Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከግማሽ ሚሊዮን ሔክታር በላይ ሰፋፊ እርሻዎች ውጤታማ አልሆኑም

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ባካሔዳቸው ቅስቀሳዎችና ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተነሳስተው በርካታ የውጭ ባለሀብቶች፣ ዳያስፖራዎችና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ሰፋፊ እርሻ ሥራዎች ቢገቡም አብዛኞቹ ውጤታማ መሆን አልቻሉም፡፡

ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም መባቻ ጀምሮ ማለትም ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ ለሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ከተሰጡት መሬቶች ቢያንስ ከግማሽ ሚሊዮን ሔክታር በላይ የሚገመት ይዞታ የነበራቸው እርሻዎች የተፈለገውን ውጤት ሳያመጡ ከስመዋል፡፡ አገር ጥለው የወጡም በርካቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ባሻገር ግን አሁንም የሚንገታገቱ አልታጡም፡፡

ይሁንና ከ100 ሺሕ ሔክታር ጀምሮ እስከ 10 ሺሕ ሔክታር መሬት በዝቅተኛ የሊዝ ክፍያ ከወሰዱ መካከል 23 የውጭ ኩባንያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥም ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የህንድ ኩባንያዎች ሆነው ይገኛሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ጥቢ ብቻም ሳይሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2008 ከተከሰተው የዓለም የፋይናንስና የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር የሚያያዘው የውጭ ኩባንያዎች አመጣጥ፣ አንዳንዶቹ በወቅቱ ከተከሰተው የምግብ እህል አቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ ምክንያት በኢትዮጵያ ሰፋፊ እርሻዎችን በማልማት ወደ ውጭ እህል የመላክ ዕቅድ ወጥነው የገቡም ናቸው፡፡

ከእነዚህ ሰፋፊ እርሻዎች መካከል በዋቢነት የሚጠቀሰው የህንዱ ካሩቱሪ ግሎባል ኩባንያ ነው፡፡ ካሩቱሪ እ.ኤ.አ. በ2008 ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በቅድሚያ በአበባ እርሻ ሥራ ቢቆይም፣ ወደ ጋምቤላ በማቅናት 100 ሺሕ ሔክታር መሬት የተረከበው ሩዝ፣ ስንዴ፣ ሸንኮራ አገዳ፣ የፓልም ዛፍና ሌሎችም ተፈላጊ ሰብሎችን ለማምረት ነበር፡፡ ይሁንና ኩባንያው ባሰበው መንገድ ሊሠራ አልቻለም፡፡ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ቢቀርቡም የወሰደውን መሬት ግን በሚጠበቀው ስፋትና ጊዜ ማልማት ሳይችል በመቅረቱ ከመንግሥት ጋር ሲነታረክ ቆይቶ በመጨረሻም መሬቱን ተነጥቆ መባረሩ ይታወሳል፡፡

እንደ ካሩቱሪ ሁሉ ከጋምቤላ ብቻም ሳይሆን፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝና ከደቡብ ክልሎች ብቻ ከ500 ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ ተረክበው የነበሩ ሻፑርጂ ፓሎጂ፣ ቢኤችኦ ባዮ ፕሮዳክትስ፣ ሩቺ ሶያ ኢንዱስትሪስ፣ ሲኤልሲ ስፔንቴክስ ኢንዱስትሪስ፣ ኋይት ፊልድ፣ ሳናቲ አግሮ ፋርም ኢንተርፕራይዝስ የተባሉትን ጨምሮ ሌሎችም የህንድ ኩባንያዎች ከ50 ሺሕ ጀምሮ እስከ 10 ሺሕ ሔክታር የግብርና መሬት በኢንቨስትመንት ስም ተረክበው የቆዩ ናቸው፡፡

የእነዚህ እርሻዎች መጠን የካሩቱሪን ድርሻ ሳይጨምር ሲሆን፣ የሼክ መሐመድ አሊ አልአሙዲን ንብረት የሆነው እንደ ሳዑዲ ስታር ያለውና የ10 ሺሕ ሔክታር መሬት የወሰደውን ዓይነት ያሉት ኩባንያዎችም እየተንገታገቱ የሚገኙ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በዳያስፖራና በአገር ውስጥ ባለሀብቶች በብዛት የተወሰዱት 5000 እና ከዚህም በታች ያሉት እርሻዎች ይካተቱ ቢባል ጠቅላላው ውጤታማ መሆን ያልቻለውና ለሰፋፊ እርሻዎች የተሰጠው የመሬት መጠን ከግማሽ ሚሊዮን ሔክታር በላይ እንደሚሆን ሪፖርተር ያደረጋቸው ምልከታዎች ይጠቁማሉ፡፡

ሪፖርተር ባደረገው መጠነኛ ቅኝት ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ የተረጋገጡት የሰፋፊ እርሻዎችን ጉዳይ በሚመለከት መንግሥት ምን አድርጓል ሲል እንደ አዲስ ተቋቁሞ ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት ያስቆጠረውን የሆርቲካልቸርና የግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ኃላፊዎች አነጋግሯል፡፡

 በባለሥልጣኑ የሰብልና የደን ዘርፍን በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት አቶ አበራ ሙላት ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ አብዛኞቹ እርሻዎች መንግሥት በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወቅት ባካሄደው የፕሮሞሽን ቅስቀሳ የመጡ ቢሆኑም፣ ከራሳቸው ችግሮች ባሻገር በመንግሥት መሟላት የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ባለመሟላታቸው ጭምር ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ከማሟላት ጀምሮ በርካታ ድጋፎች ከመንግሥት ባለመቅረባቸው ጭምር አብዛኞቹ ውጤታማ ሊሆኑ እንዳልቻሉ፣ በወቅቱ የመጡት ኢንቨስተሮችን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ የሚችል አደረጃጀት፣ የመሬት አቅርቦት ሥርዓትና ሌሎችም ተቋማዊ አደረጃጀቶች ባለመኖራቸው ሳቢያ ችግሮች መፈጠራቸውን አቶ አበራ አስታወሰዋል፡፡

በመሆኑም መንግሥት መሬት ከመለየት ባሻገር መሬት በማዘጋጀትና በማቅረብ ረገድ በአንድ ወጥ አሠራር ኢንቨስተሮችን ማስተናገድ የሚቻልበት አዲስ አደረጃጀት መፈጠሩን ያብራሩት አቶ አበራ፣ ከዚህ ቀደም በጋምቤላ ክልል የተፈጠሩትን ችግሮች በመለየት መንግሥት ጥናት ማደረጉንና ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተሰጡ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬቶች ውስጥ ችግር የገጠማቸውና ውጤታማ መሆን ያልቻሉትንም በሚመለከት ጥናት ተደርጎ ችግሮቹ መለየታቸውንና በቅርቡም ይፋ እንደሚደረጉ አስታውቀዋል፡፡

የቀድሞዎቹን የሆርቲካልቸር ልማት ኤጂንሲንና የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲን በማቀላቀል የታወቀው የሆርቲካልቸርና የግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን፣ የእንስሳት ሀብት ዘርፉን አካቶ በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች እንዲሁም አንድ ጽሕፈት ቤት በሥሩ በማካተት መዋቀሩን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡ አዲሱ አደረጃጀት በግብርና ኢንቨስትመንት መስክ፣ መሬትን ጨምሮ ይታዩ የነበሩ መሠረታዊ ማነቆዎችን በማቃለል ለአልሚዎች የቢዝነስ ፕሮፖዛል ከማዘጋጀት ጀምሮ በርካታ የአንድ መስኮት አገልግሎቶችን ለማቅረብ እየተንሳቀሰ እንደሚገኝ ተነግሮለታል፡፡

ይህ ይባል እንጂ ነባሮቹና ውጤታማ መሆን ያልቻሉት እርሻዎች ውጤታማ ካለመሆናቸው ባሻገር በእርሻዎቹ ይዞታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ በርካታ ዜጎችን በማስነሳት ጭምር መሬቱ የተመቻቸላቸው እንደመሆናቸው፣ መንግሥት እንዲህ ያሉትን እርሻዎች በሚመለከት የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ከቀድሞው ይልቅ ምን ያህል ጥንቃቄ እንደሚደረግ የሚያሳይበት፣ በነዋሪዎችና በኢንቨስተሮችም መካከል መግባባትን መፍጠር ስለሚችልበት አካሔድ በርካታ ጥያቄዎች ይጠብቁታል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች