ሰላም! ሰላም! ሰላምታዬ በያላችሁበት በኩንታል በኩንታል ተጭኖ ደጃችሁ ይድረስልኝ፡፡ ይህ ልዩ ሰላምታ ከመላው ቤተሰቤ ማለትም ከእኔ ከደላላው አምበርብር ምንተስኖት፣ በዚህ ዘመን በባትሪ ተፈልጋ ከማትገኘው ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ፣ መቼም ባሻዬንና የባሻዬን ልጅ አለመጥቀስ እንጀራ ያለ ማባያ እንደ ማቅረብ ነው፡፡
ባሻዬ፣ ‹‹አሁን አገር እያጠፋ ያለው ምቀኛና እምቦጭ ነው፤›› ብለው በፀሎት ጊዜያቸው ወደ እግዜሩ መልዕክታቸውን ሲልኩ ነበር፡፡ እምቦጭን ከምድራችን ንቀልልን በሚለው የፀሎት ርዕሳቸው ልጃቸው አልተስማማም፡፡ እንዲህ ብሎ ሲሞግታቸው ነበር፡፡ ‹‹አየህ አባባ ይህ የእግዜሩን ጣልቃ ገብነት የሚጠይቅ ችግር አይደለም፡፡ ምሁራኖቻችን፣ ሐኪሞቻችን፣ እንዲሁም የባህል ሐኪሞችን ሳይቀር በአጠቃላይ ተምረናል ተመራምረናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ መማር መመራመራቸውን እምቦጭን ከኢትዮጵያ በማባረር ካልገለጡት ድንቄም!›› ብሎ ሲተርትባቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ባሻዬ ይህ ችግር ከኢትዮጵያ አዋቂዎች በላይ ነው ብለው በማመናቸው ለእግዜሩ መፀለያቸውን ገፍተውበታል፡፡
በነገራችን ላይ ‘እምቦጭ’ ብለን የሰየምነው ጓደኛ አለን፡፡ ማለትም የሚጠጣ ነገር አቅርቡለት፣ በየትኛውም ዓይነት መሥፈሪያ የሚሠፈር ሊሆን ይችላል በሊትር በሉት፣ በጋሎን በሉት፣ በበርሜልም አቅርቡለት፣ በአካባቢው የሚፈልገው ነገር መፀዳጃ ቤት ብቻ ነው፡፡ ከበርሜሉ ወደ ሆዱ፣ ከሆዱ ወደ መፀዳጃ ቤቱ ያጋባዋል፡፡ መጠጣትን እንደ ወዳጅ አድርጎ ተቀብሎ እየኖረ ይገኛል፡፡ ቢያንስ በፆም እንኳን አትጠጣ ቢሉት ለምቦጩን ይዘረግፋል፡፡ በሚጠጣው ነገር ጉዳይ እግዜሩም ቢሆን አስተያየት እንዲሰጠው አይፈልግም፡፡
‹‹በቃ እጠጣለሁ እስከምሞት ድረስ እጠጣለሁ፡፡
ቆይ እኔን ምን አድርግ ነው የምትሉኝ? የሰው ሚስት አላማገጥኩ፣ አልሰረቅኩ፣ የባልንጀራዬን ሀብት አልተመኘሁ፣ ወይም ደግሞ ሰክሬ ማንንም አልተሳደብኩ፡፡ ለምንድነው ገና ለገና ጠጣህ ብላችሁ አንዴ ከእምቦጭ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከዓሳ ነባሪ ወይም ውኃ ከሚወዱ ፍጥረቶች ጋር የምታነፃፅሩኝ? በቃ ተውኝ በሁዳዴም እጠጣለሁ ከሁዳዴ በኋላም እጠጣለሁ…›› እያለ ተንጣጣብን፡፡
በዚህ ብቻም አይበቃም፡፡ ‹‹ስንት አለ አይደል እንዴ እየፆመ ስንቱን እያተራመሰ የሚያድር?›› በማለት ብሶቱን እንደ ጉድ አዘነበው፡፡ ‹‹እንዲያውም አንድ ገጣሚ እንዲህ ብሎ ገጥሞ ነበር…›› ሲለን፣ ይህ ሰው እንደ እውነቱ ከሆነ ቢራ ጠርሙስ ላይ የተጻፈውን ብቻ አንብቦ፣ የሚፈልገው ዓይነት ቢራ መሆኑን ከማረጋገጥ ውጪ ሌላ ጽሑፍ ያነባል ብለን ጠርጥረን አናውቅም ነበር፡፡ በዚህም መነሻነት ምን አንብቦ ይሆን ብለን አፋችንን ከፍተን ጠበቅነው እሱም ቢሆን እንዲህ ሲል አነበነበልን፡፡
እውነተኛ ፆም
ሮብ ዓርብን ሥጋ ሳይበላ ቃሉን እንዳከበረ፣
ግና አንቺ ዘንድ መጥቶ አደረ፡፡
ሲታይ ሥጋው ደካክሟል ሁለት ናቸው ምክንያቱ፣
አንድም ካንቺ ማደሩ አንድም ስብ አለመብላቱ፡፡
እንዳላደረ ጦሙን የፍየል ሥጋን ንቆ፣
መዥገር ሆኖ ተገኘ ካንቺ ሥጋ ተጣብቆ፣
የአምላክ ትዕዛዙን ሰምቶ ቃሉን ከተገበረ፣
እውነተኛ ፆም ካሉ መፆምስ አንቺን ነበረ፡፡
በማለት ሲያነበንብልን በጣም ተመስጠን አደመጥነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ሁላችንንም የኮነነች ግጥም ነበረች፡፡ ምክንያታችን ደግሞ አብዛኞቻችን ፆም ነው እያልን የሰው ሥጋ በወሬ ቅርጥፍ አድርገን ስለምንበላ ነው፡፡ ባሻዬ እንደሚሉት የሰው ሥጋ በፆምም በፍስክም ክልክል ነው፣ ነውር ነው፡፡ እኛ ግን ያው አንዳንዴ ሥራ ሲጠፋ አንድ ሰው ወደ ጠረጴዛው እንጎትትና ዘልዝለን እንበላዋለን፡፡ ታዲያ የምንጎትተውን ሰው ሁለመናውን ቦረታትፈን እንመገበዋለን፡፡ በወሬ መሆኑን ልብ በሉልኝ፡፡ የሠራቸው ስህተቶች አይቀሩ፣ የጠበሳቸው ሴቶች አይቀሩ፣ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ከብዙ አቅጣጫ እየተነሱ ይቀጠቀጣሉ፡፡
ወዳጃችን በድንቅ ሁኔታ መልስ ስለሰጠን ከእርሱ አናት ላይ ወርደን ሌላ የምንወጣበትን አናት እየፈለግን ጥቂት ተብሰለሰልን፡፡ የባሻዬ፣ ‹‹ልጅ እኛ አገር ሰው ሰውን ሳያማ ለአምስት ደቂቅ ማውራት አይችልም፤›› ያለኝ ትዝ አለኝ፡፡ በእርግጥ ወደ ወሬዎቻችን መለስ ብዬ ሳጤነው ሰው ወደ ጠረጴዛው ካልመጣ ወሬያችን ውኃ፣ ውኃ ይልብናል፡፡ ከዚህ የተነሳ አንድ ሰው ወደ ጠረጴዛ መጥራታችንን ተያይዘነዋል፡፡ ዛሬም ይኸው ወዳጃችን ሲያመልጠን መንግሥትን ወደ ጠረጴዛው ላይ አውጥተነዋል፡፡ ትንሽ እንቦጭቅ አይደል? እውነት እኮ ነው፣ ባይሆን ትንሽ ቦጨቅ ቦጨቅ አድርገን ወደ መሰነባበቻው ላይ ንሰሐ እንገባለን፡፡
‘ኢሕአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትር ከቻይና ሊያስመጣ ነው’ የሚል ወሬ ወደ ጠረጴዛው ላይ መጣ፡፡ ትንሽ ተሳቀ፡፡ የባሻዬ ልጅ ነበር ይህንን ያመጣው፡፡ ‹‹አያደርጉትም አይባልም፡፡ ከቻይና ኢትዮጵያ ያላስገባችው አንድ ነገር ቢኖር እርሱ ነበር፡፡ እርሱንም ለማስመጣት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው የሚል ወሬ ሰምቻለሁ፤›› ብሎን ትንሽ ተሳለቀ፡፡ ይኼኔ ወሬው በሙሉ በውሰት ስለሚመጡት ቻይናዊው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ፡፡ እሱ ብቻም አይደለም በውሰት ለሌላ ቡድን የሚጫወቱ ተጫዋቾች፣ እንዲሁም ተውሰን ስላልመለስናቸው ነገሮች ተተረተረ፡፡
ሁሌም ወሬውን ተቀብሎ የራሱን ሐሳብ ጨምሮበት ወደ ሌላው ያስተላልፈዋል፡፡ እንዲህም አለ፡፡ አንደኛው እንዲሁ ከአንደኛው አፍ ወሬውን ሞጭልፎ እንደዚህ አለ፣ ‹‹ከቻይና ተምረን የማንጨርሰው በርካታ ቁምነገር አለ፡፡ ስለዚህ አሁንም ከዚህ ቻይናዊው በውሰት ካስመጣነው ጠቅላይ ሚኒስትራችን በርካታ ለአገር የሚጠቅሙ ነገሮችን እንማርበታለን፡፡ በተለይ ደግሞ ከየትኛውም ዘር ስላልሆነ ለየትኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ዘር ወገንተኝነትን አያሳይም፡፡ ስለዚህ በፅድቅ ለማንም ሳያደላ ይፈርዳል…›› እያለ አብራራ፡፡
ይሁን እንጂ ወዲያው ወሬው እየጦዘ ወደ ባሻዬ ልጅ ደረሰ፡፡ የባሻዬ ልጅ ቀጠለ፣ ‹‹ቻይኖች በውሻ ስም የተሰየመውን አዲሱን ዓመታቸውን በቅርቡ ማክበር ጀምረዋል፡፡ እግዚአብሔር ያሳያችሁ እኛ ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ… እያልን እንደምናከብረው መሆኑ እኮ ነው፤›› አለ፡፡ በእርግጥ ባሻዬም፣ ‹‹ከውሻ የምንማረው በርካታ ቁምነገር አለ…›› ብለው ማስረዳት ጀመሩ፡፡ ‹‹ታማኝነቱ…›› ብለው እንደሚቀጥሉ ምንም ጥርጥር አልነበረኝም፡፡ እኔም እስማማለሁ፡፡ ዳሩ ግን ወደ ሥልጣን የሚመጣው ሰው የታማኝነት፣ የማስታረቅ፣ የመዋደድ ዓመት፣ የመቀባበል ዘመን ብሎ በአንዳንዶች ዘንድ የተቋጠረውን ጥቂት ቁርሾ ማጥፋት ካልቻለ፣ ነገርዬው እየከፋ እንደሚሄድ ለመገመት የፖለቲካ ተንታኝ መሆን አያስፈልግም፡፡
እንዲያው ግን ወዳጆቼ ከእኛ ዘመን አቆጣጠር በተጨማሪ፣ አዲስ የዘመን አቆጣጠር አምጡ ቢባሉ ምን ብለው ይመጡ ይሆን? እርግጠኛ ነኝ የውሻ ዘመን እንደማይሉ፡፡ እኔማ የአናብስት ዘመን ቢባል ብዬ ተመኘሁ፡፡ ባሻዬ ስለአንበሳ ሲያወሩ ላደመጣቸው ቤታቸው ውስጥ ያሳደጓቸው አሥር አናብስት ያሏቸው ነው የሚመስሉት፡፡ ‹‹አንበሳ ምን አንበሳ ቢሆን ብቻውን ለአደን አይወጣም፡፡ የአንበሳ ሞገሱ ብርታቱና ኃይሉ ያለው ኅብረቱ ላይ ነው፡፡ ለአንድ አንበሳ አንድ ጐሽ በቂው ነው፣ በቴስታ አሽቀንጥሮ ያፈርጠዋል፡፡ ሆኖም አናብስት ወደ ጐሽ መንጋ ሲቀርቡ መላው የጐሽ ማኅበር ይረበሻል፣ ለምን ሺሕ አሥር ሺሕ አይሆኑም፡፡ ምን ይኼ ብቻ በመላው ዱር ያሉ የአናብስትን በኅብረት መምጣት ተመልክተው ይርዳሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አንበሳ ካበረ ለምንም እንደማይበገር ያውቁታል፡፡ ስለዚህ አናብስትን ሲመለከት ምድረ አራዊት አየር ላይ እንደተረጨ አቧራ ይበተናል፤›› በማለት ሰፊ ማብራሪያ ሰጡ፡፡
በእርግጥም ይህንን ያሉበት ምክንያት አላቸው፡፡ ምክንያታቸው አንድ እንሁን ነው! ከተበታተንን የሰው ማላገጫና የአገር ድድ ማስጫ እንሆናለን፣ አንድ ከሆንን ግን በማስፈራራትና በማስደንገጥ ገናናነታችን እንደተጠበቀ እንኖራለን ማለታቸው ነው፡፡ ታዲያ ፀሎታችን ይኼ ሆኗል አንድ ትልቅ አንበሳ እንዲሰጠን፡፡ ድንበሩን የሚጠብቅ፣ ልጆቹን የማይንቅ ወንድ አንበሳ እንዲሰጠን እየተመኘሁ ዛሬን ልሰናበታችሁ፡፡ የባሻዬ ልጅ የነገረኝን ሳልነግራችሁ መጨረስ አልፈልግም፡፡ ‹‹ድር ተባብሮ አንበሳ ማሰር ከቻለ፣ አንበሳ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ከተባበረ፣ ለማንም የማይበገር ብርቱ ሠራዊት እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም ነበር፤›› ያለኝ፡፡ ልክ አይደለም?
አንዱ ወዳጄም፣ ‹‹የእኔም ዋና መልዕክት ይህ ነው፡፡ እናንተ በምድረ ኢትዮጵያ በሰሜንና በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ ለምትገኙ አናብስት በሙሉ እስካሁን ብቻ ለብቻ ልናደርግ ያሰብነውን ወዲያ ቸል ብለን፣ እነሆ አንድ ታላቅ ኢትዮጵያ የምትባል የአናብስት አገር እንፍጠር የሚል ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፤›› አለ፡፡ እንግዲህ በየአቅጣጫው ተንታኝ በዝቶ የለ? ዘመኑን የትንተና ነው ብለን ብንቀበል ምን ይለናል? ማነው ግን ስንቱን ተንትነንና አስተንትነን እንችለዋለን ያለው? መልካም ሰንበት!