Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊ‹‹አሁንም አልማለሁ››

  ‹‹አሁንም አልማለሁ››

  ቀን:

  የአካባቢው ተወላጆች ዶክተር ይሏቸዋል፡፡ እሳቸው ግን የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ገና ባለመጨረሳቸው አጠራሩን ይቃወሙታል፡፡ ቢሆንም ግን በአካባቢው ማምጣት በቻሉት ለውጥ ኗሪው በአጠራሩ ፀንቷል፡፡ ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ወይም ዶ/ር ቦጌ ይሏቸዋል፡፡ በስማቸው ግጥም ይገጥማሉ፡፡ ዜማም ይቀኛሉ፡፡

  በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ወ/ሮ ቦጋለችን የተመለከተቻቸው መንፈሰ ጠንካራ እንደሆኑ ይገምታል፡፡ ቅልጥፍናቸውም ከወጣት ያልተናነሰ ነው፡፡ በከምባታ ዞን ዱራሜ ከተማ አካባቢ የተወለዱት ወ/ሮ ቦጋለች ቀደም ሲል በአካባቢያቸው ትምህርት ከቅንጦት ይቆጠር እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ወላጆቻቸው በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ ለትምህርት ይሰጥ በነበረው ዝቅተኛ ግምት ትምህርት ቤት አልተላኩም፡፡ በአቅራቢያ ትምህርት ቤት ማግኘትም እንዲሁ ችግር ነበር፡፡ ነገር ግን አዲስ ነገር መሞከር፤ ሥልጡን መሆን ለሚያስደስታቸው ወ/ሮ ቦጋለች ይህ ችግር ሆኖ ከመማር አላገዳቸውም፡፡ የመማር ምኞት ያደረባቸው ከከተማ እየሔዱ ይጠይቋቸው የነበሩት መምህር አጎታቸው ለነገሮች የነበራቸው ዕይታን እንዲሁም ጽዱ አለባበስ በመመልከት ነበር፡፡ ሁኔታቸውም ከትምህርት የመነጨ እንደሆነ በማሰብ ፊደል የመቁጠር ጉጉታቸው አየለ፡፡

   ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ትምህርት ቤት መሔድ ጀመሩ፡፡ ውኃ ለመቅዳት ወንዝ ሲወርዱ አልያም ለከብቶች ሳር ለማጨድ ራቅ ወዳለ አካባቢ ሲሄዱ ደብተራቸውን በጎን ደብቀው ይወጣሉ፡፡ ከወላጅ እናታቸው ጋር የነበራቸው ቁርኝትም ትምህርታቸውን በመላ እንዲከታተሉ አስችሏቸው ነበር፡፡ ‹‹ውጭ ወጥቼ ስቆይ የት ሄደች ይባላል፡፡ እናቴም ውኃ ልቀዳ አልያም ሳር ላጭድ እንደሄድኩኝ በመንገር እስከ ተወሰነ ድረስ በድብቅ እንድማር ረዳችኝ›› ሲሉ ፊደል ለመቁጠር የነበረውን ትግል ያስታውሳሉ፡፡

  ማኅበረሰብ ለትምህርት የነበረውን አመለካከት ሲገልጹም ‹‹ሴት ልጅ ፈጽሞ መማር አትችልም፡፡ ወንድም ቢሆን በአካባቢው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ የመማር ዕድሉ እጅግ የሳሳ ነው፡፡ በእኛ አካባቢ የነበረው ትምህርትም በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጥ ብቻ ነበር›› ይላሉ፡፡ ሴት መሆናቸው እና ከሃይማኖታቸው ውጪ በሆነ ተቋም ለመማር መሞከራቸው ከአባታቻው ጆሮ ቢገባ ከባድ ቅጣት ይኖረዋል፡፡ ‹‹ትምህርት የጀመርኩት እንደ አጎቴ ስልጡን ለመሆን እንጂ ጥቅሙን ተረድቼ አልነበረም፡፡ የኋላ ኋላ ግን ትምህርቱን ወደድኩኝ›› በማለት በትምህርት መመሰጣቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ለጥቂት ዓመታትም በድብቅ ሲማሩ ቢቆዩም ተደረሳባቸው፡፡

  አጋጣሚው ለወ/ሮ ቦጋለች  አስደንጋጭ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ መጻፍና ማንበብ ችለው ስለነበር የተፈራው አልደረሰም፡፡ ጎረቤቶቻቸውና የወ/ሮ ቦጋለችን ዝና ከሩቅ የሰሙ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ፣ ማመልከቻ፣ ደብዳቤ እንዲያነቡላቸውና እንዲጽፉላቸው ይመጡ ጀመር፡፡ አባትም በልጃቸው ኮሩ፡፡ ግን ወንድ ልጃቸው ቢሆንም ይበልጥ ደስተኛ እንደሚሆኑ በሁኔታቸው ይታወቅ ነበር፡፡

  ወ/ሮ ቦጋለች በትምህርት ጐበዝ ከሚባሉት ተርታ ነበሩ፡፡ ‹‹ለእኔ ትምህርት በጣም ቀላል ነበር፤›› ይላሉ፡፡ በትምህርት ቤቱ የሚማሩ ብቸኛ ሴት እንደነበሩም ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ መልኩ እስከ አራተኛ ክፍል ከዘለቁ በኋላ ትምህርት ቤቱ ከአራተኛ ክፍል በላይ ስለማያስተምር ችግር አጋጠማቸው፡፡ ወንዶች ጓደኞቻው ግን ቀጣይ ክፍሎችን በሌላ አካባቢ ለመማር ስንቅ ተቋጥሮላቸው ቤት ተከራይተው ይማሩ ጀመር፡፡ ወ/ሮ ቦጋለች ዕድሉን በሴትነታቸው ተነፈጉ፡፡ ዓመት ያህልም ቤት ውስጥ መቀመጥ ግድ ሆነባቸው፡፡ አጋጣሚው አስከፍቷቸው ስለነበር ቀን ከሌት ማዘን ያዙ፡፡

  በዚህ መካከል ሌላ ከተማ ይኖር የነበረ ዘመዳቸው ሊጠይቃቸው ይመጣል፡፡ አጋጣሚው ያቋረጡትን ትምህርት እንዲቀጥሉ አስቻላቸው፡፡ ሊጠይቋቸው የመጡ ዘመዶቻቸው ወ/ሮ ቦጋለችን አስከትለው ወደ ቀዬአቸው ተመለሱ፡፡ የአንደኛ ደረጃ  ትምህርታቸውን በዚህ መልኩ ካጠናቀቁ በኋላ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አዲስ አበባ መጡ፡፡ የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በእስራኤል አገር እስኮላር ሺፕ አግኝተው ማክሮ ባዬሎጂና ፊዚዮሎጂ አጠኑ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሙያቸው ጥቂት ካገለገሉ በኋላ ለድህረ ምረቃ ትምህርት አሜሪካ ሄዱ፡፡ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያና በሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች ለማስተማር ቻሉ፡፡

  ‹‹ብዙ ህልም ነበረኝ፡፡ አሁንም አልማለሁ›› የሚሉት ወይዘሮዋ የሕፃናት ሐኪም የመሆን ምኞት እንዲሁም ባደጉበት አካባቢ የነበሩ ኋላ ቀር አመለካከቶችን የመቀየር ፍላጎት ነበራቸው፡፡ አንደኛው ባይሳካላቸውም የማኅበረሰቡን አመለካት የመቀየር ህልማቸውን ግን ማሳካት ነበረባቸው፡፡

  ‹‹በገጠር የእናቶችንና የሴት ሕፃናትን ችግር እያየ አድጎ ሁኔታውን መለወጥ የማይፈልግ የለም፡፡ አስቸጋሪው ነገር በምንና እንዴት የሚለው ነው፡፡ ለውጥ ለማምጣት ወስኖ መነሳት ግን ትንሽ ይከብዳል፤›› የሚሉት ወ/ሮ ቦጋለች ለውጥ መፍጠር የሚያስችላቸውን እርምጃ አንድ ብለው ጀመሩ፡፡

  ‹‹የእኛ አትሌቶች ማራቶን ሲያሸንፉ አያለሁ፡፡ ለሩጫም ልዩ ፍቅር ነበረኝ፡፡  እ.ኤ.አ. በ1994 ላይፍ ኢዝ ፊዲንግ ኤቭሪ ዋን የተባለ ፕሮጀክት በካሊፎርኒያ የገቢ ማሰባሰቢያ ማራቶን መዘጋጀቱን ሰማሁ፡፡ እኔም አጋጣሚው ተጠቅሜ ገንዘብ ለማሰባሰብ ወሰንኩኝ፡፡ ማራቶን ሮጥኩኝ፡፡ 682 ዶላር ያህል ማሰባሰብም ቻልኩኝ›› ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡ ገንዘቡንም ከዚህ ቀደም ከየትምህርት ቤቱና ከየዩኒቨርሲቲዎች ያሰባሰቧቸው የነበሩ መጻሕፍቶችን ወደ ኢትዮጵያ ላኩ፡፡

  ይበልጥ መሥራት እንዲችሉም ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ከአካባቢያቸው በትምህርት ስኬታማ የነበሩት እሳቸው ብቻ ነበሩ፡፡ ሁኔታውን ሲገልጹም ‹‹ብርቅዬ ነበርኩ›› ይላሉ፡፡ ተመልሰው በመጡበት ጊዜም ጥቂት ሴቶች የመማር ዕድል ቢያጋጥማቸውም ከስድስተኛ ክፍል የዘለቁ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ‹‹አብዛኞቹ አቋርጠው ትዳር ይዘዋል፡፡ ወድቀው የቀሩም ብዙ ነበሩ›› ይላሉ፡፡ አጋጣሚውም የማኅበረሰቡን ሕይወት እንዴት መለወጥ ይቻላል የሚል ጥያቄያቸውን መለሰላቸው፡፡ ትምህርትን መሠረት በማድረግ የሴቶችን ሕይወት መለወጥ የሚል፡፡ አቅማቸውን አጠናክረው ለመመለስም ዳግም ወደ ካሊፎርኒያ አቀኑ፡፡

  እ.ኤ.አ. በ1995 ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሐሳባቸውን በተግባር ለመቀየር የሚያስቸላቸውን ሥራ ጀምረው እንደገና ተመለሱ፡፡ በቦስተን በተዘጋጀው ኦሎምፒክ በመሳተፍም ዳግመኛ ገንዘብ ሰበሰቡ፡፡ ከዚያ በኋላ ስድስት የሚሆኑ ማራቶኖች ላይ በመሳተፍ ገንዘብ አሰባስበዋል፡፡ 350,000 የሚሆኑ ያሰባሰቧቸውን መጻሕፍቶችም በሰበሰቡት ገንዘብ መላክ ቻሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣትም የሴቶች ግርዛትንና ሌሎች ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስቀረት ላይ የሚሠራውን ኬኤምጂ የተባለውን ድርጅት አቋቋሙ፡፡

  ‹‹ሥራችንን የጀመርነው በአካባቢው አይነኬ በተባሉ ነገሮች ነበር፡፡›› ይላሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የሴት ልጅ ግርዛት በአካባቢው ሥር የሰደደ ነበር፡፡ የግርዛቱ ሒደትም ‹‹ቆሻሻ ማንሳት›› ይባል ነበር፡፡ ‹‹አንዲት ልጅ ቀና ብላ ከሄደች፣ ይህችን ልጅ ውኃ አላፈሰስሽባትም እንዴ ነበር የሚሉት፤›› ይላሉ፡፡ በመሆኑም ስለ ጉዳዩ ቀጥታ ከመናገር ይልቅ ሽፋን ማግኘት ነበረባቸው፡  በወቅቱ በመላው አገሪቱ ሥጋት የነበረውን የኤችአይቪ ቫይረስ በሽታ ሽፋን በማድረግ ማኅበረሰቡ ውስጥ ገቡ፡፡

  ‹‹ኤችአይቪ ኤድስ የሁሉም ችግር ስለነበር ተቀባይነትን ማግኘት ከባድ አልነበረም፡፡ ሥርጭቱን ከሚያባብሱ ነገሮች አንዱም ግርዛት መሆኑን ማስተማር ጀመርን፡፡ በዚያም የማኅበረሰቡን እሺታ አገኘን›› ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡ አጋጣሚው በቀላሉ ማኅበረሰብ ውስጥ መግባት እንዲችሉ አስችሏቸዋል፡፡ በአራት ቀበሌዎች ላይ ያደረጉትን የኤችአይቪ ሥርጭት ጥናት ለማኅበረሰቡ ባቀረቡበት ወቅትም ከፍተኛ ንቅናቄ መፍጠር ችለዋል፡፡ አጋጣሚው በማኅበረሰብ ውይይት ላይ የሚሠራው በዩኤንዲፒ ፕሮጀክት እንዲካተቱ አስቻላቸው፡፡ በፕሮጀክቱ ከታቀፉ በኋላም የመጀመሪያውን የማኅበረሰብ ውይይት በአላባ በሚገኝ ገበያ ላይ አደረጉ፡፡ በፕሮጀክቱ ከታቀፉ ሌሎች ድርጅቶች መካከልም ኬኤምጂ የኤች አይቪ ኤድስና የማኅበረሰብ ውይይት ማኑዋል ዝግጅት ላይ ሙከራ እንዲያደርግ ተመረጠ፡፡

  ‹‹አጋጣሚው የበለጠ ተሰሚነት እንድናገኝ ክፍተት ፈጠረልን፡፡ ለውጥ ማስመዝገብም ቻልን፡፡ ያልተገረዘች ወጣትም ተዳረች፡፡ ብዙዎችን አስገርሞ ነበር፤›› በማለት በወቅቱ ሙሽራዋን ለማየት ከ100,000 የሚበልጡ ሰዎች አደባባይ ወጥተው እንደ ትንግርት መመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ ለጋብቻው እንዴት ዕውቅና ተሰጠ? የሚል ጥያቄም ተነስቶ ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ግን እውነታውን ተቀብለው መኖር ጀመሩ፡፡ ዛሬ ላይ በከምባታ አካባቢ ያልተገረዙ ልጃገረዶችን ማየት ተለምዷል፡፡

   ከሴት ልጅ ግርዛት ጎን ለጎንም በአካባቢው ከሌላው ኅብረተሰብ ተገልለው በጭቆና የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማቀራረብ ረገድም ድርጅታቸው ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ‘ፉጋ’ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ከሌላው ተለይተው የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሌላው እኩል የማይታዩ፣ የራሳቸው የሆነ የሚኖሩበት የተወሰነ ቦታ የሌላቸው ነበሩ፡፡ ‹‹ፉጋዎች ከሰው መቀላቀል አይችሉም፡፡ ብዙ ጭቆና ይደርስባቸው ነበር፡፡ እዚህ ላይ ለመሥራት ያነሳሳኝም ልጅ ሆኜ አያቸው የነበሩ ነገሮች ናቸው›› በማለት የፉጋዎች እኩልነት ላይ ለመሥራት ያነሳሳቸውን ጉዳይ ይገልጻሉ፡፡

  ሁለቱን የኅብረተሰብ ክፍሎች በማቀራረብም በመካከላቸው ስለነበሩ ችግሮችና ልዩነት እንዲወያዩና እንዲቀራረቡ ተደርጓል፡፡ ፉጋ የሚለው አንቋሻሽ ስያሜም እጀ ወርቆች በሚል እንዲተካ ሆኗል፡፡ ተቀላቅለው መኖር እንዲችሉም ተደርጓል፡፡

  ወ/ሮ ቦጋለች በሥራዎቻቸው ከአሥር የሚበልጡ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ተቀዳጅተዋል፡፡ ከሽልማቶታቸው መካከልም በ2013 በመሪነትና ዘላቂ ልማት በማራመድ በሚል ከቤልጂየም ንጉሥ ያገኙት ሽልማት፣ እንዲሁም በ2011 በሰብዓዊ መብትና ለሴቶች መብት አዎንታዊ ተፅዕኖ በመፍጠር በሚል ከፈረንሳይ መንግሥት ያገኟቸው ሽልማቶች ይጠቀሳሉ፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img