Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበዓለም የሥነ ግጥም ቀን መነሻ

በዓለም የሥነ ግጥም ቀን መነሻ

ቀን:

ግጥም ጥልቀት ያለው ሐሳብ፣ እጥር ምጥን ባሉ የተዋቡ ቃላት የሚገለጽበት የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ መሆኑን ገጣሚው አያልነህ ሙላቱ ያሰምሩበታል፡፡ ከልቦለድ የሚለየውም፣ ማራኪና ምርጥ በሆኑ ቃላት ምታዊ ድርደራ የሰውን ልጅ ውስጣዊ ስሜት ጠልቆ በመግባት ህልውናን ስብዕናውን ለመግለጽ በመቻሉ ነው ሲሉም ያክሉበታል፡፡

የግጥምን ልዕልና በማሰብ የተባበሩት መንግሥታት እ.ኤ.አ. በ1999 የዓለም የሥነ ግጥም ቀን በየዓመቱ ማርች 21 ቀን (መጋቢት 12 ቀን) እንዲከበር በፓሪስ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ዕለቱ በአውሮፓና በእስያ የመፀው እኩሌ (Spring Equinox) ተብሎ ከሚከበርበት ጋር ባጋጣሚ ገጥሟል፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ክንፉ ዩኔስኮ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር በኢሪና ቦኮቫ የተተለመው የግጥም ቀን ባህልን ከመግለጥ አኳያ ልዕልና ያለው ስለሆነና በየዘመኑም እየታደሰ ስለሚሄድም ነው፡፡

የግጥም ቀኑ የፋርስ ቋንቋን በሚናገረው ዓለምም ‹‹ኖውሩዝ›› ተብሎ ከሚጠራው የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ጋር መግጠሙም ተምሳሌታዊ አድርጎታል፡፡

ከ20ኛው ምዕት አጋማሽ ጀምሮ በየዓመቱ ኦክቶበር 15 (ጥቅምት 5) የግጥም ቀን ሲከበር የኖረው ዕለቱ የሮማን ኤፒክ ገጣሚና ባለቅኔ ሎሬት ቨርጂል የተወለደበት በመሆኑ ነው፡፡ ይህ በዓለም ዙሪያ የሚከበረው የሥነ ግጥም ቀን የዩኔስኮን ልዩ በዓላት እንደ የዓለም ቱሪዝም ቀን የመሳሰሉትን የምታከብረው ኢትዮጵያ የዳበረ የቅኔና የግጥም ባህል እንዳላት መጠን ትኩረት ለምን አይሰጠውም የሚሉ አሉ፡፡ ይህም ሆኖ በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢራን ኤምባሲ የባህል ማዕከል የዓለም የሥነ ግጥም ቀንን ምክንያት በማድረግ ዓምና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል አዳራሽ የግጥም ምሽት ማዘጋጀቱና በመድረኩ የፋርሳውያን (ኢራን) ግጥሞች ከኢትዮጵያውያን ሥራዎች ተባብሮ መቅረቡ አይዘነጋም፡፡

የዓለም ሥነ ግጥም ቀን የመከበሩን ፋይዳ ዩኔስኮ ሲገልጸው ግጥምን የማንበብ፣ የመጻፍ፣ የማሳተምና የማስተማር ተግባርን በዓለም ዙሪያ ለማትጋት ብሎ ነው፡፡ ለብሔራዊ፣ ለአካባቢያዊና ለዓለም አቀፍ የግጥም እንቅስቃሴዎች ዕውቅናና ብርታትን ለመስጠትም አጋጣሚው መሠረት ይሆናል፡፡

‹‹ጎጆ›› ለሰውና ለወፍ በገጣሚው ምናብ

የዘንድሮውን የዓለም የሥነ ግጥም ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ከቀደምት ዕውቅ ባለቅኔዎች /ገጣሚዎች አንዱ በሆኑት/ በነበሩት መንግሥቱ ለማ ‹‹ሽምብራሸት›› ግጥም አንድ አንጓ ላይ የሥነ ግጥም መምህሩ ብርሃኑ ገበየሁ (1957 – 2002) አንድም እያሉ የተረጐሙበትን፣ የፈከሩበትን ነጥብ እዚህ ላይ ማንሣት ወደድን፡፡

‹‹ወፎች ተጠራሩ፣ ነውና መምሸቱ፣

ወደየጎጇቸው ገብተው ሊከተቱ

የሰው ልጅም አለው ጎጆ እንደ ወፎቹ

የሚደክምላቸው ሚስትና ልጆቹ፡፡›› በሚለው የአቶ መንግሥቱ ስንኞች የሰው ልጅ ከወፎች ጋር ተመሳስሏል፡፡ የሰው ልጅ ከወፍ ጋር የተመሳሰለው ጎጆ ስላለው አይደለም፡፡ ‹‹የሰው ልጅ አለው ጎጆ እንደ ወፎቹ/የሚደክምላቸው ሚስትና ልጆቹ›› የሚለው ንባብ ከፍ ብሎ፣ ‹‹ወፎች ተጠራሩ፣ ነውና መምሸቱ/ወደየጎጇቸው ገብተው ሊከተቱ›› የሚለው ንባብ ስለሚያጣቅስ፣ ‹‹የወፎቹ መጠራራት›› ዝቅ ብሎ በመጣው ማንፀሪያቸው ላይ የፍቺ ብርሃን ይፈነጥቃል፡፡

በሌላ አባባል ስለሚስትና ልጆች እንድናስብ ይጋብዛል፡፡ የሰው ልጅ ወፎች ሁለቱም ባለጎጆ በመሆናቸው አቻ ወይም እኩያ ናቸው፡፡ ‹‹መጠራራት›› ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የስሜትና የሥነ ልቡና ቅርርብ ያላቸው ወገኖች በአንድ ሰዓት፣ በአንድ ቦታ ለመገናኘት ወይም አብረው ለመሆን ያላቸው ፍላጎት መገለጫ ነው፡፡ በግጥሙ ትዕይንት ሰዓቱ የጀንበር ጥልቀት፣ ቦታው ደግሞ በየጎጇቸው ነው፡፡ ጎጆ ለወፎቹ ማደሪያ መጠለያ ነው፡፡ ከሰው ልጅ አንፃር ግን (‹‹ሚስትና ልጆቹ›› ስለተጠቀሱ) ቃሉ በፍካሬ ፍቺው ትዳርንና ቤተሰብን ያሳስባል፡፡ እናም የወፎቹን መጠራራት ከጎጆ አገናዝበን ስናስበው፣ ቤተሰባዊ ፍቅርን፣ መተሳሰብን በተለይ ከአሁን አሁን መጣ የሚል ቤተሰባዊ ጥበቃን፣ ከሚወዱት የትዳር ጓደኛና ከልጆች ጋር አብሮ የመሆን ፅኑ ስሜት ያሳስባል፡፡

እዚህ ላይ የሰው ልጅና ወፎችን በትይዩ ስንኖች አምጥቶ የማነፃፀሩ ፋይዳ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው ይላሉ አቶ ብርሃኑ፡፡ የንፅፅሩ ዋና ዓላማ አንባቢ በወጉ የሚያውቀውንና በየዕለቱ የሚኖረውን ገጠመኝ (የትዳር ሕይወትና ቤተሰብ) ወደ ወፎቹ በማሸጋገር ለወፎቹ ‹‹መጠራራት›› ትርጓሜ እንዲሰጥ ማድረግ ነው፡፡ በሌላ አባባል አመሻሽ ላይ ወፎች የሚጠራሩት አብሮ ለመሆን ካላቸው ፅኑ ስሜት ነው የሚለውን ገጣሚው ለተፈጥሮ የሰጠውን ስሜትና ፍቺ ወደ አንባቢው ለማጋባት፡፡

ድንቁርና እና ሎቲ በገጣሚው ምናብ   

‹‹ሀቀኛ ጠፍቶበት በዋለበት መልቲ

ጌጥ ናት ድንቁርና የገዳዮች ሎቲ፡፡››

ይህ ዕውቁ ባለቅኔ ዮሐንስ አድማሱ ‹‹ተወርዋሪ ኮከብ›› ከሚለው ግጥማቸው ውስጥ የተቀነጨበ ነው፡፡ ይህንን ሁለት መስመር ቅንጭብ ግጥምን የሥነ ግጥም መምህር የነበሩት አቶ ብርሃኑ እንዲህ አፍታተው በ‹‹አማርኛ ሥነ ግጥም›› መጽሐፋቸው ተርጉመውታል፡፡

ለዋጭ ዘይቤ ሁለት ነገሮችን እንደሚያወዳድር፣ ሲተነተንም ሰምና ወርቅን መለየት አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ወርቅ፣ ገጣሚው ለማጉላት ወይም ለማግዘፍ የፈለገው ረቂቅ ወይም የማይጨበጥ ሐሳብ፣ ስሜት፣ ሁነት ሲሆን፤ ሰም ደግሞ ገጣሚው ከወርቁ ያመሳሰለው የተጨበጠ ወይም የታወቀ ነገር ነው፡፡

በዮሐንስ ስንኞች ‹‹ድንቁርና›› ወርቅ ሲሆን፣ ‹‹ጌጥ›› ደግሞ ሰም ነው፡፡ ገጣሚው የድንቁርናን ምንነት ያጎላው በሰሙ ሁነኛ ባህርይ ሲሆን የሰሙን ምንነት በማብራራትም ረቂቁን ሐሳብ (ወርቁን) ግልጽ አድርጓል፡፡

የግጥሙ አንባቢዎች በምንኖርበት ማኅበረሰብ ልማድ አደን የታላቅነት መገለጫ ሙያ ነው/ነበር፡፡ ታዋቂ አዳኝ፣ ተኳሽ፣ የአንበሳ ወይም የቀጭኔ ገዳይ በጆሮው ላይ ሎቲ ያንጠለጥላል፡፡ ሎቲ የጌጥ ዓይነት ነው፣ ከብር፣ ከወርቅ ወይም ከመዳብ የሚሠራ፣ በጆሮ ላይ የሚንጠለጠል ቀለበት፤ አዳኝ የሚያንጠለጥለው የክብሩ፣ የጀግንነቱ መግለጫ፣ መከበሪያውና መታወቂያ፡፡

ይህን ማኅበረባህላዊ ልማድ በመንተራስ ገጣሚው የሰነዘረው ሐሳብ፣ ሥነ ምግባሩ በላሸቀ፣ በመነሰወ (ሙስና ባነቀዘው ኅብረተሰብ) አንገታቸውን አቅንተው፣ ደረታቸውን ነፍተው የሚሄዱና የሚከበሩ መልቲዎች (ሌቦች፣ አጭበርባሪዎችና ውሸታሞች) ናቸው የሚል ነው፡፡ ስለክብራቸው ተለይተው የሚታወቁበት ጌጣቸውና መለያቸው ድንቁርና እና ደንቆሮነታቸው ነው፡፡

ገጣሚው በለዋጭ ዘይቤ የተጠቀመው የድንቁርናን ምንነት ለመግለጽ ወይም ለማስረዳት ሳይሆን፣ ድንቁርና ሀቀኛ በሌለበት ኅብረተሰብ ያለውን ክብር ለማሳሰብ ነው፡፡ ሎቲ ራሱን ሳይሆን የአንጠልጣዩን ማንነት የሚገልጽ የወግ (የክብር) ዕቃ እንደሆነ ሁሉ ለዋጩ ድንቁርናም የተገለጸው ከደንቆሮዎች አንጻር ነው፡፡ ይህ በለዋጭ ዘይቤ አማካይነት ከሰሙ ወደ ወርቁ ከተሸጋገሩ ፍቺዎች አንዱ ነው፡፡

የዓለም የሥነ ግጥም ቀን ክብረ በዓል በየዓመቱ መጋቢት 12 ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር ለማድረግ ከትምህርትና ከባህል ጋር የተያያዙት ሚኒስቴሮች፣ ከሥነ ጽሑፍ ጋር የተዛመዱት የሙያ ማኅበራት የሚያስቡበት ቀን ይመጣ ይሆን? በዓሉ በየዓመቱ ሲከበርስ በቅኔዎቻቸውና በግጥሞቻቸው ላቅ በሚሉት በሕይወት ባሉም ሆነ በሌሉ ገጣሚያን መታሰቢያ ለማድረግ ይታቀድ ይሆን?

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...