Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ማገዶአችንን አታስጨርሱን!

ሰላም! ሰላም! “እንኳን በምድር በሰማይ ሳይቀር ምን ሰላም አለ?” አለኝ የባሻዬ ልጅ። የምሁር ነገር አለ አይደል። የሰማዩን ሥርዓትና አየር ካልተቹና ካልዘረጠጡ ምሁር የሆኑ የማይመስላቸው ደግሞ ይብሳሉ እኮ። እሱስ አባቱ ባሻዬ መሆናቸው በጀው፣ ብዙ አይደፍርም። ‘ምኑን?’ ሰማዩን ነዋ! ዘመኑ የፆታና የዘር ድርድር ስላየለበት እንጂ የአየር በአየር ጥቃቱ አይብስም እንዴ? ይኼው ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት መሀል ሲናይ በረሃ የሩሲያው አውሮፕላን ብው ብሎ ፈንድቶ ወደቀላችሁ። የባሻዬም ልጅ ይኼን ይዞ ‘እንኳን በምድር በሰማይስ ምን ሰላም አለ?’ ያለኝም ለዚያ ሳይሆን አይቀርም። መቼም መላዕክት መሀል አሸባሪ ሰርጎ አይገባም። እኛስ መሀል ቢሆን? የሚከፈት በር ሳይኖር የሚያንኳኳ ይመጣብናል እንዴ? አስታጣቂ ሳይኖር ታጣቂ እንዴት እንደሚደራጅስ አጣርታችኋል? እኛማ ምኑን እናጣራለን፣ እንጣራለን እንጂ!

እንዲህ እያሰብኩ ታዲያ ቤቴ አረፍ ብያለሁ። አይዟችሁ ምን ሆኖ ነው ብላችሁ አትሸማቀቁ። እንኳን ለቤት ለመኖር ዋጋ እየከፈልን መስሎኝ። የምሬን  ነው። ቆም ብለን ካሰብነው (እንኳን መቆሚያ መቀመጫ ጠፍቶ እንጂ) ምን ነፃ አለ? አየርም ቢሆን እኮ ሳይበከል ነው። አይደለም እንዴ? ስለኦክስጂንና ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ነው የማወራው ይቅርታ! ታዲያ እሱም ይኼው እየተከበብን በአየር ጠባይ መዛባት ምክንያት ለምንከፍለው ዋጋ ካሳ ክፈሉን ሙግት የጀመርነውስ መቼ በነፃ ነው? ተውትና ሌላውን መሪዎቻችን ስንት አጣዳፊ ሥራ፣ እኛንና እኛን ብቻ የሚመለከቱ ችግሮቻችን መፍታት ትተው ወደ ‘ኢንዱስትሪያል’ አገሮችን ‘ካሳዋን በዶላር ትፏት’ ሊሉ ሲሄዱ የሚቃጠለውን የአውሮፕላን ነዳጅ አስቡት። ሲሪየስ! ሒሳብ ሒሳብ ነው። እያሰቡና እያስተዋሉ ማደግ እንጂ፣ ዝም ብሎ ማደግ ብቻውን ድሮም አቅቶን ነበር ግን? ነገሩን ማለቴ ነው። ‘ስንቱ የመንግሥት በጀት እንዳይሆን እንዳይሆን በሙስና ሲመዘበር እያየን አንተ የአውሮፕላን ነዳጅ ሒሳብ ታሰላለህ?’ ስትሉ ሰማሁ? ይኼ መቼም ዲቪ ሳይሞላ ቀኑ ያለፈበት ሰው ድምፅ ነው!

ያለነገር ምድርን ማሰስ ትቼ ነገረ ሰማይ ላይ እንዳልተንጠላጠልኩ መቼም ይገባችኋል። “ያደለው በሰው ላይ እየተንጠላጠለ ‘ኢንቨስተር’፣ ‘ኤክስፖርተር’ ይሆናል አንተ ጉም ትዘግናለህ፤” ያሉኝ ጎረቤት አርፎ ሞቶ ከቀብር ስንመለስ ባሻዬ ናቸው። እኔማ እንዲያው የነገሮች ተጠጋጊ አይነካኬ ባህሪ እየደነቀኝ ነበር ጉም መዝገኔ። እዚህ ብርቁን አልለምደው ብለን በየሜዳው፣ በየገደሉ፣ በየቀለበት መንገዱ መኪና በችርቻሮ ሲጨርሰን፣ እዚያ የሰው ልጅ ከፈጠረው ፈጠራ ሁሉ እንደእሱ ያለ የለም የሚሉት አውሮፕላን በየበረሃው፣ በየተራራው፣ በየውቅያኖሱ እየፈነዳና እየተሰወረ በጅምላ ይቀጫቸዋል። አጃኢብ የዓለም ነገር! እንኳንም የግል አውሮፕላን ማሻሻጥና ማከራየት ድለላ ሥራዬ ውስጥ የለ ብያለሁ። ምን አባቴ ልበል ታዲያ? ይኼው ‘ቪትስ’ አገሩን ሞልታ ተሰለቸች ተብላ ገበያዋ ቀዝቅዞ እጄ ላይ ያሉትን መሸጥ አቅቶኛል ስላችሁ። ማንጠግቦሽን ስላችሁ! እኔ ምን አውቃለሁ? ያው ማላከክ እንጂ ግለ ሒስ መቺ እናውቅና? እንደለመደብን መኪናው ላይ አላከክነው።

‘ሲኖትራክ’፣ ‘እብዱ ትራክ’ ተብሎላችኋል። አንዳነዶች ደግሞ ‘ሲኖጭራቅ’ ይሉታል፡፡ ደግሞ ለስያሜው በሽ በሽ ነው፡፡ ትናንት አንዱ ከኋላዬ ጨዋ እንዳሳደገው በእርጋታ እየተጓዘ ቆይቶ ድንገት፣ “ያዘው ያዘው! ከአማኑኤል አምልጦ ነው ያዘው ያዘው!” ብሎ ቀወጠው። እኔ ከአሁን አሁን እንዲያ በማስጠንቀቂያ የተጮኸለት አዕምሮ ታማሚ እርግብግቢቴን ብሎ አርገበገበኝ ብዬ “የታለ የታለ?” ስለው “አታየውም?” ብሎ ምን ይጠቁመኛል ‘ሲኖትራክ!’ ከኋላው ደግሞ ‘ቪትዝ’ ካልቀደምኩ ትላለች። “ይህቺም እስኪመሰከርባት ነው፤” ይላል ከኋላዬ። ምን እላለሁ? ዝም ነዋ። ‘ፍትሕ የለም!’ ሲባል ‘የአፈጻጸም ችግር ካልሆነ ሕግና የሕግ አስከባሪ እጥረት የለብንም’ በሚባልበት አገር፣ ‘ዴሞክራሲን ሕዝብ የማይደርስበት ቦታ አስቀምጡት’ ተብሏል ወይ? ስንል ‘የማይክራፎኑ ችግር ነው እንጂ ከአፋችን እንዲህ ያለ ነገር አይወጣም’ ሲሉን። እኛም፣ ‘የማይክራፎኑ ችግር ነው እንጂ ባያምኑም አምነዋል’ እያሉ እየሰማን . . . ‘የአነዳዳችን ችግር እንጂ መኪና በራሱ አይሄድ’ ካልንማ፣ ዕድገቱን ሙሉ ልናደርገው ነዋ! ምነው ሳትኩ እንዴ?

 የእኔ ነገር። ጉዴን ረስቼው። እኔ ሆኜ እንጂ ለነገሩ ጉዱን ጉዳንጉዱን ማን እያሳየ አርዓያ ሆኖን ገመናችንን እንናገራለን ብላችሁ ነው? ምን ሆነ መሰላችሁ? ማንጠግቦሽ ድንገት መሰብ ብላ ተነሳችና አንድ ቀን፣ “ጉርድ ፎቶግራፍ ተነስተህ አምጣልኝ፤” አለች። “ለምን እጎረዳለሁ ሙሉን ተነስቼ አላመጣልሽም እንዴ?” አልኳት። በልቤ ‘አንቺም እንደ ዘመነኞቹ ሙሉ ሰው እየጎራረድሽ መቸርቸር ጀመርሽልኝ?’ እላለሁ። “የለም! በምሳተፍበት የሴቶች ክበብ ‘ሴቶች የቤተሰባቸው የጀርባ አጥንት ብቻ ሳይሆኑ፣ እንደ ወንዶች ራስ የመሆን መብት ስላላቸው የባሎቻችሁን ጉርድ ፎቶ ይዛችሁ በመምጣት እንደምትወክሉዋቸው አስመዝግቡ’ ተብለናል፤” አለችኝ። ስንቱ ቀማኛ ሀብቱን ቀርቅሮ በሰው ላብና ደም ላይ እያላገጠ የሚመዘግበው ጠፍቶ፣ እኔ በአደባባይ በሰማኒያ ያገባኋት ሚስቴ እንደ ሰረቀችኝ፣ ወይ እንደ ሰረቅኳት ሁሉ አስመዝግቢው ተባለችና አረፈችው። መቼ ይሆን የዚህን ዓለም ስላቅ ከመስማት የማርፈው አለች ፀሐይ? ጨረቃ ምን ትበል?!

በአንድ በኩል አራት መቶ ካሬ ላይ ያረፈ ዘመናዊ ባለሦስት ፎቅ መኖሪያ ቤት ለማሻሻጥ የቀጠርኳቸው ደንበኞቼ ይነዘንዙኛል። ማንጠግቦሽ እንድትለቀኝ ብዬ “እሺ” አልኳትና ወጥቼ ሄድኩ። ወዲያ ተነስቼ በሠፈር ልጅ ላኩላት። ነገሩ ግን ከነከነኝ። አካል አንድ ራስ እንጂ ሁለት ሊኖረው ይችላል? ድኅረ ዘመናውያን ግን የማይጣረስ መብት የማያቀናጁን ለምንድነው? እያልኩ እዚያም የሚጠብቀኝ ገንዘብ ነውና ቅድሚያ ለእሱ ሰጠሁ። ደንበኞቼ ቤቱን ቀደም ብለው ጎብኝተውት ስለነበር መገኘት የነበረብኝ ገንዘቡን ሲረካከቡና ውል ሲዋዋሉ ለመታዘብ ነው። በአጭሩ ገድዬዋለሁ። “አገሪቷ እየተዳደረች ያለችው በደላላ ነው፤” ተብሎ በመልካም አስተዳደር እጦት ዙሪያ በተደረገ የቴሌቪዥን ውይይት ስሰማ መጀመርያ እኔን መስሎኝ ብደነግጥም፣ እውነቱን ተናገር ካላችሁኝ ያስደነገጠኝስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉበት መባሉ ነው። ምናልባት በአቶ መለስ ዜናዊ ዘመን በጓዳ ካልሆነ በይፋ ስማችን በአሻሚ ትርጓሜ ሲነሳ ስላልሰማሁም ይሆናል። ድሮስ ጅምላ እንጂ በነጠላ ስያሜ ጣት መቀሳሰርማ ከመጣማ በምን አመላችን፣ በየትኛው ችሎታችን  ልንቻቻል ነው ብለን ብናልፈውስ? ለነገሩ እልፍ ሲሉም እልፍ ነው!

ታዲያላችሁ ሻጭና ገዥ ውል ተዋውለው እንዳበቁ ኮሚሽኔን ተቀብዬ ልሄድ ስል “ግቢው ባዶ እንዳይሆን ለአንዳንድ የቤት አስቤዛ መሸመቻ ሾፌር የሚይዛት መኪና ካገኘህ ደውልልን፤” አሉኝ ገዥዎቹ። “‘ቪትዝ’ ይሆናል?” ስላቸው “አያንስም?” ምናምን ተባብለው (ዝም ብሎ ባለቤቶቹ ሲወጡ ግቢው ጭር እንዳይል ሱቅ መላላኪያ እኮ ነው) “ይሁን በቃ” አይሉኝ መሰላችሁ? ‘እንኳንም ሀብታም አላደረገኝ’ ብዬ እንዳላመሰግነው ‘ልማታዊ ምሥጋና ብቻ ሰው’ ስለተባላ ከአፌ መለስኩት። ለባለቪትዞቹ ስደዋውል ሳይታወቀኝ ሠፈር ደርሻለሁ። ምናለበት ካደጉት አገሮች ተርታም እንዲህ እንእኔ የመንገዱ አድካሚነት ሳይታወቀን በደረስን’ ብዬ ስልኬን ዘግቼ ወደ ቀኝ ዞር ስል የሚያሳሳ ሽንጥ ከተሰቀለበት ልኳንዳ ቤት አጠገብ ረጂም ሠልፍ አየሁ። እዚያው እንደቆምኩ ‘ብለን ብለን ለማስቆረጥም እንደ ትራንስፖርት ጥበቃ ሠልፍ ጀመርን?’ እያልኩ አሽሟጥጣለሁ። ባይ ሠልፉ አይጎልም ባይ ሠልፉ አይጎልም። ግራገባኝ። ምናልባት አንድ ንብረት አስቆጥር የተባለ በሙስና የተጠረጠረ ባለሃብት የሦስት ወራት የቤት ኪራይ በእኔ ነው ብሎ ይሆን? አልኩና ጠጋ ስል አንዱ ሠልፈኛ፣ “እስከ ዛሬ ተኝቼ ወይኔ። ነገ ደግሞ በምን ጉልበቴ ለታክሲ ልሠለፍ ነው?” ይላል። “ኧረ ምንድነው?” ስለው፣ “ዛሬ እኮ የመጨረሻው ቀን ነው፤” አለኝ ዞር ብሎ ገላምጦኝ። “ዛሬ የመጨረሻው ቀን ከሆነ (ምፅዓት መስሎኝ ሳይሆን ይቀራል ብላችሁ ነው?) ነገ ምን አሳሰበህ?” ስለው፣ “ምን ይታወቃል? ላይወጣልኝ ይችላል። በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምላክ እርሱ ተዓምር ይሥራ፤” ሲለኝ ገባኝ። ለካ ወገኔ ሥጋ ቤት በር ላይ ቆሞ ምራቅ እየዋጠ የተሠለፈው ዲቪ ሊሞላ ነው። ኢንተርኔት ቤቷ በር ላይም በትልቁ ‘እነሆ ከእንግዲህ ተስፋዬ ማን ነው? ዲቪ አይደለምን?’ ተብሎ ተለጥፏል። መቼም ከዚህ በላይ የመጻፍና የመናገር ነፃነት መንግሥተ ሰማያት እንኳ አለ ብሎ ማመን ይከብዳል። አይከብድም? አይዟችሁ ካልከበዳችሁ ብቻዬን እሸከመዋለሁ!

እንሰነባበት መሰለኝ። ኧረ ተረጋጉ፣ እዚህ ለእዚህ ማለቴ ነው። “እኔ አንበርብር ምንተስኖት ነኝ ዲቪ ሞልቼ በሎተሪ አገሬን የምለቅ?” እያልኩ እንዳልተመፃደቅኩ፣ በአደባባይ በሠልፍ ስንሰደድ ሕዝቤን አንድ በአንድ አስተዋልኩት። “ይኼ ልጅ መቼም (የኢንተርኔት ቤቱን ባለቤት) ዛሬ ተጠቆረ፤” ይላል ከሠልፈኞች መሀል አንዱ። “የዛሬን ይገላግለን እንጂ እሱማ ምን ይሆናል ብለህ ነው? ግፋ ቢል ዓመታዊ ግብር ቢቆልሉበት ነው። አሁን ማን ይሙት እስከዚያ ድረስ  ቨርጂኒያ ኢንተርኔት ካፌ ለመክፈት ‘ፕላን’ አላወጣም ልትለኝ ነው?” ይላል ሌላው። የማልሰማው የለም እያልኩ ነገ አንድ ወሬ ስለዚህ ኢንተርኔት ካፌ ብሰማ ብዬ የታማውን ልጅ አጮልቄ ሳየው “ኔም? ብሎ ሲጠይቅ፣ “አንበርብር ምንተስኖት” ብላ ስታስሞላው ማንጠግቦሽን ማየት። አላምንም ብዬ ዓይኔን ባፈጠው ማርጀቴ ታወቀኝ። እንደማጥራት አፍዞ አሳየኝ። ጉርድ ፎቶው ለምን እንደተፈለገ ገባኝ። ጎትቼ እንዳላስወጣት እሷም ራስ እኔም ራስ። ዕድሜዬ ባይገፋ ኖሮ ይኼኔ ነበር ወንዶችን ሰብስቤ የምደራጀው። እኔ ልሙት!

 ምን ዋጋ አለው ከራስ በላይ ያለው ንፋስ ነው። እንደበገንኩ ወደ ባሻዬ ልጅ ደውዬ የሰርክ መገናኛችን ወደሆነችው ግሮሰሪ አመራሁ። ሲያየኝ ገና፣ “ምን ሆነሃል?” ብሎ ጠየቀኝ። ጉዴን አንድ በአንድ አጫወትኩት። እንደኔ በአገር ፍቅር ስሜት በአፈር ሽታ ናፍቆት ይጦፋል ብዬ ስጠብቅ “ብራቮ! ብራቮ!” ብሎ ጮኸና “መልካም ሚስት ለባሏ ምንድናት?” እያለ እንደ መዋዕለ ሕፃናት መምህር የግሮሰሪያዋን ታዳሚዎች ደጋግሞ እየጠየቀ ‘ዘውድ’ አስደፋልኝ። ነዶኝ፣ “ቆይ ጠብቅ ኢትዮጵያም አንድ ቀን ዲቪ ታስሞላለች፤” ስለው “እኛ አንሞላለና። ማን አልሞላም አለ? አንሞላም አልን እንዴ? ሲያስሞሉን እኮ እንሞላለን፤” አለኝና ስልኩን አውጥቶ ‘8100 A’ ብሎ ‘ሴንድ’ አለው። ምን ይሉታል ይኼን ጎበዝ? መዋለል ወይስ መደለል? እኔማ አንዳንዴ ግራ ግብት ሲለኝ የሚወራው ሁሉ አልገባህ ይለኛል፡፡ እዚህ ግራ የሚያጋቡ፣ እዚያ ጋ ግራ ተጋብተው የሚደነባበሩ አሉ፡፡ ከዚያስ? ‘ኔትወርክ’ ቅብጥርስ ይባላል፡፡ ኧረ ማገዶአችንን አታስጨርሱን፡፡ ቸር ሰንብቱ! መልካም ሰንበት!               

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት