Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና ላኪዎች በማበጠሪያ አገልግሎት ዕጦት መቸገራቸውን ገለጹ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ለወጪ ንግድ የገቡት ውለታ እንሳይሰረዝ ሥጋት ገብቷቸዋል
  • ጥያቄው ተጋኗል ያለው መንግሥት የቡና ኢንዱስትሪ ዞን ለማቋቋም እንዳሰበ አስታውቋል

የቡና ማበጠር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቢኖሩም አብዛኞቹ በራሳቸው ወደ ውጭ የሚልኩት ካልሆነ በቀር በሌሎች ላኪዎች አገልግሎቱን እንዲሰጡ ሲጠየቁ እምቢ በማለታቸው አገልግሎቱን በማጣት እንደተቸገሩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ላኪዎች ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ጥያቄውን የሚያቀርቡ ቢኖሩም ችግሩ እንደሚባለው ሳይሆን ተጋኖ ቀርቧል ሲል አጣጥሎታል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ላኪዎች እንደገለጹት ከሆነ፣ በአገሪቱ ያሉት አብዛኞቹ ላኪዎች የራሳቸው የቡና ማበጠሪያ ማዕከል ቢኖራቸውም የሌሎችን ላኪዎች ቡና ተቀብለው አገልግሎት ለመስጠት አሻፈረኝ እያሉ ይገኛሉ፡፡ በዓመት ከአሥር ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደሚያስገኙና በመስኩ ከአሥር ዓመታት በላይ ቆይታ ያላቸው ቡና ነጋዴ እንደሚገልጹት፣ የራሳቸውን የቡና ማበጠሪያ ማሽን ለመትከል ቦታ ቢጠይቁም የመንግሥት ምላሽ ዘግይቶባቸዋል፡፡

ከመሬት ጥያቄያው በተጓዳኝ ያስቸገራቸው ግን ሰሞኑን ወደ ውጭ ሊልኩት ውለታ የገቡበትንና በሰባት መኪኖች የተጫነ ቡና የሚያበጥሩበት ቦታ ማጣታቸው ነው፡፡ እኚህ ላኪ ይብሱን ያሠጋቸው ደግሞ ለዓመታት ከውጭ ገዥዎች ጋር የገነቡትን የደንበኝነት ትስስር ሊያሳጣቸው የሚችልበት አጋጣሚ እየጨመረ በመምጣቱ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንኑ ሥጋታቸውን ለመንግሥት አካላት በማቅረብ ምላሽ እንዲሰጧቸው ያደረጉት ጥረትም የሚፈልጉትን ምላሽ እንዳላስገኘላቸው ጠቁመዋል፡፡ ይህ ጥያቄ የእሳቸው ብቻ እንዳልሆነ አብዛኛው የራሱ ማበጠሪያ ማሽን የሌለው ቡና ላኪ አገልግሎቱን በማጣት መቸገሩን ይናገራሉ፡፡ 

ስለጉዳዩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ፣ በላኪዎቹ የረቀበው ችግር የተጋነነ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ሳኒ ጥያቄ የሚያቀርቡ ላኪዎች መኖራቸውን ቢያምኑም፣ በአገሪቱ 87 የቡና ማበጠሪያ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን በመጥቀስ በላኪዎቹ የቀረበው የተቸግረናል ጥያቄ የተገላቢጦች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹87 የቡና ማበጠሪያ ኢንዱስትሪዎች ከሚላከው የቡና መጠን አኳያ ከአቅማቸው በታች እየሠሩ ነው፡፡ አብዛኞቹ ላኪዎች ካላቸው ማበጠሪያ ኢንዱስትሪዎች ባሻገር የቡና ማበጠር አገልግሎት ብቻ የሚሰጡም ስላሉ የተባለው ችግር የተጋነነ ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንዲህ ያለውን ችግር ብቻም ሳይሆን፣ ቡና በሚበጠርበት ወቅት የሚወጣውን የአቧራ ብክለት ለማስቀረት፣ ብሎም በአሁኑ ወቅት ወደ ጂቡቲ ወደብ  በኮንቴይነር የሚላከው የቡና ምርት እዚሁ አገር ውስጥ ጥራቱን አስጠብቆና አሽጎ ለመላክ ያስችላል የተባለ የቡና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ዞን የመገንባት ዕቅድ መያዙን አቶ ሳኒ ተናግረዋል፡፡

ይህ የቡና ኢንዱስትሪ ዞን በአሁኑ ወቅት በአዋጭነት ጥናት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለኢንዱስትሪ ዞኑ ግንባታ የሚሆውን መሬት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወይም ከኦሮሚያ ክልል ለማግኘት እንደሚታሰብም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ምንም እንኳ አቶ ሳኒ ረዲ ይህንን ይበሉ እንጂ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ላኪዎች ግን የቡና ማበጠሪያ ቦታ ካለማግኘታቸውም ባሻገር፣ በአሁኑ ወቅት በአፋጣኝ የሚፈልጉትን አገልግሎት የሚሰጣቸው በማጣት መቸገራቸውን በመግለጽ የመንግሥትን ትብብር በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡ ‹‹አገሪቱ የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሟላት ላኪዎች እየተጋን ባለንበት ወቅት ቡናችንን የምናበጥርበት በማጣት መጉላላት አይገባንም፤›› ያሉት ላኪዎች፣ መንግሥት የሚያቀርቡትን ችግር በአግባቡ እንዲያጤነው ጠይቀዋል፡፡ አገልግሎቱ ያላቸው ላኪዎች የራሳቸውን ቡና ብቻ እንደሚያበጥሩ በመግለጽ ሌሎችን ማግለላቸው ምናልባትም ከገበያ ሽሚያ የመነጨ አድራጎት ሊሆን ስለሚችል፣ አገልግሎቱን የሚሰጡትንና እየከለከሉ የሚገኙትን በቅርብ ቢመለከታቸው እንደሚበጅም ጠቁመዋል፡፡

 የቡና ማበጠር አገልግሎት ብቻ እንደሚሰጡ የተገለጹትም ቢሆኑ፣ ከላኪው ቁጥር አኳያ አነስተኛ መሆናቸውን፣ አንዳንዶቹም የሚገለገሉባቸው ማሽኖች ለልዩ ጣዕም ቡናዎች የማይመጥኑ በመሆናቸው መንግሥት የቡና ማበጠሪያዎችን ሊፈትሻቸው ይገባል ተብሏል፡፡

ቡና የአገሪቱ ዋነኛ የወጪ ንግድ የገቢ ምንጭ በመሆን የጎላ ሚናውን እየተወጣ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከተላከው 225 ሺሕ ቶን ቡና የተገኘው የ882 ሚሊዮን ዶላር ከፍተኛውን በመሆን ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ዓመት የመጀሪያዎቹ ስድስት ወራትም ከቡና የተገኘው የ382 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ይህ አፈጻጸም ከሚጠበቀው ገቢ አኳያ የ54 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ የታየበት ቢሆንም፣ በዓመቱ መጨረሻ ከቡና የወጪ ንግድ የሚጠበቀው ገቢ ግን 1.15 ቢሊዮን ዶላር ስለመሆኑ የባለሥልጣኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች