Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትሊቀመንበሩን የሚወልደው ምርጫ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አደራ ይወስናል

ሊቀመንበሩን የሚወልደው ምርጫ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አደራ ይወስናል

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሁለቱም ሥልጣን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን (የሚለቁ መሆናቸውን) በድንገት ከገለጹ፣ እነሆ ሳምንቱ መጨረሻ ላይ 38 ቀን ሆነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሥራው ላይ ያሉት፣ ተተኪያቸው እስኪመረጥና ሥልጣኑን እስኪረከብ ድረስ ብቻ መሆኑንም በዕለቱ (የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም.) እና ከዚያ ጀምሮ ሲነገረን ቆይቷል፡፡

በኢሕአዴግ የፓርቲ የመተዳደደሪያ ደንብ መሠረት የኢሕአዴግን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበርን የሚመርጠው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ነው፡፡ (በኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 19/2/በ) በተጠቀሰው ደንብ እንደተወሰነው፣ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ግንባሩን ከአንድ ጉባዔ እስከሚቀጥለው ጉባዔ ድረስ በበላይነት የሚመራው የፖለቲካ ድርጅቱ የሥልጣን አካል ቢሆንም፣ ‹‹የግንባሩ የመጨረሻው ከፍተኛ የአመራር አካል›› ግን የኢሕአዴግ ጉባዔ ነው፡፡ እንደተጠቀሰው በራሱ በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት የኢሕአዴግን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር የመመረጥ ሥልጣን የተሰጠው፣ መደበኛውን ስብሰባ በየስድስት ወራት የሚያካሂደው የድርጅቱ ምክር ቤት ስብሰባውን የጀመረው (ስብሰባውን ስለመጀመሩ የተናገረው) ገና ማክሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው፡፡ ስለዚህም የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ገና አልተመረጠም፣ ሳይመረጥም እነሆ አሁንም ከወር በላይ እየቆጠርን ነው፡፡

የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ግን የአንድ ፓርቲ የአንድ ማኅበር፣ የአንድ ድርጅት ሊቀመንበር ብቻ አይደለም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ጉዳዩ በቀረበበት ሁኔታና መልክ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው፡፡ ብዙ ባይብራራም ተዘርዝሮ የተደነገገና ረገጥ ተደርጎ የተበየነ፣ የሕዝብም የጋራ ግንዛቤና ንቃት የሆነ ነገር ባይኖርም በሕግም የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀመንበር ምርጫ በማሸነፍ አማካይነት፣ ከፖለቲካ ሥልጣን ጋር ቀጥተኛ ዝምድና አለው፡፡ ይህ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 እና 73 ውስጥ ተደንግጓል፡፡ የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል፣ ማለትም መስተዳድሩን የሚያደራጀውና የሚመራው በምርጫ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምፅ ያገኘው የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘው ፓርቲ የመንግሥት ሥልጣን ይረከባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርም ከሕዝብ ተወካዮች የምክር ቤት አባላት መካከል ይመረጣል፡፡ እነዚህ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሥርዓተ መንግሥት ፓርላሜንታዊ ነው ከሚለው ጋር ሲነበቡ፣ ፓርቲዎች በነፃ በሚንቀሳቀሱበትና በሚወዳደሩበት፣ ነፃ ምርጫ ባለበትና በምርጫም ሥልጣን መያዝና ከሥልጣን መውረድ በሚቻልበት ፖለቲካ ውስጥ፣ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ሊቀመንበርና የአንድ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር ግንኙነትና ዝምድና ብዙም ሥውር አይደለም፡፡

በአጠቃላይና በዚህ ሁሉ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን፣ የፓርቲው ሊቀመንበር መሆንና የተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም አቶ ኃይለ ማርም ደሳለኝን የሚተካውን ተከታዩን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርላማው ‹‹መሰየም›› ይችል ዘንድ መጀመርያ ፓርቲው፣ ማለትም ኢሕአዴግ ሊቀመንበሩን መምረጥ አለበት፡፡

ኢትዮጵያ በምትገኝበት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የመልቀቂያ ጥያቄ ያቀረበ የፓርቲ ሊቀመንበርንና የአገር ጠቅላይ ሚኒስትርን ተተኪ ለመምረጥና ለመሰየም ምን ያህል ጊዜ አለን? ምን ያህል መዘግት ይፈቀድልናል? የተተኪው (የተሰናባቹ) ሊቀመንበር በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትርነት የሥልጣን ወሰንና ‹‹ጊዜያዊ›› ቆይታ ገደብ የለውም ወይ? ሊቀመንበር የመምረጥ የፓርቲው ሥልጣንና ባለመብትነትስ የራሱ የፓርቲው የብቻ ጉዳይ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ብቻቸውን የሚያብከነክኑና ምላሽም ማግኘት ያለባቸው ናቸው፡፡

እንኳንስ ሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲ የሌሎች ፓርቲዎችም የኃላፊነት ቦታዎች ምርጫና ምደባ የፓርቲዎች የራሳቸው የብቻ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ በፓርቲዎች ላይ ብቻም የታጠረ አይደለም፡፡ ማኅበራትንም ይጨምራል፡፡ ግልጽ ባለ አነጋገር የማኅበር አመራር ምርጫም የማኅበራት የራሳቸው ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን በሚገርም ሁኔታ ሕገ መንግሥቱ ይደነግጋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሠራተኞች፣ በንግድ፣ በአሠሪዎችና በሙያ ማኅበራት (አንቀጽ 38/2) በሕዝባዊ ድርጅቶች (38/4) ውስጥ ለኃላፊነት ቦታዎች የሚካሄዱ ምርጫዎች ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፈጸም አለባቸው፡፡

በዚህ ምክንያት በማኅበር የመደራጀትን መብት የሚገዙና የሚያስተገብሩ የተለያዩ ሕጎች አሉ፡፡ ከፍትሐ ብሔር ሕጉ ጀምሮ ያሉ በማኅበር መደራጀትን፣ ማኅበር ማቋቋምን የሚመለከቱ ሕጎች (ተሠራባቸውም አልተሠራባቸውም) ለምሳሌ የማኅበርተኞችን ትክክለኛነት ይወስናሉ፡፡ ማኅበርተኞቹ ሁሉ እኩል መብት አላቸው ማለት ነው፡፡ ጠቅላላላ ጉባዔው የመጨረሻው ባለሥልጣን ነው ይላሉ፡፡ የማኅበርተኞቹ ጠቅላላ ጉባዔ ለማኅበሩ የበላይ የመጨረሻ ባለሥልጣን ነው ተብሎ ተደንግጓል፡፡ ማኅበሩ የመመሥረቻ ጽሑፍና የውስጥ ደንብ ይኖረው ዘንድም ግድ ነው፡፡  

የፖለቲካ ፓርቲን በተለይ የሚገዛው የአገራችን ሕግ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2008 ነው፡፡ ይህ ሕግ የወጣው በሕጉ በራሱ መግቢያ እንደተገለጸው፣ ‹‹በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዜጎች የመደራጀት መብታቸውን ተጠቅመው በሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በመሳተፍ የፖለቲካ ሥልጣን የሚይዙበትን ሁኔታ በሕግ መደንገግ አስፈላጊ በመሆኑ›› እና ‹‹ዜጎች የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሠርቱና በአባልነት ሲንቀሳቀሱ ስለሚኖራቸው መብትና ግዴታ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊከተሏቸው የሚገቡ መሠረታዊ መርሆዎችን በመደንገግ ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ›› በማስፈለጉ ነው፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲው ሊኖሩት ይገባል ተብለው ከተዘረዘሩት ዋና ዋና የፓርቲ ሰነዶች መካከል የፖለቲካ ፕሮግራምና የመተዳደርያ ደንብ ይገኙበታል፡፡ ፕሮግራሙ ዓላማው አድርጎ የያዘውን የፖለቲካ እምነት የቀረፀበት፣ ፓርቲው ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚንቀሳቀስበትን ሥልትን የሚገልጽ የተግባር መመርያ ሰነድ ነው፡፡ መተዳደርያ ደንቡ  ደግሞ ከሌሎች መካከል የፓርቲውን የሥልጣን አካላትና የሥራ ኃላፊነታቸውን፣ አመዳደባቸውንና አመራረጣቸውን የሚወስን ነው፡፡

የእነዚህ ሰነዶች ይዘት ከላይ በሕገ መንግሥቱ፣ ከሕገ መንግሥቱ በታች ደግሞ በመሠረታዊ የፓርቲ ሕጎች የሚገዙ በመሆናቸው የፓርቲው የራሱ ጉዳይ አይደሉም፡፡ በምንነጋገርበት ዓይነትና የአንድ የፓርቲ ሊቀመንበር የአገር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን በሚችልበት አግባብ ደግሞ፣ የፓርቲው የውስጥ አሠራርም ሆነ የምደባና የሹመት ጉዳይ የፓርቲው የራሱ የብቻው ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አሠራርና የውስጥ ዴሞክራሲ በጥብቅ የሚገዙ በተግባር የተፈተሹና የተፈተኑ ሕጎች አሉን ወይ? የሚለው ጥያቄ መልስ የአገራችን የፓርቲ ፖለቲካ አካሄድና ዕርምጃ ነፀብራቅ ነው፡፡ የሚተማመኑበትና በሕግ አምላክ ብለው የሚያስፈራሩበትም ሆኖ ወጥቶ አልታየም፡፡ አንድ እያገላበጡ የሚያዩትና በዚህም ምክንያት ከተለያየ ማዕዘን ሊፈተሽ የሚገባ የሕግ ድንጋጌ ለአብነት ያህል እናንሳ፡፡

አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መንቀሳቀስ የሚችለው የተመዘገበ መሆኑን የሚደነግገው ሕግ፣ ለምዝገባ የሚቀርበው ማመልከቻ በፖለቲካ ፓርቲው መሪ ተፈርሞ መቅረብና ማመከታቸውም በሕጉ የተዘረዘሩትን ሰነዶች ማያያዝ እንዳለበት ይወስናል፡፡ ከምዝገባ ማመልከቻ ጋር ተያያዘው መቅረብ አለባቸው ብሎ ሕጉ ግዴታ ካደረጋቸው ሰነዶች መካከል አንዱ፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡ መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ›› (አንቀጽ 8/2/ረ) ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ የብዙ ‹‹ችግሮች›› መነሻ ነው፡፡ አንዳንዶችን እንጠቁም፡፡ ችግሩ የሚነሳው ድንጋጌው ከተቀመጠበት ቦታ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡ መሆን አለባቸው ብሎ፣ የአንድን የፖለቲካ ፓርቲ የመተዳደርያ ደንብ መዋቅር መነሻ (መንዕስ) ይዘት መደንገግ አንድ ነገር ነው፡፡ ፓርቲን ለማስመዝገብ ሲቀርብ የፖለቲከ ፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡ መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ ይዞ መቅረብ ያስፈልጋል ማለት ሌላ ነገር ነው፡፡ የመጀመርያው ግልጹን ይናገራል፡፡ ሁለተኛው የሚናገረው እግረ መንገዱን ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ የኢሕአዴግ መተዳደርያ ደንብ አንቀጽ 19/2/በን ይጣላል፡፡ በመተዳደርያ ደንቡ የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎችን (የሥራ አስፈጻሚ አባላትና የፓርቲ መሪዎች) ማለትም የግንባሩን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር የሚመርጠው ጠቅላላ ጉባዔው ሳይሆን፣ ከእሱ በታች ያለው ምክር ቤት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ዛሬም እሠራለሁ የሚለው በዚህ የ1999 ዓ.ም. መተዳደርያ ደንቡ መሠረት ነው፡፡

በምሳሌነት የጠቀስኩት ጉዳይ ብዙ ነገር ያሳያል፡፡ ሕገ አወጣጣችንን ያስገምታል፡፡ በቀላሉ ከሕግ በላይ መሆን የመቻልን የለመደበት አሠራር ክፍተቶችን ያመለክታል፡፡ የአንድ አገር ሕግ የማኅበሩን የመተዳደርያ ደንብ የማውጣትንና የማሻሻልን፣ እንዲሁም የማኅበሩን አመራሮች የመምረጥን፣ ማገድንና ማሰናበት ከጠቅላላው ጉባዔ ሥልጣን ወደ በታች አካል ሥልጣን መወከል ይችላል ወይ? በግልጽ መወሰን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ማኅበሩ በመመሥረቻው ጽሑፍ ወይም በተቋቋመበት ደንብ መሠረት በተሾሙ (በተመደቡ፣ በተመረጡ፣ ኃላፊዎች) ይመራል፡፡ ተቃራኒ ውሳኔ የሌለ እንደሆነ ማለትም በመተዳደርያ ደንቡ በተለየ ሁኔታ ካልተወሰነ በስተቀር ኃላፊዎችን የሚሾማቸው ጠቅላላ ጉባዔው ነው ይላል፡፡ ዝነኛውና የታወቀው የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማኅበራት አዋጅ እንኳን የማኅበሩን መተዳደርያ ደንብ ማውጣትና ማሻሻልን፣ እንዲሁም የማኅበሩን አመራር የመምረጥና የመሻር ሥልጣንን የሚሰጠው ለጠቅላላ ጉባዔው ነው፡፡ የአንድን ማኅበር በተለይም የፖለቲካ ፓርቲን ኃላፊዎች የመምረጥ ሥልጣን ከማኅበሩ/ከፓርቲው የመጨረሻ የበላይ የሥልጣን አካል የበታች ለሆነ አካል መስጠት አለበት? የሚለውን ጥያቄ የሚያነሳውን ጉዳይ በምሳሌነት ያመጣሁት ለእግረ መንገዳችን ነው፡፡ በዋነኛነት የምንመለከታቸው ዴሞክራሲያችንን የሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች አሉ፡፡

የአንድ አገር የፓርቲ ሕግና በዚያች አገር የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመተዳደርያ ደንቦች ሊገስሷቸው የማይችሉ መሠረታዊና መንዕስ የዴሞክራሲ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ ዋነኛው ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ በመግቢያው ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊከተሉዋቸው የሚገቡ መሠረታዊ መርሆዎችን ስለመደንገግ ቢናገርም፣ ይህንን አፍርጦ/አፍረጥርጦ አይደነግግም፡፡ በዴሞክራሲያዊ መርህ ፓርቲውን ማደራጀት መሠረታዊው ጉዳይ ነው፡፡ የዚህ ትርጉም የፓርቲው ተግባራት የሚከናወኑት፣ በቀጥታም ሆነ በተወካዮቻቸው አማካይነት እኩል መብት ባላቸው በጠቅላላው የፓርቲ አባላት ነው፡፡ መሪዎቹ የአመራር አካላትና የፓርቲው ተቋማት በሞላ በምርጫ የሚቋቋሙ፣ ለመረጣቸውም ተጠያቂና በሌሎችም ሊተካቸው የሚችሉ ናቸው ማለት ነው፡፡ ይህንን የፈተሸው፣ የሞከረው፣ ተጠየቅ ያለው ስለሌለ እንጂ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 (2 እስከ 4) ደንግጎታል፡፡ በዚህ ምክንያት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ምርጫም ሆነ የኢሕአዴግ የመተዳደርያ ደንብ የድርጅቱ የውስጥ ጉዳይ ብቻ ሆኖ ሊቀር አይችልም፡፡

የኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት፣ ስለዚህም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ምርጫ ገና ተወዝፎ በተቀመጠበት፣ አለመረጋጋትና ተቃውሞ በሚንጠው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ‹‹ምደባው››፣ ‹‹ሥምሪቱ›› ወይም ‹‹ምርጫው›› አፋጣኝ ዕርምጃ በሚጠይቅበት ወቅት፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢሕአዴጎች በይፋም ይፋዊ ባልሆነ መንገድም የሚሰጡት ምላሽ ‹‹በጥልቀት ከመታደስ›› አጀንዳቸው ጋር እንኳን አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ መጀመርያ ላይ በጉዳዩ ላይ ከአስተያየትና ከማብራሪያ ይልቅ የ‹‹መልስ ምት›› ዓይነት ምላሽ የሰጡት አቶ በረከት ስምዖን ሊቀመንበሩን መምረጥ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ሥልጣን መሆኑን፣ በድርጅቱ ውስጥ የሚያልቅ ሥራ እንደሆነ፣ ‹‹በሌሎች ኅብረተሰቡ ውስጥ በሚካሄድ ዘመቻም ሆነ በሚዲያ አማካይነት የሚከናወን ተግባር አይደለም፤›› ብለውናል፡፡ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በራሳቸው ውስጥ ያን የመሰለ የብሔራዊ ድርጅቶች አዲስና አዳዲስ ምርጫ በተካሄደበት፣ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ ለመመረጥ የብሔራዊ ድርጅት ሊቀመንበርና የምርጫው ውጤትም ከአገር ውስጥ ያለፈ ዜና በሆነበት አገር፣ መሆን አያስፈልግም ሲባልና የአስፈላጊው የድምፅ ቁጥር (60 ድምፅና አንድ ሦስተኛ) እየተጠቀሰ ሲነገር ሰምተናል፡፡ በዚህ የፌስቡክ ዘመን በመሀላ ቃል የሚያረጋግጡት አይደለም እንጂ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሕአዴግ ነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነውም ኢሕአዴግ ነው፣ ለኢሕአዴጎች የጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ ትልቅ አጀንዳቸው አይደለም፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የሥምሪት ጉዳይ ብቻ ነው ብሎ የነገረን የኢሕአዴግ የፌስቡክ አካውንት ነኝ ያለ ገጽም ዓይተናል፡፡ የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ የኢሕአዴግን ሊቀመንበር የመምረጥ ሥልጣን ያለው የግንባሩ ምክር ቤት መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ስብሰባ መጀመሩን፣ ምክር ቤቱም በስብሰባው ሒደት ውስጥ በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ተገምግሞ በቀረበለት ሪፖርትና በተዘጋጁለት ሰነድ ላይ የሚወያይ መሆኑን የገለጸልን የግንባሩ ጽሕፈት ቤት ደግሞ፣ ምክር ቤቱ የድርጅቱን የአመራር ክፍተት መጨረሻ ላይ እንደሚያሟላ ነግሮናል፡፡ ‹‹የአመራር ክፍተቱ የሚሞላውም በኢሕአዴግ ፕሮግራም፣ ሕገ ደንብና በተለመደው የኢሕአዴግ አሠራር መሠረት ነው፤›› ብሎናል፡፡

ይህ ሁሉ ማብራሪያ ግን ያንኑ ጥያቄ የተነሳንበትን ጉዳይ እንደ ሞኝ ጩኸትና ለቅሶ መልሶ መላልሶ ከመድገም ያለፈ ትርጉምና ማብራሪያ አልሰጠንም፡፡ ተደጋግሞ የሚነሳው የኢሕአዴግ መተዳደርያ ደንብ በምደባ፣ በውክልናና በምርጫ ስለሚወሰኑ/ስለሚሞሉ የኃላፊነት ቦታዎች የሚናገረውን ያህል ዝርዝር የለውም፡፡ ዝርዝሩን በጠቅላላና በሞላ የተወው ለመመርያ ነው፡፡ መመርያዎችን ደግሞ አናውቃቸውም፡፡ ‹‹በተለመደው የኢሕአዴግ አሠራር›› የሚባለውም እንኳን ለሕዝብ ለኢሕአዴግ አባላት የሚታወቅ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት የኢሕአዴግን በደንቡ ላይ ተመሥርቶ የተቋቋመ አሠራር ማወቅ ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ የኢሕአዴግ የመተዳደርያ ደንብ የአባል ድርጅቶችን መብት በሚደነግገው አንቀጹ (አንቀጽ 11) እያንዳንዱ አባል ድርጅት በውክልና በሚሞሉ የኃላፊነት ቦታዎች ሁሉ በእኩልነት የመወከል፣ በምርጫ በሚወሰኑ የኃላፊነት ቦታዎች ዕጩዎችን የማቅረብ፣ ወይም ከመካከሉ መርጦ የመመደብና አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ደግሞ የመቀየር መብት አለው ይላል፡፡  በዚህ ረገድ የተቋቋመ ‹‹የኢሕአዴግ አሠራር›› ነበር? ይህስ ሕገ መንግሥቱም ሆነ በእሱ ላይ የተመሠረቱ ሕጎች የሚጠይቁትን (ሊጠይቁት የሚገባቸውን) ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ ያሟላል ወይ? ኢሕአዴግ ይፋ ሊደርገው የሚገባ መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሚስጥሬ የእኔ የብቻዬ የሚለው አሠራር ሊኖር አይገባም፡፡

ኢሕአዴግ ስለምደባ፣ ስለሥምሪት ማውራቱ የተለመደ ነው፡፡ ምደባም ተባለ  ሥምሪት ይህን የሚወስነው ማነው ነው? በድምፅ ነው? ወይስ ይህን የማድረግ ሥልጣን የተሰጠው አካል አለ? ለእነዚህ ጥያቄዎች በሕግ ፊት የፀና ከዴሞክራሲያዊትና ሪፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ግንባታ አንፃር የማያሳፍር መልስ ለመስጠት ፓርቲው በዴሞክራሲያዊ መርህ መደራጀቱን፣ ማለትም የፓርቲው ተግባራት (ሊቀመንበር የመምረጥን ጨምሮ) የሚከናወኑት እኩል መብት ባላቸው የፓርቲው አባላት አማካይነት መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ዴሞክራሲን እገነባለሁ የሚልና ሥልጣን የያዘ ፓርቲ፣ የፓርቲው መሪዎች፣ የአመራርና የሥልጣን አካላትና የፓርቲው ተቋማትና ሹማምንቶቻቸው በምርጫ የተቋቋሙ፣ ለመረጣቸውም ተጠያቂና በሌላ የሚተኩ መሆኑን ሊነግረን ይገባል፡፡ ከዚህ ያነሰና ያነከሰ ‹‹የተለመደ አሠራር››ም ሆነ የመተዳደርያ ደንብ በጥልቀት ለሚታደሱለት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አይመጥንም፡፡

ይህን ጎደሎ ሞልተው፣ ቢያንስ ቢያንስ ሠልፍ አሳምረው ‹‹ሚኒማ››ውን  አሟልተው በተገኙ አገሮች ፓርቲዎች እንኳንስ የፓርቲውን መሪዎች ዕጩ፣ ተመራጮቻቸውን ጭምር የሕዝብ ተሳትፎ እንዲኖርበት ያደርጋሉ፡፡ የፓርቲው መሪዎች ማለት በፓርቲው የሥልጣን አካላት ውስጥ ተመርጠው የሚሠሩ ናቸው፡፡ ዕጩ ተመራጮች ማለት ፓርቲው ሕዝብ እንዲመርጣቸው በየምርጫ ክልሉ የሚመድባቸው የፓርቲው ሰዎች ናቸው፡

በየምርጫ ክልሉ የሚቀርቡት ዕጩ ተመራጮች እኛ እንደምናውቀው፣ እንደለመድነውና ኢሕአዴግም እንደፈረደብን እንደሚያደርገው ዝም ብሎ የድርጅቱ የብቻ ውሳኔ ብቻ አይደለም፡፡ የሥምሪትና የምደባ ጉዳይም አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ የአዲስ አበባ ወረዳ አንድ የምርጫ ክልል ቢሆን፣ በዚህ የምርጫ ክልል ኢሕአዴግ ከአባላቱ መካከል ዕጩ አድርጎ ለውድድር የሚያቀርበው ሰው መጀመርያ አንድ ብቻ አይሆንም፡፡ መራጩ ሕዝብ ወኪሉን ብቻ ሳይሆን ዕጩውንም ጭምር አማርጦ በሚወስንበት አገር ዕጩ የመምረጥ ሥራም ሕዝብን ያሳትፋል፡፡ ባደላቸውና በዚህ ረገድ በገሰገሱ አገሮች ዕጩን የመምረጥ መብት እስከ ዕጩዎች ምዝገባ የምርጫ ቦርድ በር ድረስ ብቻ የሚሄድ አይደለም፡፡ ከአንድ በላይ የሆኑ የአንድ ፓርቲ ዕጩዎች በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚሠፍርበት፣ መራጩ ሕዝብ በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠውን የአንድ ፓርቲ ዕጩ ሰርዞ የፈለገውን የሚመርጥበት አሠራርም አለ፡፡ የእኛ አገር የዕጩ ምደባ በፓርቲው ካድሬዎችና ሹማምንት ላይ የሚያልቅ ነው፡፡ ምደባና ሥምሪቱ ዕጩ ሆኖ ለመመዝገብ የሚያስፈልገውን በሕግ የተደነገገና በሥልጣኔ የፀደቀ፣ በምርጫ ክልሉ ከምርጫው በፊት ለተወሰነ ጊዜ ወይም ዓመት የመኖር ግዴታን ጭምር አልፎ የሚሄድ ነው፡፡ ተመራጭ እንደራሴን መሀል የምርጫ ዘመን ላይ ‹‹አንስቶ›› ወደ ሌላ የምርጫ ክልል በማሟያ ምርጫ ማስመረጥ ጭምር ያለጠያቂ የነገሠበት አገር ነው፡፡ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በቅርቡ ሪፖርተር ላይ የነገሩን እውነት ከሆነ፣ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከደቡብ ክልል እንደራሴነት ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹የተዛወሩት›› በዚህ ዓይነት አሠራር ነው፡፡

የሕዝብ ተሳትፎ ይህን ያህል ተፈላጊና አስፈላጊ በሆነበት ዴሞክራሲዊ ሕይወት ውስጥ የሊቀመንበር ምርጫን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የሚሰየምን ባለሥልጣን የአመዳደብ አሠራር በተገለጸው መልክና ቋንቋ የእኛ የውስጥ ጉዳይ ነው ማለት፣ አያገባችሁም ብሎ መበየን፣ ከዚያም አልፎ የ‹‹ክፍተት›› መሙላት ነገር አድርጎ ማቅለል የሚያቀለው የኢትዮጵያን ዴሞክራሲና የኢትጵያን ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ከአንደበት ወግ በላይ ክብር ይገባዋል፡፡ ይጠይቃልም፡፡

ተከታዩ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ይዘው ይመጣሉ? በከፊል የሚወስነውና ቢያንስ ቢያንስ የሚያሟሸው አመራረጣቸው ላይ ኢሕአዴግ ለሕዝብ የሚያሳየው አክብሮት፣ ግልጽነትና ‹‹ዴሞክራሲያዊነት›› ነው፡፡ ይህ ግልጽነትና ዴሞክራሲዊነት ደግሞ በግንባሩ ውስጥ፣ በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ከምንጊዜው በላይ ጎልቶ የወጣውን ልዩነት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ሲፈታ የሚያሳየን መሆን አለበት፡፡ ችግሩን አድበስብሶም ሆነ ዘልሎ ማለፍ የበዛና የከፋ አደጋ እንዳይደግስ መፍራትና ከወዲሁ መጠንቀቅ የአባት ነው፡፡ የእናት አገርም ጭምር፡፡

ብዙ ሰዎች አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ይዘው ይመጣሉ? ምንስ ይዘው መምጣት አለባቸው? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ በእኔ በኩል ይህን ጥያቄ መመለስ የሚችል ሌላ ጥያቄ አለ የሚል እምነት አለኝ፡፡ የኢሕአዴግን ሊቀመንበር በመምረጥ ሒደት ውስጥ ልዩነትን በውይይት የመፍታት ዴሞክራሲና ጨዋነት ከተለመደ፣ ልዩነቶቻችን በግንባርም ውስጥ ሆነ በእያንዳንዱ ድርጅት ውስጥ አብሮ ለመሥራት አያስችለንም የማለት አባዜ ከተሸነፈ፣ የሠለጠነ የፖለቲካ ጉዳዮች አፈታት ከተለመደ፣ የተሻለ ሐሳብ በክርክር የማንጠር፣ የተሻለ ችሎታን በድምፅ የመለየት እስትንፋስ ከተገኘ፣ የእኔ ሐሳብ አመራሩን ካልያዘ ትግሉ ይሸነፋል ባይነት ጤነኛ አለመሆኑ ግንዛቤ ካገኘ፣ የተለየ ወይም በላንጣ ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ ሳይሆን በሸር መገላገል ነውርና ሕገወጥ መሆኑ የጋራ መግባቢያ ከሆነ፣ አዲሱ ሊቀመንበር የሚመሩት ኢሕአዴግም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚነሱበት ጅምርም ጤነኛ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...