Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቴክኖ ሞባይል በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራ ካቆመ ሦስት ወራት ሆነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

– በድርቅ ለተጐዱ ወገኖች አንድ ሚሊዮን ብር ለግሳለሁ አለ

በኢትዮጵያ ሞባይል በመገጣጠም ኢንዱስትሪ ውስጥ በመሰማራት የሚታወቀው ቴክኖ ሞባይል፣ በአሁኑ ወቅት ባጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማምረት ካቆመ ሦስት ወራት ሆነው፡፡

በአገሪቱ በተከሰተው ጊዜያዊ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ድርጅቱ ላለፉት ሦስት ወራት ያህል ምርት ያቆመ መሆኑን በማስታወስ፣ ቫትን ጨምሮ ማግኘት የነበረበትን ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሳያገኝ መቅረቱን አስታውቋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ያስከተለው ችግር ጊዜያዊ መሆኑን የሚገልጹት የኩባንያው ኃላፊዎች፣ ችግሩ በቅርቡ ይቀረፋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ነገር ግን ሌላ አማራጮችን በማፈላለግ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበትን መንገድ እያመቻቹም ነው ተብሏል፡፡

በቀን እስከ አሥር ሺሕ ሞባይሎችን የመገጣጠም አቅም እንዳለው የተገለጸው ቴክኖ ሞባይል፣ ምርቱን እንደ ሩዋንዳና ናይጄሪያ ላሉ አገሮች በመላክ አጥጋቢ ውጤት ስለማምጣቱም የኩባንያው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ወደ ውጭ የሚልከውን የሞባይል መጠን ለማሳደግና የተሻለ የትራንስፖርት ዋጋ ለማግኘት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ ይህ ከተስተካከለ ለወጪ ንግድ የሚቀርበው ሞባይል መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምርም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን በአምስት ዓመት ውስጥ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሞባይል ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ግብ የተቀመጠ መሆኑንም የኩባንያው መረጃ ያስረዳል፡፡

በተያያዘ ዜና ኩባንያው በአገሪቱ ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ለተጐዱ ወገኖች ዕርዳታ የሚውል የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚለግስ አስታወቀ፡፡ ኩባንያው ባለፈው ሐሙስ በድርቅ ለተጐዱ ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡ በዚሁ ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው፣ በኤልኒኖ ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ድርቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን በመገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ አስፈላጊ ነው ብሏል፡፡ አሁን የገጠመው ችግር የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ወገን በመሆኑ ኩባንያው ከመንግሥት ጐን በመቆም የመፍትሔ አካል ለመሆን በመወሰን የወሰደው ዕርምጃ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ኩባንያው ለመስጠት የወሰነውን የአንድ ሚሊዮን ብር ዕርዳታም የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ለአደጋና ዝግጁነት ምግብ ዋስትና ዘርፍ ክፍያውን እንድንፈጽም እንዳሳወቀን ገቢ እናደርጋለንም ብሏል፡፡

ቴክኖ በአዲስ አበባና በዓለምገና ከተሞች የተንቀሳቃሽ ስልክ መገጣጠሚያ ከፍቶ በመሥራት የቆየ ኩባንያ ነው፡፡ ምርቱን በአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ የሚገኝ ድርጅት ሲሆን፣ ከ900 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት አጋጠመኝ ባለው ጊዜያዊ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራው ለሦስት ወራት የተስተጓጐለ ቢሆንም፣ ከ900 በላይ ለሚሆኑት ሠራተኞቹ ደመወዛቸውንና ጥቅማ ጥቅማቸውን ሳያቋርጥ እየከፋፈላቸው ነው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች