በደቡብ ክልል ካፋ ዞን በዴቻና በጨታ ወረዳዎች ጠረፍ አካባቢ በመኤኒት አርብቶ አደሮችና በወረዳዎቹ ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት፣ የሰዎች ሕይወት እንደጠፋና በርካታ ከብቶች እንደተዘረፉ ምንጮች ከሥፍራው ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
በሁለቱ ወረዳዎች ጮጫና አመች በተባሉ ቀበሌዎች በአርብቶ አደሮችና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል በየዓመቱ ግጭት እንደሚቀሰቀስ የገለጹት ምንጮች፣ አርብቶ አደሮቹ የጋብቻ ወቅት ሲደርስ ለጥሎሽ የሚሰጧቸውን ከብቶች በንጥቂያ ለመውሰድ ወደ መንደር እንደሚገቡ፣ በዚህም ምክንያት ግጭቶች በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ አስረድተዋል፡፡
በግጭቱ ምክንያት ከአሥር በላይ ሰዎች መገደላቸውንና ቁጥራቸው ያልታወቁ የቁም እንስሳት መዘረፋቸውን ከሥፍራው ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አባላት ምልከታ ለማድረግና መረጃዎችን ለማሰባሰብ ግጭቱ ወደ ተከሰተበት ሥፍራ መጓዛቸውን ማወቅ ተችሏል፡፡
የካፋ ዞን በደቡብ ክልል ከሚገኙ ዘጠኝ ዞኖች አንዱ ሲሆን፣ በ11 ወረዳዎች የተዋቀረ ነው፡፡ ካፋ ዞን በቡና መገኛነት የሚታወቅ ነው፡፡ ከደቡብ ኦሞ ዞን፣ ከቤንች ማጂ ዞን፣ ከኮንታ ዞንና ከሸካ ዞኖች፣ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ጋር ይዋሰናል፡፡