Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ወደ 14 በመቶ ወርዷል››

አቶ ኢሳያስ ባህረ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት

አቶ ኢሳያስ ባህረ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ ማኔጅመንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በባንኪንግ ኤንድ ፋይናንስ ከእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌልስ አግኝተዋል፡፡ በሥራ ዓለም ረዥም ዓመታትን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች፣ በስተመጨረሻም የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት ደግሞ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ ዮሐንስ አንበርብር በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያለፉት አምስት ዓመታት የሥራ አፈጻጸምና ችግሮቹ፣ እንዲሁም ቀጣዮቹን የአምስት ዓመታት ዕቅዶች በተመለከተ ከአቶ ኢሳያስ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከተመሠረተ ከመቶ ዓመት በላይ ነው፡፡ በተለያዩ መጠሪያ ስሞች ሦስት መንግሥታትን አሳልፏል፡፡ የመንግሥት የፖሊሲ ባንክ እንደሆነም ስምምነት አለ፡፡ ለመሆኑ የፖሊሲ ባንክ ሲባል ምን ማለት ነው? ይህ ተቋም በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የነበረው ተልዕኮና አፈጻጸሙ ምን ይመስላል?

አቶ ኢሳያስ፡- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የፖሊሲ ባንክ ነው የሚባልበት ምክንያት የአገሪቷን የልማት ፖሊሲ ከማስፈጸምና ከፋይናንስ አቅርቦት አንፃር የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ሆን ተብሎ በዕቅድ የሚንቀሳቀስ ተቋም ከመሆኑ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግሥት ከልማታዊ መንግሥት መርህ አንፃር የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በሚያስፈልግበት ቦታ ሁሉ በመግባት የኢኮኖሚ ሥርዓቱን፣ የገበያ ሥርዓቱን የማስተካከልና በሚፈለገው አቅጣጫ የመምራት መርህን ተከትሎ የሚንቀሳቀስ መንግሥት ነው፡፡ በዚህ በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን የሚዘጋ የፖሊሲ ባንክ አስፈላጊ መሆኑን አምኖ ድጋፍ እያደረገ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ይህም ማለት አገሪቷ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተከታታይ የሆነ ዕድገት ማስመዝገብ ትፈልጋለች፡፡ አገሪቷ የሸቀጥ ማራገፊያ ሆና መቆየትን አትፈልግም፡፡ በኤክስፖርትም እንደዚሁ ጠንካራ ሥራ መሥራት የሚችሉ የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግና ሌሎች ዘርፎች እንዲቋቋሙ ትፈልጋለች፡፡ ይህ ካልሆነ የታቀደው ዕቅድና የአገር ዕድገት ሊሳካ እንደማይችል ይታወቃል፡፡ እነዚህ ዘርፎች በፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ የታቀፉ መሆናቸውን፣ በቂ አገልግሎት የሚያገኙ መሆናቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አለ በመንግሥት በኩል፡፡ የገበያ ክፍተት ሲኖር ክፍተቱ መዘጋት አለበት የሚል እምነት አለ በመንግሥት በኩል፡፡

እንደሚታወቀው ባደጉት አገሮች ክፍተቱ ጠባብ ወይም የማይኖርበት ደረጃ ሊኖር ይችላል፡፡ በተለይ በገንዘብ አቅርቦት ረገድ ችግር የማይፈጠርበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ካደጉት አገሮች ዕድገት አንፃር፡፡ ሆኖም ግን በታዳጊ አገሮች ላይ ክፍተቱ ሰፊ ነው፡፡ ንግድ ባንኮች የሚኖራቸው የማበደር አቅም ዝቅተኛ ነው፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ወደ አንድ ቦታ ብቻ ያጋደለ ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ ለንግድ ዘርፉ የአጭር ጊዜ ብድር ማቅረብ ላይ የተንጠለጠለ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በዘላቂነት አገሪቷን ሊለውጡ የሚችሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች ትኩረት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በመንግሥት ዕቅድ የተያዙትንና የታለሙትን ፕሮጀክቶች በፋይናንስ ሥርዓቱ በቂ ድጋፍ ሳያገኙ ሲቀሩ በመሀል ላይ የመንግሥት ወደ ዘርፉ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ፋይናንስ ዘርፉ በመግባት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ክፍተቱን የመዝጋት ሥራ ይሠራል፡፡

ስለዚህ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት አድርጎ ተመሳሳይ የሆነ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አውጥቶ ነው የተንቀሳቀሰው፡፡ ይህም ማለት የብድር አቅርቦት ላይ ከፍተኛ እመርታ ለማምጣት አቅዶ ነው የተንቀሳቀሰው፡፡ ከስትራቴጂክ ዕቅድ ዘመኑ በፊት ይኼ ነው የሚባል የብድር አቅርቦት አልነበረውም፡፡ አጠቃላይ ብድሩ ከአሥር ቢሊዮን ብር የዘለለ አልነበረም፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ዕቅዱ 44 ቢሊ ዮን ብር ብድር በመፍቀድ ከዚህ ውስጥ 38 ሚሊዮን ብሩን በማስተላለፍ (Disburse) በሥራ ላይ እንዲውል አቅዶ ነው የተነሳው፡፡ አፈጻጸሙን በምንመለከትበት ጊዜ 39 ቢሊዮን ብር ብድር የፈቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ከተፈቀደ ብድር ውስጥ 26 ቢሊዮን ብር ተለቆ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ በብድር ማስመለስና መሰብሰብ ረገድ ካበደራቸው ብድሮች ወደ 13 ቢሊዮን ብር አስመልሷል፡፡ ስለዚህ በጂቲፒው ዘመን ቀደም ሲል ከነበረው አፈጻጸም ከፍተኛ የሆነ እመርታ አሳይቷል፡፡ የዕቅድ አፈጻጸሙም ከሞላ ጎደል ከ80 በመቶ በላይ ነበር፡፡ ለቀጣይ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ደግሞ ከቀደመው በላይ የተለጠጠ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት አምስት ዓመታት ባንኩ ቅድሚያ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ ትኩረት የሰጣቸው ዘርፎች የትኞቹ ነበሩ?

አቶ ኢሳያስ፡- ቅድሚያ የተሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና እና ግብርና ተኮር ማኑፋክቸሪንግ (Agro Processing) ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አተኩሮ የሚሠራው የግሉ ዘርፍ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ የግሉ ዘርፍ በእነዚህ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ሲሰማራ ተጠቃሚ ነው፡፡ በእነዚህ ቁልፍ ዘርፎች ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎውን እንዲያሰፋ የሚደረግ ድጋፍና የፋይናንስ አቅርቦት ሥራ ነው የሚሠራው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የፋይናንስ ድጋፍ በብድር ሰጥቷል፡፡ ከዚህ አኳያ የብድር አቅርቦቱን በዘርፍ ድርሻ በምንመለከትበት ወቅት፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ከ70 በመቶ በላይ የብድር ድርሻ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- የተቀሩት የግብርናና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች የብድር ድርሻና አፈጻጸማቸውስ ምን ይመስል ነበር?

አቶ ኢሳያስ፡- በግብርና ዘርፍ ላይ ቀደም ሲል እንዳልኩት ትኩረት ሰጥተን ነው የተንቀሳቀስነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ የነበረውን አረዳድ ለመቀየር ነው በአምስት ዓመታት ውስጥ መሥራት የተቻለው፡፡ ምክንያቱም የእርሻ ፋይናንስን ለማደፋፈር ብዙ ችግሮች ነበሩ፡፡ እርሻ አደጋ (Risk) አለው የሚል አመለካከት ነው ያለው፡፡ ስለዚህ እርሻን ለመደገፍ ብዙ ችግር ነበር፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ግን ተጨባጭ የሆነ ድጋፍ ለማድረግ ባንኩ ተንቀሳቅሷል፡፡ ስለዚህ ሰፋፊ እርሻዎች በዘመናዊ መስኖ ልማት የተደገፉትንና ያልተደገፉትን በመለየት፣ በጣም ሜካናይዝድ የሆኑትንና የግሪን ሐውስ እርሻዎችን ከመደገፍ አንፃር ባንኩ የራሱን ሚና ሲጫወት ነበር፡፡ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍም ትናንሽ ቢሆኑም ባለሀብቶች እዚህ ላይ እንዲሳተፉና በወተትና በወተት ተዋፅኦዎች፣ በሥጋና ሥጋ ተዋፅኦዎች፣ በቆዳ ፕሮሰሲንግ የመሳሰሉት ዘርፎች ላይ ባንኩ የብድር አቅርቦት ድጋፍ ሲያደርግ ነበር፡፡ ስለዚህ እነዚህን ዘርፎች የማነቃቃት ተሳትፎ ሲያደርግ ነበር፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ የእርሻ ብድር በመጠኑ ከ20 በመቶ የዘለለ ባይሆንም፣ በብዛት ግን በከፍተኛ ደረጃ እንዲደፋፈሩና የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ባለፉት አምስት ዓመታት ሲሠራ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል እንደገለጹት ባንኩ የመንግሥት ፖሊሲ ባንክ ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ተቋም እንደመሆኑ የባንክ ሥነ ሥርዓቶችን መከተል አለበት፡፡ ወይም ትርፋማ መሆን ይገባዋል፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን ሚዛን እንዴት ነው መጠበቅ የሚቻለው?

አቶ ኢሳያስ፡- ቀደም ሲል እንዳልኩት ባንኩ የግሉን ዘርፍ ትኩረት በማድረግ ብድር ያቀርባል፡፡ ይህንን በተሳካ መንገድ ለመፈጸም ግን ብቂ አደረጃጀት ሊኖር ይገባል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት አደረጃጀቱን አስተካክሎ ነው ወደ ሥራ የገባው፡፡ እንዲሁ ዕቅድ ብቻ አቅዶ ሳይሆን አሠራርና አደረጃጀቱን ፈትሾ፣ ልማቱን ደግፎ፣ አበድሮ ብድሩን በማስመለስ ልማቱን በቀጣይነት ለመደገፍ በሚያስችል አቋም ተደራጅቶ ነው እንዲገባ የተደረገው፡፡ ስለዚህ ከውጭ መልካም ተሞክሮዎችን ቀምሮ አሠራሩ የተሳለጠና ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርግ አደረጃጀት ይዞ ነው ባንኩ ወደ ተልዕኮው የገባው፡፡ ስለዚህ የነበሩበትን ክፍተቶች በሚዘጋበት አቋም ተደራጅቶ ነው ወደ ተልዕኮው የገባው፡፡ በመሆኑም ብድር በማስመለስ ደረጃ የብድር አቅርቦቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብድር በማስመለስ ረገድ የነበረው አፈጻጸም ወደ 90 በመቶ ደረጃ ማድረስ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ንፅፅር ግን ከዕቅዳችሁ አንፃር መሰለኝ፡፡ ይህ ከሆነ አፈጻጸሙ ትልቅ ሊመስል ይችላል፡፡ ብድር የማስመለስ ስኬት ከአጠቃላይ የተለቀቀ ብድርና ከተበላሹ ብድሮች (NPL) አንፃር ሲገመገምስ ባንኩ በምን ደረጃ ላይ ነው?

አቶ ኢሳያስ፡- ልክ ነው፡፡ ዘጠና በመቶ ብድር የማስመለስ አፈጻጸማችን ከዕቅዳችን ጋር ሲነፃፀር ነው፡፡ በአጠቃላይ ትኩረት ያደረግነው ብድር የማስመለስ ዕቅዳችንን ማሳካትና የተበላሹ ብድሮች ምጣኔ ከመቀነስ አንፃር ነው የተንቀሳቀስነው፡፡ የተበላሹ ብድሮች ምጣኔ ቀደም ሲል ወደ 40 በመቶ ይጠጋ ነበር፡፡ ይህንን ደረጃ በደረጃ እንዲቀንስ በማድረግ አሁን ወደ 14 በመቶ ለማድረስ ችለናል፡፡ ስለዚህ ይህም አንዱ አፈጻጸማችን ነው፡፡ በአጠቃላይ የብድር አቅርቦቱን በከፍተኛ ደረጃ ሲያሳድግ ብድር የማስመለስ አቅሙንና አደረጃጀቱንም ፈጥሮ ነው ያለፉትን ዓመታት የተንቀሳቀሰው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ምሳሌ ላንሳ፡፡ እርስዎ ወደዚህ ባንክ ኃላፊነት ከመምጣትዎ በፊት ይህ ባንክ ከአበባ እርሻ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ሲያበድር ነበር፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት መንግሥት የአበባ ኢንቨስትመንትን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት ነው፡፡ ይህንን ኢንቨስትመንት መሳብ ቢቻልም ባንኩ ግን የሰጠውን ብድር ማስመለስ አልቻለም ነበር፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በዚህ ዘርፍ አዋጭነት ላይ ባንኩ የተሟላ ዕውቀት ስለሌለው ነው ይባላል፡፡ አሁንስ ባንኩ እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ምን ያህል ተደራጅቷል?

አቶ ኢሳያስ፡- ልክ ነው፡፡ መንግሥት በአገሪቷ ያሉ ዕምቅ የኢኮኖሚ ዘርፎችን አይቶ ዘርፎቹን ለማነቃቃት የሚደረግ ዕቅድ አለ፡፡ ከእነዚህ ዕምቅ የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ አገሪቱ በቀላሉ በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ ልትሰማራ የምትችልበት የአበባ ዘርፍ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ የአገራችን የአየር ፀባይም ሆነ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የአበባ ዘርፍን ውጤታማ ሊያደርግ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ በዚህ የተነሳ መንግሥት የተለያዩ የድጋፍ ሥርዓቶችን በመቀየስ ባለሀብቶችን ለማበረታታት እንቅስቃሴ ሲጀምር፣ የፋይናንስ አቅርቦት ጥያቄውን የሚመልስ ተቋም ያስፈልግ ነበር፡፡ ስለዚህ የብድር ማስያዣ የሚጠይቅ የባንክ ሥርዓት ውስጥ ለአበባ ዘርፍ ማበደር በንግድ ባንኮች ዘንድ ብዙ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡ ስለዚህ በንግድ ባንኮች ዘንድ ዘርፉን ለመደገፍ ፍላጎቱ አልነበረም፣ እንዲኖር መጠበቅም አይቻልም፡፡ ስለዚህ የመንግሥት የፖሊሲ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ይህንን ዘርፍ እንዲደግፍ ያለበትን ግዴታ መንግሥት ስላሳወቀ ወደ ሥራው ተገብቷል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሥራውን ሲጀምር በተወሰነ ዕውቀት ነው የሚጀምረው፡፡ በኋላ ግን በዘርፉ ያለውን ዕድገት እያሳደገ ነው የመጣው፡፡ ስለዚህ እንደ ጀማሪ ዘርፉን ለመደገፍና ያለውን ግንዛቤ ለመቀየር ጥረት አድርጓል፡፡ ዘርፉም ሁልጊዜ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ሲጀመር ብዙ ችግሮች የነበሩበት የገበያ መዋዠቅ፣ የዕውቀት ማነስ የገጠመበት፣ ብዙ እንቅፋቶች የገጠሙበት ነበር፡፡

ያም ሲሆን ባንኩ የነበሩትን ችግሮች በመለየት፣ አጠቃላይ የሆነ ጥናት አድርጎ የማኔጅመንት ችግር ያለባቸውን በመለየት፣ ገቢ እያላቸው ብድራቸውን ለመክፈል ፍላጎት የሌላቸውን በመለየት፣ በዚህ ዘርፍ የተሰማራ ባለሀብትም ብድሩን ካልከፈለ የብድር ማስያዣውን ለሌላ ባሀብት በማስተላለፍ ብድር ማስመለስ እንደሚችል ማሳያ የሆኑትንና አንዳንድ ሆን ብለው ብድራቸውን መክፈል የማይፈልጉት ተለይተው የሽያጭ ዕርምጃ (ሐራጅ) ድረስ ተደርሶ ዘርፉን ለማስተካከል ተችሏል፡፡ ስለዚህ ከአራት ዓመት በፊት በተወሰዱት ሁሉን አቀፍ ዕርምጃዎች ዘርፉ ውጤትማ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር ድጋፍ የተቋቋሙ የአበባ ፕሮጀክቶች፣ ከሌሎች ንግድ ባንኮች በቂ የሆነ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት አቋም ላይ ደርሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዓላማም ይኸው ነበር፡፡ ሌሎች ባንኮች ለእንደዚህ ዓይነት ዘርፎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ማደፋፈር ነው፡፡ በሌሎች ንግድ ባንኮች የፋይናንስ ማዕቀፍ ውስጥ እነዚህ ዘርፎች እንዲታቀፉ በማድረግ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ጫና መቀነስ ነው፡፡ የተፈተንበትም ውጤታማ የሆነ ተሞክሮ ያገኘንበትም የአበባ ዘርፍ አንዱ ነው፡፡ ሌላው የእርሻ ዘርፍም እንደዚሁ ውጤታማነቱን እያሳየ ነው፡፡ በመሆኑም ንግድ ባንኮች በዚህ የእርሻ ዘርፍ ላይ የፋይናንስ አቅርቦት ቢያደርጉ፣ በቀላሉ ገንዘባቸውን ሊመልሱ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን እያሳየን እየሄድን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ነገር ግን ባንኩ በግብርውና ዘርፍ ላይ ውጤታማ እንዳልሆነ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በሰፋፊ እርሻዎች ረገድ የህንዱ ኩባንያ ካሩቱሪን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ባንኩ ከግብርው ዘርፍ ውስጥ የሰሊጥና የጥጥ ምርቶች ላይ አተኩሯል የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡ ይህንን ቢያብራሩልኝ?

አቶ ኢሳያስ፡- ካሩቱሪ የተባለው ኩባንያ በእኛ ባንክ ብድር ያገኘ ስላልሆነ አፈጻጸሙን አላውቀውም፡፡ ሆኖም ግን በአጠቃላይ የግብርና ዘርፍ ውጤታማ ሆኖ ሊቀጥል የሚችለው ከተፈጥሮ ተፅዕኖ የተላቀቀ አሠራር ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ ዘመናዊ አሠራር ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን የመስኖ ሥርዓት ሲኖር ካለማቋረጥ ውኃ የሚያገኝበት ሥርዓት ሲፈጠር እናግዛለን፡፡ ስለዚህ የመስኖ ግብርናን እናደፋፍራለን፡፡ አንዳንድ ዝናባማ በሆኑ አካባቢዎች የሚካሄደውን ግብርናም መደገፍ እንዳለብን እናምናለን፡፡ ስለዚህ በተለይ ሰሊጥና ጥጥን የተሟላ ዝናብ ይኖራል ባልናቸው አካባቢዎች እንደግፋለን፡፡ ይህንን ስናደርግ የሚመጣውን አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ በተወሰነ አካባቢ የዝናብ እጥረት ያጋጠማቸው አሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር የአንድ ዓመት ኪሣራ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ በቀጣይ ዓመት ግን ተስተካክሎ የሚቀጥል በመሆኑ በማንኛውም ብድር ሊያጋጥም የሚችል ችግር ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ ከማኔጅመንት የሚመጣ ችግር ሲሆን ግን ወደ ዕርምጃ እንሄዳለን፡፡

ሪፖርተር፡- የቡና ዘርፍ ትልቁ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ቢሆንም ለዚህ ዘርፍ የምታደርጉት የገንዘብ አቅርቦት ቀንሷል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው

አቶ ኢሳያስ፡- ልክ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለቡና ዘርፍ የሚሰጡ ብድሮች ነበሩ፡፡ አሁንም ኢንቨስትመንቱን ለማደፋፈር ፖሊሲያችንን አስተካክለንና ክፍት አድርገን ኢንቨስተሮችን እንጠብቃለን፡፡ ችግሩ ምንድነው? አንድ የቡና ፕሮጀክት ተቋቁሞና ተተክሎ ወደ ውጤት እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ ያለብን ረዥም ዓመታት አሉ፡፡ ለአራትና ለአምስት ዓመታት የተክል ዕድገት ጊዜ የሚያስፈልገው ፕሮጀክት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ ላይ ሲሰማሩ ደህና ካፒታል ይዘው በአራትና በአምስት ዓመታት እዚህ ፕሮጀክት ላይ ካፈሰሱ በኋላ ቀጣይነት ያለው ትርፍ ለማግኘት አምነው መምጣት አለባቸው፡፡ እኛ አዋጭነቱን እናምናለን፡፡ በአጭር ጊዜ ትርፍ የሚገኝበት እንዳልሆነም እናምናለን፡፡ ስለዚህ የዘላቂ ተጠቃሚነት ዓላማ ይዘው የሚመጡ ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ እንዲሰማሩ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ይህ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሙሉ ግንዛቤ እስኪያገኝ ድረስ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ በፖሊሲ ደረጃ ዘርፉን የሚደግፍ አደረጃጀት አለን፡፡ የተወሰኑ ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን ቁጥራቸው በቂ ነው ብለን አናምንም፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የግሉ ዘርፍ ላይ አተኩሮ ይሠራል ብለውኛል፡፡ ይሁን እንጂ ከአገር ውስጥ የግል ዘርፍ ይልቅ ለውጭ የግል ኩባንያዎች ያደላል የሚል ወቀሳ አለ፡፡

አቶ ኢሳያስ፡- ቀደም ሲል ስንጀምር ኢንቨስትመንትን በእነዚህ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ማደፋፈር ነው ዓላማችን፡፡ የምንጀምረው ከየት ነው? በአገራችን ውስጥ ያለው የካፒታል ፋይናንስ ውስንነት ይታወቃል፡፡ አገራችን የምትጠብቀው ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመርያ ደረጃ የተወሰኑ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በዚህ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ማደፋፈር ነው፡፡ ካለው የአገልግሎት ዘርፍ ትርፋማነት አንፃር የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ መግባት አይፈልጉም፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለመግባት የቆረጡበት ስትራቴጂካዊ ዓመት ነው ብለን መናገር እንችላለን፡፡ በአብዛኛው ግን ካፒታል ይዘው ከዚህ በፊት ያላቸውን የገበያ ዕውቀት ይዘው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ጀማሪ ባለሀብቶች ያስፈልጉ ነበር፡፡ ስለዚህ የውጭ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ኢትዮጵያን በአጭሩ በዓለም አቀፍ የገበያ ሰንሰለት ውስጥ እንድትገባ ለማድረግ፣ የውጭ ባለሀብቶች ከነዕውቀትና ከነልምዳቸው መጥተው በኢትዮጵያ የተመረተ የሚል ምርታቸውን ለዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ የመጀመርያውን ዕርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነበር፡፡ የውጭ ባለሀብቶች ተመልምለው ፋብሪካቸውን ነቅለው ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ወይም ደግሞ ገንዘባቸውን ይዘው መጥተው በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ አስፈላጊ ነበር፡፡ ለምሳሌ በዓለም አቀፍ የገበያ ሰንሰለት ውስጥ ልንታወቅ የቻልንበት ምክንያት የውጭ ባለሀብቶች ከጥጥ እርሻ ጀምሮ እስከ የተዘጋጀ ልብስ ድረስ ማምረት እንዲችሉ በመደረጉ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም ፕሮጀክት ቀርፀው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ውጤት ሊያገኙ እንደሚችሉ እንደማሳያነትም የሚታዩ ናቸው፡፡

ስለዚህ ባለፉት አምስት ዓመታት በብድር አቅርቦት ረገድ የውጭ ባለሀብቶች የብድር ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ በቁጥር ግን ትንሽ ነበሩ ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች አንፃር፡፡ በብድር ድርሻ መጠንም 25 በመቶ አካባቢ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ቀደም ሲል የውጭ ኢንቨስተር በማይታይበት አገር ውስጥ ከዜሮ ተነስቶ ወደ 30 በመቶ እየተጠጋ ያለ የብድር ድርሻ ይዘዋል፡፡ ይህ ማለት መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገር ውስጥ ምርትን ከማሳደግ፣ የኤክስፖርት ዘርፉን ከማሳደግ፣ ከዕውቀት ሽግግር፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግርና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ አወንታዊ አንድምታ ለመፍጠር ያደረገው ነው፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ደግሞ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በስፋት እንዴት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ በስፋት መሳተፍ ይችላሉ? የባንክን አገልግሎት ድርሻ ማስፋት ይችላሉ? እንዴትስ ተከታታይነት ያለው ዕድገት ወደ ምናስመዘግብበት ደረጃ ለመሄድ ሰፊ መሠረት ያለው የአገር ውስጥ ተሳትፎ ለመፍጠር ታቅዷል? ስለዚህ በሩ ለአገር ውስጥ ባለሀብትም ለውጭ ባለሀብትም በእኩል የተከፈተበት አሠራር ቢኖረንም፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የገንዘብ ድርሻ (Equity) ስለሚቸግራቸው በተፈለገው መልኩ መሳተፍ አልቻሉም፡፡ ይህ የፕሮጀክት ብድር ድርሻ እንደሚቸግራቸው በተደጋጋሚ በመግለጻቸውም በተወሰነ ደረጃ መልስ እየተሰጠ ነው፡፡ በብድር ፖሊሲያችን ላይ ማስተካከያ በማድረግ፡፡ በብድር ፖሊሲያችን ላይ 70/30 የብድር አሰጣጥ ሥርዓት ነው የነበረን፡፡ ይህም ማለት ፕሮጀክት አቅራቢ በትንሹ 30 በመቶውን የፕሮጀክት ወጪ ሲያቀርብ ነበር 70 በመቶው በብድር መልክ የሚለቀቀው፡፡ ይህንን በማስተካከል ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን መጀመርያ ጀምሮ ወደ 25 በመቶ እንዲወርድ ተወስኗል፡፡ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርናና በግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፎች ለመሰማራት ጥያቄ ሲያቀርቡ የእነሱ የፕሮጀክት ፋይናንስ ድርሻ 25 በመቶ፣ ባንኩ ደግሞ 75 በመቶ ያበድራቸዋል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ነገር ግን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እስከ አሥር በመቶ እንዲወርድ ይጠይቁ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ጥያቄያቸው ተመልሷል ማለት ይቻላል?

አቶ ኢሳያስ፡- አዎ፡፡ ነገር ግን ወደ አሥር በመቶ ማውረድ የሚያስከትላቸው ችግሮች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ የመንግሥት ሀብትን የሚይዝ በመሆኑ የባለቤቱን ተነሳሽነት ሊገድል ይችላል፡፡ ለዚህ ነው 25 በመቶ እንዲሆን የተወሰነው፡፡ በቀጣይ ግን በአገር ውስጥና በውጭ ባለሀብት መካከል ልዩነት ሊኖር ይገባል፡፡ ስለዚህ የውጭ ባለሀብቶች ከ30 በመቶ በላይ እስከ 50 በመቶ ፕሮጀክቱን ፋይናንስ ሲሸፍኑ የተቀረውን ባንኩ ይሸፍናል፡፡ ስለዚህ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተመቻቸ ሁኔታ ተፈጥሮ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የበለጠ ተዋናይ እየሆኑ እንዲሄዱ የሚያስችል የማሻሻያ ሥራዎችን ሠርተን ጂቲፒ ሁለትን እየተቀበልን ነው ያለነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ወደ ጂቲፒ ሁለት እንግባና የልማት ባንክ ድርሻ ምንድነው የሚሆነው? መንግሥት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ባንኩስ ይህንን ዘርፍ በመደገፍ ረገድ በአቅምና በገንዘብ ምን ያህል ዝግጅት አድርጓል?

አቶ ኢሳያስ፡- በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን የታቀደው አንዱ ትላልቅ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፋ የማድረግና የጀመርነውን ሥራ አጠናክሮ የመቀጠል፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በስፋት በዚህ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ እየተሳተፉ ሊቀጥሉ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ናቸው፡፡ የውጭ ባለሀብቶች ከፍ ያለ የፕሮጀክት ፋይናንስ ድርሻ እያወጡ፣ በማኑፋክቸሪንግና በሌሎች የመንግሥት ቅድሚያ የትኩረት ዘርፎች እየተሳተፉ እንዲቀጥሉ ማድረግ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሊዝ ፋይናንስ በኩል ሰፊ ድጋፍ ለጥቃቅንና ለአነስተኛ አምራቾች ከፍተኛ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች የማሽነሪ ካፒታል ስለማይኖራቸው፣ ማሽነሪዎችን በማቅረብ በረዥም ጊዜ ከፍለው ማሽኑን የራሳቸው አልያም ለባንኩ የሚመልሱበት ልዩ የድጋፍ ዓይነት ነው፡፡ በዚህ ልዩ አቀራረብ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ወደ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ማሳደግ ነው፡፡ እነዚህ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት አሁን እየተስተናገዱ ያሉት በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት እያደጉ ሲመጡ፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የፋይናንስ ፍላጎታቸውን ያሟላሉ ተብሎ አይታመንም፡፡

ስለዚህ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የፋይናንስ አቅም በላይ የሆኑትን ተቀብሎ እየደገፈ እንዲያሳድጋቸውና በቀጣይ በከፍተኛ የማኑፋክቸሪንግና የግብርና ዘርፎች ተሳትፈው መጨረሻ ላይ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ የሚመራ የኢኮኖሚ መዋቅርን መፍጠር ነው ዓላማችን፡፡ ስለዚህ ይህንን ቅርፅ ለማስያዝ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት በስፋት በመሳተፍ በሁለተኛው ጂቲፒ አጠቃላይ የብድር መጠናችን 20 በመቶ ለሊዝ ፋይናንስ እንዲሆን፣ በመቀጠልም እየተሻሻለ ከፍ እንዲል ነው የሚፈለገው፡፡ ስለዚህ አካሄዳችን የሚሆነው መንግሥት ሼዶችን ይገነባል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ ማሽነሪዎችን ያቀርባል፡፡ ከሌሎች ንግድ ባንኮች የሥራ ማስኬጃ ብድር ተጠቅመው ሚናቸውን እንዲወጡ ነው የታቀደው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቅርንጫፎቹን ማስፋት ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ 75 ቅርንጫፎቹን በተለያዩ የክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ አራት አቅጣጫዎች ለመክፈት እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሁተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በአጠቃላይ ምን ያህል ብድር ለማቅረብ አቅዳችኋል?

አቶ ኢሳያስ፡- የሁለተኛው ስትራቴጂክ ዘመን ዕቅዳችን በጣም የተለጠጠ ነው፡፡ በመጀመርያው ዕቅዳችን የብድር ማፅደቅ ዕቅዳችን 44 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ 112 ቢሊዮን ብር ብድር ለመፍቀድ አቅደናል፡፡ ወደ ፕሮጀክቶች ብድር ለመልቀቅ ባለፈው 38 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ አሁን ወደ 104 ቢሊዮን ብር ይሆናል፡፡ በብድር አሰባሰብ ረገድ ቀደም ሲል በመጀመርያው ጂቲፒ 14 ቢሊዮን ብር የነበረውን የብድር አሰባሰብ ዕቅዳችን ወደ 40 ቢሊዮን ብር ለማድረግ አቅደናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢኮኖሚ ዘርፎች የብድር ድርሻስ ምን ይመስላል?

አቶ ኢሳያስ፡- ቀደም ሲል እንዳልኩት 20 በመቶ የሚሆነው ብድር ለሊዝ ፋይናንስ የሚቀርብ ሲሆን፣ የተቀረው 80 በመቶ ለትላልቅ የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርና እና የግብርና ማቀነባበር ዘርፎች የሚውል ነው፡፡ እንደ ከዚህ ቀደም የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሌሎች ንግድ ባንኮች ጋር ያላችሁ ግንኙነትስ ምን ይመስላል? በተለይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር ወስደው በእነዚህ ቁልፍ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶችን በመናበብ የመደገፍ ቅንጅት፣ ወይም ደግሞ የእነዚህን ብድር ከንግድ ባንክ ወደ እናንተ የማዞር ዓይነት አሠራሮችን የመተግበር ዕቅድ አላችሁ?

አቶ ኢሳያስ፡- እኛ በቀጣዩ አምስት ዓመት ያቀድነው ከንግድ ባንኮች ጋር በጣም የተቆራኘ ሥራ ለመሥራት ነው፡፡ ይህም ማለት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የፕሮጀክት ፋይናንስ ላይ ስፔሻላይዝ አድርጎ እንዲቀጥል፣ እኛ ፋይናንስ ያደረግናቸው ፕሮጀክቶችን የአጭር ጊዜ ብድርና ተጓዳኝ አገልግሎቶችን ደግሞ በንግድ ባንኮች በአጠቃላይ እንዲስተናገዱ ነው ያቀድነው፡፡ ይህንን በቅርበት የምንሠራበት አደረጃጀት ነው የምንፈጥረው፡፡ ከብድር አሰባሰብ አንፃርም የአጭር ጊዜ ብድር ከንግድ ባንኮች፣ የረዥም ጊዜ ብድር ከልማት ባንክ ባለሀብቶች ለፕሮጀክቶቻቸው በሚወስዱበት ጊዜ የታወቀ ስምምነትን ፈጥረን፣ የብድር አሰባሰቡን የአጭር ጊዜም ሆነ የረዥም ጊዜ ብድሮች አየተከፈሉ የሚሄዱበት ሁኔታ ለመፍጠር በቅርበትና በቅንጅት መሥራት ይኖርብናል፡፡ በተናጠልም በጋራም እንዲሁም በሦስትዮሽ ስምምነት እየገነባን ለመሥራት ወጥነናል፡፡  

ሪፖርተር፡- በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በንግድ ባንኮች ላይ በጣለው የ27 በመቶ ቦንድ ግዢ የሚገኘውን ገንዘብ ልማት ባንክ ለቁልፍ ዘርፎች ሲያበድር ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ይህ የቦንድ ግዢ እንዲቆም በባንኮችም ሆነ በዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጫና እየተደረገ ነው፡፡ ይህ የፋይናንስ ምንጭ ቢቆም ዕቅዳችሁን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል?

አቶ ኢሳያስ፡- የ27 በመቶ ቦንድ ግዢ ምክንያታዊ ነው፡፡ አሁንም ይቆማል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም አሁን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተለጠጠ ዕቅድ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ስለዚህ አገሪቷ ያለመችውን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ፕሮጀክቶች መቋቋም አለባቸው፡፡ እነዚህ የረዥም ጊዜ ብድር የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁንም ይቀጥላል የሚል እምነት ነው ያለው፡፡ ሌሎች የፋይናንስ አማራጮችም እየታዩ ናቸው፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የዘሪሁን አስፋው ስሙር ምርምሮች

‹‹…በአንድ ጥራዝ ታትመው እንዲወጡ ያደረግሁት ለሥነ ጽሑፍ ተማሪዎች ስለደራሲዎችና...

የአዲስ አበበ መምህራን ማኅበር የደመወዝ ጥያቄው ምላሽ ካላገኘ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ለረጅም ዓመት ያገለገሉ መምህራን ደመወዝና...