የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የአገሪቱን አናሎግ የቴሌቪዥን ሥርጭት፣ ወደ ዲጂታል ለመቀየር የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን፣ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው የዲጂታል ቴሌቪዥን ዝርጋታ በማከናወን ብዛት ያላቸው አማራጭ የሥርጭት ጣቢያዎች በአንድ ላይ በማሠራጨት፣ ጥራቱ አስተማማኝና ተደራሽ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር የብሔራዊ ዲጂታል ቴሌቪዥን ሥርጭቱ ደኅንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ማድረግ እንደሚጠበቅ ገልጿል፡፡
በእስካሁኑ ሒደት ኤጀንሲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የአገር አቀፍ ቴሌቪዥን የሥርጭት ሽፋንንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት፣ ተስማሚ የቴክኖሎጂ መረጣ፣ አስፈላጊ መዘርዝሮችን የማውጣትና ቴክኒካዊ ግምገማ የማካሄድ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድቷል፡፡
በተጨማሪም የግንባታ መሠረተ ልማት ዲዛይን ጨረታ ማውጣት ሥራ ያከናወነ መሆኑን፣ በፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር በኩል የኩባንያ መረጣና ውል ከተፈጸመ በኋላ ወደ ሙሉ ሥራ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
ኤጀንሲው ባደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረትም 74 ነባር ትራንስሚተሮችን በማደስና አቅማቸውን በማሻሻል፣ 26 አዳዲስ ተጨማሪ የማሠራጫ ጣቢያዎችን በመትከልና መልክዓ ምድርን መሠረት ያደረገ የሞገድ ሥርጭት ዕቅድ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር በመንደፍና በመተግበር፣ የዲጂታል ቴሌቪዥን ሥርጭቱን በአገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የሚያስፈልገው ወጪ በብድር የሚሸፈን ሆኖ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ የፍላጎት ጥናትና ተያያዥ ወጪዎች ደግሞ በመንግሥት በጀት እየተከናወነ መሆኑን የኤጀንሲው መግለጫ ያስረዳል፡፡
የውል ስምምነቱ ሲፈጸም ኤጀንሲው የዕውቀት ሽግግርን በማረጋገጥ ጥራትና ቀጣይነት ያለው አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ መሆኑን፣ የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ማስታወቁን መግለጫው አስረድቷል፡፡
በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሕግና ማስታወቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ አንድ ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ ተገምቷል፡፡
የዲጂታል ቴሌቪዥን ሥርጭት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኅብረት አሠራር መሠረት አገሮች እ.ኤ.አ. እስከ 2015 መጨረሻ ድረስ፣ የአናሎግ የቴሌቪዥን አውታሮቻቸውን ወደ ዲጂታል በማስቀመጡ መሆኑን አቶ ግዛው ገልጸዋል፡፡
ይህ የዲጂታል ሥርዓት ዕውን ሲሆን 22 ያህል የቴሌቪዥን ቻናሎችን ማስተናገድ ይቻላል ተብሏል፡፡