Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የእጅ ሰዓት ጨረታ ለጊዜው ታገደ

ትኩስ ፅሁፎች

የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የእጅ ሰዓት በጄኔቭ ስዊዘርላንድ ውስጥ ከ520 ሺሕ ዶላር እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር ለመሸጥ ቀርቦ የነበረው ጨረታ ለጊዜው ታገደ፡፡

ባለፈው ሰኞ ለጨረታ ቀርቦ የነበረው የወርቅ ሰዓት ከጨረታ ሰንጠረዥ እንዲታገድ የተደረገው፣ በአሜሪካ ዴንቨር 30 ሺሕ ዳያስፖራዎችን የያዘው የኢትዮጵያ ሶሳይቲ ለአጫራቹ ኩባንያ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ነው፡፡

ዘ ዴንቨር ፖሊት እንደዘገበው፣ ከ18 ካራት ወርቅ የተሠራውን የንጉሡን የእጅ ሰዓት ለጨረታ ያቀረበው በዓለም ከትልልቆቹ አጫራቾች የሚመደበው ክርስቲስ የተባለ አጫራች ኩባንያ ነው፡፡

‹‹መልካም ዝና ያለውና ድንቃድንቅ ዕቃዎችን ለጨረታ የሚያቀርበው ክርስቲስ ኩባንያ ሰዓቱን እንዴት ሊያገኘው ቻለ›› የሚለው ለሶሳይቲው ጥያቄ ሆኗል፡፡

ንጉሡ ከመፈንቅለ መንግሥት በኋላ በ1967 ዓ.ም. ሊገደሉ፣ ንብረቶቻቸው ሁሉ እንደተዘረፉ ይነገራል፡፡ ከተዘረፉት ንብረቶች ውስጥ ደግሞ፣ ንጉሡ አንዳንዴ፣ በበዓላትና ዝግጅቶችን ሲታደሙ ብቻ ያደርጉት የነበረው የእጅ ሰዓታቸው ይገኝበታል፡፡

ሰዓቱ ክርስቲስ እስኪደርስ ከ10 ያላነሱ ሰንሰለቶችን ሊያልፍ ይችላል የሚል ግምት ቢኖርም ከሰንሰለቶቹ የመጀመሪያ የሆነውን ማግኘት አስቸጋሪ እንደሚሆንም መረጃው ያሳያል፡፡ ምክንያቱም እሳቸው ተገድለው ንብረቶቻቸው ሲዘረፍ የነበሩ ሰዎች ካልሆኑ፣ ሰዓቱ በቀላሉ ከአጫራቹ ዘንድ ሊገባ ስለማይችል ነው፡፡

የንጉሡ የወርቅ ሰዓት፣ ንጉሡ በ1946 ዓ.ም. ስዊዘርላንድን በይፋ በጐበኙበት ወቅት በስጦታ የተበረከተላቸው መሆኑንም ዘገባው ያሳያል፡፡   

*      *     *

ማንነት

ሲነጋ… ከቆመ ዕድሜዬ ላይ አንድ ቀን ሲሸረፍ

ልቤ በትዝታ ወዳገሬ ሲከንፍ

‹‹ከድህነቴ ከነመከበሬ

ምነው እግሬን ሰብሮ ባኖረኝ ሀገሬ›› እልና…

ሲነጋ… ወፎቹ ሲንጫጩ

ደርሶ ሲንፎለፎል የተስፋዬ ምንጩ

ሀገሬን ኮንኜ ሳሞግስ ስደቴን

ሳበሸቃቅጠው ያ’ምና ድህነቴን

‹‹ሳልኖር እሞት ነበር…›› እልና በዕለቱ

ሊቀር በማግስቱ

ሌላው ቀን ሲነጋ… ጨለማው ሲበራ

ነፍሴ ስትጨነቅ መግቢያ ተቸግራ

ብቸኝነት ማለት

ባዕድ መሆን ማለት ሲያጋባት ግራ

‹‹ከወገኖቼ ጋር…›› ብዬ እጀምራለሁ

ደግሞ በማግስቱ እቀይረዋለሁ

የትናንቴን ሐሳብ እጠየፈዋለሁ፡፡

እንዲህ ነው ኑሮዬ

በሚዋልል ስሜት… በማይነጥፍ እንባ

መልሶ የሚፈርስ… ደግሞ የሚገባ

እንደዚህ ነኝ እኔ

ርዝቅ ለመሰብሰብ ሰላሜን የበተንኩ

ነገን ለማበጀት ዛሬዬን የበደልኩ

እንደዚህ ነው ስደት… ከወገን መለየት

ሐሳብ ብቻ ሳይሆን

ማንነት ጣት ማታ የሚቀየርበት፡፡

– ብሩክታዊት ጎሳዬ፣ ጾመኛ ፍቅር፣ 2007 ዓ.ም.

*      *     *

የአማሬ ቁና

አመሬዎች የሰሜን ሸዋን፣ የጃማንና ከለላን አካባቢዎች አካልለው በቆላማዎቹ አካባቢ የሚኖሩ ቀደምት ሕዝቦች ናቸው፡፡ አባቶች እንደሚሉት ከለላ ላይ የነበሩት ነዋሪዎች (ቀዳሚዎቹ) በሁለት የሚከፈሉ ናቸው፡፡ አማሬዎችና አበጤዎች፡፡ የአማሬውና የአበጢው ድንበርም የመረቆ ወንዝ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከወንዝ ወዲያ ለሸዋ የሚቀርበው ክፍል አማሬ ከወንዝ ወዲህ ያለው ደግሞ አበጢ መሆኑ ነው፡፡ አማሬዎች ታዲያ የራሳቸው የሆነ ጠየበቀ የማኅበራዊ መተዳደሪያ ደንብ ነበራቸው፡፡ አንዱን ወግነው ሌላኛውን አይበድሉም፡፡ ሲሸመግሉ በደልን የሚመዝኑት ካስቀመጡት ደንብ አንፃር እንጂ ከበዳይ ተበዳይ አንፃር አይደለም፡፡ ከአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ መተዳደሪያ ሕጋቸው ሥራ ላይ እንደዋለ ይነገራል፡፡

የአማሬ ቁና ዘመናዊ የዳኝነት ሥርዓት እንዲህ እንደዛሬው ባልተስፋፋበት ወቅት በተለይ የከለላ፣ የጃማና የሰሜን ሸዋ አካባቢ ሕዝቦች በጋራ ይዳኙበት የነበረ ማኅበራዊ ስምምነት ነው፡፡ ይህ ባህላዊ ሕግ የራሱ የአደረጃጀት ሥርዓት ያለው ሲሆን፣ ይህም ቁና-ሰፊ እና ቁና-ሰጪ በመባል ይታወቃል፡፡ ቁና ሰፊ/ጠቅላላ ጉባኤ ወይም ሕግ አውጪው ደግሞ በቁና ሰፊው አካል የሚወጡ መተዳደሪያ ደንቦችን ለየተወከለበት አካባቢ ማኅበረሰብ በማድረስ ደንቦቹ በሥራ ላይ እንዲውሉ የሚያደርግ አስፈጻሚ እንደማለት ነው፡፡ እነዚህ አካላት የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ናቸው፡፡ የቁና ሰፊዎች የቀጠሮ ቦታቸው ‹‹መርባባ›› የምትባል በበቶ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ አማካይ ቦታ ናት፡፡

በየዓመቱ በህዳር ሚካኤል ማግስት (ህዳር 13 ቀን) ነው መርባባ ላይ የሚገናኙት፡፡ ይህ ዓመታዊ ቀጠሮ ነውና አይታጠፍም፡፡ ሲገናኙ ታዲያ እንዴት ከረማችሁ? ቁናችንስ እንዴት ነው?፣ የነእገሌ ጉማ ተከፈለ ወይ? ወዘተ. በማለት ይጠያየቃሉ፡፡ የሚሰየመው ይህ ባህላዊ ችሎት ከኅዳር 13 ቀን ጀምሮ የያዛቸው አጀንዳዎች እስኪቋጭ ድረስ ለወር ወይም ለሁለት ወር እየቀጠረ ጉዳዮችን ይመረምራል፤ በየአካባቢው ለአሠራርና አተገባበር ያስቸገሩ ደንቦች ካሉ ማሻሻያ ያደርጋል፣ ያልተፈጸሙና ከቁና ሰጭዎች አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ካሉ እያጣራ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ በአጠቃላይ ለሀዘን፣ ለደስታ፣ ለወንጀልና ስውር ደባ ወዘተ. መዳኛና መተዳደሪያ የሚሆን ዝርዝርና ግልጽ ድንጋጌዎች ያወጣል፡፡ ይህ የወጣ ሕግ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊትም የየአካባቢው ኅብረተሰብ እንዲመክርበት በቁና ሰጪዎች አማካይነት ለኅብረተሰቡ እንዲወርድ ይደረጋል፡፡

በአማሬ ቁና መሠረት ከእርቅ ማፍረስ እስከ ደም ማፍሰስና ነፍስ ማሳለፍ ድረስ ጥፋተኛን መዳኘት የሚያስችሉ ያልተጻፉ ነገር ግን ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ አንቀጾች ያሉ ሲሆን፣ የስውር ደባ፣ ስድብ፣ አጥንት ሰብሮ ስድብ፣ ሰንበር፣ ነጭ ደም፣ ጥቁር ደም፣ ባሳ (ግፍ) ወዘተ. በማለት እየተከፋፈሉ እንደ ጥፋት ክብደቱ ቅጣት መጣል የሚያስችሉ ናቸው፡፡ የቅጣት ዓይነቶቹም የገንዘብ፤ የጉልበትና ዓይነት ሲሆኑ አንዳንዴም የገንዘብና ጉልበት አለያም የዓይነትና ጉልበት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የአማሬ ቁና ሰጭዎችን የሚመለምለውና የሚሾመው ማኅረሰቡ ራሱ ሲሆን፣ የአመራረጥ ሒደቱም ቀድመው በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ያሉ አባቶች ከማኅበረሰቡ መካከል የዳኝነት ባህላዊ ሥርዓቱን ለሚደግፉ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተው ነገሮችን በሰከነ ህሊና የሚመዝኑ፣ የማያዳሉና በማኅበረሰቡ ዘንድ ተደማጭነት ያላቸው በሳል ሰዎችን መርጠው ለኅብረተሰቡ በማቅረብና ይሁንታ እንዲሰጣቸው በማድረግ የሚፈጸም ነው፡፡ የአማሬ ቁና ሰፊዎች ችሎት ህዳር ታጥኖ መርባባ ላይ እስከሚገናኝ ድረስ የየአካባቢው ተወካዮች እያስተዳደሩ የሚቆዩ ሲሆን፣ ከእነሱ አቅም በላይ የሆነ ነገር ከገጠማቸው ደግሞ የመራባባውና ዓመታዊ ችሎት መጠበቅ ሳይገባ የቁና- ዳኞች ጉዳዩን አይተው ውሳኔ እንዲሰጡበት ይደረጋል፡፡ ከዚህ በላይ ከሆነ ግን የመርባባን ችሎት መጠበቅ ግድ ይሆናል፡፡ የአማሬ ባህላዊ መተዳደሪያ ቁና በብዙ መልኩ ከዘመናዊ ሕግጋት ጋር የተጣጣመና አሁንም ድረስ እየተሠራበት ያለ ነው፡፡

  • የከለላ ወረዳ አስ/ም/ቤትና መንግሥት ኮሚዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ጽ/ቤት ማህደረ ከለላ፣ 2007 ዓ.ም.   

*******************

የሕልም ፍቺ በሥነልቦና ባለሙያ

በርካታ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ህልም ለመፍታት ብዙ ቢጥሩም በጥረታቸው ሊቀጥሉ አልወደዱም፡፡ የዘ ኢንዲፔንደንት ያለፈው ሳምንት ዘገባ ግን፣ አንድ የሥነልቦና ባለሙያ ለ30 ዓመታት ያህል 150,000 ሕልሞችን መፍታቱን ያመለክታል፡፡ የሥነልቦና ባለሙያው፣ ዘጠኝ በተደጋጋሚ የሚታዩ ሕልሞችን ዝርዝር ከነትርጉማቸው አስቀምጧል፡፡

ትርጉማቸውን ብቻም ሳይሆን እነዚህን ሕልሞች ሲያዩ ሰዎች ምን ዓይነት ዕርምጃ መውሰድ እንዳለባቸውም ጭምር የሥነልቦና ባለሙያው ተናግሯል፡፡

እንደ ሥነልቦና ባለሙያው ኢያን ዋላስ የህልም ፍች፤ በሕልም አገልግሎት ላይ ያልዋለ ክፍል ማግኘት፣ የማያውቁት ተሰጥኦ አለ ማለት ነው፡፡ የሚያሽከረክሩት መኪና ከቁጥጥር ውጭ መሆን ደግሞ ወደሚፈልጉት ግብ እየገሰገሱ መሆንን ያመለክታል፡፡ በሕልም መውደቅ የትኩረትና የኃይል በአንዳች ነገር ክፉኛ መያዝን እንደሚያሳይ ሕልም ፈቺው የሥነልቦና ባለሙያ ይናገራሉ፡፡

እንደ ሥነልቦና ባለሙያው፣ መብረር ከፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ማምለጥ ሲሆን፣ ፈተና ላይ ለመቀመጥ ዝግጁ አለመሆን ደግሞ በገሀዱ ዓለም ለፈተና ያለን ዝግጅነት እየመዘኑ መሆንን የሚያሳይ ነው፡፡ እራቁት ሆኖ መመልከት በገሀዱ ዓለም አለመመቸት መኖሩን፣ መፀዳጃ ቤት ማግኘት አለመቻል ሊገልጹት ያልቻሉት ፍላጐት መኖርን፣ የጥርስ መውለቅ ደግሞ በራስ መተማመንንና ጥንካሬ እየተሸረሸረ መሆኑን፣ በአንዳች አውሬ መወሰድ ደግሞ ሊጋፈጡት የሚፈልጉት የሕይወት ፈተና መኖርን ያመለክታል፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች