መስከረም 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በተሠራ ትንበያ መሠረት በክረምት ከኤልኒኖ ተፅዕኖ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የአየር መዛባት ከጥቅምት እስከ ጥር ያለው የበጋ (በልግ) ወቅት ላይ የሚቀጥል መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ፈጠነ ተሾመ ይህን ያስታወቁት ጥቅምት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡ በትንበያው መሠረት በጋውም በኤልኒኖ ተፅዕኖ ሥር እንደሚቆይና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ አልፎ አልፎ እንደሚከሰት ጠቁመዋል፡፡
‹‹በጋ የክረምት ወቅታቸው የሆነባቸው አካባቢዎች የሶማሌ፣ የደቡብና የኦሮሚያ ደቡባዊ ክፍሎች ላይ ጠንከር ያለ ዝናብ ይኖራል፡፡ ይህም ለጎርፍ መከሰት ምክንያት ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከአፋር ክልል በስተቀር በኤልኒኖ ምክንያት የክረምት ዝናብ የዘገየባቸው አካባቢዎች ላይ በበጋው ወራት ከፍተኛ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
‹‹ከኅዳር እስከ ጥር አሁን በተጀመረው ዓይነት በጋው ደረቅ በሚሆንባቸውና የዝናብ ወቅታቸው ባልሆነባቸው አካባቢዎች፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መዝነቡ ይቀጥላል፤›› በማለት ከትንበያ የተገኘውን መረጃ አቶ ፈጠነ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች አሁንም እስከ ታኅሳስ ድረስ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ተፅዕኖ ሥር ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ አርሶ አደሮች አስፈላጊውን ጥንቃቄና ግንዛቤ እንዲወስዱ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበው፣ ‹‹ኅብረተሰቡ በተለይ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ይዘጋጅ፤›› በማለት ምክር ለግሰዋል፡፡
ያለፈው ክረምት ትንበያ በተሰጠበት ወቅት በአገሪቱ ኤልኒኖ መከሰቱ ተገልጾ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዚህም መሠረት ባለድርሻ አካላት፣ ውሳኔ ሰጪ አካላትና የዘርፉን መረጃ የሚጠቀሙ ተቋማት ይህንን ተገንዝበው አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የትንበያ መረጃውን ለኅብረተሰቡ በማድረስ ከፍተኛ ሥራ መከናወኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የመገናኛ ብዙኃን በማይደርሱባቸው አካባቢዎች ደግሞ የመንግሥትን መዋቅር በመጠቀም የትንበያው መረጃ ኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲደርስ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ከኤልኒኖ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የአየር መዛበት ምክንያት ከ8.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለምግብ ተረጂነት መጋለጣቸውን፣ መንግሥትና ዓለም አቀፍ ተቋማት መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡