Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፈውስን በአጠባ

ፈውስን በአጠባ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት እሑድ ረፋዱ ላይ እንደ ነገሩ ሆኖ በታጠረው የአሜሪካ ግቢ ውስጥ ግርግር በዝቶበት ነበር፡፡ የመኪና ማቆሚያ ተብሎ በታጠረው ቅጥር መውደቂያ ያጡ ምስኪኖችና የአዕምሮ ሕሙማን ከአንደኛው ጥግ በተደረደሩት ወንበሮች ላይ ተቀምጠው ከፊት ለፊታቸው ያለው ገንዳ ሥራ እስኪጀምር በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ከለበሱት ውኃ ነክቶት የማያውቁ አፈር መሳይ ቡትቷቸውን አውልቀው ያደፈ ገላቸውን ለመታጠብ ወረፋ መጠባበቅ ይዘዋል፡፡ የፈለጉትን በነፃነት እየተናገሩ፣ ሲያሻቸውም ለዱላ እየተጋበዙ ተራቸውን ይጠብቃሉ፡፡ አንዳንድ ኃፍረታቸውን እንኳ ሳይሸፍኑ እርቃናቸውን ከሰው መሀል ተቀምጠው ይጫወታሉ፣ ይስቃሉ፡፡

ብዙ የኋላ ታሪክ የነበራቸውና እንዳልነበሩ አድርጎ ቀን የጣላቸው ምስኪኖች በሰውነታቸው እኩል ሆነው በአንድ ገንዳ የሚታጠቡበት አንድ ማዕድ በሚቋደሱበት በዕለተ ሰንበት በአሜሪካ ግቢ የተገኙት ረፋዱ ላይ ከያሉበት በታክሲ ተለቃቅመው ነበር፡፡ ለፓርኪንግ ተብሎ በተተወው ቅጥር ውስጥ በየ15 ቀኑ እሑድ ለብዙዎች ቁም ነገር የማይመስለው የገላ መታጠብ ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡

ፀሐይና ቁሩ የተፈራረቀበት ገላቸው ውኃ የሚያገኝበት፣ መዋያና ማደሪያ የሆነውና በቆሻሻ ብዛት ቆዳ መሳይ የሆነው ቡትቷቸው እንዲሁም በአቧራና በጭቃ ኃይል አንድ ላይ የተጋገረው ፀጉራቸው ተላጭቶ ንፁህ ሆነው ዝቅ የተደረገ ሰውነታቸው የሰውነት ማዕረግ የሚያገኝበት ሰዓት ሊደርስ ጥቂት ቀርቶታል፡፡ የቀረ ነገር ቢኖር በየጎዳናው የወደቁትን መሰሎቻቸውን አንድ ዙር ከያሉበት በታክሲ ጭኖ ማምጣት ብቻ ነው፡፡

በዚህ መካከል ‹‹አልታጠብም ይቅርብኝ›› ብለው ወደ መጡበት ለመመለስ የሚሞክሩ አሉ፡፡ በግቢ ውስጥ ያሉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ግን እንዲሁ እንደዋዛ አይለቋቸውም፡፡ ታጥበው እንደሚሄዱ እያግባቡ ይነግሯቸዋል፡፡ በዚህ መካከል አምልጦ ለመሮጥ የሚሞክር የአዕምሮ ሕመምተኛ ያጋጥማል፡፡ ገንዘብ ስጡኝ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚል፣ ቦክስ ካልገጠምኳችሁ ብሎ የሚያራውጣቸውና ሌላም ሌላም የሚያደርግ ብዙ ነው፡፡

በአንድ ወቅት ባለፀጋ የነበሩ፣ ባልተጠበቀ አጋጣሚ ካሉበት የስኬት ማማ ወደ ታች ያሽቆለቆሉና የሰው እጅ ጠባቂ የሆኑም በየ15 ቀኑ እሑድ ገላቸውን ለመጠታጠብ አሜሪካ ግቢ ይገኛሉ፡፡ ቡትቷቸውን እንደተከናነቡ ከዘራቸውን ተደግፈው በሐሳብ ጭልጥ ብለው ሲታዩ ያሳዝናሉ፡፡ በሰው እርዳታ የሚንቀሳቀሱ ጉስቁልናቸው፣ ትሁት አንደበታች ራሳቸውን ከማነም በታች አድርገው ማሰባቸው ሁሉ ነገራቸው አንጀት ይበላል፡፡ የሚደረግላቸው ነገር ባይመቻቸው እንኳ ሐሳብ አይሰጡም የሰው ክብር በሚያገኙበት፣ ሁሉም እነሱን በሚልበት ዕለተ ሰንበት ይህ ነገር አይመቸኝም ይቅርብኝ ለማለት ጊዜም የላቸው፡፡

ምስኪኖቹን የማጠብና የማፅዳት ፕሮግራም እስኪጀምር የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች በመኪናቸው ጭነው የመጡ በጎ አድራጊዎች ለመቀላቀል የፈሩ ይመስል በርቀት ቆመው ማየትን መርጠው ነበር፡፡ ከ1 ሰዓት ቆይታ በኋላ በየጎዳናው የወደቁ ምስኪኖችና የአዕምሮ ሕሙማን ጭና ወደ ግቢው የገባችውን ታክሲ ተከትሎ ሁሉም በየፊናው ተሰማራ፡፡

የታክሲዋ በር እንደተከፈተ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ የማይችሉ አካል ጉዳተኞች፣ ዓይነ ሥውሮች በሰዎች ዕርዳታ፣ ከታክሲው ሲወርዱ፣ ከኋላቸው የሚያሯሩጣቸው አውሬ ያለ ይመስል ተንደርድረው ወርደው የሮጡም ነበሩ፡፡ ሁሉም ግን ከግቢው መውጣት የሚፈቀድላቸው ገላቸው ከታጠበ ንፁህ ልብስ ቀይረውና ምሣ ከበሉ በኋላ ነው፡፡ የሚታጠቡት ሰዎች ቋጥር የሚወሰነው በተገኙ አልባሳት ቁጥር ልክ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት እሑድ በነበረው የአጠባ ፕሮግራምም ወደ አጠባ ፕሮግራሙ የተገባው የሚታጠቡ ሰዎች ቁጥር 200 መድረሱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡

እነኚህ ምስኪኖች በአንድነት የሚኖሩበት መጠለያም ሆነ ሌላ ማቆያ የላቸውም፡፡ የሚታጠቡበት የተለየ በስማቸው የተያዘ ቦታም የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ይህንን ዓይነት የበጎ አድራጎት ሥራ የሚሠራው አካል ተብለው በወጉ የተደራጀና የሚጠሩበት የተለየ ስም እንኳ ያለው አይደለም፡፡ የዚህ በጎ አድራጎት ፕሮግራም አስጀማሪ አስተባባሪው ሁሉም ነገር የ31 ዓመቱ አስመሮም ተፈራ ነው፡፡ አስመሮም የደህና ቤተሰብ ልጅ ሆኖ የወረሰው ንብረት ወይም የሚመካበት ሥራ ያለው ጥሩ ደመወዝ የሚያገኝ ሰው አይደለም፡፡ ያለው ነገር ቢኖር ለጋስ ልብና የድህነትን አስከፊነት ከባዱን የረሃብ ስሜት ማወቁ ብቻ ነው፡፡

ተወልዶ ያደገው እዚሁ አዲስ አበባ በርበሬ በረንዳ አካባቢ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ወደ ጎዳና የወጣው ነፍስ ሳያውቅ ነበር፡፡ ገና በልጅነቱ ወደ ጎዳና ለወጣው አስመሮም በልቶና ጠጥቶ ማደር፣ እንደ እኩዮቹ ትምህርት ቤት ገብቶ ፊደል መቁጠር የማይታሰብ የቀን ቅዥት ነበር፡፡ አንድ ሰውዬ ግን ከሌሎቹ በተለየ ያቀርቡታል፡፡ ምን እንደነበር፣ ከየት እንደመጣ የኋላ ታሪኩን ባያውቁም ሲያቀርቡት ይዘርፈኝ ይሆናል ብለው አይሠጉም፣ ጫማና ልብስ ሲገዙለትም ገንዘባቸው አያሳስባቸውም ነበር፡፡ ውሎና አዳሩ ጎዳና ላይ ቢሆንም ደግነትን ግን በእኝህ ሰው እንደተማረ ይናገራል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፓርኪንግ ሠራተኛ ሲሆን፣ በወር የሚያገኘው እዚህ ግባ አይባልም፡፡ የሚኖረው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ በሚያድርባት ከራስ ቴአትር በታች በኩል በሚገኝ አጥር ሥር በጣላት ዳስ ውስጥ ስለሆነ የቤት ኪራይ ወጪ የለበትም፡፡ የሚሠራውም እዚያው ስለሆነ ወደ ሥራ በመመላለስ የታክሲ አያባክንም፡፡

ማደሪያዬ የሚላት ዳስ በተበጣጠሰ የዕድር ድንኳን በሚመስል ሸራና ማዳበሪያ የተዋቀረች የጥበቃ ቤት ነች፡፡ ከሚተኛበት ፍራሽ በላይ በኩል ከጣሪያው ጋር እንደነገሩ ታስራ የተንጠለጠለች ቴሌቪዥን አለችው፡፡ የዕረፍት ጊዜ ኖሮት በቴሌቪዥን መስኮት በሚታዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን እያየ ባይዝናናም እንደ እሱ በልጅነታቸው ጎዳና ላይ የወጡ ልጆች የቃና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እንደሚከታተሉበት ይናገራል፡፡ ከዚህም ሲያልፍ የአስመሮም ዳስ ዝናብ ያስቸገራቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚያጋራቸው አዳራሽ ነች፡፡ የታመመች በረንዳ ላይ መተኛት የማትችል እናት ሳትቀር በአስመሮም ዳስ ውስጥ ሰሌን ዘርግታ ወይም ማዳበሪያ አጥንፋ ጎኗን ልታሳርፍ ትችላለች፡፡ በወጉ መዘጋት ብርቋ የሆነባት የአስመሮም ዳስ ችግር ለጠናባቸው ሁሉ ክፍት፣ ልማት አደናቃፊ ተብላ እስካልተነሳች የድሆች መሸሸጊያና መጠጊያ ነች፡፡

ያገኛትን ከመሰሎቹ ጋር ተካፍሎ መብላትን የሚመርጠው አስመሮም ለሁሉም ማልበስና መመገብ ባይችልም ከዳሱ ሥር በምትፈልቀው የምንጭ ውኃ የተቸገሩትንና ንፅህና ብርቅ የሆነባቸውን ማጠብ ግን አያቅተኝም ብሎ ወደዚህ ተግባር ከገባ ስምንት ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይናገራል፡፡ ሳሙና ሲቸግረው የተመለከቱ ሳሙና በመግዛት ሲያግዙት፣ ትርፍ ልብስና ጫማ እየሰጡት የእሑድ አጠባ ፕሮግራም እስካሁን ሊቆይ ችሏል፡፡ በቸርነታቸው የሚለግሱት እንጂ በማስታወቂያ ዕርዱኝ ብሎ አስነግሮ አይደለም፡፡ ማስታወቂያ የሚያስነግርበት አቅም ቢኖረው ለእነዚያ ምስኪኖች እራት ደግሞ ይገዛላቸዋል እንጂ ሌላ አይታየውም፡፡

ይህንን የበጎ አድራጎት ተግባሩን በሰው በሰው የሰሙ ያለበት ድረስ በመሄድ አስፈላጊውን ዕርዳታ ያደርጉለታል፡፡ ምግብ አዘጋጅተው አልባሳት ሸክፈው በየ15 ቀኑ እሑድ አሜሪካ ግቢ ይገኛሉ፡፡ ጎንበስ ቀና ብሎ አመስግኖ ሳይጨርስ አልታጠብም ብሎ የሚያስቸግርን ማግባባትና መለማመጥ ይጀምራል፡፡ የበደላቸው ያህል ይገላምጡታል፣ ይሰድቡታል አሯሩጦ ይዞ ብርድ ልብስ መስሎ የተያያዘ ፀጉራቸውን እየታገለ ይቆርጣል፡፡ ቆርጦ ሳይጨርስ ከአቅሙ በላይ የሆነበት መቀሱ በመሀል ይሰበርበትና ሌላ መፈለግ ይጀምራል፡፡ ሁሉንም ለይቶ እንደሚያውቅ ሁሉ በቅፅል ስማቸው እየጠራ ሲያናግራቸው የአዕምሮ ሕሙማኑ ሳይቀሩ ከቁጣቸው ሰከን ይላሉ፡፡

‹‹የሚሞሸሩበት ቀናቸው ነው›› የሚለው አስመሮም እሑድ ንፁህ ሆነው፣ በልተው ጠግበው እንዲጨፍሩ ሞቅ ያለ ሙዚቃ ይጋበዛሉ፡፡ ተቀባብለው እየዘፈኑ ሲጨፍሩ ነገሮች የተሳኩላቸውና በኑሯቸው ደስተኛ ይመስላሉ፡፡ ዕለተ ሰንበት በአሜሪካ ግቢ ደስታን ገንዘብ አይገዛውም የሚለውን አባባል እውነተኛነት የሚያዩበት ቅጽበት ነው፡፡ ለጋስ ለመሆን ደግሞ የግድ ባለገንዘብና ባለፀጋ መሆን እንደማያስፈልግ በአስመሮም ያስተውላሉ፡፡

አስመሮም በየ15 ቀኑ ከሚያዘጋጀው የአጠባ ፕሮግራም ውጪ በየቀኑ ምሣ ይጋብዛቸዋል፡፡ የምሣ ወጪውን የሚችለውም ከዳሱ ሥር የምትፈልቀውን የምንጭ ውኃ ሸጦ የሚያገኘው ገንዘብ ያብቃቃል፡፡ ያልበቃው እንደሆነ ለምነው መብላት የማይችሉ የአዕምሮ ሕሙማንን ተርበው እያየ ዝም ማለት አይቻልም ከሚያውቃቸው ሰዎችም ቢሆን ብድር ይጠይቃል፡፡ በዚህ ሥራ የተለያዩ ገጠመኞችን አስተናግዷል፡፡ ‹‹አንድ ቀን ምሣ የማበላቸውን ነገር አጥቼ በጣም ተቸገርኩ ከዚያም አንድ ባለሱቅን 300 ብር አበድረኝ አሁን እከፍልሃለሁ ብዬ ለምኜ ብር ሰጠኝ፡፡ ነገር ግን የምከፍለው አልነበረኝም፡፡ በጎደለኝ ሞልቼ ካበላኋቸው በኋላ የምከፍለው ስለሌለኝ ለተወሰኑ ቀናት ተደበቅኩኝ፤›› በማለት ያስታውሳል፡፡ የቆሸሸ ገላቸውን ሲያጥባቸው የሚተፉበትና ጆሮ ግንዱን በጥፊ የሚያሞቁለት አሉ፡፡ በአንድ እጁ ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ በወፍራሙ የተሰመሩ የሚመስሉ ሁለት ተጣሳዎችን እያሳየ ‹‹እንዲህ ያደረገኝ የአንደኛውን አዕምሮ ሕመምተኛ ሳጥብ ነው፤›› አለ፡፡ ከርቀት ሲያዩት እንደ አንዳች ነገር የሚፈረጥጡና ጠጋ ብለው ሰላም የሚሉት ብዙ ናቸው፡፡ ባደረገላቸው ክብካቤ ወደ ጤናቸው ተመልሰው አብረውት የሚሠሩም እንዳሉ ይናገራል፡፡

የአስመሮምን አርአያን የሚከተሉ እንደ አንዋር ባህሩ ያሉ ወጣቶች አብረውት ላይ ታች ሲሉ ይውላሉ፡፡ ‹‹ከሱ ጋር በመሆኔ ብዙ ጥሩ ነገር ተምሬያለሁ፡፡ በጣም ደስተኛ ነኝ፤›› ይላል፡፡ ከዚህ ቀደም በጥቁር ገበያ ላይ የገንዘብ ምንዛሪ ደላላ ሆኖ ይሠራ የነበረው ወጣት አንዋር ለማኅበረሰቡ የሚሰጠው ገንዘብ ባይኖረውም አስመሮምን ማገዝ ሥራው ካደረገ ውሎ አድሯል፡፡

በሌላው ዓይን ብዙም ቦታ የሌላቸው ነገሮች ለተቸገሩና ኑሮ ገፍቶ ጎዳና ላይ ላወጣቸው ወገኖች ሕይወት የማትረፍ ያህል ዋጋ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የአስመሮምን የበጎ አድራጎት ድርጊት ለመደገፍ ባለሀብት መሆን ግድ አይልም፡፡ ሳሙና  ገዝቶ ማቅረብ ባይችሉ መቀስ ይዘው የተባይ ምንጭ ከሆነው ፀጉራቸው ይገላግሏቸዋል፣ ገላቸውን ያጥባሉ፣ ይህንን ማድረግ ባይችሉ እንኳ ከሚያውቋቸው ጋር ስለአስመሮም ድርጊት በማውራት የሚችሉትን እንዲረዷቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡

ሳሙና፣ ቫዝሊን፣ ማበጠሪያ፣ መቀስና ሌሎችም መርጃ ቁሳቁሶች እንዲሁም 100 ሰዎችን መመገብ የሚችል ስንቅ ሸክፈው በቅጥሩ የተገኙት አቶ ታደሰ ኃይሌ ‹‹ያወጣነው ገንዘብ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ለእነሱ ግን ብዙ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከእህታቸውና ከመላ ቤተሳበቸው ጋር ነበር አስመሮምን ለማገዝ የተገኙት፡፡ ስለ ሥራው የሰሙት በማኅበራዊ ድረ ገጽ መሆኑን በመግለጽ፣ ሰዎች የአቅማቸውን ማድረግ የሚችሉበት ሌሎችን ግን የመታደግ ያህል ክብደት ያለው ሥራ መሥራት እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ እንደ አስመሮም አገላለጽ፣ በጎ ተግባር ከሚያከናውኑት በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶች ምግባረ ሠናዩን ለመደገፍ በሚመስል መልኩ የሚታጠቡትን በማጠብ እንረዳለን ብለው በማስመሰል፣ ለፌስቡክ ገጻቸው ፍጆታ በሞባይላቸው ‹‹ሰልፊ›› ፎቶ ይነሡና ይዝናኑበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...