Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየባህልና ቱሪዝም ከተግባር ያልተገናኘ ዕቅድ

የባህልና ቱሪዝም ከተግባር ያልተገናኘ ዕቅድ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተያዙ ግቦች ላይ የመንግሥትና የግል ባለድርሻ አካላት ተወያይተዋል፡፡

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ የአምስት ዓመት ዕቅዱ ከ90 በመቶ በላይ ተሳክቷል፡፡ ስኬት ተገኝቶባቸዋል ከተባሉ ዘርፎች አንዱ በአገሪቱ ከሚነገሩ ቋንቋዎች ለአምስቱ ፕሮፋይል መዘጋጀቱና ሰባት ቅርሶች በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ አቅዶ ያስመዘገበው ሁለቱን ማለትም የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ ምድርና የመስቀል ክብረ በዓልን ብቻ ነው፡፡ በቱሪዝም ረገድ አገር አቀፍ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ካውንስል፣ የቱሪዝም ቦድርና የቱሪዝም ድርጅት ከመቋቋማቸው ባሻገር፣ 60 በመቶ ፓርኮች ለቱሪዝም ምቹ መደረጋቸው ተጠቅሷል፡፡ ቢሆንም በተወሰኑ ፓርኮች ሕገወጥ ተግባሮችን ማስቆም አልተቻለም፡፡

ሪፖርቱ እንደ ክፍተት ካስቀመጣቸው ውስጥ በፌደራልና በክልል ደረጃ ያሉ ባለድርሻ ተቋሞችን አስተሳስሮ መሥራት አለመቻሉ፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለትና የሠራተኞች ክህሎት እጥረት ተጠቅሰዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርቱ ይህን ቢልም አስተያየታቸውን ከሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች መካከል ‹‹ከ90 በመቶ በላይ ዕቅዱ ተሳክቷል›› በሚለው ድምዳሜ እንደማይስማሙ የገለጹ ነበሩ፡፡ ለችግሮቻቸው መፍትሔ ያልተገኘላቸው ፓርኮች መኖራቸው፤ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚያሻ ያመለክታል ተብሏል፡፡

የአገሪቱን ባህልና ቅርስ በማስተዋወቅ ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲደግላቸውና መረጃ በሚፈልጉበት ጊዜ በአፋጣኝ እንዲያገኙ ያሳሰቡም ነበሩ፡፡ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ተረቆ በተግባር ሳይውል የዘገየው የፊልም ፖሊሲ ጉዳይ ነው፡፡ ዘርፉ ለአገሪቱ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከግምት በማስገባት፣ ሙያተኞች ያለምንም ችግር ግብአት የሚያገኙበትና ሥራዎቻቸው በአግባቡ የሚሰራጩበት መንገድ እንዲመቻች ተጠይቋል፡፡

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መነሻውን ያደረገው ኢትዮጵያ ካላት ሀብት አንፃር በቱሪስት ቁጥርና ከዘርፉ በሚገኘው ገቢ አነስተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷን በመግለጽ ነው፡፡

በ2017 ዓ.ም. አገሪቱን በአፍሪካ ከሚጐበኙ አምስት አገሮች አንዷ ለማድረግ ያለመው ዕቅዱ፣ ከያዛቸው ግቦች መካከል፣ የውጭ ጐብኝዎችን ከ2 ሚሊዮን በላይ ማድረስ ይገኝበታል፡፡ ዕቅዱ የአገር ውስጥ ጐብኝዎችን 15 ሚሊዮን ማድረስና ዘርፉ ለአገሪቱ ጠቅላላ ምርት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ወደ አምስት በመቶ ማሳደግን ያካትታል፡፡

ሕገወጥ የቅርስ ዝውውር ድርጊትን መቶ በመቶ መቀነስ፣ መቶ ከአገር የወጡ ቅርሶችን ማስመለስ፣ መቶ በመቶ የብሔር ብሔረሰቦችን ቋንቋ መመዝገብ፣ በጥብቅ ቦታዎች የሚካሄዱ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን 80 በመቶ መቀነስም ይገኙበታል፡፡

በዕቅዱ በአምስት ዓመት ይሳካሉ ከተባሉት ግቦች፣ በ2008 ዓ.ም. የሚካሄዱት ክንውኖች ሰፊ ቦታ የተሰጣቸው ይመስላል፡፡ በያዝነው ዓመት የውጭ ቱሪስት ቁጥርን ከ1 ሚሊዮን በላይ፣ የአገር ውስጥ ጐብኝን 6 ሚሊዮን የማድረስና አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ወደ 3.25 በመቶ የማሳደግ ዕቅድ ተይዟል፡፡ ሕገወጥ የቅርስ ዝውውርን 85 በመቶ መቀነስ፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ቋንቋ 70 በመቶ መመዝገብ፣ ባህላዊ እሴቶችን ማጥናትና ማስተዋወቅ፣ በርካታ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለሕዝብ ማድረስ በዚህ ዓመት በዕቅዱ የተያዙ ግቦች ናቸው፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡ የውይይቱ ተካፋዮች በበኩላቸው የቱሪስቶችና ወደ አገር ውስጥ ይመለሳሉ የተባሉ ቅርሶች ቁጥር የተጋነነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የውጭ ቱሪስቶችን ለመሳብ ምን ያህል ማስተዋወቂያ ተሠርቷል? የመሠረተ ልማት ዝርጋታው ምን ያህል የተሟላ ነው? የሚል ጥያቄ ያነሱም ነበሩ፡፡ በተለይም በያዝነው ዓመት ከግብ ይደርሳሉ የተባሉ ዕቅዶች ሰፊ በመሆናቸው ተፈጻሚነታቸው እንዲታሰብበት ሲሉ አስተያየት የሰጡ ነበሩ፡፡

ከዕቅዶቹ መካከል ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳዮች መለየት እንዳለባቸውና በተለያዩ እርከኖች ያለው የመሥሪያ ቤቱ አሠራር እንዲሻሻልም ተጠይቋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከባለድርሻ ተቋሞች ጋር ያለው ትስስር እንዲጠናከርና የሚጀመሩ ክንውኖች በአፋጣኝ እንዲቋጩም ተብሏል፡፡

ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሪፖርትና የሁለተኛው ዕቅድ ላይ የተደረገው የግማሽ ቀን ውይይት በቂ እንዳልሆነና ሰፊ ጊዜ ሊሰጠው እንደሚገባ የተናገሩ አስተያየት ሰጪዎችም ነበሩ፡፡   

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብና ዓለም አቀፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው፣ የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከመጠን በላይ የተለጠጠ ነው ቢባልም ስኬት ተመዝግቦበታል ብለዋል፡፡ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጠው በማድረግ፣ ሕዝቡን በማስተባበር ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከግብ ማድረስ ይቻልም ብለዋል፡፡ በዘርፉ ያሉ የግልና የመንግሥት ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሳሰሩ መምጣታቸውም ዕቅዱን ለማሳካት እንደሚያግዝ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...