የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ሳዑዲ ዓረቢያ በየመን ከመንግሥት ጋር እየተዋጉ ያሉትን የሁቲ አማፅያን ለማጥቃት የኤርትራን መሬት፣ ባህር፣ አየርና ወታደሮች መጠቀማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ፡፡ ተመድ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ ይህ ድርጊት በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ የሚጥስ ነው፡፡
ኤርትራ ይህን ዕርዳታ የሰጠችው በምላሹ የገንዘብ ካሳና የነዳጅ አቅርቦት ለማግኘት እንደሆነም ተመድ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ ሁለቱ አገሮች የኤርትራን የአሰብ ወደብ ለ30 ዓመታት በሊዝ እንደተከራዩትም ሪፖርቱ ያትታል፡፡
በየዓመቱ የሚወጣው በሶማሊያና በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ላይ ክትትል የሚያደርጉ የተመድ የባለሙያዎች ቡድን ሪፖርት፣ ይህ ወታደራዊ ትብብር በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ሳይከናወን እንዳልቀረ ግምቱን ያሰፍራል፡፡ ኤርትራ የሁለቱን አገሮች ጥሪ የተቀበለችው ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበላት ጂቡቲ እንቢታዋን ከገለጸች በኋላ እንደሆነም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ የኤርትራ አቅራቢያ ድንበር ከየመን 29 ኪሎ ሜትር ብቻ እንደሚርቅም ሪፖርቱ ያስታውሳል፡፡
ይህ የኤርትራ ድርጊት እ.ኤ.አ. በ2009 ተመድ ያወጣውን የውሳኔ ሐሳብ 1907 እንደሚጥስ ሪፖርቱ ያስገነዝባል፡፡ በተጨማሪም ወደ 400 የሚጠጉ የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ መካፈላቸውን ታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጡ ሪፖርቱ ያትታል፡፡ የሁለቱ አገሮች ወታደራዊ ማዘዣ የሚገኘው በሐኒሽ ደሴት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ ሐኒሽ ደሴት በየመንና በኤርትራ መካከል የግጭት ምክንያት መሆኗ ይታወሳል፡፡ ሪፖርቱ በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የማስታረቅ ሚና ለመጫወት ትጥራለች የተባለችው ኳታርም፣ በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ 200 ወታደሮች እንዳሏት አካቷል፡፡
የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ የኤርትራ አቀማመጥ ለአክራሪ ኃይሎች የጥቃት ዒላማ የተጋለጠ ስላደረገው፣ የተጣለበትን መሣሪያ የመግዛት ማዕቀብ እንዲያነሳለት የተመድ የፀጥታ ምክር ቤትን በተደጋጋሚ መጠየቁ ይታወሳል፡፡