Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የብሔር ጥያቄ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ገዥ አስተሳሰብ ሆኖ መቀጠል የለበትም››

አቶ ልደቱ አያሌው፣ የቀድሞው የኢዴፓ መሥራችና አመራር

አቶ ልደቱ አያሌው ባለፉት 26 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎአቸው ይታወቃሉ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲ ከማቋቋም ጀምሮ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አገሪቱ ስላለችበት ወቅታዊ ሁኔታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከዘመኑ ተናኘ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- እንደሚታወቀው ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ቀውስ ተከስቷል፡፡ በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ለዓመታት ያፈሩት ንብረት ወደ አመድነት ተለውጧል፡፡ በአገሪቱ አሁንም አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት አይታይም፡፡ ይህ በአጠቃላይ የሚያመለክተው ምንድነው? አገሪቱ ምን ሁኔታ ላይ ነው ያለችው ማለት ይቻላል?

አቶ ልደቱ፡- በእኔ ዕይታ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ቀውስ ወይም ደግሞ የህልውና አደጋ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ይህን በሁለት መንገድ መግለጽ ይቻላል፡፡ በአንድ በኩል አገሪቱ ለብዙ ዓመታት ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የሚባሉ የፖለቲካ ቅራኔዎች ነበሩ፡፡ እነዚህን የፖለቲካ ቅራኔዎች የያዝንበት መንገድ ወይም ለመፍታት የሞከርንበት መንገድ ጤናማ አልነበረም፡፡ በመቻቻል፣ በመደማመጥና በመደራደር ሳይሆን ፅንፍ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት ይዘን፣ ባልተለወጠ የፖለቲካ ባህል ነበር ችግሮችን ለመፍታት የሞከርነው፡፡ በዚህ ምክንያት ችግሮቹ ከመፈታትና ከመቃለል ይልቅ በሒደት እየተንከባለሉ፣ እየተጠናከሩ፣ እየሰፉና የበለጠ እየተወሳሰቡ መጥተዋል፡፡ አሁን የአገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ ነው ያለው፡፡ በአንዳንድ ክልሎች ወይም ደግሞ አነስተኛ ከተሞች እንደምናየው በአንድ በኩል ሕግና ሥርዓት የለሽ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ መንግሥት የለሽ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች መንግሥትም አለ ማለት አይቻልም፡፡ መንግሥት የለሽ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በሙሉ አቅም አይሁን እንጂ፣ የእርስ በርስ ግጭት የሚመስሉ ሁኔታዎች እየታዩ ነው፡፡ በተለይ ብሔር ተኮር የሆኑ ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፉ መጥተዋል፡፡ ቀደም ሲል በተቃዋሚዎችና በመንግሥት መካከል የነበረው ግጭት አሁን ደግሞ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ሆኗል፡፡ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ሕዝቡ ብሔር ተኮር የሆኑ ግጭቶች ውስጥ ገብቷል፡፡ አገሪቱ በአንድ በኩል ሕግና ሥርዓት የለሽ ሁኔታ ውስጥ ገብታለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ገብታለች፡፡ ይህ የሚያሳየው አገሪቱ የህልውና አደጋ ውስጥ መሆኗን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ችግር ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ?

አቶ ልደቱ፡- ሁላችንም መመለስ ያለብን ይህንን መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ  ለዚህ ያበቃን ችግር ምንድነው? በሚለው ጉዳይ በተወሰነ ደረጃ እንኳን መስማማት ካልቻልን መፍትሔውን ማምጣት እንችላለን ብዬ አላምንም፡፡ ይህ መሠረታዊና ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡ ምንጩ ምንድነው?  በሚለው ላይ በእኔ እምነት እስካሁን ድረስ መግባባት ላይ አልደረስንም፡፡ አይደለም ሕዝቡ የፖለቲካ ኃይሎችም መግባባት አልቻሉም፡፡ ኢሕአዴግም የችግሩን ምንጭ በተሟላ ሁኔታ እየዳሰሰው አይደለም፡፡ ተቃዋሚዎችም የችግሩን ምንጭ በተሟላ ሁኔታ እየዳሰስነው አይደለም፡፡ የችግሩን ምንጭ በደንብ አድርገን ዳስሰን በእሱ ላይ መግባባት ሳንፈጥር ነው ስለመፍትሔው እየተነጋገርን ያለነው፡፡ ሊያግባባን የሚችል ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር መፍትሔውም ላይ ውጤት ያለው ነገር ሊመጣ አይችልም፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ይህ ነው፡፡ በእኔ እምነት አንዱ ምንጭ በአንድ በኩል በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ጥፋቶች የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ጊዜ ሰዎች የማያዩት ሌላው ችግር ተቃዋሚዎችና የአገሪቱ ባለቤት የሆነው ሕዝብ መሥራት የሚገባንን ባለመሥራታችን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ባጠፋቸው ጥፋቶች (በድርጊት ማለት ነው) እና በፈጸማቸው ስህተቶች በአንድ ወገን፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ስህተቶች ተቋቁመንና ታግለን መለወጥ ባለመቻላችን (ተቃዋሚ ፓርቲዎች) የመጣ ችግር ነው፡፡ ኢሕአዴግ በችግር ምንጭነት የሚጠቅሳቸው የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሙስና ችግር፣ የኪራይ ሰብሳቢዎች ችግር፣ የፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት፣ የአመራር ድክመት፣ የፖለቲካ ምኅዳር ያለመስፋት ችግሮችና ሌሎች በትክክል የችግሩ ምንጭ ናቸው፡፡ ግን ብቸኛ ምንጮች አይደሉም፡፡ ለእኔ እነዚህ ችግሮች በአብዛኛው ከመልካም አስተዳደርና ከአፈጻጸም ጉዳይ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ለእነዚህም ችግር መፈጠር ምንጭ የሆነው የፖለቲካ ችግር ነው፡፡ አንዱ ደግሞ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለአስተሳሰብ ብዝኃነትና ለመቻቻል ፖለቲካ ቦታ አይሰጥም፡፡ የእኔ ብቻ አስተሳሰብ ትክክል ነው የሚል ነው፡፡ ይህን አስተሳሰብ ወደ ሕዝብ አስርጾ የበላይ የማድረግ፣ ሁለተኛው ችግር ደግሞ ከሕግ መንግሥቱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አሁን ያለውን ሕገ መንግሥት ገዥው ፓርቲ በአሸናፊነት መንፈስና ሌላ ጊዜ ደግሞ እሱ በማይችልበት መንገድ የቀረፀው ነው፡፡ በዋናነት ለኢትዮጵያ አንድነት ዋስትና ነስቶ ለብሔር ጥያቄ የበላይነት መልስ ይዞ የቀረበ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ብሔር ተኮር ፖለቲካ ከሚገባው በላይ ተለጥጦ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ቦታ ማግኘቱ ነው፡፡

ሦስተኛው ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ አገሪቱ የተደራጀችበት የፌዴራል አከላለል ነው፡፡ ፌዴራል አከላለላችን በዋናነት ቋንቋንና የብሔረሰብ ማንነትን መሠረት ማድረጉ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፓርቲዎች አደረጃጀት ብሔር ተኮር መሆኑ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች ጋር ተያይዞ ደግሞ አገሪቱ ውስጥ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሲራመድ የነበረው ፕሮፓጋንዳ አሉታዊ የታሪክ ገጽታችንና ልዩነታችን ላይ ያተኮረ ስለነበረ ነው፡፡ በእኔ እምነት አሁን የተፈጠረው ችግር ኢትዮጵያዊያን ዕድለ ቢሶች ሆነን በድንገት የተፈጠረ አይደለም፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው የሕግና የአደረጃጀት ችግሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ እነዚህን ሕጎች ይዘን፣ እንደዚህ ዓይነት አደረጃጀት ይዘን፣ እዚህ ችግር ውስጥ መግባታችን ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የዘራነውን ነው ያበቀልነው፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ ችግሮቹ እነዚህ ናቸው፡፡ እነዚህ ግን ሲነሱ አናይም፡፡ በአብዛኛው ሲነሱ የምናየው ከኢኮኖሚ ጋርና ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ቁንፅል ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህን ብቻ የችግሩ ምንጭ አድርጎ በማየት መፍትሔ ማግኘት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሰፋ አድርጎ ፖለቲካዊ ይዘቱን ማየት ያስፈልጋል፡፡

ከፌዴራል አደረጃጀቱ፣ ከፓርቲ አደረጃጀቱ፣ ከሕገ መንግሥቱ፣ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመርና ከአጠቃላይ የፕሮፓጋንዳ ቅኝታችን ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር ነው ሄዶ ሄዶ እዚህ ያደረሰን፡፡ ይህ አጠቃላይ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ጉዳይ በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆነ በገዥው ፓርቲ ሲዳሰስ አላይም፡፡     

ሪፖርተር፡- ብሔር ተኮር የፖለቲካ ሥርዓት መዘርጋት አንዱ የችግሮች ምንጭ ነው ብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የሕዝብ አኗኗርና ባህል፣ እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዮች አኳያ ሲታይ እዚህ ላይ በትክክል ያለው ችግር ምንድነው?

አቶ ልደቱ፡- ይህ የብሔር ተኮር ፖለቲካ 1960ዎቹ ላይ የዋለልኝን ወረቀት ወይም አስተሳሰብ ተከትሎ በጎላ ሁኔታ የመጣ አስተሳሰብ ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ደርግን አሸንፎ ሥልጣን ሲይዝ፣ የብሔር ፖለቲካ አሸናፊ ሆነ፡፡ ያኔ የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች ሥልጣን ላይ ሲወጡ ብሔር ተኮር ፖለቲካ ዋና አጀንዳ መሆኑ ብዙ አይደንቅም፡፡ አሁን ይህ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ 27 ዓመታት ሆኖታል፡፡ 27 ዓመታት ማለት ከአንድ ትውልድ በላይ ነው፡፡ አሁንም እነዚያው ሕጎች፣ አሁንም ያው አስተሳሰብ፣ አሁንም ያው አደረጃጀት ሳይለወጥና ሳይጨመር፣ ሳይቀነስ ነው የቀጠለው፡፡ ይህ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ የብሔር ጭቆናው ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለነበርም ነው ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔር ማንነታቸው ተደራጅተው የፖለቲካና የትጥቅ ትግል ያካሄዱት ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ በዚያ ደረጃ የትጥቅ ትግል የተካሄደበት አጀንዳ ትኩረት ማግኘት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚያ ዙሪያ ለሚነሱ ችግሮችና ጥያቄዎችም መፍትሔ መስጠት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ችግሮች ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ማግኘታቸው፣ ዜጎች በቋንቋቸው እንዲናገሩ፣ በቋንቋቸው እንዲዳኙ፣ በቋንቋቸው እንዲማሩ፣ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ፣ አካባቢያቸውን ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ዕድል ማግኘታቸው የነበረ ጥያቄ ነው፣ ተገቢም መልስ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን ይህ ጉዳይ ገዥ አስተሳሰብ ሆኖ መቀጠል አለበት ብዬ አላምንም፡፡ የኅብረተሰብ አስተሳሰብ ይቀየራል፡፡ ትውልድ በተቀየረ ቁጥር ፍላጎት ይቀየራል፡፡ ጥቅም ይቀየራል፡፡ ጥያቄም ይቀየራል፡፡   

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የሕዝብን ጥያቄ ከመፍታት አኳያ የብሔር ፖለቲካ የራሱ ፋይዳ ቢኖረውም፣ አሁን ግን ከጊዜው ጋር መለወጥ አለበት ነው የሚሉት?

አቶ ልደቱ፡- አዎ፡፡ የዋለልኝ የአስተሳሰብ ዘመን ከዚህ በኋላ ማክተም አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት ነው መቀየር ያለበት?

አቶ ልደቱ፡- የብሔር ችግሮች የምንላቸው ወይም ደግሞ አሁን ኢሕአዴግ ራሱ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ተፈተዋል የምንላቸው ተጠብቀው መቀጠል አለባቸው፡፡ ወደፊትም ዜጎች ቋንቋቸውን፣ ብሔረሰባዊ ማንነታቸውን፣ ባህላቸውን ማስፋፋትና ማሳደግ የሚችሉበት ዕድል ክፍት ሆኖ መቀጠል አለበት፡፡ ይህ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ገዥ አስተሳሰብ ሆኖ መቀጠል አለበት ብዬ አላምንም፡፡ ከዚያ በላይ ጥያቄዎች አሉ፡፡ አሁን ከድኅነት መውጣት ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ጥያቄ ሆኖ ነው የቀጠለው፡፡ የዴሞክራሲ ጥያቄ ከድሮ ጀምሮ የቀጠለ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ጥያቄ ሆኖ ነው የቀጠለው፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ቦታ ማግኘት አለባቸው፡፡ የብሔር ጥያቄ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ገዥ አስተሳሰብ ሆኖ መቀጠሉ መቆም አለበት፡፡ አንድ ጥያቄ ሆኖ ነው መቀጠል ያለበት፡፡ ስለዚህ በእኔ እምነት ከዚህ በኋላ የዋለልኝ አጀንዳ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ቁልፍ የብሔር ጥያቄ ነው የሚለው ማክተም አለበት፡፡ የአገሪቱ ፌዴራላዊ አደረጃጀትም፣ የፓርቲዎች አደረጃጀትም፣ በሥራ ላይ ያሉ ሕጎቻችንም ከወቅቱ የሕዝብ ጥያቄና ሁኔታ ጋር እንደገና መቃኘትና መጣጣም አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴራል አደረጃጀቱ በራሱ ችግር አለበት እያሉኝ ነውና ምን ዓይነት ችግር ነው? በዚህ ሳቢያስ ምን ጉዳት ደርሷል? እንዴት ነው መስተካከል ያለበት ይላሉ?

አቶ ልደቱ፡- ከሕገ መንግሥቱ ጋር በተያያዘ አገሪቱ በዋናነት የተከለለችው ቋንቋን ወይም ብሔረሰባዊ ማንነትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ አገሪቱ ብቻ አይደለችም በአገሪቱ ለሥልጣን የሚፎካከሩ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎችም የተደራጁት ቋንቋን ወይም ብሔረሰባዊ ማንነትን መሠረት አድርገው ነው፡፡ ይህ ከመጀመርያውም ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ አሁንም መቀጠል አለበት ብዬ አላምንም፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ውስጥ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ መምጣት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን ለመሰለ አገር አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የብዙኃን አገር ነች፡፡ ይህ ጥያቄ የለውም፡፡ ይህን አስተሳሰብ የማይቀበል የፖለቲካ ፓርቲ ብዙ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ዋናው ጥያቄ ይህን ስንቀበል ፌዴራሊዝሙ እንዲያፈርሰን አይደለም፡፡ አሁን ባለው የፌዴራል አደረጃጀት ልዩነታችን በሒደት እየሰፋ ነው፡፡ የአገሪቱን አንድነት እያናጋ እንጂ የሕዝቡን አንድነት እያጠናከረ አልመጣም፡፡    

ሪፖርተር፡- ይህ ችግር ነው ካሉ መፍትሔው ምንድነው?

አቶ ልደቱ፡- በእኔ እምነት ፌዴራሊዝሙ መቀጠል አለበት፡፡ አከላለሉ ላይ ግን መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በፌዴራል አደረጃጀት ግምት ውስጥ መግባት ያለበት የብሔር ጥያቄ ስለሆነ፣ ቢያንስ በቀበሌ ደረጃና በወረዳ ደረጃ ያሉን አከላለሎች አሁንም ቋንቋንና የብሔረሰባዊ ማንነት መሠረት ባደረገ መቀጠል አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ችግር የለውም፡፡ ምክንያቱም ሰዎች የሚማሩት ወረዳና ቀበሌ ላይ ነው፡፡ የሚዳኙት አብዛኛውን ጊዜ ወረዳና ቀበሌ ላይ ነው፡፡ አስተዳደር ያለው በቅርብ ነው፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰቡ በቅርበት በሚኖርበት የሚገኘው አስተዳደራዊ ሁኔታ በቋንቋው እንዲዳኝ፣ ባህሉ እንዲጠበቅና እንዲያድግ የቀበሌና የወረዳ መስተዳድሮች አሁንም ቋንቋና ብሔረሰባዊ ማንነትን መሠረት አድርገው መቀጠል ይችላሉ፡፡ ችግር የለውም፡፡ ቢያንስ ግን በዞን ደረጃና በክልል ደረጃ ያለው አደራጃጀት ግን እንደገና መከለስ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ቋንቋና ብሔረሰባዊ ማንነት ላይ ብቻ ሳይሆን አስተዳደራዊ፣ አኮኖሚያዊና የሕዝቡን አብሮ የመኖር ታሪካዊ ትስስር ግምት ውስጥ በማስገባት እንደገና መቃኘት አለበት፡፡     

ሪፖርተር፡- አገሪቱ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖርያ ነች፡፡ የተለያዩ ሃይማኖቶች ያሉባትና ብዙ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ነች፡፡ ከዚህ አኳያ ይህ ተጨባጭ መሆን ይችላል?

አቶ ልደቱ፡- ይችላል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ደቡብ ክልል ነው፡፡ ደቡብ ብንሄድ 56 የሚሆኑ ብሔረሰቦች በአንድ ክልል ውስጥ ታቅፈው ነው ያሉት፡፡ አማራ ክልል ውስጥ አገዎች አሉ፡፡ ልዩ ዞን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ኦሮሞዎች አሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው አብሮ ለመኖር አይከለክልም፡፡ ግን ደግሞ ኢፍትሐዊ የሆኑ ነገሮች ይታያሉ፡፡ የሐረሪ ክልልንና የኦሮሚያ ክልልን በቆዳ ስፋትም ሆነ በሕዝብ ብዛት ብናወዳድር ፌዴራሊዝሙ ምክንያት የለሽ መሆኑን ያሳያል፡፡ የበሬ ግንባር የምታህል አንድ አካባቢን አንድ ክልል አድርጓል፡፡ የአገሪቱ ግማሽ የሚሆነውን የኦሮሚያ ክልል አንድ ክልል አድርጓል፡፡ ትክክል አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያሰማ ይደመጣል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ኃይል የተቀላቀለበት ዕርምጃ ሲወስድ ይታያል፡፡ የፍትሕ ተቋማት ገለልተኛ አይደሉም ይባላሉ፡፡ የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ጠባብ ነው ይባላል፡፡ የምርጫ ቦርድ የገለልተኛነት ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይህ የሕዝብ እንቅስቃሴ የሚያመለክተው ምንድነው?

አቶ ልደቱ፡- እዚህ ላይ ሁለት ነገር ማየት አለብን፡፡ በአንድ በኩል ሕዝቡ ትግል እያካሄደ ነው፡፡ ትግል እንዲያካሂድ ያስገደደው በቂ ምክንያት አለው፡፡ ይህን መጠራጠር አይቻልም፡፡ እዚህ አገር ብዙ ብሶቶች አሉ፡፡ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ብዙ ግፎች አሉ፡፡ ሕዝቡ በዚህ ደረጃ አደባባይ ወጥቶ ቢታገል ይገባዋል፡፡ ተገቢ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን እየተካሄደ ያለው ትግል የራሱ የሆኑ ችግሮች አሉበት፡፡ በሥልት ደረጃ ሰላማዊ ትግል ነው መካሄድ ያለበት፡፡ ሰላማዊ ትግል መካሄድ ያለበት ምቹ ሁኔታ ባለበት ወቅት ብቻ አይደለም፡፡ ምቹ ሁኔታ በሌለበትም፣ አምባገነናዊ ሥርዓት ባለበት ወቅትም የሚካሄደው ትግል ሰላማዊና ሕጋዊ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን እንደዚህ ብለን ስለምናምን ሕዝቡ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ያካሂዳል ማለት አይደለም፡፡ ባለፉት ምርጫዎች ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ አይመጣም በሚል ተስፋ ቆርጧል፡፡ ተስፋ ለመቁረጥ የሚያስችሉ ምክንያቶችም አሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ በተካሄዱ ምርጫዎች መቶ በመቶ አሸንፌአለሁ ብሎ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ድረስ ያሉ ምክር ቤቶችን በብቸኝነት ያላግባብ ስለተቆጣጠረ ሕዝቡ ተስፋ ቆረጠ፡፡ ከዚህ አኳያ አሁን የሕዝቡ ትግል ሰላማዊና ሕጋዊ ብቻ መሆን አልቻለም፡፡ አመፅም የተቀላቀለበት፣ ኃይልም የተቀላቀለበት ሆነ ፡፡ በእኔ እምነት በየትኛውም ሁኔታ መካሄድ ያለበት ትግል ሰላማዊና ሕጋዊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን አንድ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ማድረግ የማይችልበት ሁኔታ ከተፈጠረ ብንፈልግም፣ ብንመኝም ልናስቀረው አንችልም፡፡ አሁን የምናየው ዓይነት የማይፈለግ ትግል ይካሄዳል፡፡

አሁን እየተደረገ ያለው ትግል ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ አንደኛ የተቀናጀ ትግል አይደለም፡፡ በአጀንዳና በአስተሳሰብ ደረጃ ወጥ የሆነና የተቀናጀ ትግል አይደለም፡፡ ምክንያቱም አገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሩት ትግል አይደለም፡፡ አገር ውስጥ  ያለን የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ነው ትግል ማድረግ የምንፈልገው፡፡ ግን ደግሞ እኛ የምናካሂደው ትግል ምቹ ሁኔታ አላገኘም፡፡  ሕዝቡ  በዚህ ምክንያት ተስፋ ቆረጠ፡፡ እኛን ማዳመጥ አቆመ፡፡ እኛን ለውጥ ያመጣሉ ብሎ ተስፋ ማደረግ አቆመ፡፡ በራሱ መንገድ መሄድ መረጠ፡፡ በራሱ መንገድ ሲሄድ ግን በአንድ በኩል አጀንዳው የተደራጀ አይደለም፡፡ አስተሳሰቡ የተቀናጀ አይደለም፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች በጣም አካባቢያዊ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች ክልላዊ የሆኑ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ አንዳንድ አካባቢ ደግሞ አገራዊ የሆኑ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ሥራ ይፈጠርልን ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ መንግሥት ይውረድ እስከሚለው ጥያቄ ድረስ ይቀነቀናል፡፡ ስለዚህ በአጀንዳ ደረጃ የተደራጀ አይደለም፡፡ ሁለተኛ በተደራጀ ፓርቲ የሚመራ አይደለም፡፡ ይህ ግን ሄዶ ሄዶ አይደለም የሌሎችን ዓላማ የራሱንም ሊያሳካ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ሊያካሄዱ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ የሕዝቡን ትግል እነሱ ተቆጣጥረው የሚመሩበት ሁኔታ ካልተፈጠረ፣ የሕዝቡ ትግል ሄዶ ሄዶ ኢሕአዴግን ሊያፈርስ ይችላል፡፡ ግን ኢሕአዴግን በማፍረስ ላይቆሞ ይችላል፡፡          

ሪፖርተር፡- ለምንድነው አገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትግሉን መምራት ያልቻሉት?

አቶ ልደቱ፡-  በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንዱና ዋናው በገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ሕዝብና ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲገናኙ አይፈልግም፡፡ መገናኛ ብዙኃንን ለብቻው ተቆጣጥሮ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሕዝቡ ጋር እንዳይገናኙ አድርጎ፣ መገናኘት ሲሞክሩም የተለያዩ እንቅፋቶች እየፈጠረና ምርጫዎችን እያጭበረበረ በተለያዩ  ምክንያቶች እንቅስቃሴያቸውን ገድቦታል፡፡ ሕዝቡን እንዳያነሳሱ አድርጓቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ራሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገዥውን ፓርቲ ተፅዕኖ ተቋቁመው አሸናፊ ለመሆን የሚያስችላቸው አስተሳሰብና ድርጅት ጥንካሬ አልፈጠሩም፡፡ ደካሞች ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ቦታ አጣ፡፡ በተወሰነ ደረጃ ኅብረተሰቡ ዘንድ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ያሉ ውጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው፡፡ የአክራሪ አስተሳሰብ ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በወቅቱ ትግል ትርጉም የለሽ ሆንን፡፡ ኢሕአዴግ ለመጪዎቹ 30 እና 40 ዓመታት ይችን አገር ማስተዳደር ያለብኝ እኔ ብቻ ነኝ በማለት አስቀድሞ ወስኗል፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እዚህ አገር እንዲኖሩ የሚፈለገው ለይስሙላ ነው፡፡ ለፕሮፓጋንዳና ለዲፕሎማሲ ጥቅም ነው፡፡ በሕግ ተመዝግበናል እንጂ ኢሕአዴግ ልብ ውስጥ ቦታ የለንም፡፡ ዕውቅና የለንም፡፡ እንደ ጠላት ነው የምንቆጠረው፡፡ በዚህ ምክንያት ሕዝቡ ራሱ በወሰነውና በመረጠው መንገድ ትግል ማካሄድ ምርጫው ሆነ፡፡ ይህ ግን ለኢሕአዴግ ጎዳው እንጂ አልጠቀመውም፡፡ ኃላፊነት የሚወስድ አካል የለም፡፡ በዚህ ሁኔታ የተካሄዱ ትግሎች ውጤት አያመጡም፡፡ በዚህ መንገድ የተካሄዱ ትግሎች በሌሎች አገሮች ዓይተናል፡፡ ለምሳሌ በዓረብ አገሮች መንግሥትን ለማውረድ ባልተቀናጀ ሁኔታ የተደረጉ ትግሎች መንግሥትን በማፍረስ አልቆሙም፡፡ አገር ነው ያፈረሱት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሐሳብ አጣብቂኝ አለ፡፡ በአንድ በኩል ያልተቀናጀና ያልተደራጀ የሕዝብ ትግል አለ፡፡ አደጋ ሊያመጣ የሚችል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጠንካራ የሕዝብ ትግል ካልሆነ በስተቀር፣ በመስዋዕትነት ካልሆነ በስተቀር፣ ሥልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት የሌለው አምባገነን ሥርዓት አለ፡፡ ይህ የሕዝቡን አስተሳሰብ አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶታል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መጠናከር ወሳኝነት እንደዚህ ከሆነ፣ እንዴት ነው ራሳቸውን ማጠናከር ያለባቸው?

አቶ ልደቱ፡- ወሳኝነት ብቻ ሳይሆን ምትክ የሌለው ነው፡፡ ኢሕአዴግ የማይገነዘበው ነገር ይህንን ነው፡፡ ሁል ጊዜ በሥልጣን ላይ መቆየት ይፈልጋል፡፡ ኢሕአዴግ ለሃያ ሰባት ዓመታት በሥልጣን ላይ በመቆየቱ ብቻ ይበቃዋል፣ ከሥልጣን መውረድ አለበት ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ማንም ሥርዓት ይሰለቻል፡፡ በአንዳንድ አገሮች አንዳንድ ፓርቲዎች ሥልጣን የሚለቁት ጥሩ ነገር ስለማይሠሩ አይደለም፡፡፡ ስለሚሰለቹም ጭምር ነው፡፡ ኢሕአዴግ አሁን ማሰብ ያለበት ጥሩ  ነገር ሲሠራ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ 27 ዓመታት በሥልጣን ላይ በመቆየቱ ይበቃሃል ውረድ ተብሎ ጥያቄ ለማቅረብ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ከበቂ በላይ የሆነ ምክንያት ነው፡፡ ግን ችግሩ ምንድነው? ተቃዋሚ ፓርቲዎች በፍፁም እሱን ሊተኩ በማይችሉ ሁኔታ ደካማ እንዲሆኑ ነው ሲሠራ የነበረው፡፡ ማድረግ የሚገባውን ባለማድረግ ብቻ አይደለም፡፡ ማድረግ የማይገባውን እያደረገ ነው ያለው፡፡ ኢሕአዴግ ታሪካዊ ድርጅት ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የብዙኃን ፓርቲ አስተሳሰብ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና እንዲያገኝ ያደረገ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት ራሱ ጥረት አድርጎ ነበር ተቃዋሚ ድርጅቶች እንዲጠናከሩ ማድረግ የነበረበት፡፡ ግን ያደረገው የራሱ ኃላፊነት መሆኑን ዘንግቶ እነሱን የማዳከምና ከዜሮ በታች እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ነው እያከናወነ ያለው፡፡ ኢሕአዴግም አልተጠቀመም፣ አገሪቱም አልተጠቀመችም፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ፖለቲካ ወጥተን ወደ መቻቻል፣ ወደ መደማመጥ፣ ወደ ሰጥቶ መቀበል የፖለቲካ ባህል ካልገባን ሄደን ሄደን አገሪቱን ነው የምናፈርሰው፡፡ ለዚህ ነበር ሦስተኛ አማራጭ ያስፈልጋል እያልን ለብዙ ዓመታት የጮኽነው፡፡ የሰማን ግን የለም፡፡ አሁንም ያለን አማራጭ ሌላ አይደለም፡፡ ከእንዲህ ዓይነት የፅንፍ የፖለቲካ ባህል ወጥተን በምክንያቶች መደገፍና በምክንያት መቃወም የምንችልበት፣ በመቻቻልና በመደማመጥ የፖለቲካ ችግርን የምንፈታበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡          

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይጠናከሩ አንድ ምክንያት የገዥው ፓርቲ እጅ ረዥምነት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ አብዛኛዎች ፓርቲዎች በብሔር ሲደራጁ ይታያል፡፡ ገና በተቃዋሚ ፓርቲነት እያሉና መንግሥት ሳይመሠርቱ የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ ገብተው ችግር ውስጥ ሲገቡ ይታያል፡፡ ገና ከጅምሩ የጥቅም ሽኩቻዎች አሉባቸው ይባላል፡፡ ከዚህ አኳያ የእነሱ መሠረታዊ ችግርስ ምንድነው? እንደ አብነት የኢትጵያዊያን ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢዴፓን) መወሰድ ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊት ጠንካራ ፓርቲ ነበረ፡፡ አሁን ግን በፓርቲው ውስጥ ክፍፍል ተፈጥሯል ይባላልና ዋነኛው ችግር ምንድነው? 

አቶ ልደቱ፡- ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመዳከማቸው የገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ ምን ያህል እንደሆነ ከተግባባን፣ ሁለተኛው ነገር በውስጣችን ያለው ድክመት ምንድነው የሚለው ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመተቸት እንታወቃለን፡፡ እኔም በግሌ፣ የተደራጀሁበትም ፓርቲ ከዛሬ 18 ዓመት ጀምሮ የኢትየጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ቁጭ ብለው መገምገም የማይችሉ፣ ራሳቸውን ማረም የማይችሉ ከሆነ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለሃያና ለሰላሳ ዓመታት ሥልጣን ላይ ይቆያል እያልን ስንናገር ነበር፡፡ በወቅቱ ይህን የሰማን የለም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሩ እንደምናስብ፣ ገዥውን ፓርቲ ለመጥቀም ብለን እንደምንናገር አድርጎ ነው ሰው ያስብ የነበረው፡፡ በተግባር እያየን ያለነው ይህ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሒደት ድክመታቸውን አርመው ወደ ጥንካሬ ከመሄድ ይልቅ የበለጠ እየተዳከሙ ነው የመጡት፡፡ ከመዳከምም አልፈው አሁን እንደሌሉ የሚቆጠሩበት ሁኔታ ውስጥ ነው የገቡት፡፡ ስለዚህ አንደኛው የትውልድ ችግር ነው፡፡ ኢሕአዴግም ውስጥ ያሉ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ውስጥ ያሉ አብዛኛዎች አመራሮች የ1950ዎችና የ1960ዎች ትውልድ ናቸው፡፡ የግራ ፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ ያደጉ ናቸው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ባህላቸው ችግር አለበት፡፡ ሦስተኛ አማራጭን አይቀበሉም፡፡ የእኔ ብቻ አማራጭ ትክክል ነው፣ የእኔ ብቻ አማራጭ ገዥ መሆን አለበት ብለው የሚምኑ ናቸው፡፡ እንደ ገዥው ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የሚመሩት እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ባህል ባላቸው ግለሰቦች ነው፡፡ ስለዚህ የዚያ ችግር አካላት ናቸው፡፡ ፀረ ዴሞክራሲ የሆነ አስተሳሰብ ገዥው ፓርቲ ውስጥ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ውስጥ አለ፡፡ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ችግርም ገዥው ፓርቲ ውስጥ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ውስጥም አለ፡፡      

ሪፖርተር፡- ከዚህ አኳያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነገ አገር ለመምራት የሚያስችል ዕድል ቢያገኙ አገሪቱ ወዴት ትሄዳለች ይላሉ?

አቶ ልደቱ፡- ለዚህ ነው እኮ እኛ ሁልጊዜ ተቃዋሚ ራሱን ቆም ብሎ ይመልከት፣ ኢሕአዴግን መተቸት ብቻ ሳይሆን እኔ ምን ላይ ነው ያለሁት? ሕዝቡ በሚፈልገው መጠን ጥንካራ ነኝ ወይ? የሕዝቡን ትግል አስተባብሬ ለመምራት የሚያስችል ድርጅታዊ ጥንካሬ አለኝ ወይ? ብሎ ራሱን መገምገም አለበት፡፡ በዚህ ደረጃ ግን ራሱን ለመገምገም ተቃዋሚ ፓርቲ መቼም ቢሆን ዝግጁ ሆኖ አያውቅም፡፡ ሁልጊዜም ሥርዓቱን መተቸት ነው እንጂ እኛ ያለብን ችግር ምንድነው? ብሎ የመገምገም ባህል የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ ኖሮም አያውቅም፡፡ ከዚህ በፊት በስሜት ቅንጅትን ብዙ ሰዎች እንደ ጠንካራ ስብስብ ይቆጥሩታል፡፡ ግን አልነበረም፡፡ በተለይ ችግርን ከመፍታት፣ ከዴሞክራሲ ባህል አንፃር በጣም ደካማ ስብስብ ነው የነበረው፡፡ ለዚያ ነው ችግሩን ሳይፈታ የተበታተነው፡፡ ገዥው ፓርቲ እንኳ ሥልጣን ላይ ሆኖ ራሱን ሲገመግም እናያለን፡፡ ከዚህም መማር ነበረብን፡፡ አንድም ቀን ተቃዋሚ ፓርቲ ስለኢሕአዴግ ከማውራት ውጪ ራሴን መገምገም አለብኝ ብሎ ሲመክር ሰምተን አናውቅም፡፡ አሁንም እየመከርን አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ከሥልጣን ይውረድ እንጂ የእኛ ችግር የለም ብለው ነው የሚያስቡት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህን ጉዳይ በጣም በጥንቃቄ ማየት አለበት፡፡ ተቃዋሚ ሆኖ ዴሞክራሲን በውስጡ ያልተለማመደ ነገ አራት ኪሎ ገብቶ ዴሞክራሲ ሊያሰፍን አይችልም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አገር እንለውጣልን ሲሉ ይደመጣል፡፡ መጀመርያ ግን ራሳችንን አልለወጥንም፡፡ ራሳችንን ሳንቀይር ሕዝብንና አገርን ልንቀይር አንችልም፡፡ ለዚህ ነው የፖለቲካ ባህሉ በሽተኛ ሆኖ የቀጠለውና ይህች አገር እንዲህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ የገባችው፡፡ ስለዚህ ሥርዓቱ ውስጥ አሉ የምንላቸው ችግሮች ሁሉ ይነስም ይብዛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥም አሉ፡፡ በእኔ እምነት አሁንም አንድም ጠንካራ የሚባል ተቃዋሚ ፓርቲ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፣ ኢዴፓን ጨምሮ፡፡ እንዲያውም ኢዴፓ በመፍረስ አደጋ ውስጥ ነው ያለው፡፡   

ሪፖርተር፡-  ስለዚህ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት ምን መደረግ አለበት? ምን ማድረግ አለባቸው?

አቶ ልደቱ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰቱ ችግሮች እኛም ተጠያቂነት አለብን፡፡ የመፍትሔው አካል ብቻም አይደለንም፡፡ የችግሩም አካል ነን፡፡ ድክመት አለብን፡፡ ይህን ድክመታችንን ቁጭ ብለን በውይይት መፍታት አለብን፡፡ የተበታተነ የተቃዋሚ ፓርቲ እንቅስቃሴ ማብቃት አለበት፡፡ ሲቻል ወደ አንድ ሳይቻል ወደ ሁለትና ሦስት የፖለቲካ ጎራ መቀየር አለበት፡፡ በአስተሳሰብ ራሳችንን አጠናክረን ተጨባጭ የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም ለሕዝቡ ማቅረብ አለብን፡፡ የሕዝቡን ትግል የመምራት ሚና በእጃችን ቀርፀን መንቀሳቀስ ካልቻለን፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመጪው 20 እና 30 ዓመት ሥልጣን እንይዛለን ብዬ አላምንም፡፡ እየተዘጋጀን አይደለም፡፡ ሕዝቡም ኢሕአዴግን ብቻ አይደለም መታገል ያለበት፡፡ አስተሳሰቡንና እምነቱን ሊወክሉለት የሚችሉ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲኖሩ መታገል አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ሕዝቡ ጥረት ሲያደርግ አይታይም፡፡ እንዲያውም የሕዝቡ ትግል ውጤት ያመጣልና አራት ኪሎ እንገባለን ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ መሪ መሆን ሲገባን ተከታይ ነው የሆንነው፡፡ ሕዝቡ እየመራ ነው፡፡ እኛ ተከታይ ነው የሆንነው፡፡ እኛ ነበርን የሕዝቡን ትግል መምራት ያለብን፡፡ የጋሪውና የፈረሱ ቦታ ተለዋውጧል፡፡   

ሪፖርተር፡- የተቃዋሚ ፓርቲዎች ችግር እንደገለጹት ሆኖ ገዥው ፓርቲ ውስጥም ችግር እንዳለ ይነገራል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት አድርጎት በነበረው ዝግ ሰብሰባ በብሔራዊ ፓርቲዎች መካከል አለመተማመን ተፈጥሮ እንደነበርና የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ችግር እንደገጠመው ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ ከዚህ ጋር የሕወሓት የበላይነት አለ የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ፓርቲው ግን በዚህ ረገድ ችግር እንደሌለ ገልጿል፡፡ የኢሕአዴግ አደረጃጀትም በአንዱ የበላይነትና የበታችነት ላይ እንዳልተመሠረተ አብራርቷል፡፡ እዚህ ላይ የሚሉት ነገር አለ?

አቶ ልደቱ፡- ሁለቱ የተያያዙ ነገሮች ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ የአራት ድርጅቶች ፓርቲ ነው፡፡ አራቱም ድርጅቶች ራሳቸውን በብሔረሰብ ማንነት ወክለው ነው የተደራጁት፡፡ በየትኛውም የዓለም ታሪክ እንዳየነው ራሱን በብሔርና በሃይማኖት ያደራጀ አካል በመካከሉ ጤናማ የሆነ ግንኙነት ሊፈጥር አይችልም፡፡ በሒደት ቅራኔ ውስጥ ሆኖ ግጭት ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ውስጥ እያየነው ያለው መፈረካከስና አለመግባባት ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በመጀመርያ ግን በብሔራዊ ድርጅቶች መካከል አለመግባባት አለ ብለው ያምናሉ? 

አቶ ልደቱ፡- በደንብ አለ፡፡ ይህን ኢሕአዴግ ራሱ ባለፈው ጊዜ ለ17 ቀናት ግምገማ ተቀምጦ በነበረበት ጊዜ ገልጿል፡፡ በፓርቲዎች መካከል ከፍተኛ የሆነ ጥርጣሬና አለመተማን ሰፍኖ ነበር ነው ያሉት፡፡ ችግሩን እንዳልፈቱት አሁንም እያየን ነው፡፡ ሊፈቱትም አይችሉም፡፡ ጉዳዩን በአጭር ለማስቀመጥ ኢሕአዴግ ከብሔር አደረጃጀት ወጥቶ፣ አንድ ወጥ ድርጅት እስካልሆነ ድረስ በውስጡ የሚፈጠሩ ቅራኔዎች የበለጠ እየተባባሱና እየሰፉ ይሄዳሉ እንጂ ሊፈቱ አይችሉም፡፡ እስካሁንም ህልውናው ተጠበቆ የኖረው በሕወሓት የበላይነት ነው፡፡ የሕወሓት የበላይነት እንዳለ ተጠራጥሬ አላውቅም፡፡ ይህ ማለት ግን የትግራይ ሕዝብ የበላይነት አለ ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዶች ነገሩን የሚያወሳስቡት የትግራይን ሕዝብና የሕወሓትን የበላይነት አንድና አንድ አድርገው በማየታቸው ነው፡፡ ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ የትግራይ ሕዝብ የበላይነት ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብዬ አላምንም፡፡ የሕወሓት የበላይነት ግን በድርጅት ደረጃ ነበር፡፡ በተወሰነ ደረጃ አሁንም አለ፡፡ አሁን ሕዝቡ ውስጥ እየተደረጉ ያሉ አመፆችን ብናይ፣ በአመፅ ውስጥ የሚያዙና የሚስተጋቡ መፈክሮችን ብናይ የሕወሓት የበላይነት ጉዳይ ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ እንዲያውም የኢሕአዴግ ግምገማ ዋናው ውደቀት የሕወሓት የበላይነትን እንደነበረና እንዳለ ተቀብሎ አለመውጣቱ ነው ትልቁ ውድቀት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ራሱ ለኢሕአዴግም አይጠቅመውም፡፡ ይህ ደግሞ የትግራይን ሕዝብ ተጎጂ እያደረገው ነው፡፡

ነገር ግን በሒደት የኃይል አሠላለፍ እየተለወጠ ነው የሚሄደው፡፡ ምክንያቱም የሚወክሉት ሕዝብና ክልል በስፋትም፣ በሕዝብ ብዛትም የተለያየ ነው፡፡ የኃይል ሚዛን ሁልጊዜ እንዳለ የሚቀጥል አይደለም፡፡ እየተለወጠ ነው የሚሄደው፡፡ ኢሕአዴግ ውስጥ የኃይል ሚዛን ለውጥ መምጣቱ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የማይቀር ነበር፡፡ አሁን የኃይል ሚዛን ለውጥ እየመጣ ነው፡፡ የሕወሓት የበላይነት እየቀነሰ የመጣበትና ሌሎች ኃይሎች ደግሞ የበለጠ ራሳቸውን ወደ በላይነት ለማምጣት እየጣሩ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው አሁን በፓርቲው ውስጥ ግጭቶች እየተፈጠሩ ያሉት፡፡ እነዚህ ግጭቶች የተፈጠሩት ኢሕአዴግ ዕድለ ቢስ ሆኖ ወይም አመራሮቹ ደካሞች ስለሆኑ አይደለም፡፡ ራሱን በሃይማኖትና በብሔር ያደራጀ አካል ሄዶ ሄዶ ወደዚህ ዓይነት ቀውስ ነው የሚገባው፡፡ ለወደፊት ኢሕአዴግ ቅራኔውን ለመፍታት ከፈለገ ከብሔራዊ አደረጃጀት ወጥቶ የአስተሳሰብ ድርጅት መሆን አለበት፡፡

ላለፉት 26 ዓመታት ትግል ውስጥ ቆይቻለሁ፡፡ አብዛኛውን ዕድሜዬን ያሳለፍኩት ትግል ውስጥ ነው፡፡ ብዙ ነገር ተሳስቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ትግሉ ውስጥ ስገባ የነበርኩት ልደቱና አሁን ያለሁት ልደቱ የተለያዩ ናቸው፡፡ እንደገና የመወለድ ያህል ልዩነት አለኝ፡፡ አንድ ነገር ግን እንዳልተሳሳትኩና እስካሁን ድረስ በእርግጠኝነት ትክክለኛ አቋም ነው ብዬ የማምነው አለ፡፡ በብሔር ተደራጅቶ መታገልና የአገሪቱን አደረጃጀት በብሔር መሥፈርት ማደራጀት ሄዶ ሄዶ ለእንዲህ ዓይነት ብጥብጥ እንደሚያበቃን ተጠራጥሬ አላውቅም፡፡ እስካሁን ድረስ ወጥ የሆነ የማልጠራጠረው ትክክለኛ ነገር ይኼ ነው፡፡ ሌሎች ነገሮችን ግን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ሊከብደኝ ይችላል፡፡ እኔ እንዲያውም እዚህ እንድቆይ ያደረገኝ ይህ ችግር ነው፡፡ ይህን በማስቀረት ረገድ ትንሽም ቢሆን አስተዋጸኦ ካለኝ ብዬ ነው ፖለቲካ ውስጥ የቆየሁት፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን ኢሕአዴግ ሌሎች ቅንጭብጫቢ ነገሮችን በማድረግ ችግሮችን እፈታለሁ ማለት ተገቢ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ  እንደሚሉት ኢሕአዴግ በብሔር ከመደራጀቱ አኳያ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ባሻገር የራሳቸውን ውስጣዊ ችግር እስካልቀረፉ ድረስ አገሪቱ ያጋጠማት ቀውስ ሊፈታ እንደማይችል እየገለጹ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት  አገሪቱ ወዴት እየሄደች ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ልደቱ፡- አንደኛው ኢሕአዴግ ቅድም በምንጭነት የጠቀስኳቸውን ጉዳዮች በአግባቡ ተንትኖ ተገቢ የሆነ መፍትሔ ከሰጠ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እዚህ አገር በነፃነት እንደሠሩ ዕድል ከፈጠረ፣ ሕዝቡ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የሚፈልገው ፓርቲ የሚመርጥበትን ዕድል ካመቻቸ፣ ለዚያ የሚመጥኑ ተቋማትን ካቋቋመ፣ ሕጎችን ካሻሻለ፣ ኢትዮጵያ ወደ ጥሩ አቅጣጫ ልትገባ የምትችልበት ዕድል ይኖራል፡፡ አንዱ አማራጭ ይኼ ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ኢሕአዴግ በለመደው መንገድ ይቀጥላል፡፡ ያልተደራጀውና ያልተቀናጀው የሕዝብ ትግልም ይቀጥላል፡፡ የሕዝቡ ትግል ማሸነፍ ከቻለ ኢትዮጵያ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ነው የምትገባው፡፡ ኢሕአዴግ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አሁን እየተካሄደ ያለውን የሕዝብ ትግል ማፈን ወይም ማስቆም ከቻለ የማስመሰሉ ዴሞክራሲ፣ የማስመሰሉ የሰብዓዊ መብት ጭራሽ በማይኖርበት ሁኔታ ፍፁም በሆነ አምባገነንነት ኢትዮጵያ የምትገዛበት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው በጎ አማራጭ ዕድል ያለው አይመስልም፡፡ የቀሩን አሁን ሁለት አማራጮች ናቸው፡፡ ወይም ያልተቀናጀውና ያልተደራጀው የሕዝብ ትግል አሸናፊ ሆኖ አገሪቱ ወደ አደጋ ትገባለች፡፡ ወይ ኢሕአዴግ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አሸንፎ ፍፁም የሆነ አምባገነናዊ መንግሥት ሆኖ የሚወጣበት ሁኔታ አለ፡፡ ምናልባትም ወታደራዊ መንግሥትም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ዓይነት ሁኔታ ነው እየተፈጠረ ያለው፡፡  

ሪፖርተር፡-  ኢሕአዴግ አሁንም ችግሩን እፈታዋለሁ ሲል ይደመጣል፡፡ ሰሞኑን የፓርቲው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው፡፡ በአቶ ኃይለ ማርያም ምትክ ሊቀመንበርና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ይመርጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ እንዴት ነው ያዩት? ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርስ ለውጥ ያመጣል ብለው ያስባሉ?

አቶ ልደቱ፡- ሁለት ነገር ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ማንኛውንም ጉዳይ መወሰን በኢሕአዴግ ውስጥ ቀላል አይሆንም፡፡ ቀላል ሆኖ የነበረው አንድ ፓርቲ ከፍተኛ የበላይነት ስለነበረው ነው፡፡ ይህ የኃይል ሚዛን በሒደት እየተቀየረና የበላይነቱን ለመያዝ እየተፎካከሩ ያሉ ሌሎች ፓርቲዎች እየመጡ ስለሆነ፣ ከዚህ በኋላ እንደ እስካሁኑ በቀላሉ የሚወሰን ነገር ኢሕአዴግ ውስጥ አይኖርም፡፡ መረጃው የለኝም፡፡ ግን አዲስ መሪ ለመምረጥ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ ከሚፈለገው በላይ ጊዜ እየወሰዱ ነው፡፡ መገመት እችላለሁ፡፡ እንዴት አድርገው ሊወስኑ እንደሚችሉ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባት ሲወስኑም ሌላ አዳዲስ ቅራኔዎች በውስጣቸው ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም አሁን በከፍተኛ ደረጃ ጤናማ ባልሆነ ግንኙነት ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በቅርቡ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ይኖራል፡፡ ያ ጠቅላይ ሚኒስትር ተዓምር ይፈጥራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾምልኝ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ አስተሳሰቡን ይቀይር፣ አሠራሩን ይቀይር ጥያቄው ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን አውቆ ወደ ፖለቲካዊ መፍትሔ ቶሎ መግባት እንጂ፣ ማንም መሪ ቢመጣ ለውጥ አይመጣም፡፡ አንደኛ ያ መሪ በብቸኝነት የሚወስነው ነገር እንደሌለ ሁላችንም እናውቃን፡፡ እንደ አቶ መለስ በከፍተኛ የበላይነት ሁሉን ነገር ሊወስን የሚችል መሪ በቀላሉ አይገኝም፡፡ ስለዚህ የጋራ የሆነ አመራር ነው ሊቀጥል የሚችለው፡፡ ሁለተኛ በፓርቲዎቹ ውስጥ ያለው አለመግባባት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ ስለዚህ ያ ሰውዬ ከአንድ ፓርቲ የሚመረጥ ነው፡፡ ከአራቱ ፓርቲዎች አይደለም፡፡ ስለዚህ በዚያ የኃይል ሽኩቻ ውስጥ አዲሱ ሰውዬ የራሱ ቦታ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ነገሮችን በራሱ ሊወስን አይችልም፡፡ እኔ ከሚመጣው ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙም የምጠብቀው ነገር የለኝም፡፡ እኔ እንዲያውም የምሠጋው ሌላ መሪ መምረጣቸው ለሌሎች ችግሮች ምንጭ እንዳይሆን ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- በኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል አለመግባባቶች እንዳሉ እየገለጹ ነው፡፡ በተለይ የኃይል ሚዛኑ እየተለወጠ መጥቷል ብለዋል፡፡ ምን ዓይነት የኃይል ሚዛን ነው? ወደዚህስ እንዴት ሊገባ ቻለ?  

አቶ ልደቱ፡- ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕወሓት የበላይ የሆነበት ምክንያት አለው፡፡ ከትግሉ ጊዜ ጀምሮ ሕወሓት ከፍተኛ ሠራዊትና የራሱ ኢሕአዴግን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና የነበረው ድርጅት ነው፡፡ ግንባሩን እሱ ነው የፈጠረው፡፡ ግንባሩን ብቻ አይደለም አንዳንድ ፓርቲዎችንም እሱ ነው የፈጠራቸው፡፡ ስለዚህ ለተወሰኑ ዓመታት እያዘዘና እየተቆጣጠረ የሚቀጥልበት ዕድል ነበረው፡፡ በሒደት ግን ፓርቲዎች ራሳቸውን እያጠናከሩ መጡ፡፡ የሕዝቡን ጥያቄ እያዳመጡ፣ የራሳቸውን የሥልጣን የበላይነትም ለማስከበር የሚጥሩበት ሁኔታ እየተፈጠረ መጣ፡፡ ስለዚህ አንድ ፓርቲ እዚያ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ የሚሆንበት ዕድል ከአሁን በኋላ የለም፡፡ ስለዚህ መፍትሔው መሆን ያለበት ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ መምጣት ነው፡፡ ይህን ስታደርግ ሁሉም ነገር ቀላል ይሆናል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ለዚህ ሁሉ አገራዊ ችግር በተለይም በኢሕአዴግ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በሕዝቡ ዘንድ መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው? በአጠቃላይ አገራዊ መግባባት ፈጥሮ አገሪቱን ካለችበት ቀውስ ለማውጣት መፍትሔው ምንድነው መሆን ያለበት?

አቶ ልደቱ፡- ይህ መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ወደ መፍትሔው ከመሄዳችን በፊት መደረግ ያለበት አንደኛ በችግሩ ጥልቀት መተማመን፡፡ ሁለተኛ ለዚህ አደጋ የዳረጉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ የተቀራረበ አስተሳሰብ መያዝ ከቻልን ነው መፍትሔው ላይ ትርጉም ያለው፣ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው፡፡ ይህ ችግር መፈታት ያለበት በኢሕአዴግ ብቻ አይደለም፡፡ ችግሩ ከፖለቲካም በላይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ብቻ አይደለም የሚፈታው ኢሕአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቁጭ ብለን ልንፈታው የምንችለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ፖለቲከኞች በተገቢው ጊዜና ሁኔታ መስጠት ያለብንን ሳንሰጥ ቀርተን ጉዳዩን ከፖለቲካ በላይ አድርገነዋል፡፡ የአገርን ህልውና ችግር ውስጥ ያስገባ ጉዳይ አድርገነዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያዊያን ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ ችግር የመፍትሔ አካል ኢሕአዴግ ብቻ መሆን አይችልም፡፡ ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎችም ብቻቸውን ሊፈቱት አይችሉም፡፡ ሕዝቡን በስፋት የሚያሳትፍ መፍትሔ መሆን አለበት፡፡ ሲቪክ ማኅበራት መሳተፍ አለባቸው፡፡ የአገር ሽማግሌዎች መሳተፍ አለባቸው፡፡ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶች፣ ስፖርተኞችና ኅብረተሰቡን በተለያየ መንገድ ሊወክሉ የሚችሉ ክፍሎች የሚሳተፉበት ተሃድሶ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ ችግሩን እኔ እንደ ፈጠርኩት እኔ ብቻዬን እፈታዋለሁ ከሚለው አባዜ መውጣት አለበት፡፡

በእኔ እምነት አንድ የተሃድሶ ኮሚሽን መቋቋም አለበት፡፡ ይህ ኮሚሽን በፓርላማ በአዋጅ መቋቋም አለበት፡፡ ይዘቱና ኃላፊነቱ በሕግ መወሰን አለበት፡፡ ይህ የተሃድሶ ኮሚሽን በሁለት መንገድ ሊቋቋም ይችላል፡፡ ፓርቲዎች ከተስማማን ከሁላችንም ገለልተኛ በሆነ አካል ሊቋቋም ይችላል፡፡ በዚህ መስማማት የምንችል ከሆነ ከሁላችንም የተውጣጣ ሆኖ ሊቋቋም ይችላል፡፡ ገዥው ፓርቲም፣ ተቃዋሚዎችም፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች ያሉበት መድረክ ሆኖ ሊቋቋም ይችላል፡፡ መሠረታዊ ኃላፊነቶች ያሉት ኮሚሽን መሆን አለበት፡፡ አንዱ ኃላፊነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ፣ ያለፍንበትን የፖለቲካ ጥላቻ፣ መገዳደል፣ ደም መፋሰስ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቆም የሚችል ብሔራዊ የእርቅ መድረክ መፍጠር የሚችል መሆን አለበት፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ ሕዝቡ መድረክ እየተፈጠረለትና እየተወያየ ያለፉትን የታሪክ ጠባሳዎችን ለዛሬውና ለወደፊቱ የፖለቲካ ሒደት እንቅፋት የማይሆኑበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ሕዝቡና የፖለቲካ ኃይሎች ይቅር የሚባባሉበት፣ ያለፈውን ታሪክ የማንደግምበት የጋራ የምክክር መድረክ መፈጠር አለበት፡፡

ሁለተኛው ኃላፊነቱ የሚመጣው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ ፍትሐዊ ምርጫ እዚህ አገር ላይ ተካሂዶ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቂ ጊዜ አግኝተው፣ ሕዝቡ ውስጥ በቂ ሥራ ሠርተው፣ በአስተሳሰብም፣ በድርጅታዊ አቅምም የበለጠ የሚደራጁበት፣ የሚጠናከሩበት ዕድል አግኝተው፣ ሕዝቡም ያለ ምንም ፍርኃትና ሰቀቀን ማንኛውንም ፓርቲ የሚደግፍበት፣ የሚፈልገውን ፓርቲ እንዲመርጥ የሚያስችል ሥራ የሚከናወን ኮሚሽን መሆን አለበት፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማትን የሚያሻሽል ኮሚሽን መሆን አለበት፡፡ ሕግና ሥርዓት ዝም ብሎ ሊሰፍን አይችልም፡፡ መጀመርያ ትክክለኛ የሆነ የፖለቲካ መፍትሔ ለማምጣት የጀመርከው መሆኑን ለሕዝቡ በአሳማኝ ሁኔታ ማሳየት አለብህ፡፡ ከኢሕአዴግ የሚጠበቀው ይህ ነው፡፡ ይህን ካደረገ እርግጠኛ ነኝ ሕዝቡም ከሕገወጥና ሰላማዊ ካልሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ራሱን አቅቦ የመፍትሔው አካል የማይሆንበት ምክንያት አለ ብዬ አላምንም፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ወገኖች ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥሪ ተደርጎላቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከቂም በቀልና ከጥላቻ ፖለቲካ ነፃ የምንሆንበት፣ ቃል ኪዳን የምንገባበት መድረክ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ጉዳይ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በብዙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም በመሪዎቻቸው የሚቀርበው ጥያቄ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚል ነው፡፡ በእኔ እምነት አሁን ለገባንበት አገራዊ ችግር መፍትሔው  ይህ ነው ብዬ አልወስድም፡፡

የመጀመርያው ምክንያቴ ብዙውን ጊዜ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በትጥቅ ትግል ከፈረሰ፣ የግድ መንግሥት የማቋቋም ጥያቄ ግዴታ ከሆነ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ሊቋቋም ይችላል፡፡ በሕዝብ ተመርጬ ነው ሥልጣን ላይ ያለሁት የሚለው ኢሕአዴግ ይህን ጥያቄ ሊቀበለው እንደማይቸል ቀድመን እናውቃለን፡፡ ስለዚህ የምንፈልገው መፍትሔ ከሆነ የማይቀበለውን ጥያቄ በተደጋጋሚ ማቅረብ ጥቅም ያለው አይመስለኝም፡፡ ሁለተኛው የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ጥያቄ ከሕዝብ የሥልጣን የበላይነት መርህ አንፃር ስናየው የራሱ ችግር አለበት፡፡ ጊዜያዊም ይሁን ቋሚ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ማቋቋም ያለበት ሕዝቡ ነው፡፡ የፓርቲዎች ሚና መሆን ያለበት ሕዝቡ በፍትሐዊ ምርጫ የራሱን መንግሥት የሚያቋቁምበት ወይም የሚመርጥበት ዕድል ማመቻቸት ነው፡፡ ሦስተኛው የሽግግር መንግሥት ማቋቋም የሚጠይቃቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ መለስተኛ ፕሮግራምና የሥልጣን ድልድል ይጠይቃል፡፡ መንግሥት ስለተቋቋመ አሁን ተቃዋሚዎች ብቻችንን የሽግግር መንግሥት አቋቁሙ ብንባል፣ እንደዚህ ዓይነት የሥልጣን ድልድል ለማድረግ መስማማት የሚያስችል ቁመና አለን ወይ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ዋናው ነገር ሕዝቡ የራሱን መንግሥት መምረጥ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ ነው እንጂ ትኩረት ማድረግ ያለብን፣ ኢሕአዴግ ሊቀበለው የማይችለውን ጥያቄ ማቅረብ ተገቢ መስሎ አይታየኝም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕገ መንግሥትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ...