Monday, March 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያና ደቡብ ግሎባል ባንክ ለግብይት አገልግሎት ስምምነት ፈጸሙ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቀድሞው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድማገኝ ነገራና የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር በየወሩ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚገናኙበት መድረክ ነበራቸው፡፡

የአገሪቱን ባንኮች በአባልነት ባቀፈው የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ወርሃዊ ስብሰባ ሲገናኙ የቆዩት የባንክ ሰዎች፣ ማክሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ሁለቱም ኃላፊዎች በሌላ አጋጣሚ ተገናኝተዋል፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ወንድማገኝ ነገራ አቶ አዲሱ የሚመሩትን የደቡብ ግሎባል ባንክ በመወከል ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ ሁለቱ የባንክ ባለሙያዎች ስምምነት የፈጸሙበት ዓብይ ጉዳይም፣ የደቡብ ግሎባል ባንክ የምርት ገበያውን ክፍያዎች ማስተናገድ የሚችልበትን አሠራር ለመዘርጋት ነው፡፡ ምርት ገበያው እንዲህ ያለውን ስምምነት ከዚህ ቀደም ከ12 ባንኮች ጋር በመፈጸም እየሠራ ይገኛል፡፡ ደቡብ ግሎባል ባንክ 13ኛ ክፍያ ፈጻሚ ባንክ በመሆን አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡

ስምምነቱን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምአገኝ እንዳሉት፣ ስምምነቱ የምርት ገበያውን የክፍያ ሥርዓት ተደራሽ ለማድረግና ለማቀላጠፍ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ምርት ገበያው ከባንኮች ጋር በመሥራቱ የምርት ገበያው ተዋናዮች ግብይት በፈጸሙ ማግሥትና አቅራቢዎችም ምርታቸውን የሸጡበትን ገንዘብ ከገዢው የባንክ ሒሳብ በቀጥታ ወደ ሒሳባቸው እንዲዛወርላቸው ያስችለዋል፡፡ ይህ አሠራር ላለፉት አሥር ዓመታት ሲተገበር በመቆየቱ አስተማማኝ የግብይትና የክፍያ ሥርዓት እንዲኖር ስለማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ መሠረት ቡና አምራቾች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች በርካታ ቅርንጫፎችን የከፈተው ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ ለምርት ገበያው አባላትና ተገበያዮች ተጨማሪ አገልግሎት ሰጭ በመሆን ግብይቱን እንደሚያቀላጥፍ ታምኖበታል፡፡ ከሐምሌ 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እየተተገበረ በሚገኘው አዲሱ የቡና ግብይት ሥርዓት አማካይነት በምርት ገበያው አባል ያልሆኑ ተገበያዮችም ጭምር እንዲገበያዩ በመፈቀዱ፣ ከባንኩ አገልግሎት አርሶ አደሮች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና የግል ድርጅቶችም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡

ምርት ገበያው ከባንኮች ጋር በመሆን የሚሠራው ተገበያዮች የተቀላጠፈ የክፍያ አገልግሎት እንዲያገኙ በማሰብ ነው፡፡ በዚህም ግብይት በተፈጸመ ማግሥት አቅራቢዎችና ሻጮች ላቀረቡት የምርት ሽያጭ ከገዢው የባንክ ሒሳብ ወደ ሒሳባቸው እንዲዛወር የሚያደርግ አሠራር ተፈጥሯል፡፡ ይህ አሠራር ላለፉት አሥር ዓመታት ተዓማኒነት ያተረፈ የግብይትና የክፍያ ሥርዓት እንዲሰፍን ስለማስቻሉ ምርት ገበያው ባወጣው መግለጫ ጠቅሶ፣ እስካሁን 5,800 ያህል የባንክ ሒሳብ የከፈቱ ተገበያዮች ከምርት ገበያው ፈጣን አገልግሎት እያገኙ ስለመሆናቸውም ተመልክቷል፡፡

እንደ አቶ ወንድማገኝ ገለጻ፣ ምርት ገበያው ከባንኮች ጋር ያለውን ትስስር የሚያጠናክርባቸው ሌሎች አገልግሎቶችም ወደፊት ይኖራሉ፡፡ ለአብነት የጠቀሱት በሐዋሳና በሌሎች ከተሞች በቅርቡ ሥራ የሚጀምሩት የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላትን ሲሆን፣ በቡሌ ሆራና በሌሎችም አካባቢዎች የሚከፍቷቸው የምርት መቀበያና ማቆያ ቅርንጫፎች ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ ስለሚፈልጉ፣ የባንኮች አገልግሎት ከእስካሁኑም የበለጠ ተፈላጊ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

ምርት ገበያው የተንዛዛና ጥቂቶችን ተጠቃሚ ሲያደርግ እንደቆየ የሚታማውን  የገበያ ሥርዓት በማስቀረት በአዲስ አሠራር ተተክቷል፡፡ ከአምራቹ አርሶ አደር ጀምሮ አቅራቢው፣ ላኪውና ተቀባዩ ድረስ ሁሉም የገበያው ተዋንያን በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉም ተወስቷል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ከአርሶ አደሩ ይልቅ የደላሎችን ኪስ ሲያደልብ እንደቆየ የሚነገርለትን የአገሪቱን የግብይት ሥርዓት በማሻሻል ሁሉም የላቡን ዋጋ በወቅቱ እንዲያገኝ ማድረግ እንደተጀመረ ተገልጿል፡፡

ቀደም ሲል የክፍያና የርክክብ ሥርዓቱ ያልተማከለና መተማመን የራቀው ሆኖ የቆየበትን አካሄድ የምርት ገበያው መቋቋም የግብይት ሥርዓቱን በማዘመንና ባንኮችን በማሳተፍ ገበያውን በመተማመን ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ እንደቻለ ተመልክቷል፡፡ ባንኮችንም ተጠቃሚ የሚያደርገው አገልግሎትን በተመለከተ የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ ሲናገሩ፣ ስምምነቱ በምርት ገበያው ውስጥ ግብይት ለሚያካሂዱ ደንበኞቹ በባንኩ በኩል የተቀላጠፈ ዘመናዊ የክፍያ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በባንኩ በኩል እንዲስተናገዱ ማደረጉ የባንኩን ደንበኞች በማበራከትና በባንኩ በኩል የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ በማበራከት በኩል ለባንኩ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የወጪ ንግድን ማጠናከር ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ቀልጣፋና ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት መስጠት ሲሆን፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ በምርት ገበያው በኩል ግብይት ለሚፈጽሙ ተዋናዮች ፈጣን የክፍያ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ላኪዎችንና አቅራቢዎችን ለማገልገል የሚያስችለው አቅም እንደሚፈጥርለት ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡

ባንኩ ብዛት ያላቸው የቡና አርሶ አደሮች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ላኪዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች በርካታ ቅርንጫፎች ያሉት በመሆኑም ምርት ገበያው ከሚሰጣቸው ግብይቶች መካከል አንዱ ለሆነው የቡና ግብይት ሥርዓት መቀላጠፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ምርት ገበያው ከሐምሌ 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የምርት ገበያው የቡና ግብይት አባል ያልሆኑ ተገበያዮች እንዲገበያዩ በመፍቀዱ የቡና አርሶ አደሮች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ አቅራቢዎችና ሻጮች ያለምንም የክፍያ  መዘግየት ችግር በባንኩ በኩል ከገዢ ወደ ሻጭ ገንዘብ የሚዘዋወርበት አገልግሎት እንዲኖር ያስችላል፡፡

እያንዳንዱ የምርት ገበያው ተዋናይ የግብይትና የገንዘብ እንቅስቃሴውን በባንኮች በኩል ብቻ የማድረግ ግዴታ የተጣለበት ሲሆን፣ ባንኮችም የክፍያ አገልግሎቱን ለመስጠት ከምርት ገበያው ጋር መስማማት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከ18ቱ ባንኮች ውስጥ 13ቱ ወደዚህ አገልግሎት የገቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹም የክፍያ ሥርዓታቸውን ከምርት ገበያው ጋር ለመሥራት የሚያስችላቸውን ዝግጅት መጀመራቸው ታውቋል፡፡

 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በግማሽ በጀት ዓመቱ ብቻ ከ14 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ማገበያየቱ አይዘነጋም፡፡  

ደቡብ ግሎባል ባንክ ከዘጠኝ ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ተቋም ሲሆን፣ ከ80 ሺሕ በላይ ደንበኞችም የባንኩ ተገልጋዮች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን 2.7 ቢሊዮን ብር እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች