Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርይዋል ይደር እንጂ አህያ የጅብ ናት!

ይዋል ይደር እንጂ አህያ የጅብ ናት!

ቀን:

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለ26 ዓመታት መንግሥትን ሲጠይቅ ከነበሩት ጥያቄዎች መካከል የዴሞክራሲ መብቶች አለመከበር፣ የመልካም አስተደደር ዕጦትና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹ ሲንከባለሉ ቆይተው አሁን አገሪቱ ለገጠማት የፖለቲካ ቀውስ ሰበብ ሆነዋል፡፡ ለዚህ ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት መንግሥት ነው፡፡

ሕዝቡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ ሲያቀርብ ለቆያቸው ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ምላሽ በማጣቱ ለተፈጠረው ግጭትና ለጠፋው የሰው ሕይወት የመንግሥት ባለሥልጣናት ተጠያቂ ናቸው፡፡ ተቃውሟቸውን ያሰሙ በነበሩ ሰላማዊ ሠልፈኞች ላይ በመተኮስ ግድያ የፈጸሙ የፀጥታ ኃይሎችም ለፍርድ የሚቀርቡበት ጊዜ ይመጣል ብለን እንጠብቃለን፡፡

በደርግ ዘመን ነጭ ሽብርና ቀይ ሽብር እየተባለ ላለቁ ወገኖቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በተሠራው የሰማዕታት ሐውልት ውስጥ ያለውን የአፅም ክምችት እያየን ፀፀቱ ከህሊናችን ሳይወጣ፣ አሁንም የጭካኔ ዕርምጃ ሲወሰድ ማየታችን የዚች አገር መከራ መቋጫው መቼ ነው? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ ለችግሮቹ መፈጠር መሪ ተዋንያን የሆኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ታላላቅ መድረኮችን በመቆጣጠር በሙሰኞች መራባት፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦትና በፍትሕ መዛባት ዙሪያ መፍትሔ አምጥተናል የሚሉትን ተግባር አልባ ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብና ባዶ ዲስኩር በመደስኮር አጃቢዎቻቸውን ያስጨበጭባሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አንድ ሙሰኛ ሌላኛውን ሙሰኛ ደፍሮ መናገር ስለማይችል፣ ችግሮቹን በግንባር አፍረጥርጦ ለመናገርና ለመጋፈጥም ተራው ዜጋ ለሕይወቱ ዋስትና ስላጣ ችግሮቹ አብጠው ሊፈነዱ ግድ ሆኗል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በነፃነት መዘዋወርና ንብረት ማፍራት በዚህ አገር አልተከለከለም፡፡ እንዲህ የሚሉ ካሉ ግን የሚሉን እነማን ናቸው? የሚያሰኝ ነው፡፡ እስከሚገባኝ ድረስ በየአካባቢው በተነሱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች የወደሙ ንብረቶች ሆነ ተብለው ተለይተው እንጂ በጅምላ እንዲቃጠሉ ወይም እንዲወድሙ አልተደረገም፡፡

ብሔር ተለይቶ ጥቃት ተፈጽሟል የሚሉ ወገኖችን አቤቱታ አምኖ ለመቀበል የሚያግደን ዋናው ምክንያት ሀብት ለማፍራት ዓመታትን ያስቆጠሩ፣ ላባቸውን ያፈሰሱና ጉልበታቸውን ሲጨርሱ የኖሩ የየትኛውም ብሔር ተወላጆች ንብረት ከመውደም ይልቅ ጥበቃ ሲደረግለት መታዘባችን ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ብሔር ላይ ያተኮረ ጥቃት ተፈጽሟል የሚል ቅስቀሳ በሚዲያ እንዲተላለፍ የፈቀዱ ፖለቲከኞች ሕዝቡን ወዴት እየወሰዱት እንደሆነ ለሚያስብ ሰው ነገሩ ግልጽ ነው፡፡ ድርጊታቸው ኃላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን ነውረኛነትም ነው፡፡

ሙሰኞቹ በተፈጠረላቸው የሙስና መረብ ተቧድነው ሕንፃ መገንባታቸውና የንግድ ድርጅቶች ማቋቋማቸው አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ነው፡፡ አልጠገብ ባይነት የፈጠረው፣ ቁጭት ያስነሳው የማግለል ዕርምጃ እንጂ በሁከትና ብጥብጥ ብቻ በጅምላ የሚፈረጅ አካሄድ አይለም፡፡ በዕድሜያቸው ለጋ የሆኑ ወጣቶች የሪል ስቴት ባለቤቶች ሲሆኑ፣ በመቶ ሺሕዎች በሚቆጠር ዶላር መርከብ ተከራይተው የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ከቻይናና ከቱርክ ሲያስጭኑ ገንዘቡን ከየት እንዳመጡት ከማጣራት ይልቅ ሙስና ስለመፈጸሙ ማስረጃ የለንም በሚሉ ድፍን ባለሥልጣናት ሽፋት ሲሰጣቸው ሰምተናል፡፡ ታዝበናል፡፡

በግጭቱ ሕይወታቸውን ያለፈ ወጣቶችም ቢሆኑ የአማራን፣ የኦሮሞን፣ የትግሬንና የሌሎችንም ብሔሮች ተወላጆችን ያካተተ አሳዛኝ ክስተት ተፈጽሟል ተብሎና በአግባቡ ተጠንቶ እውነተኛው ነገር ለሕዝብ መቅረብ ሲገባው፣ የሚታየው ግን የፖለቲካ ፍጆታ ለመሸመት የሚደረግ ማቀጣጠል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ እነዚህ ሙሰኞች በሥርዓቱ የተፈለፈሉ እንደመሆናቸው መጠን ገና ኮሽ ሲል ይሸበራሉ፡፡ በቀበሌ መታወቂያ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተበደሩት ገንዘብ ፎቅ ገንብተው በዶላር የሚያከራዩ ስንት ናቸው፡፡

የፋብሪካ ባለቤቶች፣ በሪሞት የሚከፈትና የሚዘጋ ውድ መኖሪያ ቤት የገነቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ እጅግ ዘመናዊ መኪና በማሽከርከር የሚታወቁ፣ የረቀቀ የሙስና መረብ ስላላቸው የተበደሩትን የሕዝብ ገንዘብ የተበላሸ ብድር በማስባል የሚያሰርዙ ስንትና ስንት እንደሆኑ አይታወቅም ማለት ክህደት ነው፡፡ አንድ ምስኪን ዜጋ ተበድሮ የዶሮ እርባታ ቢጀምርና ወደ ገበያ ገብቶ መሸጥ እስኪጀምር ድረስ አበዳሪው ባንክ የዕፎይታ ጊዜ ስለማይሰጠው የተበደረውን ከወለዱ ጋር አዳምሮ በወቅቱ አልከፈልም በማለት አንገቱን አንቆ ንብረቱን ለሐራጅ ሽያጭ ያዘጋጀዋል፡፡ ይህ አሠራር ተገቢነት የለውም ለማለት ሳይሆን፣ ለሁሉም በእኩልና በፍትኃዊነት አይሠራም ነው ነጥቡ፡፡

ምግብ በማጣት፣ እየራባቸው በየትምህርት ቤቱ እያዞራቸው የሚወድቁ ሕፃናት ተማሪዎች በብዛት ባሉበት አገር ውስጥ ሙስና ፈጽመው የደለቡ ዝሆኖችን ለይቶ መቃወም ከብሔር ጥቃት ጋር ሆን ተብሎ የሚያያዝበት አካሄድ ተገቢ አይደለም፡፡ ለመሆኑ በዩኒቨርሲቲዎች፣ እንደ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ በሜቴክና በሌሎችም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስለተመዘበረው የሕዝብ ገንዘብ ዋናው ኦዲተር ለፓርላማው ያቀረበው ሪፖርት ለሕዝቡ ይፋ የሚወጣውና የሚገለጸው መቼ ነው?

ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ከ17 ቀኑ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ማግሥት በሰጡት መግለጫ ከሰማይ በታች ያልተነጋገርንበት ነገር የለም ብለውን ነበር፡፡ ሙስናን እንደ ሥራ ቋንቋ ቆጥረው አልፈውት ይሆን እንዴ?

(ወ.ተ፤ ከብሶት አደባባይ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...