Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ካንጋሮ ፕላስት በሕግ የተመለሰለትን የንግድ ምክልት ሐይኒከን ከሕግ ውጪ መጠቀሙን ተቃወመ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ዋልያ የንግድ ምክልት በሕግ አግባብ የተሰጠው ለሐይኒከን ነው›› ወይዘሮ ሠራዊት በዛብህ የኮርፖሬት ሪሌሽን ሥራ አስኪያጅ

‹‹በዳግም ምዝገባ ሒደት ላይ ስለሆንን ሠርተፊኬቱ ተዘጋጅቶ ይሰጣል›› አቶ ተሻለ ዮና የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር

ካንጋሮ ፕላስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በሕግ አግባብ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያስመለሰውን የዋልያ ምሥል ያለው የአይቤክስ ቢራ የንግድ ምልክትን፣ ሐይኒከን ኩባንያ ከሕግ አግባብ ውጪ እየተጠቀመበት መሆኑን ተቃወመ፡፡

ካንጋሮ ፕላስት ባቀረበው ተቃውሞ ላይ ምላሻቸውን የሰጡት የሐይኒከን ኮርፖሬት ሪሌሽን ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሠራዊት በዛብህ፣ ‹‹ዋልያ የንግድ ምልክት ለሐይኒከን አክሲዮን ማኅበር በሕግ አግባብ የተሰጠ ምልክት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የካንጋሮ ፕላስት የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ታፈሰ ይርጋ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የሕግ የበላይነት መከበር አለበት፡፡ የዋልያ ምሥል የንግድ ምልክት የያዘ አይቤክስ ቢራ፣ ቀደም ብሎ በካንጋሮ ፕላስት ሥር ከተመዘገቡ የንግድ ሥራዎች አንዱ ነበር፡፡ የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ለሌላ ኩባንያ በመስጠቱ ምክንያት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተደረገ ክርክር ምልክቱ ከጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲመለስለት ፍርድ ማግኘቱን አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ባዘዘው መሠረት ሐይኒከን ኩባንያ እየተጠቀመበት ያለውን የዋልያ ምሥልን የያዘውን የንግድ ምልክት ሰርዞ ለካንጋሮ ፕላስት እንዲሰጥ ለጽሕፈት ቤቱ ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ደብዳቤ ማስገባታቸውን አቶ ታፈሰ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ከ15 ቀናት በላይ ወደ ጽሕፈት ቤቱ ቢመላለሱም፣ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተፈጻሚ ሊሆን እንዳልቻለ አስታውቀዋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/98 መሠረት ዕግድ ባለመጣሉ ሐይኒከን ኩባንያ ከሕግ ውጪ እየተጠቀመበት በመሆኑ፣ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት እንደሚያስከትልም አስረድተዋል፡፡ እንደ አቶ ታፈሰ ገለጻ፣ የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የሆነ የአስተዳደር በደል እያደረሰባቸው ነው፡፡ ይህንንም በመጥቀስ በድጋሚ ጥቅምት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ቅሬታ አቅርበዋል፡፡

‹‹የሕግ የበላይነት ካልተከበረ መልካም አስተዳደር እንዴት ይመጣል?›› በማለት የሚጠይቁት ጠበቃ ታፈሰ፣ ማንም አካል የፍርድን ውሳኔ ሊያግድና ሊያስቆም እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ሐይኒከን ድንበር ዘለል ኩባንያ ሆኖ የቱንም ያህል ገንዘብ ቢያፈስ ለአገሪቱ ሕግ መገዛት እንዳለበት የገለጹት አቶ ታፈሰ፣ ማንም ሰው በሕግ ፊት እኩል እንደሆነና ማንነቱ በገንዘብ እንደማይለካም አስረድተዋል፡፡ በሕገ መንግሥት ሥርዓት ውስጥ የተሰጠን ውሳኔ ማንም ሊቀለብሰው እንደማይችል አሳስበዋል፡፡ መንግሥት በተለይ በአሁኑ ጊዜ ትኩረት ሰጥቶ እየተነጋገረበትና ቆራጥ አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ ባለበት የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ፣ ለሕግ የበላይነትን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ዜጎች እኩል የሚታዩበትን ሁኔታ ያረጋግጣል የሚል ሙሉ እምነት እንዳላቸውና በሕግ የተወሰነላቸው መብት በአፋጣኝ እንዲሰጣቸው እንደሚያደርግ እምነታቸው መሆኑ ጠበቃ ታፈሰ ተናግረዋል፡፡

ካንጋሮ ፕላስት ባቀረበው ቅሬታ ላይ አስተያየት የሰጡት ወይዘሮ ሠራዊት በዛብህ፣ ሐይኒከን በነበረው የሕግ ጉዳይ ውስጥ እንዳልነበረበት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ በካንጋሮ ፕላስትና በሌላ ግለሰብ መካከል ነበር፡፡ ጉዳዩም አይቤክስን በተመለከተ እንጂ ዋልያን በተመለከተ አልነበረም፡፡ ዋልያ የንግድ ምልክት ለሐይኒከን ሼር ካምፓኒ በሕግ የተሰጠ ምልክት ነው፡፡ ዋልያ ማለት አይቤክስ ማለት አይደለም፡፡ ሁለቱ የተለያዩ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ ዮና የካንጋሮ ፕላስትን ቅሬት በሚመለከት እንዳብራሩት፣ ‹‹የፍርድ ሒደቱ አላለቀም፡፡ የፍርድ ቤት ውሳኔን አናስፈጽምም አላልንም፡፡ ማስፈጸም ግዴታችን ነው፡፡ የካንጋሮ ፕላስት ሠርተፊኬት ሳይሠራ ሐይኒከንን ልናግድ አንችልም፤›› ብለዋል፡፡ በሕግ አግባብ እንዲሰረዝ ውሳኔ ያረፈበትን የንግድ ምልክት ለመሰረዝ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ የተጠየቁት አቶ ተሻለ፣ ጊዜ እንዳልተቀመጠለትና እንደየ ጉዳዩ ሁኔታ እንደሚለያይ ገልጸዋል፡፡

ሐይኒከን እየተጠቀመበት ያለው ምልክት ‹‹ይሰረዛልም፣ አይሰረዝምም አልልህም፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሠርተፊኬት እየተዘጋጀ መሆኑን ግን ጠቁመዋል፡፡ በአንድ የንግድ ምልክት ሁለት ኩባንያዎች መጠቀም ስለመቻላቸው ተጠይቀው፣ ‹‹የንግድ ምልክቱ አንድ ነው ወይስ ሁለት›› የሚለው ይታያል ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ድርጅቱ በዳግም ምዝገባ ሒደት ላይ ስለሆነና የምዝገባ ሒደቱ ሲስተካከል ሠርተፊኬቱ ተዘጋጅቶ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ የፍርድ ባለመብት ቶሎ እንዲያልቅለት ቢፈልግም፣ ዝም ብሎ ሌላውን ሰርዞ እንደማይሰጥና ሌላውንም ማየት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለካንጋሮ ፕላስት ሠርተፊኬት ሳይታተም፣ ‹‹ከአሁን በኋላ ይህንን ንግድ ምልክት መጠቀም አይቻልም፤›› ማለት እንደሚያስቸግር የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ምክንያቱ ደግሞ ንግድ፣ መልካም ዝናና ኢንቨስትመንት ስለሆነ ከአገር ገጽታ አንፃርም ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚገባ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች