በአበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጄር ጄኔራል)
የሰው ዘር ከሌሎች ፍጡሮች አንፃር ሲታይ አንድ ነው፡፡ ሰው፣ ሰው ነውና፡፡ ነገር ግን በውስጡ ይለያያል፡፡ በዘር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በዕድሜ፣ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በመደብ፣ በአገር፣ ወዘተ ይለያያል፡፡ እነዚህ ልዩነቶች በቁሳዊ ጥቅምና በእሴት (Values) ቅራኔዎች ይንፀባረቃሉ፡፡ ተመሳሳይ ቁሳዊ ጥቅምና እሴቶች አለን የሚሉ እኛ ሲሉ፣ ከዚህ የተለየ ያላቸው እነሱ ይባላሉ፡፡ ከሌሎች አንፃር እኛ ሲሉ የነበሩት በመካከላቸው የቁሳዊ ጥቅምና እሴቶች ልዩነት ስላላቸው ተመልሰው ተከፋፍለው እነሱም እኛና እነሱ ይባላሉ፡፡
ኢትዮጵያ፣ የመን፣ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ጀርመን ወዘተ እንባላለን፡፡ ዜግነት የሰው ልጅን ከፋፍሎታል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ካልን በኋላ እነዚያ ሀብታሞች፣ እነዚያ ክርስቲያኖች ወይም ሙስሊሞች፣ አማሮች፣ ትግራዮች፣ ኦሮሞዎች፣ ወዘተ እንላለን፡፡ ወሎዬ፣ ጎንደሬ፣ ጎጃሜ፣ ወዘተ ተብሎ እኛና እነሱ ይባላል፡፡ በቤተሰብ መካከል እንኳን የቁሳዊ ጥቅምና እሴት ልዩነት ስላለ ወላጆች፣ ልጆች፣ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ወዘተ ተብሎ እኛና እነሱ ይባላሉ፡፡ ወላጆች መሀል ባልና ሚስት ተብሎ ይፈረጃሉ፡፡ በመሳፍንታዊ ኅብረተሰብ ባልየው የቤተሰቡ ሀብት ወሳኝ፣ እሴቱን የሚያረጋግጥ ተብሎ ታሳቢ ይደረጋል፡፡ በባልና ሚስትም ቁሳዊ ቅራኔና የእሴት ልዩነት መንፀባረቃቸው የግድ ነው፡፡
ስለሆነም ‹‹እኛ እና እነሱ›› ባህሪያዊ ነው፡፡ ‹‹እኛ እና እነሱ›› በኅብረተሰብ ውስጥ በዕድገት ጎዳና ሆነው ግን የሚለዋወጥ ነው፡፡ ማርክሲስቶች እንደሚሉት ኅብረተሰብ በከፍተኛ ኮሙዩኒስት ሥርዓት ዕውን እስካልሆነ ድረስ የቁሳዊ ጥቅም ቅራኔና የእሴት ልዩነት መኖሩ አይቀርም፡፡ እኛ ማድረግ የምንችለው ቅራኔዎችና ልዩነቱ ማጥበብ ብቻ ነው፡፡ እነዚህን ቅራኔዎችና ልዩነቶችን ለማስተናገድ ‹‹መንግሥት›› የሚባል ኅብረተሰባዊ አደረጃጀት ፈለግነውም አልፈለግነውም ተፈጠረ፡፡ እንደ የመንግሥቱ ዓይነት ተፈጥሮ እነዚያ ቅራኔዎችና ልዩነቶች በተለያየ መንገድ ኃይልን ጨምሮ ለማስተናገድ ይሞክራል፡፡
ዘመናዊ መንግሥታት የሚተዳደሩበት ሕግ ይኖራቸዋል፣ ሕገ መንግሥት ይባላል፡፡ ይኼን ተከትሎ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ይበጃል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት (Constitutional Order) የአንድ አገር መሠረታዊ ውሳኔዎች የሚሰጡበት በተነፃፃሪ የተረጋጋ ተቋማት ያሉበትና መርሆዎችን የሚያጠቃልል ነው ይላሉ በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን፡፡ ሥርዓቱ የተቋማትና የመርሆዎች ጥምረት መሆኑ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ስንመጣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የተወካዮች ምክር ቤት፣ ፈጻሚው አካል፣ ፍርድ ቤትና ፖለቲካዊ ፓርቲዎች በሥርዓቱ ዋነኛ ተቋማት ሲሆኑ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሁሉም መርሆች ማጠንጠኛ ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥታችን ከመግቢያው ጀምሮ እስከ አንቀጽ 44 ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ማዕከል ያደረጉ መርሆዎች ሲሆኑ፣ ከአንቀጽ 45 ጀምሮ ሥርዓተ መንግሥቱ ፌዴራላዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፓርላሜንታዊ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ በእኔ አመለካከት የሕገ መንግሥቱ መንፈስ መንግሥትና ፖሊሲዎቹ የሕዝቦች መብቶች ለማስከበርና ለመጠበቅ ብቻ ነው የተዋቀሩት፡፡ ከዚያ ውጪ መንግሥት ሌላ ሚና የለውም፡፡ የነበሩትና እያደጉ የሚገኙትን የብሔር፣ የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የመደብ፣ ወዘተ ቁሳዊ ቅራኔዎችና የእሴቶች ልዩነቶች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ የተዋቀረ ሥርዓት ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማክበር ወይም መናድ የሚባሉት ጽንሰ ሐሳቦች በዚህ ማዕቀፍ ነው መታየት አለባቸው፡፡
የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ማክበር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማበልፀግ ሲሆን፣ በተቃራኒው እነዚህን መብቶች መጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መናድ ነው፡፡ ከላይ የተገለጹት ተቋማት ሕገ መንግሥቱ በደነገገው መሠረት ያስቀመጠላቸውን ግዴታዎች ካልፈጸሙ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መናድ ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአንቀጽ 94 መሠረት በንዑስ አንቀፆች አራት፣ አምስት፣ ስድስትና ሰባት ተግባራዊ በማይሆንበት ጊዜ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እየተናደ ነው፡፡ በተለይም በአንቀጽ አራት ማለት የምክር ቤቱ አባላት በመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው፣ ተገዢነታቸውም፡-
ሀ. ለሕገመንግሥቱ
ለ. ለሕዝቡና
ሐ. ለህሊናቸው ብቻ ይሆናል ይላል፡፡
የተወካዮች ምክር ቤት፣ በመንግሥት ሥልጣን ቁንጮ በመሆኑ በሆነ ምክንያት ላይ በተጠቀሱት መሥፈርት የማይወስን ከሆነ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ እየተናደ ነው ማለት ነው፡፡ ፓርቲዎች በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕግ መሠረት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመንቀሳቀስ የሚፈጠርባቸው እንቅፋት ሁሉ፣ ሕገ መንግሥቱ በከፍተኛ ደረጃ እየተናደ ነው ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በኅብረተሰቡ ባሉት ጠንካራ እሴቶች ኋላቀርነት፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥንካሬና ድክመት የሚበለፅግና የሚናድ ቢሆንም፣ ገዥው ፓርቲና መንግሥት ግን ሥርዓቱን በማበልፀግ ወይም በማፍረስ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ወንጀሎች ሁል ጊዜ የማፍረስ ሚና እንዳላቸው ያስተውሏል፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከል የሚኖረው ቁሳዊ ጥቅሞችና እሴቶች ሰብዓዊ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ ሲችል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንደሚጎለብት ሁሉ፣ ከዚህ በተቃራኒ ተቋማቱ ከመርሆዎች በተፃራሪ ሲጓዙ ሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ ይናዳል፣ ለወንጀሎች የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጠርና አገሪቱ ለማያባራ ሁከት ትዳረጋለች፡፡
ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቶች ቀስ በቀስ የሚገነቡ፣ የሚለወጡ (Constructed And Transformed) እንደሆነ በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ተንተርሰው ታዋቂው የሕግ ፕሮፌሰር ብሩስ አክርማን ግን የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቶች ዕድገት በተለያዩ ሕገ መንግሥታዊ አፍታዎች (Constitutional Moments) እና ከዚያ ቀጥሎ የሚያየው መደበኛ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሊተረክ ይችላል ይላሉ፡፡
አገራችን የረዥም ጊዜ የመንግሥት ታሪክ ያላት ቢሆንም፣ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ከ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በመለስ ያለውን ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ በሽግግር መንግሥት ቻርተርና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ይዞታና ሒደት (Process) አከራካሪ ጉዳዮች ቢኖርም፣ እስከ 1990 ዓ.ም. ድረስ የሰላም መረጋጋት ሥራ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡ በኤርትራ መገንጠልና በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው ግንኙነት በተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ቅሬታ ባለበት ነበር የኤርትራ ወረራ የተካሄደው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በኤርትራ መንግሥት ላይ የተጎናፀፉት ድል ሕገ መንሥታዊ ሥርዓቱን ለማጠናከር ከፍተኛ ሞራላዊ እሴት ቢኖረውም፣ በሕወሓት ብሎም በኢሕአዴግ በነበረው ውስጣዊ ቀውስ ምክንያት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ክስተት ተፈጠረ፡፡
የ1993 ሕገ መንግሥታዊ አፍታ
በግንባሩ ብሎም መንግሥት የነበረው የቀውስ አፈታት የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚያረጋግጥ ነበር ወይ የተካሄደው? የሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታዎችን በመተግበር እንዴት ተንቀሳቀሱ? የሚሉት ጥያቄዎች ነው የአፍታ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሚያጎለብት ወይስ በሚንድ ነው ወይ የተካሄደው ብሎ ማየት የሚቻለው፡፡ በአጠቃላይ የቀውስ አፈታት በሕግና በሕግ ነው ወይ የተካሄደው? የፕሬዚዳንቱ ጉዳይ፣ የፀረ ሙስና አዋጅ አወጣጥ፣ የፍርድ ቤት ነፃነት፣ የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነትና የአመኔታ ማጣት (Recall) ሒደት፣ የመንግሥት መገናኛ ቡዙኃን አጠቃቀምና የእህት ድርጅቶች ነፃነትን በመመርመር ጥያቄዎችን መመለስ ይቻላል፡፡ የሕግ የበላይነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው ሒደት እንደነበር እናያለን፡፡ በሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጠባሳ ትቷል፡፡
የ1997 ታሪካዊ ምርጫ እንደ ሕገ መንግሥታዊ አፍታ
ህልም እንኳ የታለ
በህልሜ ተኝቼ
ሸጋ ህልም አይቼ
በአገሬ በአፍሪካ ዴሞክራሲ በቅሎ
ፍትሕ እኩልነት መብት ተደላድሎ
ወገኔ ሲያጣጥም የሰላምን ፍሬ
ሽብር ተወግዶ በመላው አገሬ
ይኼን እያለምኩኝ አልጋ ውስጥ አርፌ
ጥይት ቀሰቀሰኝ ከሞቀው እንቅልፌ
ከፀሐይ በታች በሰሎሞን ሞገስ 2004 ዓ.ም
ምርጫው ታሪክ እየተሠራ ነው እንዴ የሚያሰኝና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሕዝቦች የተመዘገቡበት፣ ከተመዘገቡት እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት የመረጡበት ነበር፡፡ እስከ ምርጫው ቀን ድረስ የተለያዩ እክሎች ቢያጋጥሙም፣ በመሠረቱ ሰላማዊ ተስፋ የሚሰጥና የኅብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ የታየበት ነበር፡፡ የምርጫው ውጤት በጣም አከራካሪ ቢሆንም፣ 12 ተቃዋሚ አባላት የነበረው ፓርላማ 174 መድረሱ እመርታውን ያንፀባርቅ ነበር፡፡ በቅድመ ምርጫ በነበረው የተሻለ ዴሞክራቲክ ምኅዳር በመጀመርያ የነበሩ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ማዕከል ያደረጉ ውይይቶች አይረሱም፡፡ በመጨረሻው መዘበራረቅ መፈጠሩ የሚያስቆጭ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች የሕዝቡን ስሜት መሠረት አድርገው ያደረጉት የአጭር ጊዜ እንቅስቃሴ፣ የመገናኛ ብዙኃን ሚና፣ የቅድመ ምርጫ የምርጫ ቦርድ ተሳትፎ፣ የኢሕአዴግ ‹‹እንከን የለሽ›› ምርጫ ማለት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችን አደገ ተመነደገ ሲባል፣ የኢትዮጵያ ወርቃማ ጊዜ እየታየ ነው ሲባል በመጨረሻ ድብልቅልቁ ወጣ፡፡
ከምርጫው ጥቂት ቀናት በፊት የነበረው ዘርን ማዕከል ያደረጉ ውንጀላዎች በምርጫው ማግሥት ሥርዓት ያጣ እኔ አሸነፍኩ፣ እኔ አሸነፍኩ ፉከራዎች ምክንያት ተቋሞቻችን የባሰ ሽባ ሲሆኑ፣ በተፈጠረው ግርግር በርካታ ሕይወትና ንብረት መጥፋቱ፣ መታሰርና መንገላታት፣ የተቃዋሚዎች መሪዎች ወደ ወህኒ መውረዳቸው ያ የተስፋ ጭላንጭል አፈር ድሜ እንዲበላ አደረጉት፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በፊት የነበረው ፓርላማ ሥራውን ጨርሶ ከመበተኑ በፊትና የተካው ፓርላማ ያወጣቸው አፋኝ ሕጎች ለጊዜው ፋታ የሚሰጡ ቢመስሉም፣ አሁን ላለው ከፍተኛ ቀውስ ግን መሠረት የሆኑ ነበሩ፡፡
በሕዝቦች ላይ በተለይ በወጣቱ ላይ የደረሰው የሥነ አዕምሮ ጠባሳ፣ ፍራቻ፣ ጥርጣሬ እንደገና ‹‹ፖለቲካ እና ኮረንቲ›› እንዲል አድርገውታል፡፡ ኢሕአዴግ ያገኘውን 60 በመቶ፣ የአጋር ድርጅቶች ስምንት በመቶ ተጨምሮበት 68 በመቶ ይዞ በብዙ ቦታዎች ሲሸነፍም ሳያደርግ የሕገ መንግሥቱ አቀንቃኝ በመሆኑ፣ ከቁጥር በላይ ሌላ ከፍተኛ ድል ማድረጉ አስቦ የ32 በመቶ ድምፅ ማጣትን በፀጋ ተቀብሎ ተቃዋሚዎችን አዲስ አበባን እንዲረከቡና በተወካዮች ምክር ቤት ያላቸውን ቦታ እንዲይዙ የተመቻቸ ሁኔታ ቢፈጥር ኖሮ፣ ተቃዋሚዎች በተለይ ቅንጅቶች በዚያን ጊዜ የነበረው የወጣቱ ብልህ መሪ አቶ ልደቱ አያሌው ሐሳብ ተቀብለው ችግሮች ቢኖርበትም የያዝነውን ይዘን እንቀጥል ቢሉ ኖሮ አሁን የት እንደርስ ነበር?
ችግሩ መዋቅራዊ ነው፡፡ በአንድ በኩል ሁለት ሽግግሮች ማለትም ወደ ካፒታሊስት ሥርዓትና ወደ ዴሞክራሲ በአንድ ጊዜ የሚደረግ ሽግግር ከምናውቀው ወደ ሌላ አዲስ እየተጓዝን ስለሆነ ሲሆን፣ በሌላው ወገን ይህን ሽግግር የሚመራው በመስፍናዊ (ፊውዳል) አስተሳሰብ የተገነባ ዴሞክራሲ የተሸከመ አመፀኛው ትውልድ ስለሆነ ነው፡፡ የእኛ ትውልድ ስለዴሞክራሲ ብዙ የሚናገር ግን ዴሞክራሲ ያልገባው ነው፡፡ በተለይ ሥልጣንን የተቆጣጠረው ልሂቅ ጦርነቱን በማሸነፉና ልማቱን በመምራቱ በትዕቢት ተወጥሮ እኔ ያልኩህ ብቻ ተቀበል የሚል ሆነ፡፡ ሕዝቦች ይበቃሀል አልቻልክም ሲሉት ሽንፈት፣ የሁሉ ጊዜ ሽንፈት ስለሚመስለውና በሆነ መንገድ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ስለሚከጅል ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ተንታኝ ኦቢኒክ (2006) የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ችግር የሚመለከት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ባህል ከአምባገነንነት፣ ከልሂቃን ግዛትና ከሞግዚትነት (Patronage) ያልተላቀቀ ነው ይለዋል፡፡ ከ1998 እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ባሉት አሥር ዓመታት ከፍተኛ የልማት ጉዞ ቢመዘገብም፣ እየተጠራቀመ በመጣ ብሶት ምክንያት አሥር ዓመት ሳይሞላው ወደ ከፍተኛ ቀውስ ገብተናል፡፡ ዋናው ምክንያቱም የሕግ የበላይነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት በየጊዜው በከፍተኛ ደረጃ በመናዳቸው ነው፡፡
የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሕልፈት ተከትሎ በኢትዮጵያ ውስጥ የሥልጣን ክፍተት ወይም ሽኩቻ ይኖር ይሆን እንዴ የሚል ጥያቄ በታዛቢዎች ቢነሳም፣ ከተወሰነ መወላወል በኋላ በገዥው ግንባር ሕገ መንግሥቱን በተከተለው መንገድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን ክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ሥልጣኑን በመረከባቸው ለብዙዎች ዕፎይታ ፈጥረዋል፡፡ ከዚህ በላይ የኢትዮጵያ የሥልጣን ቁንጮ ታሪክ ከአማራ ወይም ከትግራይ ብሔሮችና ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማኝ ውጪ መሆናቸው አዲስ ታሪክ እየተሠራ መሆኑን የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚያጠናክር ክስተት ሆኖ ተመዝግቦ ነበር፡፡ በትጥቅ ትግል ያልተሳተፉና የተማሩ መሆናቸው በአንዳንድ ሰዎች ተስፋ የጫረ ቢሆንም፣ ለሌሎች ደግሞ በገዢው ፓርቲ በነበራቸው ቦታና እጅግም የማይታወቁ በመሆናቸው፣ እንዲሁም የአቶ መለስ አመራር ውርስ (Legacy) የሚያንዣብብባቸው እንደመሆኑ በእውነት ይመሩናል ወይ የሚል ጥርጣሬ የነበራቸው ነበሩ፡፡ የመንግሥት ማዕከል የት እንዳለ የማይታወቅበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምባገነን ናቸው ሳይባሉ፣ ነገር ግን ሥራ አሥፈፃሚው አምባገነን የተባለበት እንቆቅልሽ ባለበት ሁኔታ የሥራ መልቀቂያ አቀረቡ፡፡
1987 እስከ 2007 ዓ.ም. የነበረው 20 ዓመታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረት የጀመረበት ከፍተኛ ልማት የተመዘገበበት፣ ሰላም የሰፈነበትና ብዙ ተሞክሮዎች የተቀመረበት ቢሆንም፣ ከዴሞክራሲና ከተቋማት አንፃር አጠቃላይ ጉዞ የኃልዮሽ ይመስላል፡፡ በ1987 ዓ.ም. አካባቢ ሕዝቦች በመሰላቸው መንገድ ተቃውሟቸውን የሚገልጹበት ሰላማዊ ሠልፍ በየቀኑ የሚታይ የኑሮዋችን አንደኛው ገጽታ በሚመስል ሁኔታ ሲገለጽ ነበር፡፡ ፕሬስ እንደ አሸን የፈላበት፣ ተነፃፃሪ ነፃነት የነበረበት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአዲስ መንፈስ መንቀሳቀስ የጀመሩበት፣ በሕግ አውጪውም በተወሰነ ደረጃ የተለየ አማራጭ ሐሳቦች የሚንፀባረቅበት ሁኔታ ነበር፡፡
ይኼ ጉዞ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት በከፍተኛ ደረጃና ተስፋ ሰጪ ሆኖ ቢከሰትም፣ ከምርጫው ማግሥት ጀምሮ ከፍተኛ ማሽቆልቆል የጀመረበት ሁኔታ ዓይተናል፡፡ ከ1997 እስከ 2007 ዓ.ም. ሕዝቦች ተቋውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ ነውር እንደሆነ በሚያስመስል ሁኔታ የቀጨጨበት ሁኔታ፣ የኢሕአዴግ አባልና አባል ያልሆነ የሚባሉ ሁለት ዓይነት ዜጎች የተፈጠሩበት፣ ሕዝቦች በፍትሕ ማጣት ምክንያት በእሳት የሚለበለቡት፣ ሙስና በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋበት፣ ፕሬሱ የተሽመደመደበት፣ ተቃዋሚዎች በሥርዓቱ ጫናና በራሳቸው ድክመት ምክንያት ልፍስፍስ የሆኑበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ብሔር ተኮር ጥቃቶች በሚገባ ያልተዳኙበት፣ በአጠቃላይ የሕግ የበላይነት ግልጽነትና ተጠያቂነት እየጠፋ በመሄዱ በ2008 ዓ.ም. የሕዝቦች ቁጣ ፈነዳ፣ ወንጀለኞችም ተጠቀሙበት፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ለከፍተኛ አደጋ ተጋለጠ፡፡
2007-2010 ምስቅልቅል እንደ ሕገ መንግሥታዊ አፍታ
የ2007 ዓ.ም. ምርጫ በኢሕአዴግና በአጋር ድርጅቶች 100 በመቶ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ገዢው ግንባር በድል ሰክሮ የአደጋ ደውል ማንቂያ መሆኑን በተወሰነ ደረጃ ማየት ሳይችል ቀርቶ፣ ስድስት ወራት ባልሞላ ጊዜ የሕዝቦች አመፅ ተነሳ፡፡ ተሃድሶ ብሎ በዋናነት በመልካም አስተዳደርና በልማት ተጠቃሚነት ዙርያ ችግሩን እፈታዋለሁ ቢልም አልቻለም፡፡ ወላፈኑ መቀዝቀዝ ባለመቻሉ እንደገና ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ቢልም፣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴው ሊቀለበስ ባለመቻሉና ወንጀለኞችም ሁኔታውን ስለተጠቀሙበት በ2009 ዓ.ም. በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጣለ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ የቀዘቀዘ ቢመስልም እንደ ገና በማገርሸቱ ወንጀለኞች ከሕዝቦች እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ተሠልፈው ብሔር ተኮር ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ በመታየቱ ከፍተኛ የንብረት ውድመት የደረሰ በመሆኑ፣ በየካቲት 2010 ዓ.ም. እንደገና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደነገገ፡፡ መንግሥት የሕዝቦችን ፍትሐዊ ጥያቄዎች የማይመልስ ከሆነና ፅንፈኞችም የሕዝቦች ጥያቄዎችን ለራሳቸው አጀንዳ በሚመች መንገድ የሚቀለብሱት ከሆነ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየዓመቱ የሚደጋገም ከሆነና አዋጁ በመላው አገሪቱ የሚታወጅ ከሆነ፣ እንደ ኢትዮጵያ ዓመታዊ ክብረ በዓል የምናስተናግደውና የሚበታትነን እንዳይሆን ብርቱ ሥጋት አለኝ፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ትግል በፈጠረው ከፍተኛ ጫና የገዥው ግንባር አባል የሆነው ኦሕዴድ በ2009 ዓ.ም. አዲስ አመራር መድረኩን ተቆጣጠረ፡፡ ፌዴራል ሥርዓቱንና ኢትዮጵያዊነትን ያነገበው ‹‹Team Lemma›› ተብሎ የሚጠራው የጎልማሶች አመራር የነበረውን ኢዴሞክራሲያዊና ኋላ ቀር አመራር በመቀየር፣ የተለየ አዲስ አስተሳስብ የያዘ ከኦሮሞና ከሌሎች ብሔሮች ሊሂቃን በተነፃፃሪ የተሻለ ተቀባይነት ያለው አመራር ብቅ አለ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁለት ዓመት እንኳን ያልሞላው አመራር እየተፈጸሙ የነበሩት ወንጀለኞች መቆጣጠር አለመቻሉና በተሞክሮ ማነስ ምክንያት አጣብቂኝ የገባ ይመስላል፡፡ ሕወሓት ከረዥም ማቅማማት በኋላ የዴሞክራሲ መሠረታዊ ችግርን ማዕከል አድርጌያለሁ ብሎ የአመራር ለውጥ በማድረግ ብቅ ብሏል፡፡ ተስፋ የጣልንበት ጎልማሳ አመራር ግን ተደብቋል፡፡ ኢሕአዴግ ሕወሓት ያደረገውን ግምገማ መሠረት አድርጎ ራሱን የፈተሸ ይመስላል፡፡ ሆኖም ብአዴን ትርጉም ያለው የአመራር ለውጥ ሳያደርግ ጉዞውን ሲቀላቀል፣ ደኢሕዴን ሊቀመንበሩ ሲቀይር የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር የሥራ መልቀቂያ በማቅረባቸው በተወሰነ ደረጃ ሌላ ቀውስ የፈጠረ ይመስላል፡፡
አገራችን የዴሞክራሲ ሰብዕና በተላበሱ፣ በጥናትና ምርምር የሚመሩ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቁ፣ እውቀትና ጉልበቱም ባላቸው ጎልማሳ አመራሮች ልትመራ ነው እንዴ የሚል ተስፋ እየሰነቅን እንገኛለን፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ የተሟላ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ያለ አይመስልም፡፡ ይኼ አመራር አገራችን እየተቃጠለች ባለችበት ሁኔታ በስብሰባ መዘፈቁ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ በሌለበት መቋጫ የሌለው ግምገማና ሒስና ግለ ሒስ የኢዴሞክራሲ ኃይሎች ወጥመድ ውስጥ መጫወት ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ ወጥመድ ለመውጣት የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ተቋሞቻችን እንዴት አሁን ካለው ልፍስፍነትና ፀረ ሕዝብነት ተላቀው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ይታደጉት የሚለውን አጀንዳ ይዘው በአስቸኳይ ወደ ሕዝቦች መድረክ ይቅረቡ፡፡ እየታየ ያለው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ይጎልብት፡፡
የተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሲወስን የነበረው የድምፅ አሰጣጥ ሒደት ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ አዋጁ እንዳይፀድቅ ድምፅ የሰጡት ዴሞክራሲያዊ ጥርነፋ የሚሉትን የተግባር ግብ አምባገነናዊ ጥርነፋ ጥሰው ነው፡፡ ውሳኔው ትክክል ስለመሆኑ አከራካሪ ቢሆንም፣ ለህሊናቸው ድምፅ መስጠታቸው ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ገዥው ግንባር እነዚህ የምክር ቤት አባላት ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከድርጅቱም ከምክር ቤቱም ካባረረ የ1993፣ 1997 ዓ.ም. ወዘተ ጠባሳዎች ስለሚደገሙ አንድምታው አደገኛ ነው፡፡
ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሁን በሚል በወጣቱ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ መመዘኛዎችን በማስቀመጥ ክርክር እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ገዥ ግንባር በመሆኑ በሕዝቦቻችን ሕይወት ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ አባል ያልሆኑ ሰዎች ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ሲሞክሩ የሚደገፍ እንጂ፣ ምን አገባችሁ መባል የለበትም፡፡ በተለይ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል የሚል የተለምዶ እምነት ስላለ፣ ወጣቶች ይህ ነገር በአራት ኪሎ የሚደረግ ሴራ (Conspiracy) ብቻ መሆን የለበትም በማለት ያለው ተሳትፎ መበረታታት አለበት፡፡
ዶ/ር ዓብይ የኦሕዴድ ሊቀመንበር ከሆኑ በኋላ ራሳቸውን ዕጩ አድርገዋል፣ ‹ሎቢ› እያደረጉ ነው፣ የይምረጡኝ ዘመቻ ጀምረዋል፣ ኧረ ካቢኔ እያቋቋሙ ነው የሚል ወሬ ሲሰማ እውነት ይሁን አይሁን ብዙ ክርክር አስነስቷል፡፡ በአንድ በኩል ከኢሕአዴግ አሠራር ውጪ ነው፣ ‹ሎቢ› ማድረግ ለድርጅቱም ለሕዝቡም ውርደት ነው፣ ራስህን ዕጩ ማድረግ አሳፋሪ ነው የሚሉ አስተያየቶች አሉ፡፡ በእኔ እምነት እየተባለ ያለው እውነት ከሆነ የዴሞክራሲም የሥልጣኔም በር ከፋች ነው፡፡ የኢሕአዴግ አመራረጥ ዛሬ የባህታዊ አይሉት የመሳፍንቶች እየሆነ ነው፡፡ በትጥቅ ትግል ወቅት የነበረው አመራረጥ ሌላ አማራጭ የሌለው ቢሆንም፣ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ እሱን እንዳለ መከተል ኢዴሞክራሲያዊ ይመስለኛል፡፡ በአንዱ መጣጥፌ እንደገለጽኩት ሁኔታው የሚፈጥረው የለውጥ አጀንዳን መሠረት ያላደረገ የመሪዎች መረጣ መጨረሻው በተወሰኑ መሪዎች ቡራኬ ይሁንታ የሚቆም ነው የሚሆነው፡፡ ምርጫው ዋናው የለውጥ አጀንዳ መሆኑ ቀርቶ ሥነ ምግባርንና የትግል ዕድሜን ብቻ ማዕከል እንዲሆን ያደርጋል፡፡ በተለይ ወጣቱ ምሁር ወደ አመራር እንዳይወጣ የሚያጠብ ነው የሚሆነው፡፡ የትግል ዲሲፕሊንና ዕድሜ ብቻ ግምት ውስጥ ያስገባ ለዘመኑ የማይመጥነውና አሁን ላለው ስትራቴጂካዊ አመራር ድክመት ያመጣው አካሄድ ስለሆነ፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕገ መንግሥቱን መንፈስ ተከትሎ ሲደነገግ፣ የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ለመተግበር እያጋጠሙ ያሉትን ጋሬጣዎች ለማስወገድ ለአጭር ጊዜ የሕዝቦችን የተወሰኑ መብቶች ይከለክላል፡፡ ለምሳሌ ሰላማዊ ሠልፍ ሕዝቡ የሚከለከለው በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ ነው፡፡ የሥርዓቱ ተቋማት የሕዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለመጠበቅ የተቋቋሙ ናቸው ከሚል እሳቤ ነው ከወንጀሎች የሚጠበቁት፡፡ የ27 ዓመታት ጉዞአችንን ስንገመግመው አሁን ለደረስንበት ቀውስ ዋና ምክንያቱ የሕግ የበላይነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለመኖሩ የተከሰተ ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስላልተከበሩ ነው፡፡ ተቋሞቻችን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን በሚገባ ስላልሠሩ ነው፡፡ መፍትሔውም ሕገ መንግሥታችንን በተሟላ ሁኔታ ማክበር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማጠናከር ነው፡፡ ለዚህም ነው ከአዲሱ ጎልማሳ አመራር ዴሞክራሲን ማዕከል ያደረገ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳና እንቅስቃሴ የምንጠብቀው፡፡
ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ
በሕወሓት ከ43 ዓመት፣ በብአዴን ከ37 ዓመት፣ በኦሕዴድ ከ30 ዓመት በፊት አመራርና መሥራች የነበሩ ሰዎች ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ አገር እየታመሰች ስለሆነች ተሞክሯቸውን ቢያካፉሉን ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እናንተ ሕጋዊ ሥልጣን ያላችሁ ጎልማሶች አልቻላችሁምና እንምራችሁ በሚል ትዕቢት በሚመስል እየተንቀሳቀሱ ይመስላል፡፡ እነሱ በኢሕአዴግ በማዕከላዊ ኮሚቴ ወይም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ካልተገኙ ድርጅቱ ዋጋ የለውም እያሉን ነው እንዴ? በትጥቅ ትግልና ከዚያም በኋላ በ25 ዓመቱ የሰላምና የልማት ዓመታት ከፍተኛ ሚና የነበረቸው በመሆኑ ተሞክሮዋቸውን መቀመር አስፈላጊ ቢሆንም፣ ላለው ፀረ ዴሞክራሲያዊ ጉዞና ቀውስ መፈጠር ዋና ተጠያቂዎች እያሉ አዲስ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ እንመራለን፣ ያለ እኛ አይሆንም ማለት የሕዝቦችን ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ የሚያጨናግፍ አዲስ ክስተት እየታየ ይመስለኛል፡፡ በሁሉም ድርጅቶች ያሉ ሽማግሌዎች የሕዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዴት እናስጠብቅ፣ ተቋሞቻችን እንዴት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ያጎልብቱት ከማለት ይልቅ የራሳቸውን ተፅዕኖ በማሳደግ አንጋሽ (Kingmaker) ለመሆን የሚሹ ይመስላሉ፡፡ ይኼ ዓይነት የጥላ (Shadow) አመራር ለአገራችን ውርደት ነው!! ሕዝባዊ እንቀስቃሴውን ለመቀልበስ የሚደረግ ወጥመድና ሴራ ሊሆን ይችላል፡፡ እነሱ በተካኑት ግምገማና ሒስና ግለ ሒስ አዲሱን አመራር በማበሳጨት ተስፋ እንዲቆርጥ ወደ ሕዝቡ እንዳይደርስ እያደረጉት እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በሁሉም ድርጅቶች ያሉ የለውጥ አመራሮች ከእነዚህ ሞግዚትነት ራሳቸውን ነፃ ያውጡ!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ የኢሕአዴግ ታጋይና የአየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡