Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊ‹‹ሜድ ኢን ኢትዮጵያ›› የጉድለት ምልክት ሆኖ እስከመቼ?

‹‹ሜድ ኢን ኢትዮጵያ›› የጉድለት ምልክት ሆኖ እስከመቼ?

ቀን:

ከየቤቱ በሚወጣ ደረቅ ቆሻሻና ፍሳሽ የተበከለውን የመሿለኪያን ዳገት እንደወጡ ሞቅ ወዳለው የሃዲድ ገበያ ይደርሳሉ፡፡ በዳገቱ አናት ላይ የማይሸጡ የአልባሳት ዓይነቶች የሉም፡፡ በውድነታቸው የሚታወቁ የአውሮፓና የሌሎች አገሮች ብራንድ ልብሶች፣ ጫማዎችና የውስጥ ልብሶች ሳይቀሩ በርካሽ ይሸጣሉ፡፡ በቡቲኮች እስከ 500 ብር ድረስ የሚያወጡ ካናቴራዎች፣ 5000 ብር ድረስ የሚሸጡ ውድ ውድ የራት ልብሶችና ሌሎችም ከ40 እስከ 400 ብር ድረስ ባለው የዋጋ ሠንጠረዥ ይሸጣሉ፡፡ ምክንያቱም ገበያው በሕገወጥ መንገድ ድንበር ተሻግረው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ልባሽ ምርቶች መሸጫ በመሆኑ ነው፡፡

በሳምንት ሁለት ጊዜ ረቡዕና ቅዳሜ በሚቆመው የልባሽ ጨርቆችና አልባሳት መሸጫ ወደሆነው ሃዲድ ጎራ የሚሉ አዲስ አበቤዎች በማንኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ጀምሮ ያላቸው የሞላ ኑሮ የሚኖሩ ሳይቀሩ ቅንጡ መኪናቸውን ከዳገቱ ስር አቁመው ወደ ገበያው ይጣደፋሉ፡፡

በሰፋፊ ማዳበሪያዎች ተጠቅጥቀው ለገበያ ከሚቀርቡ ልባሾች መካከል አዳዲስ የመሸጫ ዋጋ ምልክቶች (ፕራይስ ታጋቸው) ያልተነሳላቸው አልባሳት ያጋጥማሉ፡፡ ሃዲድ በየሱቁ ተዘዋውረው በስንት ልፋት ማግኘት ያልቻሉት ዓይነት ልብስ እንደልብ የሚያገኙበት የሰልባጅ ገበያ ነው፡፡ ጊዜ ያለፈባቸው የድሮ ፋሽኖች ሳይቀሩ በሃዲድ ገበያ እንደ አዲስ ይሸጣሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ከቡቲክ በውድ ዋጋ ገዝተው የለበሱትን ምርጥ ሱሪ አልያም ቀሚስ ከሰልባጅ መካከል እዚህ ግባ በማይባል ዋጋ ሲሸጥ ሊያጋጥሙ ይችላል፡፡ አልያም የከተማውን ሽቅርቅር ወጣቶች ከአንደኛው ዳስ ገብተው የሚሆናቸውን ልባሽ ሲመራርጡ፣ ሲያነሱ ሲጥሉ ያያሉ፡፡

- Advertisement -

እስከ 5000 ብር የሚሸጡ ኮምፈርቶች፣ ውድ ውድ አልጋ ልብሶች አልያም ዘናጭ መጋረጃዎች እዚህ ግባ በማይባል ዋጋ ይሸጣሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አዲሱን ከሱቅ መግዛት በሚችሉበት ዋጋ የሚሸጡን ዕቃዎች ተሻምተው የሚገዙ ሰዎችን ሊያዩ ይችላሉ፡፡

የሃዲድ ነጋዴዎች አጥበውና ተኩሰው ለሽያጭ የሚያቀርቧቸውን ልባሾች ከአዲሱ የሚለዩት ፕራይስ ታግ ስለሌላቸው፣ አልያም የሚሸጡት ከልባሽ ጎራ በመሆኑ ብቻ እስኪመስል አዲስ ዕቃ እንደሚያጋጥም ገበያውን የሚያዘወትሩ ይናገራሉ፡፡ አንድ ሁለት ቀን የተለበሱ የሚመስሉን ‹‹ሴትየዋ አንድ ቀን ለብሳ ብቻ የጣለችው›› እያሉ ደንበኛን አሳምነው ለመሸጥ በሚጣጣሩ ነጋዴዎች የተሞላው ሃዲድ ለመንቀሳቀስ እስኪያስቸግር ድረስ በገዥና ሻጭ የተጨናነቀ ነው፡፡

በአንድ ጎኑ ተለማምጠው ለመሸጥ በሚጣጣሩ፣ በሌላው ደግሞ ርካሽ ዕቃ በማግኘቱ ተደስቶ ያገኘውን ሁሉ ለሚሸምት ደንበኛ ዕርዳታ እንደሚያደርጉ ሁሉ ቅብርር የሚሉ ነጋዴዎች ሞልተውበታል፡፡ አንዳንድ የተረገጡ ጫማዎችን አድሰው፣ በቀለም አሽሞንሙነው የሚያቀርቡ ነጋዴዎች የሚጠሩት ዋጋ ደንበኛ የአገር ውስጥ ቆዳ ጫማ የሚሸጥበትን ያህል ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲያውም ያገለገሉ የአገር ውስጥ ጫማዎች ሳይቀሩ ‹‹ቶርሽን›› ተብለው ይሸጣሉ፡፡ በየሱቁ ገዥ የራቃቸው የቻይና ጫማዎች ሳይቀሩ በቶርሽን ስም በውድ ዋጋ ሊሸጡ ይችላሉ፡፡ ገዥው የሚታየው ከሃዲድ የሚገዙ ዕቃዎች ጠንካራ የውጭ ምርቶች በሚል ስም ስለሆነ ጥንካሬያቸውን የሚጠራጠር፣ አዲሱን ከሱቅ በምን ያህል መግዛት እችላለሁ ብሎ የሚያገናዝብ ከስንት አንድ ነው፡፡

እንዲህ ካሉ የልባሽ መሸጫ ገበያዎች ገዝተው ከአዳዲስ ልብሶች ጋር ቀላቅለው የሚሸጡ አንዳንድ ነጋዴዎች እንዳሉ፣ በአዲስ ስም የሚሸጡ የሱቅ ልብሶች ለወራት ማሳያ (ዲስፕሌይ) ላይ ሲቆዩ ስላለመለበሳቸው በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል የሚሉ ምክንያቶችን በመደርደር ጥራት የሌላቸውን ምርቶች ለዚያውም በተጋነነ ዋጋ የሚሸጡ ነጋዴዎች ባለበት አገር እንደ ሃዲድ ካሉ ገበያዎች ልባሽ መግዛት ምንም ክፋት እንደሌለው ማንነታቸውን ያልገለጹ አንዲት ወይዘሮ ይናገራሉ፡፡ አራትና ከዚያ በላይ ልብሶች መግዛት በሚችሉበት ዋጋ ከቡቲክ አንድ ሲገዙ መኖራቸው እንደሚቆጫቸው የሚናገሩ ወጣቶችም ያጋጥማሉ፡፡

አገሮች እንደ ኢኮኖሚያቸው የዕድገት ደረጃ የሚያመርቷቸውና ከሌሎች አገሮች የሚያስገቧቸው ምርቶች መጠንና ዓይነት የተለያየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ያላቸው ዜጎቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ማናቸውንም ዓይነት ምርቶች በራሳቸው አምርተው ቀሪውን ለጎረቤት ለዓለም ገበያ ሲያቀርቡ በተቃራኒው ያሉ አገሮች ደግሞ ከሚያመርቱት ይልቅ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቧቸው ምርቶች መጠን ሲበልጥ ይታያል፡፡

እንዲህ ካሉ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስለመሆኗ ከማንም የተደበቀ ምስጢር አይደለም፡፡ ግብርና መር ኢኮኖሚዋ እንኳንስ የዜጎቿን ፍላጎት ማሟላት በሁለት እግሩ ለመቆም የሚንገዳገድ ነው፡፡ ለዘመናት ወደ ውጭ ከሚላከው እንደ ቡና ያሉ የግብርና ምርቶች ባሻገር የኢንዱስትሪ ምርቶች ብዙም አይታወቁም ነበር፡፡

የአገር ውስጡን ገበያ ፍላጎት በተወሰነ መልኩ ሲሸፍኑ የሚታወቁት በተለይም በቆዳና በጨርቃ ጨርቅ ረገድ የዓይን ማረፊያ ከሆኑ እንደ አንበሳ ጫማ፣ ፒኮክ፣ አደይ አበባና የመሳሰሉት የቆዩ ፋብሪካዎች ውጪ ብዙም የሚጠቀሱ የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ያኔ በተቋማቱ ይመረቱ የነበሩ የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች የጥራት ደረጃ ብዙዎች ያውቁታል፡፡ በፋሽን መልክ ጥቅም ላይ ለማዋል አስቸጋሪ ከመሆን ባለፈ ምቾት የሚነሱ እንደበሩ የሚታወስ ነው፡፡ ባልለፋ ቆዳ በሚሠራው ጫማ እግሩ ያልተላጠ የለም፡፡

ወደ አገሪቱ የሚገቡ የውጭ ምርቶች የሕዝቡ ዋነኛ አማራጭ እንደነበሩም አይዘነጋም፡፡ ባህር ማዶ ዘመድ ያለው ከአሜሪካ ጫማ፣ ሱሪ አምጣልኝ ብሎ ያስቸገረ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ይህ ሙሉ ለሙሉ ቀርቷል ማለት ባይቻልም በመጠኑም ቢሆን መቀነሱን ማየት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በየአገሩ  በተለይም በአዲስ አበባ እንደ አሸን የፈሉት የልብስ ሱቆችና ጫማ ቤቶች ገንዘቤ ይቸገር ለሚሉ ዓይነተኛ አማራጭ እንደሆነ ሁሉም ያውቃል፡፡

ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ የአገር ውስጥ አምራቾችም የተሻሉ ምርቶችን ይዘው በመውጣት ተጨማሪ አማራጭ መሆን ችለዋል፡፡ በጋርመንትና ጨርቃ ጨርቅ ቆዳና ሌዘር ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ቁጥርም በዚሁ መጠን ከፍ ብሏል፡፡ ቦርሳ፣ ጫማ፣ ቀበቶ፣ ጃኬት፣ ካናቴራ፣ ቱታ፣ ሱሪና ሌሎችም ምርቶች በተሻለ ጥራት እየሠሩ የሚያቀርቡ ጥቂት የማይባሉ ድርጅቶችን ማፍራት ተችሏል፡፡

ካለው የሕዝብ ቁጥር አንጻር ማቅረብ የሚችሉት የምርት መጠን ምን ያህል በቂ ነው የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ጥሩ ጅምር እንዳለ ግን ማየት ይቻላል፡፡ በዋጋም ረገድ ከሌሎቹ ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች አንጻር ኪስ የማይጎዱ ሊባሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ ይህ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የአገር ውስጥ ምርትን እንዲያዘወትሩ መንገድ የከፈተ ቢሆንም የተለያዩ መስተካከል ያለባቸው ወሳኝ ችግሮች መኖራቸው አይካድም፡፡ ሰፊው ሕዝብ በአገር ውስጥ ምርት እንዳይተማመን፣ ይህም ጥራት አላቸው ብሎ የሚያምንባቸውን የባህር ማዶ ምርቶችን በውድ እንዲገዛ፣ ሲያልፍም እንደ ሃዲድ ያሉ የልባሽ ጨርቆች መሸጫ ገበያዎችን እንዲመርጥ መንገድ የሚከፍት ሆኗል፡፡

በልባሽ ጨርቆች ዘንጦ ያደገውና በኋላም ወደ ልባሽ ጨርቆች ንግድ ገብቶ የነበረው የኔነህ ቶሎሳ አዲስ ተብለው በየሱቁ ከሚሸጡ ልብሶች ልባሽ ጨርቆች በጥራት እንደሚበልጡ ይናገራል፡፡ በጥንካሬም ሆነ በአንዳንድ የጥራት መለኪያዎች የተሻሉ መሆናቸውንም ይመሰክራል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሰልባጅ ንግዱን ትቶ በሌላ ሙያ የተሰማራ ሲሆን፣ አጋጣሚው በልባሽ ጨርቆች ቦታ አዳዲስ አልባሳትን ገዝቶ እንደሚጠቀም አስገድዶታል፡፡ ነገር ግን በዚህ ደስተኛ ሊሆን አልቻለም፡፡ ሁለቱን ምርቶች ሲያወዳድር የሰማይና የምድር ያህል የጥራት ልዩነት እንዳላቸው ይሰማዋል፡፡

ለአገር ውስጥ ምርቶች ቅድሚያ ቢሰጥም በታጠበ ቁጥር የመጨማደድ፣ የመሞላቀቅ ሲያልፍም የመንጣት ባህሪ ስላየባቸው በአገር ውስጥ ምርት መዘነጥ አይታየውም፡፡ ብርድ ለመከላከል ብቻ ከውስጥ ይለብሳቸውና በላያቸው ሸሚዝ ይደርባል፡፡ ያለባቸው የስፌት ችግርም እንዲሁ በአገር ውስጥ ምርት እንዳይተማመን አድርጎታል፡፡ ስለዚህም በውድ ዋጋ የሚሸጡ የአውሮፓ ብራንዶች ተጠቃሚ ለመሆን ተገዷል፡፡ በተራመደ ቁጥር እግሩን የሚልጥ የአገር ውስጥ ጫማ ከማድረግም ናይኪ ስኒከሮችን ማዘውተር ይመርጣል፡፡

‹‹ማኅበረሰቡ የአገር ውስጥ ጫማ ከማድረግ ከባህር ማዶ የሚገቡ ጫማዎችን በ3000 ብር ገዝቶ ማድረግ ይመርጣል፤›› የሚሉት የመታገስ አዱኛው ልብስ ስፌትና አምራች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ተረፈ ታደሰ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ ችግሩ የማኅበረሰቡ ፍላጎት ላይ መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ባለመሠራታቸው የተፈጠረ ክፍተት መሆኑን ‹‹አምራቹ የኢትዮጵያን ተጠቃሚ ንቋል፡፡ አንድ ነገር አምርቶ ለመሸጥ ደንበኛ የሚፈልገውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ልክ እንደ ቻይና ሁሉ ይኼኛው ምርት ለዚህኛው የማኅበረሰብ ክፍል ይኼኛው ደግሞ ለአንዱ ብሎ መለየትና ደንበኛው የሚፈልገውን ምርት ማቅረብ ግድ ይላል፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለአገር ውስጥ ገበያ ከሚቀርቡ የአገር ውስጥ ምርቶች አብዛኞቹ ገበያ ላይ መውጣት የሌለባቸው ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡ ይህም ደንበኛውን የሚያርቅና የውጭ አገር ምርቶችን በውድ ዋጋ እንዲገዛ አልያም እንደ ሃዲድ ያሉ የልባሽ ጨርቆች መሸጫ ገበያዎችን እንዲያዘወትር መንገድ እየከፈተ ይገኛል፡፡

‹‹ደንበኛው ጥራት ያለው በልኩ የተዘጋጀ ልብስ ይፈልጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በኤክስፖርት ስታንዳርድ ከተዘጋጁ ልብሶች ግማሹ ወደ ውጭ ይላክና ግማሹ ይቀራል፡፡ እነዚህ ግን አገር ውስጥ አይሸጡም ምክንያቱም የሚዘጋጁበት መጠን (Size) በአውሮፓ ስታንዳርድ ነው፤›› የሚሉት የኮቴክስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ድልነሳው ንብረት ናቸው፡፡

የጥራት ነገር ሲነሳ ከስፌቱ እንደሚጀምር የሚናገሩት አቶ ድልነሳው የአገር ውስጥ ምርቶች ከስፌት ጀምሮ የተለያዩ ጥራት ችግሮች እንዳሉባቸው ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹ አልባሳት አምራች ድርጅቶች ጥሬ ዕቃ ለማግኘት ብዙ ይቸገራሉ፡፡ ‹‹ጨርቅ በበቂ አይመረትም፣ ከእኛ ጋር አብረው ሥራ የጀመሩ ድርጅቶች ጨርቅ ከቻይና ማስመጣት ጀምረዋል፤›› ያሉት አቶ ድልነሳው ሰዎች ለሥራ መነሳሳታቸውን ኮልፌ አጠና ተራ አካባቢ ወርዶ ማየት እንደሚቻል፣ ነገር ግን ባለው የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ያለው መነሳሳት ፍሬ እንዳይዝ እያደረገው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በጨርቃ ጨርቅ ረገድ ያለው መነሳሳትና አበረታች ጅምሮች ከውጭ የሚገባውንና በተጋነነ ዋጋ ለገበያ የሚቀርበውን ምርት ማስቀረት እንደሚችል ያምናሉ፡፡ ይሁንና ያለውን መሠረታዊ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረቱን መቅረፍ ካልተቻለ የምዕራባውያንንና የቻይና ምርቶች ናፋቂነቱ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

‹‹እስካሁን በገበያ ውስጥ መቆየት የቻልነው የተሻሉ ዕቃዎችን አፈላልገን አግኝተን ስለምንሠራ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከኤክስፖርት የተረፉ ጨርቆችን ገዝተን ነው የምንሠራው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ጨርቆች በጣም አነስተኛ ስለሆኑ እንቸገራለን፡፡ አንዳንዴ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ድርጅቶች ወደ ውጭ ከሚልካቸው ምርቶች መካከል በጥራት መጓደል እስከ ሦስት ኮንቴይነር ጨርቅ ይመለስባቸዋል፡፡ እኛ ግን እንኳንስ አንቀበልም ልንል ለምነን ነው የምናሠራ፤›› ይላሉ፡፡

እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች አንድ ዓይነት የሚመስሉ ነገር ግን የጥራት ደረጃቸው የተለያየ የሆነ ቀለማቸው ቢመሳሰልም ጨርቅነታቸው ለየቅል ሆኖ የሚዘጋጁ አልባሳት ያጋጥማል፡፡ አንዳንዴም የገዙት ጫማ ግራና ቀኙ በተለያየ የቆዳ ዓይነት የተሠራ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዓይኔ ይሆን ብለው ራስዎን እስኪጠራጠሩ የገዙት መጫሚያ ቀለም፣ እንዲሁም በአሠራሩ ተመሳሳይ ሆኖ የግራው በለፋ የቀኙ ደግሞ ባለፋ ቆዳ ተሠርቶ ያገኙታል፡፡ ከቀናት በፊት የገዙት ቦርሳ ዚፑ ሊያስቸግር አሊያም እስከነአካቴው አልሠራ ሊል ይችላል፡፡ አጨራረሱ ያላማረው ጫማ ሶሉ የተመታበት ሚስማር እግርዎን እየወጋ ምቾት ሊነሳዎ አሊያም ከአንደኛው ጥግ በወጉ ያልተቀመቀመ ትርፍ ቆዳ አግኝተው ሊሆን ይችላል፡፡ የአገሬ ምርት ብለው በኩራት የገዙት ጫማ ምቾትን አጓድሎ አውልቀው የጣሉትን ከዱባይ የገዙትን ስኒከር መልሰው እንዲጫሙት ተገደው ይሆናል፡፡ እነዚህና ሌሎችም የአገር ውስጥ የቆዳ ምርቶችን ተጠቅመው በሚያውቁና እየተጠቀሙ ባሉ ሰዎች የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው፡፡ 

‹‹ቆዳችን ምንም አይወጣለትም በጣም ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ያሉብን አንዳንድ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ቆዳው ዋጋ እንዲያጣ አድርጎታል፤›› የሚለው የኤሌላን ሌዘር ከመሠረቱ ሁለት ጓደኛሞች አንዱ ናሂል ሞሲሳ ነው፡፡ ናሂል እንደሚለው፣ ቆዳ ለማለሰልስ የሚረዱ ኬሚካሎችን ከማግኘት ጀምሮ ይቸገራሉ፡፡ የሚያዘጋጇቸውን ቦርሳዎችና የወንድ ጫማዎች በሚስብ መልኩ ቀለማቸውን ከስታይል አዋደው ቢሆንም ግብዓቶች (አክሰሰሪስ) አያገኙም፡፡

ምቹ ጫማ ለማዘጋጀት ደረጃውን የጠበቀ ሶል ከገበያው ማግኘት ዘበት ነው፡፡ ዚፕና ሌሎች አክሰሰሪዎችም የተዋጣለት ምርት ይዘው ገበያ እንዳይወጡ ለብዙዎቹ የአገር ውስጥ አምራቾች ማነቆ ሆነውባቸዋል፡፡ ስለዚህም ተስማሚውን ሶልና እንደ ዚፕ ያሉ አክሰሰሪዎችን በውድ ዋጋ ከባህር ማዶ ለማስመጣት ይገደዳሉ፡፡ ይህ የተሻለ ምርት እንዲያቀርቡ ቢያስችላቸውም ዋጋቸው ወደድ እንዲል፣ ከውጭ በርካሽ ከሚገቡ ምርቶች ጋር እንዳይወዳደሩ እያደረጋቸው እንደሚገኝ ናሂል ይናገራል፡፡ 

እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ደግሞ ከዋጋም ከጥራትም አንፃር ማኅበረሰቡ የባህር ማዶ ምርቶችን እንዲመርጥ እያደረገ ይገኛል፡፡ ጥራትንም ዋጋንም አሻሽሎ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ኢንጂነር ተረፈ ደግሞ የአገር ውስጥ ምርቶች በዋግ ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻሉ ይህም ሌላው ገበያን ሰብሮ መግባት እንዳይቻል ማነቆ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እንዲያውም ማኅበረሰቡ ለአገር ውስጥ ምርቶች ቅድሚያ ሠጥቶ እንዲገዛ የማስታወቂያ ሥራ መሠራት እንዳለበት፣ ምርቶችን በቅናሽ ዋጋ ከመሸጥ ሲያልፍም በነፃ እየሰጡ ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ መሠራት እንዳለበት ያምናሉ፡፡

እንደ ቱርኩ አይካ ያሉ የውጭ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን በሙሉ ኤክስፖርት ለማድረግ ይገደዳሉ፡፡ አልመዳ፣ አርባ ምንጭ፣ ኮምቦልቻ፣ ባህርዳር፣ ማ ጋርመንት የመሳሰሉ የአገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች አሥር እንደማይሆኑ፣ እነዚህ ፋብሪካዎች ግን ከ20/80 እስከ 40/60 ድረስ ምርታቸውን ለአገር ውስጥ ገበያና ለወጭ ንግድ መላክ ይችላሉ፡፡ ‹‹ጥራት ያላቸው ምርቶች ኤክስፖርት ይደረጋሉ፡፡ ዝቅተኛ ጥራት ያላቸው ናቸው ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርቡት፡፡ ይህም የመንግሥት ስትራቴጂ ነው፤›› የሚሉት የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንቱ አቶ ፋሲል ታደሰ ናቸው፡፡

ስትራቴጂው የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ችግር ከመቅረፍ ባሻገር በኤክስፖርት ንግድ ዘርፍ የተሠማሩ፣ ልምድ እንዲቀስሙ፣ ብቁ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ ነው፡፡ አቶ ፋሲል ፋብሪካዎቹ ብቁ መሆን አለመቻላቸው በዓለም አቀፉ ገበያ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውስጥ ገበያም እንዲወጡ የሚያደርጋቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ወቅት ያለው ሥር የሰደደ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ያላቸውን ፋብሪካዎች አቅም በሙሉ ተጠቅመው እንዳይሠሩ ማነቆ ሆኗል፡፡

‹‹ዘንድሮ ጥጥ የለም፡፡ የዶላር ዋጋ ሲጨምር የጥጥ አምራቾች ያላቸውን በሙሉ ኤክስፖርት አደረጉ፡፡ ቀድሞ ከገዛው ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ በስተቀር ሁሉም ተቸግረዋል፡፡ ባለው የጥጥ እጥረት የአቅማቸውን 20 እና 30 በመቶ ብቻ ነው እየሠሩ የሚገኙት፤›› ብለዋል አቶ ፋሲል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በየዓመቱ ከውጭ የሚመጣው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዋጋ አንድ ቢሊዮን ዶላር እየደረሰ ነው፡፡ በማኑፋክቸሪን ዘርፉ የተሠማሩ ግን አንዳንድ ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን የሚገዙበት የውጭ ምንዛሪ አጥተው ቆመዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ቅድሚያ ለማኑፋክቸረሮች ይሰጥ ብሎ ያወጣው መመርያ በተገቢው መንገድ እየተተገበረ አይደለም፡፡ በተለይ የግል ባንኮች መመርያውን ለማስተግበር ወደ ኋላ ይላሉ፡፡

እንዲህ ያሉ በውጭ ምንዛሪ እጥረት አደጋ ላይ የሚወድቁ ዘርፎችን በዘላቂነት ለማገዝ የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች እዚሁ የሚያገኙበት መንገድ ማመቻቸት ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ በጨርቃ ጨርቅና ጋርመንት በቆዳና ሌዘር ዘርፍ ለተሠማሩ ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችን የሚያመርቱ ድርጅቶን መፍጠር አሊያም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስመንት እንዲሠማሩ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ይህንንም ለማድረግ የልብስና የጫማ ፋብሪካዎች ቁጥር አሁን ካለበት በከፍተኛ ደረጃ መጨመር አለበት፡፡

እንዲህ ያሉ የአገር ውስጥ ምርቶችን አንድ ዕርምጃ ወደፊት ማስኬድ የሚችሉ አቅርቦቶች በበቂ መቅረብ እስኪችሉ ምን ያህል ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል በውል አይታወቅም፡፡ ታዲያ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ እንደ ምርት ሳይሆን፣ እንደ ጉድለት የሚታየው የአገር ውስጥ ምርት፣ በአገር ምርት ለሚኮሩ ብቻ ሆኖ እስከ መቼ ይዘልቃል የሚለው ጉዳይ አሳሳቢና አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ምርት ከጉድለት ጋር ተያይዞ ስለሚነሳ የተሻለ ጥራት ያላቸውን ዕቃዎች የሚያመርቱ የአገር ውስጥ አምራቾች ‹‹ሜድ ኢን ኢትዮጵያ›› የሚለውን መለያቸውን እንዲተውት በቸርቻሪዎች ጫና እንደሚደረግባቸው የኮቴክሱ አቶ ድልነሳው ይናገራሉ፡፡ እነኚህ ተደራራቢ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ የቻይናና ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች፣ የምዕራባውያንን ልባሽ ጨርቆች አሁንም ዘርፉን እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...