Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የኤታኖል ፋብሪካ ሊገነባ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር በ1.1 ቢሊዮን ብር ወጪ የኤታኖል ፋብሪካ ሊገነባ ነው፡፡ የኤታኖል ፋብሪካው የሚገነባው በደቡብ ኦሞ ኩራዝ ሦስት የስኳር ፋብሪካ ሲሆን፣ ኤታኖሉ የሚመረተው ከኩራዝ አንድና ኩራዝ ሦስት የሚወጣውን ሞላሰስ በማጣራት እንደሆነ ታውቋል፡፡

በማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን የነዳጅና ባዮፊውል ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ናደው ታደለ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬሽናቸው ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ተባብሮ የኤታኖል ማምረቻውን መገንባት የሚያስችለውን ስምምነት ሰኞ መጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ተፈራርሟል፡፡

በስምምነቱ መሠረት የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን በሚገነባው የኤታኖል ማጣሪያ ላይ የ80 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ሲኖረው የስኳር ኮርፖሬሽን የ20 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ እንደ አቶ ናደው ገለጻ የኤታኖል ማጣሪያው በሁለት ክፍል ይገነባል፡፡ በ872 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው የመጀመሪያው ክፍል የኤታኖል ማጣሪያ በቀን 50,000 ሊትር ኤታኖል የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡ የሁለተኛው ክፍል ግንባታ 218 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የማምረት አጠቃላይ አቅሙን 100,000 ሊትር በቀን እንደሚያደርሰው ይታመናል፡፡ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ 1.1 ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚያስወጣ ተገምቷል፡፡ የፋብሪካው ግንባታ ሁለት ዓመት እንደሚፈጅ ተገልጿል፡፡

ለፋብሪካው ግንባታ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ከኢንዱስትሪ ልማት ፈንድ በብድር እንደተገኘ አቶ ናደው ገልጸዋል፡፡ ‹‹የፕሮጀክት አማካሪ ለመቅጠር በሒደት ላይ ነን፡፡ በቀጣይ ግንባታውን የሚያካሂድ ኮንትራክተር ቀጥረን ሥራውን በቅርብ ጊዜ እንጀምራለን፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ኤታኖልና ቤንዚን በማደባለቅ ተሽከርካሪዎች ለማንቀሳቀስ የምትጠቀም ሲሆን፣ እስካሁን 64 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል በማደባለቅ 50 ሚሊዮን ዶላር ማዳን እንደተቻለ ተገልጿል፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳወቅ አብቴ የፊንጫና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች የኤታኖል ማጣሪያዎች ገንብተው በዓመት 30 ሚሊዮን ሊትር በማምረት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬሽኑ 13 የስኳር ፋብሪካዎች በመገንባት ላይ እንደሆነ የገለጹት አቶ እንዳወቅ፣ የፋብሪካዎቹ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በቀን 158,250 ቶን ሸንኮራ አገዳ የመፍጨት አቅም፣ 6,330 ቶን ሞላሰስና 1.5 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል የማምረት አቅም እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን ሦስት የኤታኖል ማጣሪያዎች ለመገንባት አቅዷል፡፡ የአገሪቱ የነዳጅ ፍላጎት በየዓመቱ ከአሥር እስከ 15 በመቶ በማደግ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ደርሷል፡፡ መንግሥት በየዓመቱ ከ2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለነዳጅ ግዥ ወጪ የሚያደርግ በመሆኑ፣ የባዮፊውል ልማት በማስፋፋት ለነዳጅ የሚወጣውን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይና የካርቦን ልቀት ለመቀነስ የሚያስችል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት መርሐ ግብር ነድፏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች