የተወለደው ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ነው፡፡ ከወላጆቹ ተለይቶ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ የሁለት ዓመት ልጅ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ካሉ አጐቱ ጋር እየኖረ ትምህርቱን መከታተል ጀመረ፡፡ የሙዚቃ ዝንባሌ ስለነበረውም በትምህርት ቤቱ ክበባት በማቀንቀን እየታወቀ ሔደ፡፡ የ24 ዓመቱ ዳዊት ጽጌ ድምጻዊ የመሆን ሕልሙ የተወጠነው ያኔ ነበር፡፡
ህልሙ ላይ ለመድረስ የጀመረው ጉዞ ግን ቀላል አልሆነም፡፡ በአሥራዎቹ መጀመሪያ ላይ እያለ ከአጐቱ ጋር በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ ከቤት ለመውጣት ተገደደ፡፡ አለኝ የሚለው ነገር የሙዚቃ ችሎታው ብቻ ነበር፡፡ ራሱን ለመቻል ብዙ ውጣ ውረዶችን ካለፈ በኋላ የእንጨት ሥራ ጀመረ፡፡ በድምጻዊነት መግፋት ቢሻም መተዳደሪያው ሊያደርገው ስላልቻለ በእንጨት ሥራ ዓመታትን አስቆጠረ፡፡ ዛሬ ያንን ወቅት ሲያስታውሰው ፈታኙን የሕይወቱን ክፍል ያለፈው በሙዚቃ ፍቅሩ እንደሆነ ይናገራል፡፡
በ2001 ዓ.ም. አየር ኃይልን መቀላቀሉ ድምጻዊ የመሆን ተስፋውን ያለመለመ አጋጣሚ ነበር፡፡ ከዓመት ቆይታ በኋላ ኮልፌ አካባቢ በሚገኝ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኦርኬስትራ እንዲሁም በማረሚያ ቤቶችና በተለያዩ ባህላዊ መዝናኛዎች መዝፈን ጀመረ፡፡ ከዚያም ዱባይ እየተመላለሰ መሥራት ከጀመረ በኋላ ‹‹ገላዋ›› የተሰኘውን ዘፈን ሠራ፡፡
በወቅቱ አብርሃም ወልዴ ባላገሩ አይዶልን ሊጀምር እንደሆነ ሲሰማ ‹‹በውድድሩ ራሴን ማሳወቅ አለብኝ›› ብሎ ዛሬ ነገ ሳይል ተመዘገበ፡፡ ውድድሩን የጀመረው ሕዝብ እንዲያውቀውና የራሱን ሥራዎች ለመሥራት መነሻ ሊሆነው እንደሚችል አምኖ ነበር፡፡ ግቡን ለመምታት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ዙር በጥንቃቄ መጓዙን ይናገራል፡፡ ከአንዱ ዙር ወደ ቀጣዩ ሲያልፍ አንድ ዕርምጃ ወደ ህልሙ እየተጠጋ እንደሆነ ይሰማው ስለነበር ልምምዱ ላይ ይበልጥ ይበረታ ያዘ፡፡
ዳዊት የተለያዩ ዘፈኖችን አንድ ላይ አከታትሎ ማዜሙ በውድድሩ ያሳየው ልዩ ብቃት እንደሆነ ይሰማዋል፡፡ ውድድሩን ሲያካሂድ ሙዚቃዎቹን በማዘጋጀት ያግዙት የነበሩት ጓደኞቹ ዘወትር ከጐኑ መሆናቸው እንደረዳውም ይናገራል፡፡ በሙዚቃ ያለመው ደረጃ ለመድረስ ውድድሩ በእጅጉ እንደሚያግዘው አስቦ ሙሉ ትኩረቱን ቢሰጠውም፣ በውድድሩ ወቅት ዱባይ እየተመላለሰ ይሠራ ስለነበረ ሁለቱን ማጣጣም ይቸግረው ነበር፡፡
በመጨረሻው ዙር አምስት ተወዳዳሪዎች ሲቀሩ፣ የባላገሩ መዝጊያ ዝግጅቱ ለሚወደው ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ መታሠቢያ የማድረግ ሀሳብ አደረበት፡፡ ተሳክቶለት ዝግጅቱ በጥላሁን የልደት ቀን (መስከረም 17) በመዋሉም የተሰማውን ደስታ ያስታውሳል፡፡ ከውድድሩ መድረኮች የማይረሳውም ይኸው ነው፡፡ በስተመጨረሻም ሦስት ዓመት ተኩል ገደማ የወሰደው ባላገሩ አይዶልን አሸንፎ የ300,000 ሺሕ ብር ተሸላሚ ለመሆን በቃ፡፡
በአሁኑ ወቅት የባላገሩ ቁጥር 4 ነጠላ ዜማና ባላገሩ አልበም ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ ነጠላ ዜማው በቅርቡ እንደሚለቀቅ የሚገልጸው ዳዊት፣ ‹‹ያለሁበት ደረጃ እስከ ዛሬ የለፋሁበት ስለሆነ ከመድረክ ሳልጠፋ ብዙ ጥሩ ሥራዎችን ለሕዝበ አደርሳለሁ፤›› ይላል፡፡
በቅርቡ የሚካሔድ የምስጋና የሙዚቃ ምሽት አዘጋጅቷል፡፡ በውድድሩ ከጐኑ ለነበሩ እንዲሁም ለግርማ በየነ፣ ዓለማየሁ እሸቴና ሌሎችም አንጋፋ ድምጻውያን ምስጋና ለማቅረብ እንዳዘጋጀው ይናገራል፡፡ አልበሙ ከወጣ በኋላ በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ኮንሠርቶች የማቅረብ ዕቅድም አለው፡፡
ህልማቸው አንድ ዓይነት ቢሆንም የዳዊትና የባላገሩ አይዶል ሁለተኛ ኮከብ መንገድ የተለያየ ነው፡፡ የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር በኢሳያስ ታምራት ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ የያዘ ስፍራ ነው፡፡ ቴአትር ቤቱን የተቀላቀለው በልጅነቱ ነበር፡፡ ትምህርት አቋርጦ ወጥቶ ሙዚቃ ለመለማመድ ወደ ቴአትር ቤቱ የሚሔድበት አጋጣሚ ብዙ ነበር፡፡
የቴአትር ቤቱ ሠልጣኞች የራሳቸውን ሙዚቃ እንዲያዘጋጁ ይጠየቁ ሰለነበር በርካታ የፈጠራ ሥራዎችን ለማሰናዳት ዕድል አግኝቷል፡፡ ቅዳሜና እሑድ በሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት በጉጉት የሚጠበቁ ቀናት ናቸው፡፡ በእነዚህ ቀናት ኢሳያስና ጓደኞቹ ለሳምንታት የተለማመዷቸው ሥራዎች ለመድረክ ይበቃሉ፡፡
ኢሳያስ በሚማርበት ትምህርት ቤትም ታዋቂ አቀንቃኝ ነበረ፡፡ በትምህርት ቤቱ ይሠሩ የነበሩትን እናቱን ጨምሮ፣ መምህራንና የዕድሜ እኩዮቹ ‹‹ዘፋኝ ይሆናል›› ይሉት ነበር፡፡ እሱም ድምጻዊ እንደሚሆን ያምን ነበርና መድረክ ባገኘበት አጋጣሚ ሁሉ ይዘፍናል፡፡
በልጅነቱ 50 ሳንቲም እየተከፈለ ተማሪዎች በሚታደሙበት መድረክ የበርካታ አንጋፋ ድምጻውያንን ዘፈኖች ማቅረቡን ያስታውሳል፡፡ ከሌሎች ድምጻውያን ለየት ባለ መልኩ የሴቶችን የወንዶችንም ዘፈን ያቀነቅናል፡፡ 28ኛ ዓመቱን የያዘው ድምጻዊው፣ ለዓመታት አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ክለቦች ዘፍኗል፡፡ ክለብ ውስጥ መዝፈን ሲጀምር የተከፈለው 500 ብር ሲሆን፣ ከጊዜ በኋላ በተሻለ ሁኔታ ዱባይና ሌሎችም አገሮች እየተዘዋወረ ይሠራ ጀመረ፡፡
ዱባይ በሚገኝ አንድ ክለብ ኮንትራት ተፈራርሞ ለዓመት የሠራበትን ወቅት ልዩ ትዝታ አለው፡፡ ምክንያቱ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሙዚቃ በጉጉትና በናፍቆት ስሜት ሲያዳምጡ መመልከቱ ነበር፡፡
‹‹በሥራዎቼ በሙዚቃው ካሉ ባለሙያዎች ጋር ብገናኝም፣ በምፈልገው መጠን ሕዝቡን ለማግኘትና ያለኝን አቅም ለማሳየት ውድድሩን ተቀላቅያለሁ›› ይላል ባላገሩ አይዶል ከመግባቱ ጀርባ ያለውን ነገር ሲገልጽ፣ ውድድሩን በሁለተኛነት አጠናቆ የ150,000 ብር ተሸላሚ ለመሆን ችሏል፡፡ ተሸላሚ በመሆኑ ውድድሩን ሲጀምር የነበረው ዓላማ እንደተሳካለትና ከሕዝብ እንደተዋወቀ ይናገራል፡፡
ውድድሩ ስለ ሙዚቃ ዕውቀት እንዳስጨበጠውም ይገልጻል፡፡ በዘልማድ ከማቀንቀን ባለፈ ስለ ሙዚቃ ተጨባጭ መረጃ ይዞ መሥራቱ በሙዚቃ ሕይወቱ ያሳየው ለውጥ እንደሆነ ያክላል፡፡ ውድድሩ ከሙዚቀኞች ጋር አብሮ ስለመሥራት የተማረበት ነበር፡፡ የአንጋፋዎችን የወጣቶችንም ሙዚቃ ያደንቃል፤ በተመሳሳይ እሱም በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ የጐላ አሻራ ጥሎ እንደሚያልፍ ያምናል፡፡
አሁን እየሠራቸው ያሉትን ነጠላ ዜማዎች በቅርቡ ለአድማጭ ጆሮ የማድረስና በተለያዩ አገሮች እየተዘዋወረ ኮንሠርቶች የማዘጋጀት ዕቅድ አለው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር የወደደውን አድርጐ ውጤቱን አግኝቻለሁ፤ ጊዜውን ጠብቄም ሥራዎቼን አቀርባለሁ፤›› ይላል፡፡
ሦስተኛዋ የአይዶል ኮከብ የ23 ዓመቷ ሜላት መንገሻ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ፣ ልደታ አካባቢ ነው፡፡ ሙዚቃ የጀመረችው በልጅነቷ ቢሆንም፣ ለቤተሰቦቿና ለጓደኞቿ መኝታ ክፍል ውስጥ ከመዝፈን ባለፈ ሰፊ መድረክ አልገጠማትም፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ትምህርት ቤቷ በተዘጋጀ ካርኒቫል ተጋብዛ መዝፈኗን ታስታውሳለች፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኢንጂነሪንግ በምትማርበት ወቅት ግን ትኩረቷን ያደረገችው ትምህርቷ ላይ ነበር፡፡ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሆና የባላገሩ አይዶል ውድድር ምዝገባ ተጀመረ፡፡ የመወዳደር ሀሳቡ ባይኖራትም በጓደኞቿ ግፊት ተመዘገበች፡፡
ለመጀመሪያው ዙር የዘፈነችው የአር ኬሊ ‹‹አይ ብሊቭ አይ ካን ፍላይ››ን ነበር፡፡ እስከመጨረሻው ዙር ድረስ ካለፈችባቸው ዙሮች በተለየ ያን ዕለት ታስታውሰዋለች፡፡ ምን ይጠብቀኝ ይሆን ሳትል በነፃነት የተጫወተችበት መድረክ ነበር፡፡ በቀጣዮቹ ዙሮች ጫናው እየበረታ መጣ፡፡ በሙዚቃ መሣሪያ ታጅቦ መዝፈን፣ የአማርኛ ዘፈኖችን ማቅረብም ለሜላት ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ወደ ውድድሩ ስትገባ ያላትን ችሎታ ከመፈተሽ ያለፈ ግብ አልነበራትም፡፡ ዘፋኝ ስለመሆን አስባም አታውቅም፡፡
እንደእሷው ቤተሰቦቿም በሙዚቃው እንደምትገፋበት የተረዱት በውድድሩ ወደ መጨረሻዎቹ ዙሮች ስታልፍ ነበር፡፡ ልምምድ ስታደርግ የሚያግዛት ባለሙያ ባይኖርም ከድረ ገጸ ሙዚቃ በማውጣትና በሌላም መንገድ ራሷን ታዘጋጅ ነበር፡፡ የመጨረሻ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷና ውድድሩ ቢደራረብም ብዙም እንዳልተቸገረች ትናገራለች፡፡
የማርያ ኬሪና እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ዘፈኖች ከምትመርጣቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በውድድሩ መሳተፏ ችሎታዋን እንድታውቅና ስለሙዚቃ በጥልቀት እንድትገነዘብ እንደረዳት ትናገራለች፡፡ ከሙያተኞች የሚሰጣትን ቀና ምላሽ ተከትላ ድምጻዊ ስለመሆን ማሰብም ጀመረች፡፡ ለሙከራ ብላ በጀመረችው ውድድር ሦስተኛ ሆና በማጠናቀቅ 75,000 ብር ተሸለመች፡፡
‹‹ሕዝብ ፊት ቆሞ የመዝፈን ልምዱም ድፍረቱም አልነበረኝም፤ ፍርኃቴ ቀስ በቀስ ለቆኛል፤ አሁን በራሴ የምተማመን ሰው ሆኛለሁ፤›› ትላለች፡፡ እዚህ ደረጃ እንደምትደርስ አስባ ባትወዳደርም የሕይወቷ አቅጣጫ መለወጡን ትናገራለች፡፡
አሁን በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ፒያኖ ትማራለች፡፡ በማማስ ኪችን የመዝፈንም ዕቅድ አላት፡፡ ‹‹ማተኮር የምፈልገው ስለ ሙዚቃ ማወቅ ላይ ነው፤ በሒደት ነጠላ ዜማ፣ አልበምም አወጣለሁ፤›› ትላለች፡፡