Saturday, April 20, 2024

በየአሥር ዓመቱ ኢትዮጵያን የሚወዳጃት ድርቅና በትግራይ ያስከተለው ጉዳት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኤልኒኖ በሰላማዊ  ውቅያኖስ የአየር ንብረት ዑደት የሚከሰት ቢሆንም፣ ለየት የሚያደርገው በአየር ንብረት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ዓለምን የሚፈታተን መሆኑ  ነው። ኤልኒኖ  ምክንያት የሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ የሚስተዋለው በዋናነት በምድር ወገብ አካባቢ ሲሆን፣ የሰላማዊ  ውቅያኖስ ሙቀት እንዲጨምር በማድረግ  የሚከሰት ነው። ይኼ ዑደትም ኢትዮጵያን በየአሥር ዓመቱ ያጠቃታል፡፡ ዘንድሮም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ድርቅ ተከስቷል፡፡ በተለይ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ከብቶች መሞታቸው ካለፉት ሦስት ወራት ጀምሮ እየተዘገበ ይገኛል፡፡

በኢልኒኖ ክስተት ምክንያት ከፍተኛ የድርቅ አደጋ ከተጋረጠባቸው የአገሪቱ ክልሎች መካከል ዘግይቶም ቢሆን ይፋ የሆነው የትግራይ ክልል አንዱ ነው። የትግራይ ክልል ከዚህ በፊትም ኢትዮጵያን በጎበኟት የድርቅ ክስተቶች በተደጋጋሚ ከተጎዱ አካባቢዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ በክልሉ በቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣  በሃያ አንድ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ አንድ ሚሊዮን ያህል  ሰዎች  የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በምሥራቅ ኦሮሚያና በአፋር ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ በማስመልከት ሪፖርተር ዘገባዎች መሥራቱ ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ በትግራይ ክልል ድርቁ ያስከተለውን ጉዳት በማስመልከት ዮናስ ዓብይ የተለያዩ ሥፍራዎችን  ተዘዋውሮ በማየት ያቀረበው ዘገባ እንዲህ ተቀናብሯል፡፡

ጥቅምት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀትር ላይ አናት በሚበሳው ጠራራ ፀሐይ  አዛውንቱ አርሶ አደር አፈራ ኃይሉ፣ የወዳጃቸው ልጅ ከሆነው የ28 ዓመቱ ወጣት ሐጎስ ጋር በመሆን በስንዴ እርሻቸው ላይ የደረሰውን የስንዴ ሰብል በእጃቸው በመንቀል ተጠምደዋል፡፡  

ከአዲስ አበባ በ857 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሰሜን ምሥራቅ የትግራይ ክልል በምትገኘው የአፅቢ ወንበራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አዛውንቱ አርሶ አደር አፈራ፣ ከግማሽ ሔክታር የማይበልጠውን የእርሻ መሬት አለስልሰው ሲያርሱ እርጅና የተጫነውን ጉልበታቻውን ያን ያህል እንዳልፈተናቸው ያስታውሳሉ፡፡ በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. አንድ ጊዜ አርሰው ሐምሌ አጋማሽ ላይ በመድገም የተሻለ ምርትን ለማግኘት አልመው ነው፣ ምርጥ የስንዴ ዘር ሉግዳ በሚባለው ቀበሌ የዘሩት፡፡

‹‹ይህች ምኗ ለማጭድ ተርፋ ነው የማጭዳት?›› በማለት ነበር በአብዛኛው በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ምርትን ለመሰብሰብ ዋነኛ የመገልገያ መሣሪያ የሆነውን ማጭድ ለምን እንዳልተጠቀሙ ከሪፖርተር የተነሳላቸውን ጥያቄ የመለሱት፡፡ በእርግጥም የአዛውንቱ መልስ ትክክለኛነትና ሚዛን የሚደፋ ትርጉም ሰጪነቱን፣ እዚሁ የስንዴ እርሻ ውስጥ ቀረብ ብሎ ላስተዋለ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በሐምሌ ወር የተዘራው ስንዴ አፍርቶ የመሰብሰቢያው ትክክለኛ ወቅት ላይ ቢሆንም፣ እውነታው ግን ፍፁም አስደንጋጭ በመሆኑ የአዛውንቱን ቅስም የሰበረና በተስፋ መቁረጥ አንገታቸውን ያስደፋ ነበር፡፡

ባለፈው ዓመት ይጠበቅ በነበረው የበልግ ወቅትና በክረምቱ ወራት ሊኖር በሚገባው የዝናብ እጥረት ምክንያት፣ በአገሪቱ አብዛኛው ክፍል የተከሰተው ድርቅ ክፉኛ ከጎዳቸው ሥፍራዎች መካከል፣ የአርሶ አደር አፈራ ወረዳ የሆነችው የአፅቢ ወንበርታ ወረዳና ከደቡብ ምሥራቅ እስከ ሰሜናዊ ምሥራቅ የሚገኙ የትግራይ አካባቢዎች ይካተታሉ፡፡

‹‹ዘንድሮ እርሻ አለኝ ማለት ከንቱ ሆኗል፡፡ እህል የሚባል ነገር የለም፣ ቡቃያው ከእኛ እርቋል፡፡ አንድ ኩንታል ምርጥ ዘር ነበር የዘራነው፡፡ ይኸው አሁን አንድ ኩንታል ዘር ዘርተን አንድ ኩንታል ስንዴ እንኳን ብናገኝ ብለን ነው ይችኑ የተመናመነች የስንዴ ዘንግ በእጃችን የምንነጨው፤›› ሲሉ አዛውንቱ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ ባለፉት የምርት ዓመታት ከዚሁ ተመሳሳይ የእርሻ መሬት ከስምንት እስከ አሥር ኩንታል ስንዴ ያመርቱ እንደነበርና የወቅቱ ድርቅ ግን ምን ያህል ምርት አልባ አድርጎ እንዳስቀራቸው ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ በሥፍራው አዛውንቱን በማገዝ ላይ የነበረውን ወጣቱን ሐጎስ ሪፖርተር ባነጋገረበት ወቅት፣ ድርቁ በአካባቢው ካደረሰው አስደንጋጭ ተፅዕኖ አንፃር አቶ አፈራ አንድ ኩንታል ስንዴም ብትሆን አገኝበታለሁ የሚሉት እርሻ ‹‹እንዲያውም ዕድለኛ ነው›› ብሏል፡፡ የሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች እርሻዎች ሙሉ ለሙሉ ፍሬ መስጠት ባለመቻላቸው የከብት ሲሳይ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡

የአሁኑ የኤልኒኖ ክስተት በወጣቱ አርሶ አደር ሐጎስ ላይ ድንጋጤም ሆነ አግራሞት ቢያመጣም፣ በአዛውንቱ አርሶ አደር ላይ ግን የፈጠረው ድንጋጤ የከፋ መሆኑ ከፊታቸው ገጽታ ጎልቶ ይታያል፡፡ ለዚህም ደግሞ ዋና ምክንያቱ አዛውንቱ ከዚህ በፊት የከፋውን በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የተከሰተውን የ1965 ዓ.ም.  እና በደርግ ጊዜ የታየውን የ1977 ዓ.ም. የረሃብ ዘመን አይተው የነበረ መሆኑ ነው፡፡

‹‹እርሻው ሁሉ እንዲሁ ባዶ አስቀረን፡፡ መብቀል የቻለው ቡቃያ እንዲሁ በቁሙ ለከብት ከተሰጠ የነገን ነገር እኔ እንጃ፡፡ ያው የድሮውን እልቂት እንዳያመጣብን ብዬ ነው እየፈራሁ ያለሁት፤›› በማለት ሊፈጠር የሚችለውን የምግብ እጥረት ካሁኑ እያሰቡት ይጨነቃሉ፡፡

በዚሁ የሉግዳ ቀበሌ ከአቶ አፈራ ማሳ ትንሽ አለፍ ብሎ ሌሎች ሁለት አዛውንት አርሶ አደሮች የደረሰ፣ ነገር ግን ለጎተራ የሚያበቃ ፍሬ ማፍራት ባልቻለው የስንዴ እርሻ ውስጥ ይታያሉ፡፡ አለቃ አረጋዊና ወልዱ መለስ ይባላሉ፡፡ በእዚህኛው ማሳ ያለው እውነታ ግን ምናልባትም የባሰ አሳዛኝና አስደንጋጭ ጭምር ነው፡፡ ቡቃያው ምንም ዓይነት ለሰው ምግብነት የሚውል የስንዴ ፍሬ አላፈራም፡፡ በቀደመው ማሳ ወጣቱ አርሶ አደር እንደገለጸው፣ አርሶ አደሩ አለቃ አረጋዊ አንድ ኩንታል አገኛለሁ ብለው የሰለለች ተስፋ ከሰነቁት አዛውንቱ አቶ አፈራ አንፃር ዕድለኛ እንዳልሆኑ ፍሬ አልባው ማሳ በግልጽ ያሳያል፡፡ ‹‹ዘንድሮ ሰማዩም ከዳን፡፡ ዝናቡም ከእኛ ራቀ፤›› በማለት አርሶ አደሩ አቶ ወልዱ ባለፈው ክረምት ዝናቡ ከሚጠበቀው በታች በመሆኑ ምክንያት በምርት ላይ ያደረሰውን ተፅዕኖ ከገለጹ በኋላ፣ የደረቀውን የስንዴ ቡቃያ በቀጥታ ለከብቶቻቸው ምግብ እንዲሆን በጥንቃቄ እየሰበሰቡት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በድርቁ ምክንያት ሊያገኙት ይገባ የነበረው ሰብል ከመውደሙ ባሻገር፣ አርሶ አደሮችን ትልቅ የአደጋ ሥጋት ውስጥ የከተታቸው ካለፈው ዓመት ምርት ያስቀመጡት እህል በመመናመን ላይ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ከአምና ያቆየነው እህል አሁን አልቆ እዚህ ግቢ የማትባል እህል ነች የቀረችን፡፡ ችግሩ እየከፋ ሲመጣ በቤት ከነበሩን አምስት ከብቶች አንድ ወይፈንና አንድ በሬ ሸጠን ነው ሰሞኑን የከረምነው፤›› ሲሉ ለሪፖርተር የገለጹት አለቃ አረጋዊ፣ ድርቁ ከምርት መውረድ በተጨማሪ በከብቶች ገበያ ላይም ያስከተለውን ተያያዥ ችግር ጠቁመዋል፡፡

የቤተሰቦቻቸው ሕይወት ለማቆየት ሲሉ እስከ 7,000 ብር እና ከዚያ በላይ ዋጋ የሚያወጣ በሬያቸውን በ1,500 ብር ለመሸጥ መገደዳቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ከብት (በሬና ላም) ዋጋ አጥቷል፡፡ ከአንድ ከብት ይልቅ ፍየል የተሻለ ዋጋ አለው፤›› ሲሉም በገበያ በኩል ያለውን ችግር አመልክተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ከመቐለ ከተማ 43 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው የአጉላዕ ከተማ ጀምሮ በሰሜን ምሥራቁ ከፍል በተደረገው ቅኝት፣ በአብዛኛው አካባቢ ድርቁ ያስከተለው ተፅዕኖ ተመሳሳይ ይዘት እንዳለው መገንዘብ ተችሏል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ የውኃ እጥረት በመከሰቱ፣ አርሶ አደሮች ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ እንደ አፅቢ ወንበራ ሁሉ በሌሎችም ወረዳዎች በተለይም በክልተ አውላሎ፣ ደብረ ብርሃን (ከለሻ እምኒ)፣ አጎሮ፣ ውቅሮ፣ ፈንታ አውላሎ፣ ኢሮብ የመሳሰሉት ወረዳዎች ክፉኛ የተጠቁ ቦታዎች ናቸው፡፡ እንዲሁም በደቡባዊ የትግራይ ክልል በተለይም በራያ አዘቦ፣ በአላማጣ፣ በማይጨውና በአጎራባች አካባቢዎች ያለው ችግር ተመሳሳይ ነው፡፡ በክልሉ ካሉ 46 ወረዳዎች በ21 ወረዳዎች የሚገኙ 109 ቀበሌዎች እስካሁን አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን፣ ከክልሉ መንግሥት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

አብዛኛው አካባቢ ቀድሞ የታረሰና በዘር የተሸፈነ ቢሆንም፣ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ የእርሻ መሬቶቹ የቀጨጨ ቡቃያ ከማብቀል አልፈው ለውድማም ሆነ ለጎተራ የሚበቃ ፍሬ መስጠት አልቻሉም፡፡ አጉላዕ፣ ደሴ፣ አጉሮ፣ ቢርኪ የሚባሉ አካባቢዎች ከመቐለ ተነስቶ በአፋር በርሐሌና አፍዴራ አድርጎ፣ ጂቡቲ ወደብ ድረስ በሚዘልቀውና በቅርቡ በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የተገነባውን መንገድ ተከትለው የሠፈሩ ናቸው፡፡ በሁሉም አካባቢዎች የአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ከብቶች ተለቀው ይታያሉ፡፡ ከብቶቹ ማፍራት ያልቻለውን የገብስ፣ የስንዴና የሌሎች ቡቃያ በቁሙ እየጋጡት ይስተዋላል፡፡ ይባስ ብሎ አንድ እርሻ ሙሉ በሙሉ በከብቶች የተበላ በመሆኑ፣ ከወራት በፊት ምንም ያልበቀለበት እስኪመስል ድረስ ወደ አፈርነት ተለውጧል፡፡

በዝናቡ እጥረት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል የነካ ሲሆን፣ ይኼንን ተከትሎ ጠቅላላ የተጎጂውንና የዕርዳታ ፈላጊውን ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡ ምናልባት ቀድሞ ከተገመተው በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን፣ መንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

በተለይ ቀደም ብሎ ይፋ የተደረጉት የአፋርና የሶማሌ ክልሎችን ጨምሮ የምሥራቅና የሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ጉዳይ አሳሳቢነት እየጨመረ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የአማራ ክልልንና በከፊል የኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ አጠቃላይ የዕርዳታ ፈላጊው ቁጥር 8.2 ሚሊዮን መድረሱን መንግሥት በቅርቡ ገልጿል፡፡ ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሥሩ ያሉ ተቋማትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ይህ ቁጥር በቅርቡ ወደ 15 ሚሊዮን ከፍ ሊል እንደሚችል ተንብየዋል፡፡ የአሁኑ ድርቅ አገሪቱ ባለፉት 30 ዓመታት ካጋጠሟት የድርቅ ክስተቶች ሁሉ የከፋ እንደሆነም በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

ቀደም ባሉት ወራት በተለይም የዝናብ እጥረቱ ካጋጠመ ጀምሮ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች በከብቶች ላይ ከተከሰተው የሞት አደጋ በኋላ፣ መንግሥት ድርቁ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በራስ መቋቋም እንደሚችል መግለጹ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን  ችግሩ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ በመጨመሩ አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በፍጥነት ማዳረስ ሲጀምር ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጥሪ መደረጉም ይታወሳል፡፡

በእርግጥ እስካሁን የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ያሳየው ምላሽ እዚህ ግባ ባይባልም፣ ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ግን የእንግሊዝ መንግሥትን ጨምሮ የተወሰኑ ለጋሾች መጠነኛ ዕርዳታ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡

እስካሁን መንግሥት 22 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ወደ አገር ውስጥ በግዢ ያስገባ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ ደግሞ 50 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በቆሎ ገዝቷል፡፡ በተጨማሪም አንድ ሚሊዮን ቶን ስንዴ ለመግዛት ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱን ባለፈው ሳምንት ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከእዚህም ውስጥ 400,000 ቶን የሚሆነው በድርቁ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ በአጠቃላይ ለድርቁ 12 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል የተባለ ሲሆን፣ እስካሁን መንግሥት አራት ቢሊዮን ብር ማውጣቱን እየገለጸ ነው፡፡

ነገር ግን በአብዛኛው የትግራይ ክልል እየታየ ላለው ችግር መንግሥት ከችግሩ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የዕርዳታ እህል በቅርቡ ካላጓጓዘና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ርብርብ ካልተካሄደ፣ ችግሩ ከፍተኛ ወደ ሆነ ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል ሥጋት አለ፡፡ የክልሉ መንግሥትም ሆነ ታዛቢዎች ይህንኑ በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

በተለይም አብዛኛው አርሶ አደር ካለፈው የምርት ዘመን ጀምሮ በጎተራ የነበረው ጥሪት እያለቀበት በመሆኑ፣ በሁሉም አካባቢዎች እንደ ዋና ችግር እየተገለጸ ያለው የውኃ እጥረት እየተባባሰ በመምጣቱ፣ በክልሉ ላይ የተደነቀረው ችግር የመጨረሻው የማስጠንቀቂያ ‹ቀይ መብራት› ላይ መድረሱ በግልጽ ይታያል፡፡

      ለዚህም ነበር ከአንድ ሳምንት በፊት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ዓባይ ወልዱና የክልሉ የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎች የችግሩ ሰለባ በሆኑ አካባቢዎች በመዘዋወር ለመጎብኘት የተገደዱት፡፡

      ርዕሰ መስተዳድሩ ከተለያዩ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የድርቁ ችግር ጎልቶ በታየባቸው ወረዳዎች በመጓዝ የችግሩን ስፋት በቀጥታ የተገነዘቡት መሆኑን፣ በክልሉ መንግሥት በኩልም ሆነ በፌዴራል መንግሥት አማካይነት አስፈላጊውን ዕርምጃ በመውሰድ ለአርሶ አደሩ እንደሚደርሱ ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በዚህ ሰዓት ያጋጠማቸውን የምርት መውደቅና ለወደፊት ሊከሰት የሚችለውን የእህል እጥረት ለአቶ ዓባይ እንዳስረዱ፣ የክልሉ መንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገብረ ሚካኤል መለስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይም በድርቁ ምክንያት፣ ‹‹በምንም ዓይነት ሁኔታ ሰውም ሆነ ከብት በረሃብ መሞት አይኖርበትም፡፡ አንድም ሰው፣ አንድም እንስሳ እንዳይራብ ጥረት እናደርጋለን፤›› ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አቶ ገብረ ሚካኤል ይህንን ይበሉ እንጂ፣ የክልሉን መንግሥት አካሄድ የሚተቹ ደግሞ የክልሉ መንግሥት የድርቁን ሁኔታና የዕርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር ከሌሎች ክልሎች አንፃር በመዘግየት መግለጹን፣ እንዲሁም ለመደበቅ ሙከራ አድርጓል የሚሉ ወቀሳዎች ሰንዝረዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ግን የድርቁ ተፅዕኖ እስከዚህ አስከፊ ደረጃ ይደርሳል የሚል እምነት እንዳልነበረው ይገልጻል፡፡  

‹‹የዝናብ እጥረቱ መከሰቱ እንደታወቀ ዝግጅት እየተደረገ ነበር፡፡ ነገር ግን እዚህ ደረጃ ይደርሳል የሚል እምነት አልነበረም፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩም ሆኑ አጠቃላይ የክልሉ መንግሥት ችግሩ ከአቅም በላይ ሆኖ ሲመጣ ያለውን እውነታ በመደበቅ፣ በወገን ላይ የሞት አደጋ እስኪያስከትል ዝም ብሎ የማየት ፍላጎት የላቸውም፡፡ ፕሬዚዳንቱም ቢሆኑ የወገናችንን ረሃብ በመደበቅ በታሪክ ተወቃሽ መሆን ስለሌለብን ያለው ሀቅ ሁሉ በይፋ መገለጽ እንዳለበት አስታውቀዋል፤›› ሲሉ አቶ ገብረ ሚካኤል ወቀሳውን አጣጥለዋል፡፡

ጽሕፈት ቤቱን የክልሉ መቀመጫ በሆነችው መቐለ ከተማ ያደረገው ተቃዋሚው ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዲሞክራሲ ግን፣ የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት በክልሉ ለተከሰተው ድርቅ አስቸኳይ ምላሽ መስጠት አልቻሉም ይላል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ሀቁን ለመደበቅ በመሞከር ‹‹ከታሪክ ሊማር ባለመቻሉ›› ባለፉት መንግሥታት የተፈጸሙትን ዓይነት ስህተቶች እየደገመ ነው ሲል ወቅሷል፡፡

ከዚሁ የድርቅ ክስተት ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት በኩል ሊገኝ ይችላል ተብሎ ከሚጠበቀው የዕርዳታ እህል ቀደም ብሎ፣ በእጁ የሚገኘውን እህልና የአልሚ ምግብ ዓይነቶችን ለማዳረስ እየሞከረ መሆኑን አቶ ገብረ ሚካኤል ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ በሰውም ሆነ በእንስሳት በኩል የሞት ሪፖርት አለመቅረቡንም አስታውቀዋል፡፡

የዓረና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገብረ ሥላሴ ግን፣ በመንግሥት በኩል የተደረገው እንቅስቃሴ ዘግይቶ የመጣ በመሆኑ ራሳቸው ባደረጉት የግል የዳሰሳ ዕይታ፣ ሦስት ሰዎችና ተጨማሪ አንዲት ሴት በረሃቡ መሞታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹የድርቁ ሽፋን እየጨመረ በአብዛኛዎቹ ዞኖች በግልጽ ከመታየቱም አልፎ፣ ብዙዎች ለከፋ ረሃብና የውኃ እጥረት ተዳርገዋል፡፡ እኔ በበኩሌ ከመቐለ ወጣ ብሎ በእንደርታና በአካባቢው ያለውን ችግር ለማስተዋል ሞክሬያለሁ፡፡ አምዶራታ በሚባል አካባቢ እንኳን ሦስት ሰዎች መሞታቸውን ከነዋሪዎቹ ተነግሮኛል፡፡ በቅርቡ ደግሞ እንዲሁ አንዲት ሴት በሴፍቲኔት አማካይነት የሚደርሳት ዕርዳታ በመቋረጡ ለሞት ተዳርጋለች፤›› በማለት ሰዎች በድርቁ ምክንያት እየሞቱ መሆናቸውን አቶ አምዶም ገልጸዋል፡፡ እሳቸው ይህንን ይበሉ እንጂ ከገለልተኛ ወገኖች ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

ችግሩ መታየት የጀመረው ባለፈው ዓመት ገና በበጋ ወቅት በመሆኑ ‹‹የኅብረተሰቡ ሞራል ወድቋል፤›› የሚሉት አቶ አምዶም፣ ተዘዋውሬ አድርጌያለሁ ባሉዋቸው ቃለ መጠይቆች ኅብረተሰቡ ‹‹ሁላችንም ፈርተናል፤›› በማለት ችግሩ መክፋቱንና በክልሉ መንግሥትም ቸልተኝነት ተስተውሎ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

‹‹ችግሩ የተከሰተባቸው የአፋር፣ የሶማሊ፣ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ቀደም ብለው እንቅስቃሴ በመጀመር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ በትግራይ ግን ለሕዝብ እንኳን ደፍረው ይፋ ያደረጉት በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎች መሞት የጀመሩት በነሐሴና በመስከረም ወር መጀመርያ ነው፤›› በማለት የሚከራከሩት የዓረና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ ‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት ከደርግም ሆነ ከኃይለ ሥላሴ ስህተቶች እየተማረ አይደለም፡፡ ሦስቱም ሥርዓቶች ድርቁንና ረሃቡን ለመደበቅ ሞክረዋል፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ችግሩ አፍጥጦ ስለወጣበት እንጂ ለመደበቅ ሞክሮ ነበር፤›› ሲሉ ይከሳሉ፡፡

ከመዘግየቱ ጋር የሚነሳውን ወቀሳ የማይቀበለው የክልሉ መንግሥት ግን፣ በተፈለገው ፍጥነት ለተጎጂዎች ዕርዳታ እያደረሰ መሆኑንና አስቸኳይ የሆኑ የአርሶ አደሮችን ፍላጎቶች ለማሟላት እየሠራ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግሥት እስካለፉት ሁለት ሳምንታት ድረስ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ችግሩ ጎልቶ በታየባቸው አካባቢዎች የምግብና የአልሚ ምግቦችን ዕርዳታ፣ እንዲሁም ከፍተኛ የውኃ እጥረት ባላቸው አካባቢዎች ውኃ በተሽከርካሪና በጊዜያዊ  ውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖች በማቅረብ እርብርብ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባስተዋላቸው ቦታዎችም ከፍተኛ የሆነ የውኃ ችግር በአርሶ አደሮች የሚነሳ ጥያቄ ሲሆን፣ በአንዳንድ ቦታዎችም ከምግብ ዕርዳታ በፊት ‹የውኃ ያለህ› የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ በክልሉ የውኃ እጥረት ቀድሞውንም በተደጋጋሚ የሚነገርለት አንገብጋቢ ችግር ሆኖ የቆየ ቢሆንም፣ የወቅቱ ድርቅ ግን ችግሩ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳባባሰው አርሶ አደሮቹም ሆኑ የክልሉ መንግሥት እያስተጋቡት ነው፡፡

የተጎጂዎችን የከፋ የውኃ ፍላጎት ለማሟላት የክልሉ መንግሥት በራሱ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ፣ በአካባቢዎቹ የሚገኙ ጥቂት የመንግሥትና የግል ድርጅቶች የራሳቸውን ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ለማስተዋል ተችሏል፡፡ ለአብነትም ያህል በአፅቢ ወንበርታ ወረዳ አጎሮ በሚባለው አካባቢ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ፣ በአካባቢው ባለው ካምፕ ውስጥ በሚገኙ ውኃ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ለኅብረተሰቡ እያከፋፈለ መሆኑ በነዋሪዎቹ ተገልጿል፡፡ በተመሳሳይም በራያ አካባቢ የሚገኘው የራያ ቢራ ፋብሪካ ለራሱ ከጉድጓድ አውጥቶ የሚጠቀመውን ውኃ ለነዋሪዎች በማቅረብ ላይ ሲሆን፣ በተጨማሪም የፋብሪካውን ተረፈ ምርት ለአካባቢው አርሶ አደሮች ለከብቶች መኖነት በማቅረብ ላይ ነው፡፡ እንዲሁም በአላማጣ አካባቢ በወይንና በአትክልት የእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማራው አማኑኤል የተባለ የግል ድርጅት 23 ሺሕ ሔክታር የሚሆን የእርሻ መሬት በመስኖ ለማጠጣት ከሚጠቀምበት የጉድጓድ ውኃ ለኅብረተሰቡ በማከፋፈል፣ ከ70 ሺሕ ሔክታር በላይ የሚሆን የአርሶ አደሩን ማሳ በመስኖ ለማዳረስ እየሞከረ ነው፡፡

ግለሰቦች በራሳቸው ተነሳሽነት እያደረጉ ያለውን እገዛ ያደነቁት የክልሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ የውኃ ፍላጎትን ለማሟላት የክልሉ መንግሥት ከአቅሙ በላይ እየሆነበት በመምጣቱ፣ ችግሩ መቀረፍ የሚችለው የፌዴራል መንግሥትና የግል ሴክተሩ በጋራ መረባረብ ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በአብዛኞቹ አካባቢዎች የውኃ ምንጮች እየደረቁ ሲሆን፣ ውኃው ያላቸው አካባቢዎች ደግሞ ውኃን ከጉድጓድ አውጥተው ለመጠቀም የውኃ መሳቢያ ፓምፕ፣ የጄኔሬተርና የትራንስፎርመር አለመኖር ችግር መሆኑን ሪፖርተር ከነዋሪዎችም ሆነ ከክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች ማረጋገጥ ችሏል፡፡

‹‹የውኃ ችግርን አርሶ አደሮች በዋናነት ለርዕሰ መስተዳድሩ ያነሱ ሲሆን፣ አቶ ዓባይም ይህንን ችግር በቦታው ያዩት በመሆኑ በተለይ ለክልሉ የውኃ ቢሮ ኃላፊ አስቸኳይ የመሳቢያ ፓምፕና የጄኔሬተር ግዥ እንዲያከናውኑ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ በግዥ ሒደት የመንግሥት የግዥ ሕጉን ለመጠበቅ ሲባል ጊዜ እንዳያቃጥሉ ጭምር ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል፤››  በማለት አቶ ገብረ ሚካኤል በክልሉ መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በትራንስፎርመር በኩል ያለው ችግር ቀድሞውኑ የቆየ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ገብረ ሚካኤል፣ ክልሉም ትራንስፎርመር ማቅረብ የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ መንግሥትን እየጠየቀ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተያያዥነት የትምህርት መስተጓጎል፣ የነዋሪዎች ፍልሰት መከሰትና እንዲሁም በጤና በኩል የማጅራት ገትር፣ የውኃ ወለድና ተላላፊ በሽታዎች ሥጋት ሊሆን እንደሚችል ተፈርቷል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ከእነዚህ ሥጋቶች አንዱም ያልተከሰተ መሆኑን፣ በተለይ በጤና ጉዳይ ምንም ዓይነት ምልክት ከታየ የወረዳ ኃላፊዎች በቀጥታ ሪፖርት እንዲያደርጉ ርዕሰ መስተዳድሩ ማሳሰባቸውን፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ የድርቁ ተፅዕኖ በክልሉ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ በእርሻ ምርት መክሰም አማካይነት የአደጋ ምልክቱን አብርቷል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የገጠር ነዋሪዎችም ሥጋታቸውን ከፍ አድርገው እያሰሙ ነው፡፡ በተለይ ከሚቀጥለው ወር ምናልባትም ከሁለትና ከሦስት ወራት በኋላ አፋጣኝ ዕርዳታ ወደ ቦታው ማድረስ ካልተቻለ፣ ችግሩ ከ1977 ዓ.ም. ረሃብ በከፋ ሁኔታ እንዳይሄድ ብዙዎች ሥጋታቸውን ከወዲሁ እየገለጹ ነው፡፡

አጉላዕ ከተባለው አነስተኛ ከተማ ደሴ ወደምትባል የገጠር ቀበሌ በእግሯ የሁለት ሰዓት መንገድ በመጓዝ ላይ የነበረችው አብረኸት ግደይ ለሪፖርተር እንደተናገረችው፣ ቤቷ ውስጥ የነበረው እህል በማለቁ ከባለቤቷ ዘመዶች ያገኘችውን አራት ኪሎ ገብስ በጀርባዋ ተሸክማ እየተመለሰች ነው፡፡ ‹‹ምንም የሚበላ የለም፡፡ ውኃም የለም፡፡ ዘንድሮ ምንም ነገር የለም፤›› በማለት ድርቁ ያደረሰውን ቀውስ ትገልጻለች፡፡ የሦስት ልጆች እናት የሆነችው አብረኸት ስለነገ የቤተሰቧ ሕይወት ለተነሳላት ጥያቄ፣ ‹‹እኔ እንግዲህ ምን አውቃለሁ? እርሻው እንቢ አለ፡፡ መንግሥት ካልደረሰልን ምንም የምንበላው የለም፤›› የሚል ነበር መልሷ፡፡ የሌሎችም የድርቅ ተጎጂዎች ፍርኃት በአብረኸት ይስተጋባል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -