Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትእስኪ እንነጋገር! አለ ብዙ ነገር!

እስኪ እንነጋገር! አለ ብዙ ነገር!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጊዜና ዓለማችን

ይህ ጊዜ በዓለማችን ነገሮች ቶሎ ቶሎ የሚለዋወጡበት አስገራሚ ጊዜ ነው፡፡ ኃያልነቷ እያቆለቆለ ቢሆንም ዓለምን በብቸኛ ዕልቅና በማሽቆጥቆጥ የበላይነት ውስጥ የነበረችው አሜሪካ (ከአውሮፓ ጋር) በተራዘመ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ቀውስ ተመትታለች፡፡ ገንዘቧ የዓለም አቀፍ መገበያያነቱ እስኪያጠያይቅ ድረስ ወድቆ እዚያም እዚያም ጀምራው ከነበረው ድንበር የተሻገረ ጦርነት መውጫ ስትሻ፣ የነፃ ገበያ ምላሷ ተቆልፎ ገበያ ስለመጠበቅና ራሷን ስለመሸጥ ስታወራ፣ ወደ ኃያልነት እያደገች ያለችው ቻይና ደግሞ በተገላቢጦሽ የነፃ ገበያ ተከራካሪ ስትሆን፣ ከዚሁ ጋር አሜሪካ ከጉድ አውጪኝ እያለች ቻይናን ብድር ስትማጠን በቅርብ ማየትን ማንም የጠበቀ አልነበረም፡፡ አውሮፓን መቀላቀል ዕድገትንና ብልፅግናን እንደመቀላቀል ተቆጥሮ፣ ብዙ የምሥራቅ አውሮፓ ደጅ ጠኚዎችና ተሳዮች የነበሩትና በጀርመን መሪነት ሌላ የኃያልነት እምብርት ይሆናል የተባለለት የአውሮፓ ኅብረት በዕዳ ክምችትና በባዶ ካዝናዎች ተመትቶ የኅብረቱ ዘላቂነት እስኪያጠራጥር ሲዝረጠረጥ ማየትን ማን ገምቶት? ያም ያም ወደ ጀርመንና ቻይና ሲያንጋጥ፣ መድኃኒት አዛዥነቱም በጀርመን እጅ ውስጥ ገብቶ ጀርመንን በአድራጊ ፈጣሪነትና በብቸኛ አትራፊነት አውሮፓ-ገብ የሕዝብ ቁጣ ሲጠምድ፣ የእነ ፈረንሣይ ውስጡን ለቄስነት ተለባብሶ ቀውስ የከፋባቸው እንደ ግሪክና ስፔይን የመሳሰሉት ከመንግሥት እስከ ኩባንያ አቅጣጭ የወጪ ቅነሳ ትዕዛዝ ተቀባዮች ሲሆኑ ማየት አስደማሚ ነበር፡፡ ፈረንሳውያን፣ ግሪካውያን፣ ስፔናውያን፣ የሜድትራኒያንን ባህር እያቋረጡ ወደ አካባቢው ያፍሪካ አገሮች እንጀራ ፍለጋ መሰደድንስ በዛሬው ጊዜ ይሆናል ብሎ ማን ገምቶ ነበር? ከቀውሱ ጋር ተያይዞ በአውሮፓና በአሜሪካ በደረሰው በአንድ ጀንበር ሥራ የለሽ፣ ገንዘብና መጠለያ የለሽ እየሆኑ በመራገፍ ምክንያት ከተሞች የሕዝብ ቅዋሜ ማመላለሻ መሆናቸው ውሎ ያደረ ቢሆንም፣ በቱኒዚያ ተጀምሮ በግብፅ ፀረ ሆስኒ ሙባረክ ትግል የተባው አደባባይ ተቆጣጥሮ መንግሥትን የማንበርከክ ዘይቤ ተቀሳሚነቱ አውሮፓና አሜሪካ ድረስ ተሻግሮ ‹‹ለንደንን ተቆጣጠር››፣ ‹‹ወል ስትሪትን ተቆጣጠር›› እየተባለ የታየው ትንቅንቅም አስገርሞ ያለፈ ነው፡፡ የአሜሪካን የኢንዱትሪ ከተማ ዲትሮየትን የዋጣት ዕዳ ያደረሰው የሥራዎችና የአገልግሎቶች መታጠፍ/ መዘጋት እስከ ፖሊስ አገልግሎት ረዝሞ፣ ነዋሪዎች ወዶ ገባ የፀጥታ ጥበቃ እስከማድረግ ተገደው ነበር፣ የከተማዋ ሕዝብ ብዛት በሚሊዮን ቤት ከመቆጠር በመቶ ሺዎች ወደ መቆጠር ወርዶ ነበር የሚል ዜናንስ የማን ጆሮ ጠብቆ ነበር?

የሀብት ማግበስበስና የመራገፍ ምጣኔውን አንድ ለዘጠና ዘጠኝ በመቶ (ከዚያም በላይ የጥቂት ኩባንያዎችና የዓለም ግጥሚያ) አድርጎ እስከማየት የሄደውን የፀረ ወጪ ቅነሳ ተቃውሞ ቀረብ አድረገን ስናስተውለው፣ አሁን የሚታየውን የአየር ንብረት ዘብራቃነትንና አውድምነትን መንስዔ ኢንዱስትሪያዊው የኢኮኖሚ ግስጋሴ ታሪክ ካስከተለው የሕዝብ ቁጥር፣ የብክለትና የመሬት ሙቀት እመርታ ጋር አገናኝቶ ፕላኔታችንን ከመምከኗ በፊት እናድን ከሚለው (ተሰሚነቱ እየሰፋ ከመጣው) የፀረ ብክለት/የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር ስናዛምደው የምናገኘው፡- ‹‹ኮሙዩኒስት›› ‹‹ካፒታሊስት›› በሚል ክፍልፍሎሽ ያልተቆረሰ፣ ግን ከጥፋት የወጣ ስሉጥ (ራሽናል) ዓለማዊ ሥርዓትን የሚጠይቅ ዓለም አቀፋዊ ትግልን ነው፡፡ ዛሬ መከታተል ከምንችለው በላይ በአንድ ጎን የሚጣደፈውና በሌላ ጎን ለትርፍ አሳዳጅነት ባለመስማማቱ ተዳፍኖ ወይም አድቦ የሚገኘው የቴክኖሎጂ ፈጠራም የነገውን የተራቀቀን የስሉጥ አኗኗር በር ማንኳኳቱን ቀጥሏል፡፡

በተራዘመ የኢኮኖሚ ቀውስ ጦስ ውስጥ ዛሬም አሜሪካና አውሮፓ የውስጥ ቅሬታን ከማቅለል፣ በትሪሊዮኖች የሚቆጠር የዕዳ ክምችትን ከመቀነስና አለልክ የተፈናከረ ገቢና ወጪን ከማቀራረብ ፈተና ጋር እንደተፋጠጡ ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ባላቸው የተሳሳተና አድሎኛ የፖለቲካ አያያዝ አራብተው ለሌላውም ዓለም ዕዳ እንዲሆን ያበቁት ሽብርተኛነትንና አክራሪነትን በዓለም ዙሪያ የማነፍነፍ፣ በየአገራቸው የሚኖረውን ሰው፣ የሚገባና የሚወጣውን ሁሉ የመሰለል እስረኛ አድርጎ ከፍተኛ ወጪ ያስገፈግፋቸዋል፡፡ በዚህ ላይ ከመጠመድና ከኪሳራ በቀር ያልፈየዷቸው ነባር ጦርነቶችና በግማሽ ልብ ለኮፍ ያደረጓቸው የቅርብ ጦርነቶች በዳፋቸው እየጠለፏቸው ነው፡፡ ያለንበት ጊዜ አስገራሚነት ድንክ ውርጭቶችና ሥሌቶች የፈለቁበት በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ ይሆናል ብለን ያልጠበቅነው የጥቁር ፕሬዚዳንት ከአሜሪካም አልፎ ዓለምን በነቀነቀ ድጋፍ ሥልጣን ላይ ሲወጣ እንዳላየን፣ ያ ሁሉ ድጋፉ እንደ ጤዛ በንኖ ለስሙ መጠሪያ ቁና እንዳይሰፋ ሁለቱን የአሜሪካ ምክር ቤቶች የተቆጣጠሩ ወግ አጥባቂዎች ባገጠጠ ዘረኝነት ሲተናነቁት፣ ጭራሽ በተራ ኑሮ ውስጥ በጥቁሮች ላይ የሚፈጸም የጥላቻ ጥቃት ሲጨምር፣ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ገብቶ እስከመግደል፣ የጥቁሮችን ቤተ ክርስቲያናት እስከ ማቃጠልና በአሜሪካ የባለባርነት ዘመን እስከመኩራት ድረስ ነጭ ‹‹ባርነት›› ኃፍረት ሲያጣ አስተዋልን፡፡ (በነገራችን ላይ፣ ባራክ ኦባማ ዓለማዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ያስቻለው ከንግግር አዋቂነቱ ይልቅ ለአሜሪካ ምዕራባዊ ሸሪኮች ሳይቀር ራስ ምታት የነበረውን የሪፐብሊካኖች ጦርነት ወዳድ ፖሊሲ መቃወሙ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን የሪፐብሊካኖች ወደ ሥልጣን የመውጣት ነገር ዓለምን ማሳሰቡ  እንዳለ አለ፡፡)

ቅሌት አላልቅ ያላት የቤንጃሚን ኔትናያሁ እስራኤልም፣ የአሜሪካ ወግ አጥባቂዎች ፓርቲ አባል ‹‹ሆና›› በመሪዋ በኩል ከርቀትና አሜሪካ ድረስ እየዘለቀች ለወግ አጥባቂዎቹ ሪፐብሊካኖች የምርጫ ዘመቻ ስትሠራ መቆየቷ አልበቃ ብሎ፣ ፕሬዚዳንቱ በይፋ በማያውቀው አመጣጥ የአሜሪካ ኮንግሬስ ውስጥ ገብታ ለሊኪድ ፓርቲና ለሪፐብሊካኖች ቢጠቅም የተባለ፣ ግን ሪፐብሊካኖች ኦባማን ያዋረዱ መስሏቸው የአገረ መንግሥታቸውን ክብር ያዋረዱበት፣ እስራኤልም ከኢራን ጋር ጠላትነቷን ያጠናከረችበት ዲስኩር ሲደረግ ታየ፡፡ ከማገገም ይልቅ እንደገና ቀውስ ሳያገረሽባት አይቀርም እየተባለ የሚሰጋላት አውሮፓ የሶሪያ-ኢራቅ ጣጣ ውስጥ መሳተፍ ሳያንሳት፣ የሩሲያን ጎረቤቶች እየቦጨቀ የሚሰፋ አውሮፓ አፍቃሪ የኢኮኖሚ ክልል በመፍጠር አባዜ፣ የንግድ ባልንጀራዋና የጋዝ ዋና ምንጯ ከሆነችው ሩሲያ ጋር የማያስፈልግ ትንንቅ አነሳሳች፡፡ የሩሲያን አለማደብ በማዕቀብ ለመሸንቆጥ ከአሜሪካ ጋር እንጣጥ እንጣጥ ማለቷ የጎተተው ጉዳት አስተዛዛቢ ነበር፡፡ የግብርና ምርት ከአውሮፓ ያለመግዛት የሩሲያ አፀፋ ዕርምጃ ፖላንድንና ግሪክን በመሰሉ በቀውስ የደከሙ ላኪዎች ላይ ያስከተለው የዋጋ መውደቅና የምርት ብልሽት፣ ሩሲያ በሩብልና በነዳጅ ዋጋ መውደቅ ኪሳራዋ መደራረቡ፣ ዩክሬንም በአውሮፓ አፍቃሪነትና በሩሲያ አፍቃሪነት መከፋፈል ካመጣው የግዛት መቆረስ አለመዳኗና እንደገና የበረዶው ወቅት ሲቃረብ ከሩሲያ የሚመጣው የኃይል አቅርቦት መቀጠሉን ለማስተማመን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የነዳጅ ዕዳዋን ዩክሬን ለሩሲያ እንድትከፍል አውሮፓውያኑ ሲያስማሙ መታየታቸው፣ እነዚህ ካስተዛዛቢ ክንዋኔዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ ነገሮች እየተገማመዱና እየተባባሱ አካባቢው ላይ የኔቶ-አሜሪካና ሩሲያ ፍጥጫና የመሣሪያ እሽቅድምድም ማገርሸቱ ያልተጠበቁ ድርጊቶች ገና ገና ብዙ ምናልባት እንዳላቸው የሚጠቁም ነው፡፡

ታላላቅ አዕምሮዎች (አሳቢዎችና ፈልሳፊዎች) የፈለቁባት፣ ለአውሮፓና ለዓለም የተረፈ የፀረ ሒትለር ተጋድሎ ውለታ በሚሊየኖች መስዋዕትነት አንፃ ያለፈችው ሶቪየት ኅብረት አካል የነበሩት ሩሲያና ዩክሬን የብልህነት ድርቅ የመታቸው መሆናቸው፣ በተለይ ሩሲያ ከተነጠሏት አገሮች ጋር ዝምድናዋን አጥብቃ የምዕራባውያንን ሠፈር አስፊነት የቴክኖሎጂ መቦጥቦጫ ለማድረግ (ጎረቤቶቿ አባል እንዲሆኑ በመምከር ጭምር) አለመቻሏ፣ ይህ ይቅርና ከተነጠሉ ወዲያ መልካም ኑሮና ነፃነት የማግኘት ተስፋ በመብነኑ ምክንያት በተወሰነ ደረጃ ወደ ሩሲያ ማጋደል ለተከሰተባቸው የቤተኛ ጎረቤቶቿ፣ በግርግር ግዛት ከመቦደስ የተሻለ ግብ የሌላት መሆኗ ውርደት ነበር፡፡ ዓረብ ኤምሬትስ የግብርና-የውኃ ቴክኖሎጂንና የምሕንድስና ጠበብትን ከምዕራባውያን እየገዛች የበረሃ ገነት ለመፍጠር የምትሞክረው በነዳጅ ገንዘብ ነው፡፡ ሩሲያም ነባር የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቅርሷን በጋዝና በነዳጅ ሀብቷ ማደስና ማንተግተግ አውቃበት ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ የነዩክሬይንና የነጆርጂያ የአውሮፓ ጫማ ላሽነት ባልተከሰተ፣ ኔቶም ባልተዳፈራት ነበር፡፡ መሆን የሚገባው ሳይሆን ቀረና እንኳን ኔቶ ሳዑዲ ዓረቢያም ወግ ደርሷት ቁንጥንጫ አሳረፈችባት፡፡ [በዶላር መቶ አሥራ ቤት የረጋ ይመስል የነበረው የበርሜል ነዳጅ ዋጋ እየተምዘገዘገ 50 እና 40 ቤት በወረደ ጊዜ የነዳጅ አምራች አገሮች ምርት በመቀነስ የዋጋ ቁልቁለቱን እንግታ ሲሉ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ ‹‹በርካሽ ዋጋ ብዙ ሸጬ የማተርፈው ይበልጥብኛል›› በሚል ሰበብ የማፋረሷ እውነተኛ ምክንያት የሶሪያውን በሽር አል አሳድ የምትደግፈውን ሩሲያን የመቅጣት በቀል ነበር፡፡] ይህን መሰሉ ቅሌት አልበቃ ብሏት በምንዛሪና በነዳጅ ዋጋ ውድቀት በተመታ አቅሟ ጠባቡንና ግፈኛውን የሶሪያውን በሽር አል አሳድ በውጊያ መደገፏ ወደ ቀዝቃዛ ጦርነት ከመመለስ ይልቅ፣ በዓለም አቀፋዊ እስላማዊ ሽብርተኛነት በመጠመድ በምትበልጣት አሜሪካ የቀናችና ለመጨረሻ ውድቀቷ ቆርጣ የተነሳች ያህል አስፈርቷል፡፡

ከሩሲያ ደግሞ የዩክሬይን! ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟ በራሱ በአውሮፓና በሩሲያ ፍትጊያ ውስጥ ካንዱ ጋር ተቃርኖ ሌላው ጋር መወተፍን የማይፈቅድ እንደመሆኑ፣ የሁለት በኩል ጥቀሞቿን አቻችሎ (ሕዝቧንም በተቃራኒ ወገናዊነት ሳታስበረግድ) መጠበብ ተስኗት ትርፏ በፖለቲካ መከፋፈልና አውዳሚ የመነጠል ጦርነት ሆኖ አረፈ፡፡ ይህ የዩክሬን ልምድ ለየትኛውም አካባቢና አገር እኔን ያየህ ዕወቅበት የሚያሰኝ ትምህርት ነው፡፡ የዩክሬንን ልምድ ጨምሮ የጠመንጃ መንገድ ባለብዙ ገደልና ኪሳራ የመሆኑ ተሞክሮ አይንና ጆሮ ላለው በሽበሽ ሆኗል፡፡ ለኩርዶች መብት ሲዋጋ የነበረው ቡድን (PKK) ከቱርክ ጋር ሰላማዊ ድርድር መጀመሩ (በቱርክ መንግሥት መሰሪ ትንኮሳ ቢሰናከልም)፣ በኮሎምቢያም በጫካ ትግል ረዥም ጊዜ ያሳለፈው ቡድን (FARC) ወደ ሰላማዊ መፍትሔ ፍለጋ መዞሩ (እንዲያውም ከተዋጊው ጋር የተጀመረው ድርድር መቀጠልና አለመቀጠል ባገሪቱ የምርጫ ውድድር ላይ የመሸናነፊያ ጉዳይ ሲሆን መታየቱ)፣ እነዚህ ሁሉ ዘመኑ የሰላማዊ መፍትሔ መሆኑን የሚመሰክሩ ናቸው፡፡ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ የማሊ፣ የሊቢያና የሶሪያ እልቂትና ውድመት የበዛባቸው የቁርቀስ ልምዶችም ዞሮ ዞሮ የሰላማዊ መፍትሔ ፈላጊነትን መሻል የሚደግፉ ናቸው፡፡

ይህንን የመሳሰለው ስንቱ ነገር ሲካሄድ ቻይና ብልጧ አድፍጣ (ያውም በቀውስ አለመመታቷ በኢኮኖሚ መደንበዝ ይዳሽቁ ለነበሩት አሜሪካና አውሮፓ የማንሰራራት ተስፋ ተደርጎ እየታየላት) ሸቀጦቿን፣ ካፒታሏንና ሥራ ተቋራጭ ኩባንያዎቿን ‹‹ሦስተኛው ዓለም›› ወደሚባሉት አገሮች እያሻገረች መደርጀትና መስፋፋት ላይ አትኩራ ነበር፡፡ ተስፋ የላትም የተባለችው አፍሪካም በዚህ የቻይና የመስፋፋት ሒደት ውስጥ እዚያም እዚያም መላወስ ይታይባትና የዕድገት አንድ አካባቢ ተደርጋ የመቆጠር ወግ ይደርሳታል፡፡ ወግም ብቻ አደለም፡፡ ‹‹የአውሮፓ አፍሪካ ፎረም››፣ ‹‹የፈረንሣይ አፍሪካ ፎረም”፣ ‹‹የጃፓን አፍሪካ ፎረም›› ወዘተ. የሚል ስብሰባና ጠጋ ጠጋ ከየአቅጣጫው ይመጣጣል፡፡ ቻይናን ግን ማን ደርሶ ሊፎካከራት! በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ አነሰም በዛ የሚታየው የማደግ አዝማሚያና አካባቢያዊ ስብስብ፣ እንዲሁም የዲሞክራሲና የሰላም ፍላጎት እየጨመረ መሄድ፣ የመንግሥት ግልበጣዎችንና ውጊያዎችን በአካባቢም ሆነ በአኅጉር ደረጃ ተጋግዞ የመቃወምና የማቃናት ጥረት የመታደስ መጀመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ በዚህ ተስፋ ሰጪ የታሪክ ምእራፍ ውስጥ በፀረ ቅኝ ትግል የተጀመረውና አንክሶ ሲደናበዝ የቆየው የአፍሪካ ነፃነት ህልም የመሟላቱ ጭንላጭል ይታያል፡፡

የአገር ውስጥና የአካባቢ ጣጣን እያስተካከሉና እየተጋገዙ የመራመድ ይህ የአፍሪካ የተስፋ ጭላንጭል አሳዛኝ ገጽታም የተዳበለው ነው፡፡ ዕድገት የደነቆረባቸው ሥፍራዎች ድንገት እየተደረመሱ ምሕረት የለሽ (የውድመት፣ የውጊያና የትርምስ) ቅጣቶች ሲቀምሱ የሚታይበት ሒደት አሁንም ቀጥሏል፡፡ የቤተ ዘመድ ጥሪትና የብድር ገንዘብ የቃረሙ የአፍሪካ ወጣቶች፣ ከመንደሮቻቸው አንስቶ ወደ ታች እስከ ደቡብ አፍሪካ፤ ወደ ላይ እስከ ሊቢያ፣ እስከ የመንና እስከ መካከለኛው ምሥራቅ በተዘረጋ የስደተኛ አሸጋጋሪዎች ካዚኖ ውስጥ፣ እንደጎርፍ እየተገማሸሩ ከመቼውም በበለጠ ብዛት ከጫካ እስከ በረሃ በሰፉ ፌርማታዎች ላይ የሞትና ሕይወት ጭፍን ሎተሪ እየተጫወቱ ናቸው፡፡ ግርፋት፣ መደፈርና ግድያዎችን (ምርጥ የሆድ ዕቃ ብልቶች ዘረፋን ጭምር) አልፈው ዋናው የሎተሪ ማውጫ የሜዲትራኒያን ‹‹የሞት ባህር›› ላይ መደፋታቸው ማብቂያ ማጣቱ፤ በደቡብ አፍሪካም የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን ሕይወት ያነሳ ለውጥ አለመታየት ላስከተለው ማኅበራዊ ቀውስ ስደተኞች ማሳበቢያና እልህ መወጫ መደረጋቸው፣ የጅምላ ጥቃቱ የተደጋገመ ሆኖም ዕድል ያውጣኝ ብሎ የመኖር ፍላጎትና ስደቱ አለመድከሙ ለባለተስፋዋ አፍሪካ የጊዜያችን ታላቅ ውርደቷም ነው፡፡ ውርደቱ ግን በአፍሪካ ብቻ አይወሰንም፡፡ አውሮፓና ዓለምም፣ ከአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከመካከለኛ ምሥራቅም በባህር በኩል የሚተምሙ ስደተኞችን ከሞት ከማትረፍና ስደትን ከመመከት የተሻለ መላ ማጣታቸውውርደታቸው ነው፡፡ ሊቢያንና ሶሪያን እንዲያ ነካክቶ፣ በስተኋላም የመንን ለሳዑዲ ጥቃት ትቶ የሙስሊሞች የስደት ታላቅ ጎርፍ ሲመጣ አውሮፓን ከ‹‹ኢስላማይዜሽን›› ስለመጠበቅ መጨነቅ ይሉኝታ ማጣት ነው፡፡ ታሪክ ግን እነሱ ይሉኝታ ስላጡ አልተገበረችላቸውም፡፡ አጥር በማይመልሰው ፍልሰት አጥለቅልቃ ለአውሮፓ አገሮች ስደተኛ እንደ ራሽን እስከ ማከፋፈል አዝረጥርጣቸዋለች፡፡ እንግሊዝን የመሰለች ጥይት አስተኳሽ በስደተኛ ፍልሰቱ ጊዜ መደበቂያ ሲጠፋት፣ አንፃራዊ ድሆቹ ምሥራቃዊ የአውሮፓ አገሮችም የጥቂቶቹ በጥባጭነት ያስከተለውን ዕዳ ተጋሪ እንዲሆኑ ሲፈረድባቸው ታየ፡፡ ኃያላኑ ጥፋት አያልቅባቸውምና ነገ ደግሞ ከዛሬው ፍልሰት ውስጥ ፀረ ምዕራብነትን እያመረቱ የታሪክን ሌላ ቁንጥጫ ሲቀምሱ “እናያለን ገና”፡፡

የአፍሪካ ቀንድ

ሁሉም ዓይነት ፍዳ (ጦርነት፣ ሽብር፣ ረሃብና ስደት) የተገማሸሩበት የአፍሪካ ቀንድ ከአፍሪካ ውስጥ በትምህርት ሰጪነቱ ወደር የለውም፡፡ በጦርነት ውስጥ ጎልምሰውና ደርግን ጥለው ኢትዮጵያን እንደ ድርሻ የተካፈሏት ተዋጊዎች ፍቅራቸው ወደ ጠላትነት ተቀይሮ እንደገና ወደሚሰቀጥጥ ጦርነት የገቡት በዚህ ቀጣና ውስጥ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ጠላትነታቸውና የእጅ አዙር ውጊያቸው ገና አላከተመም፡፡ ከጎረቤቶቿ ሒሳብ አወራርዳ ታላቋን ሶማሊያን በመገንባት ምኞት ተወጥራ በከፈተችው ወረራ ጦስ በጎሳ የጦር ጌቶች ከመቦዳደስ አንሥቶ የሽብር መነኸሪያ እስከመሆን ተንኮታኩታ የነበረችው ሶማሊያ፣ ብዙ እጅ ከገባበት አዘቅት የመውጣት ውጣ ውረድ በኋላ፣ የግዛት አንድቷን እንኳ መመለስ አቅቶ ሦስት ያህል ቅርፆች ፈጥራለች፡፡ ሞቃዲሾ ላይ በስንት ርብርብ የተቋቋመው መንግሥትም ሕይወትና ዕድሜ  ያለው ሆኖ የመዋጣቱና ሽብርን የማሸነፉ ነገር የረዥም ዳገት ያህል ከባድ እንደሆነ ነው፡፡ መነጠልና ነፃነት ፍጥረታቸው ምንና ምን እንደሆነ መረዳት ለሚሻም የአፍሪካ ቀንድ ሁነኛ መማሪያ ነው፡፡ የልማት ምድረ በዳ ሆና ኖራ ከሱዳን የተላቀቀችው ደቡብ ሱዳን ተቦጭቆ ከቀረ የነፃነት ትግልና ከነዳጅ ጋር የተያያዘ ጣጣ ገና ከሰሜኑ ጋር አለባት፡፡ ይህ ሳያንሳት ተሳስቦ ራስን ማስተዳደር፣ ከመዳህ ወደ መሮጥ እንደማለፍ ከብዷታል፡፡ ከበረሃ የትግል ኑሮ ወጥተው የዕርዳታና የነዳጅ ሀብት ውስጥ የተዘፈቁት መሪዎቿ ጎሰኛ መልክ የያዘ የመናጠቅ ጦርነት ከፍተው እልቂት፣ ረሃብና ስደቱን መልሰው አምጥተውባታል፡፡ የሚገርመው ደግሞ የጎረቤት እበላ ባይነትም አንዱን ወይ ሌላውን ቡድን በመደገፍ ችግር ሲያባብስ መገኘቱ ነው፡፡ ከጫካ ወደ ቤተ መንግሥት ተሻግሮ በልማትና በፍትሕ ጎዳና አገርን መምራት ለማንም ከባድ ፈተና ነው፡፡ የኡጋንዳው ሙሴቬኒም ሆነ ኢሕአዴግና ሻዕቢያ በሀብት ሽሚያ ድጥ ላይ ተፈትነዋል፡፡ በዚህ ውሱን ቀጣና ውስጥ ብቻ ሦስት ወይም አራት ያህል አዳዲስ አገሮች ተፈጥረዋል፡፡ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳንና የሶማሊያ ክፍልፋዮች፡፡ የእነዚህ አዲስ መጦች የሰላምና የዕድገት ፈታና የጎረቤቶቻቸውም ፈተና መሆኑ ገና ተጀመረ እንጂ አላለቀም፡፡

ይህ ቀጣና ሌሎች ዓይነተኛ ባህርያትም አሉት፡፡ ኢትዮጵያን የቀንዱ መሀል አድርገን ዙሪያ አዋሳኞቿን ብናስተውል ከአርቲፊሻሉ የፖለቲካ ወሰን ሥር የአምሳያ ሕዝቦች የተቀላቀለ ሥርጭት አነሰም በዛ እናገኛለን፡፡ በዚህ ላይ ክርስትናና እስልምና በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊና ስብጥርጥር ሥርጭት ያላቸው ዋነኞቹ ሃይማኖቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁኔታዎች መገንዘብ እንደሚቻለው ከየትኛውም የወሰንተኛ ጎረቤት የጠረፍ አካባቢ የሚነሳ የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ጣጣ በቀጥታ ኢትዮጵያንም መንካቱ አይቀርም፡፡ ከቀንዱ ራስጌ እስራኤልና ፍልስጥኤምን እንዲሁም ሱኒና ሺአን መሠረት ያደረገ ቁርቁስ የማያጣው መካለኛው ምሥራቅ አለ፡፡ የዚህ አካባቢ ግለት የሚፈጥረው ስሜታዊ ወላፈን የቀንዱን አገሮች ሁሉ መዳሰስ የሚችል ነው፡፡ ለጠብና ለፍቅርም ሊውል የሚችል የድንበር ተሻጋሪ ውኃዎች ግንኙነትም በኢትዮጵያና በጎረቤቶቿ መሀል አለ፡፡ በተለይ ዓባይ ኢትዮጵያን – ደቡብ ሱዳንን – ሱዳንን – ግብፅን የፈለገ ቢቀቀያየሙ እንኳ በቃኸኝ መባባል እንዳይችሉ አድርጎ አስተሳስሯቸዋል፡፡

ሌላው አስተሳሳሪ የባህር በር ጉዳይ ነው፡፡ አዲሷ ደቡብ ሱዳን የወደብ ግልጋሎት ለማግኘት ወደ ኬንያ ወይ ወደ ሱዳን ማቅናት፣ አለዚያም በኢትዮጵያ አቆራርጣ ወደ ጅቡቲም ሆነ ወደ ሌላ ወደብ ማለፍ አለባት፡፡ ገቢና ወጪ ንግዷ የሰፋውና ገና ይበልጥ የሚሰፋው ኢትዮጵያም በንግድ አቅጣጫዋ መለያየትና በአንድ ጂቡቲ ላይ ላለመጣበብ ስትል፣ ከሰሜን እስከ ደቡባዊ ምሥራቅ በምታገኛቸው ወደቦች ለመጠቀም ተገዳለች፡፡  የጠብና የጦርነት ሁኔታ እስካላወካትም መጠቀሟ ይቀጥላል፡፡ ከእነዚህ ጋር የሚሸራረቡና አካባቢያዊ የጋራ ትብብርን የሚሹ ሌሎች ጥቅሞችም አሉ (ከሰላም፣ ተዛማች ተባዮችንና በሽታዎችን ከመቆጣጠር፣ ወዘተ. ጋር የተያያዙ)፡፡ እስካሁን ያነሳናቸውን ነገሮች አገናዝበን ብናጠቃልል ከየትኛውም የአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ የሚመጣ መታመስ ለኢትዮጵያ ህልውናዋንና ዕርምጃዋን የሚወስን ሥጋቷና ጉዳቷ መሆኑን እናጤናለን፡፡ ከዚህ ጎን፣ በአፍሪካ ፀረ ቅኝ ትግልና አኅጉራዊ ኅብረት ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላት ሥፍራ የሚጠይቀው ኃላፊነት አለ፡፡ መሸምገልና ማስታረቅ፣ በጥቅሉ ቢያንስ በአካባቢያዊና በአኅጉራዊ የሰላም ጥረት ውስጥ አርዓያነት ያለው ባህርይ ይዞ መገኘትና የመሳሰሉት፡፡ ይህንን ኃላፊነትና አገራዊ ጥቅምን አስማምቶ ማስኬድ ግን ቀላል ሥራ አይደለም፡፡

ጎረቤት አገር ለተቃዋሚ ተገን ቢሆን ወይም በተቃዋሚ ሽፋን ድንበር እያለፈ መጎድፈር ቢጀምር፣ በዚያው ሥልት የአፀፋ ጉድፈራ መክፈት ወይንም የወረራ ትንኮሳ ተደረገብኝ በሚሉ ማማካኛ ውጊያ ውስጥ መግባት፣ ብዙ አገሮችንና ኢትዮጵያን ሲያማቅቅ የቆየ አሮጌ መንገድ ከመሆኑም በላይ የሰላምና የእርቅ ምሳሌ ከመሆን ፍላጎት ጋር በቀጥታ ይጋጫል፡፡ በሰብዓዊነትና በአፍሪካዊነት ኃላፊነት የሚካፈሉት ችግር ከአገር ደኅንነት ሥጋትና ልማትን ከመፈታተን ጋር የሚገጥምበትም ሁኔታ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ከዙሪያዋ ስደተኞች ቢጎርፉባትና ዝም ብላ ተቀባይ ብትሆን፣ በተፈጥሮና በማኅበራዊ አካባቢዋ ላይ የሚደርሰው ጫና ብቻውን ለውስጣዊ የፖለቲካ ጣጣ መዘዝ መሆን ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንኳ ከሰሜን፣ ከምዕራብና ከደቡብ ምሥራቅ የፈለሱ ስደተኞችን እያስተናገደች ነው፡፡ ውስጣዊ መዘዝ እንዳይኖረው አድርጎ ስደተኛን መንከባከብ በራሱ ጊዜና ትኩረትን ይሻማል፡፡ ይህ ቀላሉ ነው፡፡ ስደትን መደበቂያ አድርጎ አሸባሪነት መሰስ ካለ፣ ኦኦ!!!

ሽብር ሶማሊያን መናኸሪያ አድርጎ ወደ ጎረቤት እየሰረገ መጉዳቱና በሥጋት ማዝረጥረጡ ዛሬም አለ፡፡ ከቅርብ ጎረቤቶችም አልፎ በስደት አማካይነት አውሮፓና አሜሪካ የገባበትና ከዚያ ደግሞ ለሥልጠናም ሆነ ለውጊያ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የተሻገረበት ሒደት ሁሉ ተከናውኗል፡፡ የሽብር ችግር ባይኖርም ኢትዮጵያ ብቻዋን የልማት ደሴት ለመሆን ብትሞክር (ልማት የዙሪያዋ ሁሉ እስካልሆነ ድረስ) በስደት መወረር የማታመልጠው ፈተና መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ውስጥ እየተመዘዙ ያሉት ኢንዶኔዢያና ማሌዢያ ለባንግላዴሽ ማኅበራዊ ችግሮች ዕድገታዊ መፍትሔ እስካልፈለጉ ድረስ፣ የስደተኛን ጣጣ በማገድም ሆነ በማባረር እስከ መቼውም ሊገላገሉት አይችሉም፡፡ ሚየንማር (በርማ) የስደት ታሪክ አካሏ ያደረጋቸውን የሮሂንጋ ሙስሊም ማኅበረሰብን በሥልት አበርራ አትጨርሳቸውም፤ ስላባረረችም አዲስ ላለመተካታቸው መተማመኛ መዝጊያ አታበጅም፡፡ እንዲያውም የዚህ ዓይነቱ አካሄድ እያሳሳቀ ዘር ወደ ማጥፋት ጭፍጨፋ ሊያደርስና እንደገና ተነጥሎ ወደ መጠመድና ወደ መማቀቅ የሚወስዳት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ልምድና ምልከታ የሚነግረን ለፍልሰት መፍለቂያ ለሆነው ቀውስ መቃለያ በመፈለግ ላይ መረባረብ ይበጃል፡፡  ጎረቤት ለጎረቤት ከመጣመድም ወጥቶ የጋራ ልማትን የተቆናጠጠ (በቀላሉ የማይፈረከስ)  ትስስር መፍጠር ይመረጣል ወደሚል ማጠንጠኛ ነው፡፡ ሞቃዲሾ ላይ ቢያንስ ሽብርን የመመከትና የመቆጣጠር አቅሙ እያደገ የሚሄድ መንግሥት ሥር እንዲያበጅ አስተዋፅኦ ከማድረግ ጋር፣ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በርካሽ ዋጋ የማቅረብ የጋራ ጥቅምን ተመርኩዛ የምታካሂደው ልማትና ከጎረቤቶቿ ጋር በሚኒስትሮችና በፀጥታ ኮሚሽኖች ተባብሮ የመሥራት ልምምድ፣ በእሳትና በእልቂት ቀጣናነት የሚታወቀውን የአፍሪካን ቀንድ ገጽታ የሚቀይርና ምሳሌ ወደ መሆን የሚወስድ ነው፡፡

አሁን የተጀማመረው የትስስር እንቅስቃሴ በወዳጅነት አብሮ የማደግ አካል እንጂ የመፍትሔው ሁለመና አይደለም፡፡ በመንገዶች፣ በኤሌክትሪክ መስመር፣ በንግድና በመሳሳሉት መተሳሰር ከሚዳብር ሰላም ጋር አብሮ ካልተገመደ ከንቱ ነው፡፡ ከሆነ አቅጣጫ የሚነሳ የጥፋት እንቅስቃሴ የተለፋበትን ሁሉ ሊያወድመው ይችላል፡፡ ይህንን አደጋ ለመዝጋት የፀጥታና የመረጃ ጉድኝትም ሆነ የጋራ የተጠንቀቅ ጦር ማዘጋጀት ብቻውን አይበቃም፡፡ ለትርምስ መፈልፈያ የሚሆኑ ችግሮች እስካሉ ድረስ ውሎ አድሮ የፀጥታ ትብብሮች ራሳቸው ሊሽመደመዱና ሊቋረጡ የሚችሉበት ዕድል ክፍት ነው፡፡  ለምሳሌ የአንዱ ተጓዳኝ አገር የውስጥ ፖለቲካ ለሃይማኖታዊ ፖለቲካ (ፓርቲ) በር ቢከፍት ያ አገርም ሆነ አካባቢው ከአደጋ ምናልባት ጋር መኖራቸው የማይቀር ነው፡፡ ሆስኒ ሙባረክን ያወረደው የግብፅ አብዮት መንገድ ለመሳት የተጋለጠው መሐመድ ሙርሲ መራመድ ሲያቅተው ሳይሆን፣ ሃይማኖታዊ ድርጅት የፖለቲካ ሥልጣን ሩጫ ውስጥ እንዲገባ ዕድል ባገኘ ጊዜ ነበር፡፡ በጦርነትና በሽብር ስትታመስ የቆየችው የአፍሪካ ቀንድ ከዚህ ዓይነቱ ልምድ ሁሉ ትምህርት መውሰድ አይበዛባትም፡፡ ከዚህም በላይ፣ የእስካሁኑ የፍዳ ልምዷ ለሽብር መብቀያና መራቢያ ሊሆኑ የሚችሉ የመከራ፣ የኋላ ቀርነትና የማኅበራዊ አድልኦ ጉረኖዎችን በፍትሐዊ ለውጥና በዕድገት ግስጋሴ መበጣጠስን ይጠይቃታል፡፡ በሌላ አነጋገር ከጥሎ ማለፍ ይልቅ ‹‹ጠንካራው›› ደካማውን እየረዳ ተያይዞ መጓዝ አማራጭ የለሽ ነው፡፡ ይህ የጋራ ተግባር ፍሬ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት የዝና ወይ ‹‹የአካባቢ ኃያልነት›› ወጓ ሳይሆን፣ በአካባቢው ውስጥ ያላት ጂኦግራፊያዊና ማኅበራዊ አቀማመጥ ግድ የሚላት የህልውና ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህ የጋራ ልማት ተግባር ላይ ህልውናን የማስተማመንና ለሌላው አርዓያ የመሆን ሥራዎች ይገጣጠማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግብዝ ቱልቱላና መንጠራራት ሳያስፈልጋት ጥንካሬዋን እያሳደገች ሳትሰስት ካካፈለችና የቀንዱ አካባቢ ጎረቤታሞች በሙሉ የሚሳሱለት የጋራ ጥቅም መቀናበር ከቻለ፣ የስኬቱ ማንፀባረቅና ለመማሪያነት መፈለግ አብሮት ይመጣል፡፡

ትስስሩ ሄዶ ሄዶ መገበያያ ገንዘብን እስከመቀላቀል ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ይገመታል፡፡ ይህ ደግሞ ቀጣይነት ያለው የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ መረጋጋትን የሚጠይቅ – ይህም በቀጥታ የማይወላከፍ ልማትንና የተረጋጋ ዴሞክራሲ ግንባታን የሚመለከት ሌላ ፈተና ነው፡፡ የአካባቢው አገሮች ዴሞክራሲና ልማት ውስጥ ቢገቡ እንኳ የኢትዮ ኤርትራና የአውሮፓ ኅብረት ልምድ እንደሚያስተምረው የጋራ ገንዘብ ምሥረታ ዘሎ የማይገባበት (በአንድ አገር ጥፋት የጋራ ምንዛሪ ተገልጋይ አገሮች ኢኮኖሚ ሊናጥ የሚችልበት) እንደመሆኑ፣ ከፖለቲካዊ ውህደት ጋር ተጎዳኝቶ መምጣት ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡ የመደላድል ዝግጅቱም ቢሆን በስብሰባ እነዚህን ነገሮች እናሟላ ብሎ ከመወሰን ይልቅ የአንዱን ስኬት ሌላው እየቀሰመ የሚሟላ ነው፡፡ (ገንዘብ የማቀላቀል ዕርምጃም ቢሆን ከውድቀት የሚያመልጠው በብዙ ነገር በተጣጣሙ ሁለት ሦስት አገሮች መዋሀድ ተጀምሮ እየሰፋ የሚሄድ ቢሆን ነው፡፡) በዚህ አቅጣጫ ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ዓይን ማረፊያ (ሞዴል) መሆን ከፈለገች የሕዝብ ኑሮን ትርጉም ባለው ደረጃ ያነሳች፣ ሙስናንና የግብር ሸፍጥን ያሸነፈች፣ የሐሰተኛ ገንዘብና የሐሰተኛ ምርቶችን ወንጀሎች የበጣጠሰች፣ ቀልጣፋና መልካም አስተዳደር የሰመረላት በመሆን ጎዳና የተቃና ጉዞ ማድረግ ግድ ይላታል፡፡ እዚህ የስኬት ጎዳና ውስጥ መግባት ለኢትዮጵያ “ከሆነ ሆነ ካልሆነ መቼስ” ተብሎ ሊተው የማይችል ጉዳይ ነው፡፡

በተዳፈነ ጉርምርምታ እየተወዘወዙና በአምባገነንት እየተዋቡ ይህንን መሰሉን የስኬት ጉዞ ማከናወንና ልምድ አካፋይ መሆን አይቻልም፡፡ ከጎረቤት ጋር እየተናጩ የሰላምና የወዳጅነት መካሪ መሆን አትስሙኝ ከማለት ብዙም አይሻልም፡፡ ኢትዮጵያ በአንፃራዊ መረጋጋት ውስጥ የምታካሂደው በልማት መፍጨርጨር ገና በአሁኑ ደረጃ እንኳ ትኩረት ከሳበ፣ የውስጡን ለቄስ ሥራዎችን እያጠራች፣ እያጠለቀችና ድህነትን በማራገፍ የሕዝብ እርካታን እያጣጣመች፣ የፖለቲካና የሃይማኖቶች ሰላም አምባ መሆን ብትችል አስቀኒነቷ እንኳን በቅርብ ጎረቤቶቿ ላይ በሩቆቹም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናል፡፡

ምን ያህል ቤታችንን አደላድለናል?

ከዚህ አጠቃላይ የዕይታ ማዕዘን አኳያ ኢትዮጵያ ምን ያህል ቤቷን አደላድላለች? ምን ያህል የሚያዛልቅ መሰናዶ አላት? አፄ ኃይለ ሥላሴ ራሳቸውን ‹‹ፀሐዩ ንጉሥ … የኢትዮጵያ ብርሃን … የአዲስ ዘመን ጮራ›› አድርገው ቀርፀው አልፈዋል፡፡ በስማቸው ስንምል፣ ከነቤተሰባቸው ፎቶአቸውን በየደብተራችን አቅፈን ስንማር፣ ልደታቸውንና ንግሥናቸውን ስናከብር የኖርነው ከዚህ ምሥል ጋር ነበር፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴን የተካው ደርግ ሥልጣን ላይ የመጣበትን ቀን የአብዮት ቀን አድርጎ ሾሞ ሠርቶ አደሮች ሶሻሊስታዊ ኢኮኖሚና ባህል የገነቡባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ አነፅኩ ባይ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ የሥልጣን አያያዙን ‹‹በኢትዮጵያ አብዮት›› ታሪክነት፣ የድቀት ኢኮኖውሚውን ‹‹በሶሻሊስት ኢኮኖሚነት›› በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሳይቀር የሚሰጥ ትምህርት አድርጎት ነበር፡፡ ሲወድቅ ሁሉም ቀረ፡፡ ደርግን ገፍቶ በቦታው የተተካው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ደግሞ ሲፈራ ሲቸርና አካሄዱን ለዘብ ሰፋ ሲያደርግ ቆይቶ ያው ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. (ሥልጣን የያዘበትን ዕለት) የኢትዮጵያ ሕዝቦች ልደት እያለ ያከብራል፣ ያስከብራል፡፡ (በአዋጅ በዓል አድርጎ ሳይደነግግ ግን ‹‹በፍላጎት የሚከበር›› ከማለት ጋር ዓመታዊ ዕለቱን ሥራ የማይኖርበት በዓል አድርጓል፡፡ ከቀኑ በፊትና በኋላ የሚመጡት ሳምንታትም የኢሕአዴግ ድሎችና ግንቦት 20 የሚደለቅባቸው በዓል አከል ጊዜያት ናቸው፡፡) ከ2006 ክረምት እስከ 2007 ዓ.ም. ጥቅምት አካባቢ ድረስ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሥልጠና›› እየተባለ ለከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች፣ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና ለመንግሥት ሠራተኞች በተሰጠ ‹‹ትምህርትም›› ውስጥ ‹‹የአዲሲቱ ኢትየጵያ ታሪክ የሚጀምረው ከደርግ ውድቀት በኋላ›› መሆኑን ተምረናል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግልና አገራዊ ህዳሴያችን›› (የተባዛ ጥራዝ) ሐምሌ 2006፣ ገጽ 24፡፡ ኢሕአዴግ ይህ ለራሱ የሰጠው ሞገስ ሲቀር የሚቀር (እንደ አፄ ኃይለ ሥላሴና ደርግ ከታሪክ ካለመማር የመጣ) ነው? ወይስ ከእሱ በፊት የነበረውን ዘመን ሁሉ ጨለማ ውስጥ የሚከት ተዓምር በ24 ዓመታት ቆይታው ውስጥ አከናውኗል? ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ፣ በሽግግር ጉባዔና በሽግግር መንግሥት፣ በሕገ መንግሥት ማርቀቅና በኢፌዲሪ ምሥረታ ጉዞ ውስጥ ሁሉ ሰላም ሲያምስ የነበረውን የቡድኖች ሹኩቻ፤ እንዲሁም፣ ከደርግ መፈንገል አንሥቶ በግልጽና በሥውር በኢትዮጵያ ላይ ተሠማርቶ የነበረውንና በዘግናኙ የ1991/92 ዓ.ም. ጦርነት የተደመደመውን የሻዕቢያን የዘረፋ ዘመን፣ ከ1983 ግንቦት 20 የሕዝቦች ልደትነትና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መጀመሪያነት ጋር ማስታረቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

የቀሪውን ዓለም ልምድ እንተወውና የኢትዮጵያ የአዲስነት ታሪክ ከቀዳሚ ጊዜያት ጋር ሳይነካካ ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን ጀመረ ለማለትስ አንዱ በሌላው ላይ እየተመረኮዘና እየታከለ የሚጓዝ የታሪክ ባህርይ ያመቸናል? በምኒሊክ ጊዜ ብቅ ብቅ ያሉት ‹‹የዘመናዊነት›› ጅምርማሪዎች ሁሉ የአዲስ ታሪክ ገጽታዎች ናቸው፡፡ ለጥቆ በተፈሪ/ኃይለ ሥላሴ ዙሪያ በመሰባሰብ ‹‹ሥልጣኔ››ን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የተካሄደው ጥረትና እንቅስቃሴ የአዲስ ለውጥ ታሪክ አንድ አንጓ መሆኑ ሊካድ አይችልም፡፡ የአዲሷ ኢትዮጵያ ታሪክ መነሻ እስከ ዓድዋ ድል ድረስ ከዚያም አልፎ እስከ ቴዎድሮስ ድረስ ይረዝማል ብሎ የሚከራከርም አይታጣም፡፡ እንዲያውም የቴዎድሮስ ‹‹ጥበብ አምጡ፣ መድፍ ሥሩልኝ…›› ባይነት እንደ ሥልጣኔ ዕይታና ትልም በምኒሊክና በተፈሪ ጊዜ እንኳ ጎልቶ አልወጣም ነበር፡፡ ጥበብ ከማስገባት ይልቅ አይሎ የነበረው የአውሮፓ ቁሳቁስንና አኗኗርን የማስገባት ሩጫ ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ አስተሳሰቡም ሸቀጡም፣ ባህሉም መጣ፡፡ በስተኋላ ፋብሪካ ብጤውም ተንጠባጠበ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግን በመሠረቱ ያረጀ ታሪክን ከመኖር አላመለጡም፡፡ ከፋሺስት ኢጣሊያ መምጣት በፊት የነበረው የለውጥ ደፋ ቀና ንጉሠ ነገሥታዊ አዛዥ-ናዛዥነት ከማጥበቅ በቀር አሮጌውን የገባር-ጭሰኛ ሥርዓት አላናጋም፡፡ ይህ ቀርቶ ቅኝ ግዛታዊ በቀልን ለመመከት የሚያስችል መሰናዶ ለመሰነቅ እንኳን አላበቃም፡፡ ፋሸስት ጣሊያን ከተባረረ በኋላም ያው አሮጌ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት ነው ተመልሶ የተዘረጋው፡፡

የ1966 ዓ.ም. አብዮት ስንት ጥያቄዎች በየአቅጣጫው ሲያነሳ ማኅበራዊ ህሊናን የገነዘው የኃይለ ሥላሴን ተመላኪነት ቦተራርፎ ማለፍ ተስኖት ነበር፡፡ ደርግ መጥቶ ለራሱም እየፈራ ሲቦተራርፍለት ደግሞ ውጤቱ የአብዮቱን መክሰርና የወታደራዊ አምባገነንነት መቋቋም ሆኖ አረፈ፡፡ የባተተውን የገባር ጭሰኛ ሥርዓትና መሳፍንታዊ-መኳንንታዊ ጌትነትን ነቃቅሎ የመጣል ትግሉ ግን የሚቀለበስ አልነበረም፡፡ የደርግ ስም ተለጥፎባቸው ሥራ ላይ የዋሉት የገጠር መሬትና የከተማ ቦታና ቤት አዋጆች የዘመና ዘመናቱን የገባርነት ሥርዓት ከኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሰረዙ (የመላ ኢትዮጵያ አሳረኛ ሕዝቦች ‹‹ዋይ ዋይ ባላበት!›› እያሉ የፈነደቁበት፣ ‹‹ደርጉ››፣ ‹‹አብዮት››፣ ‹‹ነፃነት›› የሚሉ ስሞች ለልጆች እስከማውጣት ስሜትን የነዘሩ) የአዲስ ታሪክ ወሳኝ ምዕራፎች ናቸው፡፡  ይህ ታሪካዊ ለውጥ ግን ወደ አዲስ ሕይወት አልወሰደም፡፡ በፀረ ፊዩዳልና በፀረ ወታደራዊ አምባገነንት ትግሉ ጊዜ ውስጥ የነበረው አታጋይነት እንኳ ከአሮጌ ወጥመድ አላመለጠም ነበር፡፡ ጉልህ የትግል ይዞታ የነበረው ኢሕአፓ ለእሱ ካላደሩ በቀር የተለየ አቋም ይዞ በተቃውሞ ትግል ውስጥ መኖርን የማይሻ፣ ተመላኪነትን የሚወድና ትችትን ከጥቃት የሚቆጥር የተቃውሞ ‹‹አፄ›› ነበር፡፡ አስመላኪነትና አምልኮ በድርጅቱ ውስጥ ሐሳቦች እንዳይንሸራሸሩና አስጨራሽ የትግል መንገድ እንዳይታረም በመከልከሉ፣ (ችግሩን ያስተዋሉ መሪዎችና አባላትም ሌላ መፍትሔ ከመውሰድ በመዘግየታቸውም ምክንያት)  ለብዙ ወጣቶች እልቂትና ላገር  የተረፈ ውድቀት ደረሰ፡፡ ኢሕአፓ የገነነበት ኅብረ ብሔራዊ የተቃውሞ ትግል ከተመታ በኋላም የደርጉ ቁንጮ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በሶሻሊዝም የሚምሉ – የማይተቹ፣ የማይከሰሱ፣ የተነፈሱት ሁሉ በየስብሰባው፣ በየጋዜጣውና በሬዲዮው እየተጠቀሰ የሚወደሱ ‹‹አፄ›› ሆነው ወጡ፡፡ የኢትዮጵያ አርሶ አደር ገባርነትና ጭሰኝነት ቢቀርለትም፣ ትርፍ ምርቱን በመንግሥት በሚወሰን ርካሽ ተመንና ኮታ በኩል፣ እንዲሁም እቀዬው ድረስ መረባቸውን ለዘረጉ የ‹‹ማኅበሩ›› መኳንንቶች እፍ እንካ ከማለት አላመለጠም ነበር፡፡ በአብዮታዊ ቃላት ከመብለጭልጩ በቀር ያው አጎንብሶና አዘጥዝጦ ማደር፣ በጉቦና በእጅ መንሻ በ‹‹እከክልኝ ልከክልህ›› መተዳደር አጠቃላይ የኑሮ ዘይቤ ሆኖ ቀጠለ፡፡ አሮጌ ታሪክ እንደገና የዕለት ተዕለት ኑሮ ሆኖ አረፈ፡፡

ከላይም ከሥርም የነበሩት የያኔ የፖለቲካ ተዋንያን ለልማቱም ለጥፋቱም ኃላፊነቱን በተግባር ተጋርተውና ተጣምዶና ተነጣጥሎ ዳግመኛ ያለ መጠፋፋት ትምህርትን በአጥንትና በደም ጽፈው አልፈዋል፡፡ ተርፈው በትግሉ ሜዳ ውስጥ የቀሩ ወገኖች ፊት ለሆነው ሁሉ ድርሻን ከመጋራት ባለፈ፣ ይህንን ትምህርት ከመሬት አነሱት? ጥያቄው እነ‹ኦነግ›፣ ‹ሕወሓት›፣ ‹ሻዕቢያ›፣ ወዘተ. ይመለከታል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ‹‹የሥልጠና›› ወረቀት ስለሕወሓት እንዲህ ይለናል፡-

‹‹ከመኢሶንም ሆነ ከኢሕአፓ በተለየ አኳኋን በብሔርም ሆነ በሌሎች የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ላይ በዘላቂነት ትክክለኛ አቋም ይዞ ትግሉን የጀመረ … የአሁኑ ሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ… ነበር

‹‹ለአጭር ጊዜ የቆየ የትግራይ ነፃ መንግሥት የመመሥረት አቅጣጫ እከተላለሁ ያለበት ወቅት የነበረ ቢሆንም፣ ይህንን ስህተት በፍጥነት አርሞ በዴሞክራሲያዊ አንድነት ማዕቀፍ ለብሔራዊ እኩልነት የሚካሄደውን ትግል በከፍተኛ ደረጃ ለማጠናከር የቻለ ድርጅት ነው፡፡

‹‹ሕወሓት በመላ አገራችን ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ የሚካሄደውን ትግል ለማቀጣጠል የሚያስችሉ አቋሞችና የጠሩ ሐሳቦችን ለማመንጨት ልዩ ሚና የተጫወተ ከመሆኑም በላይ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ያልተመጣጠነ በነበረበት ወቅት ከባዱን የትግል ሸክም በተሟላ የኃላፊነት መንፈስ በመሸከም ከፍተኛ መስዋዕት የከፈለና አኩሪ የትግል አስተዋፅኦ ያደረገ… የትግራይ ሕዝብም ከባዱን ሸክምና መስዋዕት በጋራ የተሸከመ ሕዝብ ነው፡፡›› (ሰረዞች የተጨመሩ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግልና አገራዊ ህዳሴያችን፤ የተባዛ ጥራዝ፣ 21-22)

በቅድሚያ፣ የ1960ዎች ለውጥ ፈላጊዎች በነበረባቸው የብስለትና የትግል ልምድ ማነስ ምክንያት የትኞቹም ቢሆኑ ከድክመትና ከስህተት ያላመለጡ፣ እንደ እውነቱም ማንኛቸውም ተመፃዳቂ መሆን የማይችሉ ሆነው ሳለ፣ (ያውም ውስጥ አዋቂ እንደሚነግረን የተሐሕት/ሕወሓት ትጥቅ ትግል ከተጀመረ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ፕሮግራም እንኳ ያልነበረ ሆኖ)፣ (ገብሩ አሥራት፣ 2007፤ ገጽ 40) በዚያን ጊዜ ከነበሩት ድርጅቶች ሁሉ ትክክለኛ የእኔ ነበር እያሉ መገበዝ (በሕወሓት 40ኛ ዓመትም ሲደጋገም ነበር) ለሥልጣን ትርፍ ሲባል የነኮካ ኮላ ዓይነት ማስታወቂያ ከመርጨት የላቀ ዕርባና የለውም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፣ አንባቢ አመዛዝኖ የራሱን የህሊና ፍርድ እንዲወስድ ጥቂት ነጥቦችን እናስፍር፡፡ ከጥቅሶቹ እንደምናጤነው ነፃ መንግሥት ከመመሥረት ፍላጎት በቀር ሌላው (በብዙ ብሔረሰባት ተሳትፎ የሞቀ የከተማ ቅዋሜ ትንንቅ በነበረት በዚያ የካቲት 1967፣ የብሔር ጥያቄንና ጥቂት ጠመንጃን ይዞ ከጣት ቁጥር ባልበለጠ ብዛት ወደ ብሔረሰባዊ አካባቢ በረሃ መግባት ሁሉ) ትክክል መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ዋናው ቅራኔና አታጋዩ ጥያቄ የብሔር ጥያቄ›› የሚለውን ደግሞ ፈንከት እናድርገው፡፡ የብሔር ጭቆና የሚባለው ዞሮ ዞሮ የአንድ ወይ የጥቂት ብሔረሰቦች በብዙዎቹ ላይ የበላይ የመሆን ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ብሔረሰባዊ የበላይነት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ ወዘተ. ቢባል ዞሮ ዞሮ ገዢ ክፍልን የሚመለከት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የብሔር የበላይነት ይዘቱ መደባዊ ነው፡፡ በዚያ በደርግ ጊዜ የነበረው የመደብ ጭቆና ይዘት በቀጥታ የወታደራዊ ፈላጭ ቆራጭነት ጥርስ ያለው (ዘረፋ፣ የመብት አፈና፣ እስራት፣ መሳደድ፣ ግድያ ሁሉ ያለበት) ረገጣ ነበር፡፡ በዚህ ረገጣ ውስጥ ያለውን ብሔረሰባዊ ድርሻ ቢያስቡት ጠብ የሚል ነገር አልነበረም፡፡  የነበረውን ፈላጭ ቆራጭነት እንዳለ ታግሎ ከመጣል ውጪ ወደ ነፃነትና ወደ ብሔረሰብ እኩልነት መሄጃ አማራጭ አልነበረም፡፡ በጊዜው ከብሔር የበታችነት ይበልጥ መድረሻ ያሳጣና ያሳምም የነበረውም ወታደራዊው ፈላጭ ቆራጭነት ነበር፡፡ ሕወሓትም ዋናው ቅራኔ የብሔር ነው እያለም ቢሆን ይህንኑ አምባገነንነት በመታገል ላይ ከማተኮር አላመለጠም ነበር፡፡ በአጭሩ ሕወሓት ዋናው ቅራኔ የብሔር ነው ይል የነበረው እውነቱ ያ ሆኖ ሳይሆን በብሔር የተቧደነ ብሔርተኛ ስለነበረ ነበር፡፡

የደርግን አምባገነንነት አዝረጥርጦ ለማሸነፍስ ያኔ ለግልጽና ለህቡዕ ሰላማዊ ትግል ምቹ ፖለቲካዊ አየር በነበረባቸው ከተሞች ትግልን ማጦፍ ይሻል ነበር? ወይስ በተናጠል ብሔሬ እያሉና አሮጌ ጠመንጃ እየያዙ በረሃ መግባት? ያኔ ከኦሮሞ፣ ከአማራ፣ ከትግሬ፣ ከሲዳማ፣ ከጉራጌ ወዘተ. የወጡ ግፍ በቃኝ ባዮች በከተሞች አሟሙቀውት የነበረ የፖለቲካ ትግልና በዚያ ወቅት ወደ ጫካ የሮጡት ብሔረተኞች ከነመኖራቸውም አስታዋሽ ያልነበራቸው መሆኑ ራሱ ማን ትክክል እንደነበር የሚመሰክር ነው፡፡ ኢሕአፓም ሆነ እነ መኢሶን ተንኮታኩተው የወደቁት ኢሕአፓ በከፈተው የግድያ ሥልት መጠመዳቸው ተባብሶ ስለተፋጁ እንጂ፣ የከተማ ፖለቲካዊ ትግል ላይ ስላተኮሩ ወይም ደርግን ስላልቻሉት አልነበረም፡፡ ከሥርም ሆነ ከላይ ያካሄዱት ትግል የመደጋገፍ ብልህነት ቢኖረው ኖሮማ አሸናፊነታቸው ከ1969 ዓ.ም. አያልፍም ነበር፡፡ ከትንሽ ከተማ እስከ አዲስ አበባና እስከ ደርግ ጽሕፈት ቤት የተዘረጋው የኢሕአፓ ድብቅ መረብ ከመኢሶንና ከወዝ ሊግ መረብ ጋር ገጥሞ ቢሆን ኖሮ፣ አንድ ሁለት ግለሰቦችን በሉ ወደቤታችሁ ሂዱ ከማለት በቀር የቀራቸው ምን ነበር? ኢሕአፓ በነተፈሪ በንቲ የሞከረው የቤተ መንግሥት ግልበጣ ለነመኢሶንና ለወዝ ሊግ የሞት ሽረት ዕጣ ባይሆን ኖሮስ ብሎ ማሰብም ያው ሌላ ግልባጩ ነው፡፡

ገጠር ገብቶ ስለጠመንጃ፣ ስለተዋጊ፣ ስለስንቅ፣ እያሰቡ ከትንሽ ውጊያ ጀምሮ ኃይል እያበጁ፣ ነፃ መሬት እየፈጠሩና እያሰፉ፣ እያፈገፈጉ ተንፏቆ ተንፏቆ ከረዥም ዓመታት በኋላ ማዕከላዊ ከተማ የመግባት ሥልት (በቻይናና በሌሎችም ሥፍራዎች እንደሆነው የጎመራ የለውጥ አየር በሌለበት ደረጃ ላይ ተጀምሮ የማያስፈልግ ውድመትና መስዋዕትነት የሚከምር በመሆኑ) የተሳሳተ የትግል መንገድ ነው፡፡ (በኃይል የማይመጣጠኑት የውጭ ወረራ ደርሶ ነፃነት የታጣበትና ረዥም ትግልን ግድ የሚያደርግ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳ ከሕዝቡ የነፃነት ሙቀትና ከአቅም ጋር የተገናዘበ ሕዝብን ላለማስጨፍጨፍ ጥንቁቅና ብልህ አረማመድን የሚጠይቅ ነው፡፡ ከኢሕአዴግ ሰዎች አካባቢ ሲባል እንደምንሰማው፣ ያኔ ደርግ በውዴታ ሥልጣን የሚለቅበት ሁኔታ ወይም ዴሞክራሲ ስላልነበር ከትጥቅ ትግል ውጪ አማራጭ አልነበረም እያሉ ለአምባገነንነት የትጥቅ ትግል ‹‹መድኒት›› ማዘዝ አለማስተዋል ነው፡፡ ያውም በጥቂት ቀናትና ሳምንታት የአደባባይ ቅዋሜ አምባገነኖች ሲናወጡ የሚታይበት ዘመን ውስጥ እየኖሩ!)

በ1960ዎች የነበርን ታጋዮች በዚያ ወቅት ይህንን ለመገንዘብ አለመቻላችን የማያስገርምና የሚጠበቅ የነበር ቢሆንም፣ ዳክሮ ዳክሮ ሥልጣን ለመያዝ መቻል ስህተትነቱን አይቀይረውም፡፡ ይህ በውል መጤኑ ለዛሬያችንም አስፈላጊ ነው፡፡ ሻዕቢያና ሕወሓት የሄዱበት በኅብረ ብሔር አገር ውስጥ የአንድ አካባቢ ወይም ብሔረሰብ ጉዳይ ላይ ተገድቦ የሚካሄድ ረዥም የትጥቅ ትግልማ የባሰ ችግር ያለበት ነው፡፡ የስብስቡና የዓላማው አካባቢያዊ ውሱንነት ወንዝን አልፎ ሌሎች ክፍሎችን ለማንቀሳቀሰም ሆነ ቀጥታ ገዢውን ጥሎ ሥልጣን ወደ መያዝ ለማለፍ ወጥመድ ይሆናል፡፡ ወይ ወጥመዱን ለማለፍ የሚሆን ካባ በመስፋት ወይም ስውር ቀዳዳ በመፈለግ ለመትረክረክ ይዳርጋል፡፡ የሻዕቢያ ሕወሓትን ተከልሎ ወደ አዲስ አበባ መምጣትም ሆነ የሕወሓት ‹‹ኢሕአዴግ››ን መፍጠር ከዚህ አኳያ ሊብራሩ የሚችሉ ናቸው፡፡

የትግራይ ነፃ መንግሥት የመመሥረት ስህተትን ‹‹በፍጥነት አርሞ… ለብሔራዊ እኩልነት የሚካሄደውን ትግል በከፍተኛ ደረጃ›› ሕወሓት አጠናክሯል ማለትና ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ያልተመጣጠነ በነበረበት ወቅት ከባዱን የትግል ሽክም….›› ተሸከመ ማለት የሚጋጩ ከመሆናቸውም በላይ፣ ለብዙ ጥያቄዎች አሳማኝ መልስ መስጠት ይሳናቸዋል፡፡ ስህተቱን ካረመ በኋላ ወዲያው ኅብረ ብሔራዊ ቅንብር ፈጥሮ ነፃ መሬቱን የኢትዮጵያ አቀፍ ትግል መናኸሪያና መንደርደሪያ ለምን አላደረገውም? ኢሕዴግን ለመፍጠር የአዲስ አበባ መንገድ ወለል እስኪል ድረስ ለምን ቆየ? እነኦሕዴድን የመሰሉ ድርጅቶችስ ለመፍጠር ለምን ዘገየ? ከየብሔረሰብ ታጋዮች ለማሰባሰብ የስደት ሜዳው ራሱ ከሱዳን እስከ አውሮፓና አሜሪካ ድረስ ችግር ነበር? ለብቻ መታገልና ብዙ መስዋዕት መሆን ግድ ነበር ወይስ ስህተት ነበር? የተመጣጠነ ትግል የጎደለው ሌላው ሕዝብ አልታገል ብሎ ወይስ የሚያታግል ጠፍቶ? ሸክም የበዛበት ሕወሓት ሸክሙን የሁሉም ለማድረግ ምን የተጨበጠ ድርሻ አዋጥቷል? ገብሩ አሥራት እንዳጋለጠው ኢሕዴን ‹‹የካቲት›› ከሚባል ቡድን ጋር እንዳይገናኝ ሕወሓት ይከለክል የነበረው (ገብሩ አሥራት፣ 2007፤ ገጽ 109) ለምን ነበር?Anchor ሕወሓት ካንጀቱ ቢያንስ ከ1977 ዓ.ም. በኋላ እንኳ ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር የሚቻለውን ያህል ቅንጅት ፈጥሮ ቢሆን፣ ወይም ኅብረ ብሔራዊ ቅንብሩን አስፍቶ ቢያንስ በአማርኛ ጭምር ሁሉን አቀፍና ብልህ ቅስቀሳ አድርጎ ቢሆን ኖሮ ለትግል የሚጎርፈውን የብሶተኛ ብዛት ነፃ መሬቱ ይችለው ነበር? የውጊያ አጋጣሚ ሳይጠብቅ ሊፈልስ ይችል የነበረውንስ ወታደር መገመት ይቻል ነበር? የላሸቀው የደርግ የፀጥታ አውታር አሳድዶ የማይደርስበት የከተማ ድብቅ መዋቅር እስከ መፍጠር ድረስ ትግሉን ማርዘም ቀላል አይሆንም ነበር?

ለመሆኑ ‹‹ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ የሚካሄደውን ትግል ለማቀጣጠል የሚያስችሉ አቋሞችንና የጠሩ ሐሳቦችን ለማመንጨት ልዩ ሚና የተጫወተ›› የተባለለትስ ምኑ ነው? ከደርግ ኢሰፓ ግፍ መቼ ተላቅቄ በተነፈስኩ በሚል መንገሽገሽ ላይ ‹‹የብሔር መብት እስከ መገንጠል›› እያሉ መደስኮርና የኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ጥያቄ አድርጎ ማቅረብ የጠቀመው የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የዴሞክራሲ ትግል ለማደናበር ወይስ ለማቀጣጠል? ‹‹ሶሻሊስት›› የሚባል ጎራ ከፈራረሰ ወዲያ በ1983 ዓ.ም. ውስጥ ሳይቀር ‹‹ማርክሲስት ሌኒኒስት አመራር›› ምንትስ እያሉ መቀባጠርስ የሕዝቦች ትግል ማቀጣጠል ወይስ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀመር ጫካ ገብቶ እንደቀረና አውሮፕላን ሲመጣ እንደሚደበቅ አልሰሜ ዘመንና እውነታ የጠፋበት መሆን? እነዚህን ከመሰሉ ችግሮች ሕወሓት ተላቆ የኤርትራን ጉዳይ ቅኝ ቅብጥርሶ ሳይል፣ በድርድርና ሁሉም አማራጮች በቀረቡበት ውሳኔ ሕዝብ የሚፈታበትን የመፍትሔ አቋም ወስዶ፣ የብሔር ጥያቄን የዴሞክራሲ አካል አድርጎና መብቶችን ከማወቅ ጋር በማያሻማ ሁኔታ በዴሞክራሲያዊ ነፃነትና አኩልነት ላይ ለሚቋቋም አንድነት ተከራካሪ ሆኖ ከ1980 ዓ.ም. ወዲህ እንኳ መላ ሕዝብ አቀፍ የትግል ቅንጅት ላይ በነፃ መሬቱም፣ በስደት አካባቢዎችም፣ በሬዲዮውም ቢሠራ ኖሮ ሬዲዮውን እየጎረጎ ሲንቆራጠጥ የነበረን ብሶተኛ ይዞ፣ ሲቪልና ወታደር የተመመበት የከተማ ማዕበል ከበረሃ ሆኖ መምራት በቻለ፡፡ ድል ለመጨበጥ ከሻዕቢያ ጋር መጣበቅ ባላስፈለገው፡፡ የመላ ሕዝቦች ድጋፍ ማነስና በጥርጣሬ መታየት አጠገቡም ባልደረሰ፡፡ የአንድ ብሔር/ብሔረሰብ ገዢ ክፍልን ለይቶ በጥርጣሬም ሆነ በጥቃት በትር ለመጥመድ ባልተቻለ፡፡ ከአንድ አካባቢ ጋር የተያያዘ ምርኮ ሰብሳቢነትም ሆነ በታጋይነት ጥንቅር ውስጥ ያገጠጠ ያንድ አካባቢ ተዛነፍ ችግር በተቃለለ ነበር፡፡ እነዚህን መሰሎቹ ችግሮች በቅጡ ሳይታረሙ ወደ አዲስ አበባ መገስገስ ቀጠለ፡፡ የግዳጅ ስግደትና አምልኮ ቅስሟን አድቅቆ አዕምሮዋን አደንዝዞ ያማቀቃት አዲስ አበባም በመጨረሻ የመንጌ ‹‹አፄነት›› ሬሳ ቀረሽ ሲሆን፣ ሬሳ ከቤተ መንግሥት ለማውጣት የሚያስችል የፖለቲካ ብልኃትና አሰባሳቢነት ከየት ታምጣ? ጭራሽ ከፈረጠጠ በኋላም ባዶ ቤተ መንግሥት ውስጥ ለመግባት የሚያስችል አቅም ታጥቶ የሚጎርፈው ረሃብተኛ ወታደር እንዴት ያደርገኝ ይሆን እያለች በፖለቲካው እጅግም ያልጣማት፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ መጥቶ የሚያደርገውን እስከሚያደርጋት ከመጠበቅ ሌላ አማራጭ አልነበራትም፡፡

ሥልጣን ተይዞና የሚሆነው ሁሉ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ የደደቢት ትግል የኢትዮጵያ የትግል ታሪኮች አካል እንጂ ዋነኛ የኢትዮጵያ ታሪክ አይደለም፡፡ የማይመለስ ታሪክ ላይ ተቸንክሮ ወቀሳ ሲያላዝኑ መኖር ወይም አይነቃብኝም በሚል አዕምሮ ታሪክን ከልሶ ለመጻፍ መሞከር፣ ወይም ደደቢት የተገባው ለኢትዮጵያ ታስቦ እንደነበር ማስመሰል ማንንም አይጠቅምም፡፡ በተቃዋሚውም ሆነ በኢሕአደግ በኩል ምንም ተባለ ምን ኢሕአዴግን መፍረድ የምንሻው ባለፈ አመጣጡ ሳይሆን በዛሬ ባህርዩ ነው፡፡ ለኢሕአዴግም የሚበጀው ታሪክ ከመፈልሰፍ ፈንታ ዛሬ ላይ ማተኮር ነው፡፡ ምን ያህል እንከን እየጣልኩ ተራምጃለሁ? ምን ያህል የመላ ኢትዮጵያ ትርታ መሆን ችያለሁ? ምን ላይ አንክሻለሁ? የሚሉ ጥያቄዎችን በአጥጋቢ ደረጃ ቢመልስ ስኬቱ ራሱ የታሪክ ገድል ጸሐፊና ሐውልት ሠሪ ይዞለት ይመጣል፡፡

ሕወሓት የመሰጠንቅ አደጋ ከደረሰበት በተሃድሶ የአንጃ ሽታን የማጥራት ሥራ ከተካሄደ በኋላ የ1994-95 ዓ.ም. የመንግሥት ሠራተኛን ያዳረሰ ፕወዛና ግምገማ ከተከናወነበት ምዕራፍ ወደዚህ፣ በአሥራ ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የታየው የልማት ሩጫ ያለፉት መንግሥታት የማይወዳደሩት ነው፡፡ ግብርናውን በዓይነት በማበራከት ምርታማነትን በማሳደግና አርቢነትን ከአራሽነት ጋር በማጎዳኘት ረገድ የሚደረገው መጣጣር እንከን ባያጣውም፣ ወደፊት መጓዙን ቀጥሏል፡፡ በቱሪዝምና በአገልግሎት ዘርፍ፣ በኢንዱስትሪ ግንባታም ዕድገትና ጥድፊያ አለ፡፡ እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ መብራት፣ ውኃ፣ ስልክ የመሳሰሉትን አገልግሎቶች በየአካባቢ የማዳረሱ ሥራ ከእጥረትና ከጥራት መጓደል ባይላቀቅም እየጨመረ ነው፡፡ በመሠረተ ልማት የሚካሄደው ግንባታ በተለይ በመንገዶች አውታር (ሩቅ ተልሞና ጥራት ጠብቆ የማያዳግም ሥራ የመሥራቱ፣ ተንከባክቦ ዕድሜ የማርዘሚያ አቅምና ሥልቱ አብሮ የመፈጠሩ ነገር ከማሳሰቡ በቀር) አስገራሚ ነው፡፡ አጠቃላይ ኢኮኖሚው በዕድገት ውስጥ መሆኑም የማይታበል ነው፡፡ የተያዘው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ከተፋሰስ ልማትና ከታዳሽ የኃይል ምንጭ ግንባታ ብዙ ፈቀቅ ያላለ (የወንዞቻችንና የከርሰ ምድር ሀብትን በተለይ በከተማ ከብክለት ገና ያልጠበቀ፣ ያሉትንና የሚመጡትን ፋብሪካዎች ከበካይነት መስመር ገና ያላወጣ) ቢሆንም፣ ቢያንስ በነገ አቅጣጫ ውስጥ እንድናነጣጥርና እንድናስብ የሚረዳ ነው፡፡

በመንግሥታዊ መዋቅር ረገድም በኢትዮጵያ ታሪክ የፌዴራላዊ ሥርዓት የተደራጀው በዚሁ በዘመነ ኢሕአዴግ ነው፡፡ በዚህ መዋቅር ውስጥ ያለው ይዘት ምንድነው ለሚለው ጥያቄ ግን ፖለቲከኞቹ የሚሰጡት መልስ የሰማይና የምድር ያህል የተራረቀ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከግንቦት 1987 ዓ.ም. ታሪካዊ ምርጫ ጀምሮ ሕዝቦች መንግሥታቸውን አቋቁመዋል፣ ራሳቸውን በራሳቸው በዴሞክራሲ ማሰተዳደር ጀምረዋል ይላል፡፡ አሁን እንዲያውም ዴሞክራሲ ባህል እየሆነ ነው ባይ ሆኗል፡፡ (የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ ገጽ 20) በተቃራኒው ደግሞ ዴሞክራሲ ከስሙ በቀር መቼ አለና? በፌዴራላዊ መልክ የተዘረጋውም ገዥነት የአንድ ፓርቲ አምባገነንት ነው ይባላል፡፡ የዴሞክራሲ ጥያቄ ገና 1966 ዓ.ም. ላይ እንደተገተረ ነው? የአምባገነንነትንና የአምልኮ ዘመንን እንደገና በሌላ መልክ እየኖርን ነው? ወይስ ዴሞክራሲን? እውነቱ የቱ ጋ ነው? ተሃድሷችን ምን ያህል አእምሯችንን ዳብሷል? ከ1960ዎቹ የፖለቲካ ልምዳችን ተምረናል? ወይስ ቃላት ከመቀየር በቀር በመጠማመድ ውስጥ መዳከሩ ቀጥሏል? ትምክህትና ጠባብነት እየተፍተለተሉ የፀብ እሳት የመጫራቸው አደገኝነት በ24 ዓመታት ውስጥ ያልመከነው ለምንድነው? ሊለመጥጡንና ሊያናውጡን የሚችሉ ረመጦች አመድ ለብሰው አሉ? ወይስ ጠፍተዋል?

ከተፈቀደልኝና የአንባቢዎችም መልካም ፈቃድ ከሆነ ቀጣዩ ጽሑፌ ከፍትሐዊና ከዴሞክራሲያዊ ትድድር አኳያ አሳሳቢ ጥያቄዎችን በየፈርጁ እያነሳ ሰላምን፣ መከባበርንና ግስጋሴን የሚተናኮሉ ችግሮችን እያሳየ፣ አብሮም ይበጃሉ የሚላቸውን የማቃለያ ሐሳቦች ይሰነዝራል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...