራቅ ራቅ ብለው ተሠርተዋል፡፡ በእያንዳንዱ መፀዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ ውኃ የያዘ ጀሪካን ተሰቅሏል፡፡ ጀሪካኑ መክፈቻና መዝጊያ ቧንቧ የተበጀለት ነው፡፡

ብዙዎቹን ነዋሪዎች አነጋግረናቸዋል፡፡ ካነጋገርናቸውም መካከል ወ/ሮ ብርቱካን ከተማ ይገኙበታል፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ጥልቀት ያለው የመፀዳጃ ጉድጓድ ማስቆፈራቸውን ገልጸውልናል፡፡ በፊት በየሜዳው ይፀዳዱ፣ ይህም ለከፋ በሽታ ያጋልጣቸው እንደነበር በማስታወስ በመፀዳጃ ቤት መጠቀም ከጀመሩ ሦስት ዓመታት መቆጠራቸውን ይናገራሉ፡፡

አቶ ደምሴ ደገፌ የ86 ዓመት የዕድሜ ባፀጋ ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉትና የተዳሩትም በዚሁ ቀበሌ ነው፡፡ 11 ልጆች አላቸው፡፡ የልጅ ልጅም አይተዋል፡፡ ቀደም ሲል ሰዎች ሜዳ ላይ ይፀዳዱ ስለነበር አካባቢው በጣም ቆሻሻ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ መጥፎ ጠረን እየገባ እጅግ ይቸገሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ አሁን ግን ነገሮች መለዋወጣቸውንና ሕፃናት እንኳ ሜዳ ላይ እንደማይፀዳዱ ያስረዳሉ፡፡

ወ/ሪት አልማዝ አምበሶ የቀበሌው ጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኛ ናት፡፡ በዚሁ ቀበሌ ተመድባ መሥራት ከጀመረች ሰባት ዓመት ሆኗታል፡፡ ሥራም እንደጀመረች ማኅበረሰቡ ስለግልና አካባቢ ንጽህና አጠባበቅ የሚያውቀው ነገር እምብዛም ነበር ትላለች፡፡

በቂ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ከተሠራ በኋላ ማኅበረሰቡን በማደራጀት የመፀዳጃ ጉድጓድ እንዲያዘጋጁ ለማድረግ መቻሉን ትገልጻለች፡፡ በየእምነት ተቋማት፣ በገበያ ሥፍራና በአጠቃላይ ሰው በሚዘዋወርባቸው አካባቢዎችም የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች እንደተሠሩና ይህ ዓይነቱም ሁኔታ ቀበሌው ከእዳሪ ነፃ ለመሆን እንዳስቻለው የኤክስቴንሽን ሠራተኛዋ ታስረዳለች፡፡

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ካሳዬና አቶ አበበ ማሞ የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊን ስለዚህ ጉዳይ ጠይቀናቸው ነበር፡፡ በወረዳው 33 ቀበሌዎች እንዳሉና ከእነዚህም መካከል ሰባቱ ከመንገድ ላይ እዳሪ ነፃ እንደሆኑ ነግረውናል፡፡ የቀሩትን ቀበሌዎችና መንደሮች ክፍት አካባቢዎች ከእዳሪ የፀዱ ለማድረግ ሁሉ አቀፍ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል ኃላፊዎቹ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...