Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በአዲስ አበባ የመሬት ችግሮች ላይ ጥናት ሊያካሂድ ነው

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በአዲስ አበባ የመሬት ችግሮች ላይ ጥናት ሊያካሂድ ነው

ቀን:

የፖሊስ ጥናትና ምርምር ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ በመሬትና በይዞታ አስተዳደር ላይ የተንሰራፋውን የመልካም አስተዳደር ችግር መንስዔ ለመለየትና የውሳኔ ሐሳብ ለማመንጨት ጥናት ሊያካሂድ ነው፡፡

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል አስተባባሪ አቶ ዓባይ ፀሐዬ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጻፉት ደብዳቤ፣ ማዕከሉ በመሬት ጉዳዮች ላይ ጥናት ለማካሄድ የተዘጋጀ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከዚህ ቀደም በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች እንዲላኩም ጠይቀዋል፡፡

በዚህ መሠረት የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፣ ማዕከሉ የጠየቀውን መረጃ ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት በፌዴራል ደረጃ በተካሄደ የውይይት መድረክ፣ የፖሊስ ጥናትና ምርምር ማዕከል ከፐብሊክ ሰርቪስና ከሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በተዘጋጀ የጥናት ሰነድ ላይ ውይይት መደረጉ ይታወሳል፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በተካሄደው ጥናት በርካታ ችግሮች ሲነሱ፣ ከአዲስ አበባ መሬት ሥሪት ጋር የተያያዙ ችግሮች ተካተዋል፡፡

ማዕከሉ የአዲስ አበባን የመሬት ችግሮች ለብቻ ለመዳሰስ የተዘጋጀውም፣ በጥናቱ የተካተተው በቂ ባለመሆኑ እንደሆነ ምንጮች አመልክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከሳምንታት በፊት በመሬትና በይዞታ ላይ ያሉ የከተማው ችግሮችን ከነመፍትሔያቸው የሚያቀርብ የባለሙያዎች ቡድን ማቋቋሙን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

እንደ መረጃው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሰጡት ቀጥተኛ ትዕዛዝ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከመሬት ሥሪት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የጥናት ቡድኑን በዋናነት የሚመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም ናቸው፡፡ አቶ አወቀ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ የከተማው ምክትል ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት የመሬት ዘርፍን በዋናነት ይመሩ ነበር፡፡

አቶ አወቀ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠቡም፣ ምንጮች እንደሚሉት ጥናቱ የሚያተኩረው የአዲስ አበባ መሬትና የዜጐች ይዞታ ከሙስናና ካልተገባ ድርጊት ነፃ ሆኖ የሚተዳደርበትን መፍትሔ መፈለግ ላይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ የዜጐችን ጥያቄ በቀልጣፋ አሠራር መመለስ ላይም ያተኩራል ተብሏል፡፡

ምንጮች እንደገለጹት፣ የጥናት ቡድኑ ዋነኛ ትኩረት የሆነው የሊዝ ደንብና መመርያ ውስጥ ማነቆ የሆኑ አንቀጾችን በድጋሚ እንዲሻሻሉ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ፣ ከቀበሌ ቤቶች ጋር የተያያዙ ችግሮችን መፍታት፣ መንግሥት የመሠረተ ልማት ባለማሟላቱ አልሚዎች በወሰዱት ቦታ ግንባታ ባለማካሄዳቸው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችል አቅጣጫ መጠቆምና የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮና አመራሮች ሥልጣንና ኃላፊነት መከለስ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ከእነዚህ ማነቆዎች በተጨማሪ፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አመራሮችና ሠራተኞች ከፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በየጊዜው የሚገጥሙት ግብ ግብ ለአገልግሎት አሰጣጡ እንቅፋት እንደሆነ ይገለጻል፡፡ በዚህም በኩል መንግሥት መከተል ያለበት አቅጣጫ በኮሚቴው እንደሚጠቆም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ ጥናት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከከንቲባ ድሪባ ኩማ ጋር በጉዳዩ ላይ ከመከሩ በኋላ ዕርምጃ ይወስዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች አስረድተዋል፡፡ በአቶ በረከት ስምዖን የሚመራው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ሊያካሂድ የተዘጋጀውን ጥናት ካጠናቀቀ በኋላ፣ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደረጃ ውይይት ይደረግበታል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...