Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የንብረት ማዘዋወር ሥራ ሕዝቡ እስኪለምደው ዋጋ ያስከፍለኛል››

‹‹የንብረት ማዘዋወር ሥራ ሕዝቡ እስኪለምደው ዋጋ ያስከፍለኛል››

ቀን:

ወ/ሪት ሰላም ተስፋዬ፣ የሻሎም ሐውስ ኤንድ ኦፊስ ሙቨር ባለቤት

አብዛኞቹ ጓደኞቿ የዕድሜ እኩዮቿ አይደሉም፡፡ በአሥር ዓመትና ከዚያ በላይ ይበልጧታል፡፡ በሙያም ሆነ በዕውቀት ከእሷ የላቁ መሆናቸውን ትናገራለች፡፡ ይህ የሆነው እንዲያው በአጋጣሚ አልነበረም፡፡ ‹‹ከሚበልጡኝ ጋር ስውል እማራለሁ›› የሚል እምነት ስላላት ምርጫዎቿ ሆነው እንጂ፡፡ ብዙ ነገሮችን ትሞክራለች፡፡ ለነገሮች ያላት ቀና አመለካከትም አጋጣሚዎችን ወደ ሥራና ገንዘብ ለመቀየር እንድትሞክር አስችሏታል፡፡

የ25 ዓመቷ ወ/ሪት ሰላም ተስፋዬ፣ የተወለደችው ከአዲስ አበባ 480 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምተገኘው በደሌ ከተማ ነው፡፡ ወላጅ አባቷ የመንግሥት ሠራተኛ ነበሩ፡፡ እናቷ ደግሞ ነጋዴ፡፡ በጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ቤተሰቦቿ ሰላም ብቸኛ ልጅ ነች፡፡ እስከ 13 ዓመቷ ድረስ በደሌ ቆይታለች፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷንም እዚያው በደሌ አጠናቅቃለች፡፡ ቤተሰቦቿ በሥራ ምክንያት ወደ ጅማ በመዘዋወራቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በጅማ ነው፡፡ በትምህርት ቀዳሚ ከሆኑት ጐራ የምትመደበው ወጣቷ፣ በ2001 ዓ.ም. በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን መማር ጀመረች፡፡ በማታው ክፍለ ጊዜ ደግሞ በዲፕሎማ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ትማራለች፡፡ ይህ ለብዙዎች ከባድ መስሎ ቢታይም፣ ሰላም አልከበዳትም፡፡ በሌላ ተጨማሪ የትምህርት ዘርፍ መማር ጀመረች፡፡ ‹‹ከሁለቱ ጐን ለጐን ነርሲንግ መማር ጀመርኩ፡፡ ብዙዎች ይከብዳል ብለው ቢያስቡም በወቅቱ የተሻለ እሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን እስከ ሁለተኛ ዓመት ድረስ ከተማርኩ በኋላ ፈተና እንዲሁም የትምህርት ክፍለ ጊዜ ይደራረብብኝ ስለነበር ማገባደድ አልቻልኩም፡፡ በመሆኑም የነርሲንግ ትምህርቴን ማቆም ነበረብኝ፤›› በማለት ለትምህርቱ የነበራትን ከፍተኛ ፍላጐት ታስታውሳለች፡፡

ለቤተሰቧ ብቸኛ ልጅ የሆነችው ሰላም አንዳንድ የቤት ውስጥ ኃላፊነት ይጣልባት ነበር፡፡ ለቤት ውስጥ ወጪ የተሰጣትን ገንዘብ ቦታ ቦታ ማስያዝ፣ የጎደሉ ነገሮችን አይቶ ማሟላት ተቀዳሚ ተግባሮቿ ነበሩ፡፡ ይህም ኃላፊነት መወጣት እንድትችል ረድቷታል፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ራሷን ለመቻል እንደምትጣጣርና ለንግድ ልዩ ፍቅር እንደነበራት ትናገራለች፡፡ ፍላጐቷን ‹‹ትምህርቴን ሳገባድድ እጀምራለሁ›› ብላ በቀነ ቀጠሮ አላቆየችውም፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለች በሚኖራት የሴሚስተርና የክረምት ዕረፍት አዲስ አበባ በመምጣት ትነግዳለች፡፡ ከባህር ማዶ የሚመጡ የተለያዩ አልባሳትንና ልዩ ልዩ ኤሌክትሮኒክሶችን ትሸጥ ነበር፡፡ በቀን እስከ 1,000 ብር ድረስ ታገኝም ነበር፡፡ የዕረፍት ጊዜዋ ሲጠናቀቅም ወደ ትምህርቷ ትመለሳለች፡፡ ሠርታ ያገኘችውን ገንዘብ ለነገ ሥራዋ መነሻ ይሆናት ዘንድ ታስቀምጣለች፡፡

ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ የንግድ ሥራዋን ለማጠናከር አዲስ አበባ መጣች፡፡ በተለመደ ሥራዋ ብተቀጥልም የተሻለ መሥራት እንዳለባት ተሰማት፡፡ በመሆኑም ከቅርብ ዘመዷ ጋር የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስችላቸውን ፈቃድ አውጥተው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ጀመሩ፡፡ በመካከል ግን ያላሰበችው ችግር አጋጠማት፡፡ ለሥራው ማስኬጃ 300,000 ብር አብሯት በሚሠራው ዘመዷ የባንክ ደብተር ካስገባች በኋላ የዘመዷ ደብዛ ጠፋ፡፡ ድንገተኛ ችግር ገጥሞት ይሆናል በማለት ታግሳ ብትጠብቀውም የውኃ ሽታ ሆኖ እንደቀረ ትገልጻለች፡፡

በወቅቱ ልትገልጸው የማትፈልገው የሕይወት ገጠመኝ አጋጥሟትም ነበር፡፡ ተደራራቢ ችግር ሐዘኗን አክብዶት ነበር፡፡ በእጇ ይህ ነው የሚባል ገንዘብ አልነበረም፡፡ ‹‹ካለሁበት ጓደኛዬ ጋር ለመድረስ የሚያስፈልገኝ 12 ብር ለታክሲ አጥቼ ተቸገርኩኝ፤›› የምትለው ሰላም፣ሰ የቤተሰብ ዕርዳታ አልጠየቀችም፡፡ ሁሉንም በሆዷ ይዛ በቅርበት የምታውቃት ጓደኛዋ ዘንድ መኖር ጀመረች፡፡ በዚህ ትንሽ ብትጽናናም ሊያዛልቃት አልቻለም፡፡ ጓደኛዋ የውጭ ዕድል አግኝታ ሄደች፡፡

ሁኔታውን የሰማ ሌላ የቅርብ ዘመዷም ወደ ቤቱ ወሰዳት፡፡ ወደ ቀድሞው ሁኔታዋ እስክትመለስ ልዩ ልዩ ዕርዳታዎች እየተደረጉላት ስድስት ወራት ቆየች፡፡

ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ እንደ ቀድሞዋ ባትሆንም ራሷን ለመቻል የመጀመሪያ ሙከራ አደረገች፡፡ በአንድ ድርጅት ውስጥ ተወዳድራ በሰው ኃይል አስተዳደርነት ተቀጠረች፡፡ ለሙያው አዲስ እንደመሆኗ የሚያደናግሯት ነገሮች ነበሩ፡፡ ይህንንም አባቷን እያማከረች ትሠራ ጀመር፡፡ በመሥሪያ ቤቱ የተመሰገነች ወጣት ሠራተኛ ሆነች፡፡ በዚህ መልኩ ለወራት ካገለገለች በኋላ የተለየ የሥራ ሐሳብ መጣላት፡፡

ቤት ተከራይቶ ይኖር የነበረ ከባህር ማዶ የመጣ ጓደኛዋ ነበር፡፡ ይኖርበት የነበረው ቤቱ ብዙም ስላልተመቸው ሌላ መፈለግ ነበረበት፡፡ የሚፈልገውን ዓይነት ቤትም ፈልጐ አገኘ፡፡ ክፍያውንም ፈጸመ፡፡ ነገር ግን ከነበረው የተጨናነቀ ጊዜ አንፃር ነገ ዛሬ ሲል ቤቱ ሰይገባ ወር አለፈው፡፡ ለሁለቱም ቤቶች የወር ኪራይ መክፈልም ግድ ሆነበት፡፡ ‹‹በሆነ ተዓምር ከዚህ ንቅል አድርጎ አዲሱ ቤቴ የሚያስገባኝ ነገር ቢኖር›› በማለት ምኞቱን ይገልጻል፡፡ ችግሩን ያጤነችው ሰላም ግን ሌላ የሥራ ጥሪ አድርጋ ተቀበለችው፡፡ ‹‹እኔ ልሥራልህ አልኩት፡፡ ሳቀብኝ አላመነኝም፡፡ እኔ ግን ማሰላሰሌን ቀጠልኩ፡፡ ከተለያየን በኋላም ቤት ገብቼ መቼ መልቀቅ እንደሚፈልግ ጠየቅኩት፡፡ ‹ዛሬስ ቢሆን› የሚል ምላሽ ሰጠኝ፤›› በማለት ለመጀመሪያ ዕቃ ወደ ማዘዋወር ሥራ የገባችበትን አጋጣሚ ታስታውሳለች፡፡

በጅምሯ ብዙም አልተከፋችም፡፡ ጓደኛዋ ይኖር የነበረው ጃክሮስ አካባቢ ሲሆን፣ አዲስ ተከራይቶ የነበረው ቤት ደግሞ ሲኤምሲ አካባቢ ነበር፡፡ ዕቃ ለማሸግ የሚያስፈልጉ ካርቶኖችን ያዘጋጀው እሱ ነበር፡፡ መኪና ተከራይታ ጫኝና አውራጆች ቀጥራ ዕቃውን አዘዋወረችለት፡፡ 1,400 ብርም ተከፈላት፡፡ ለሠራተኞችና ለመኪና ኪራይ ስታከፋፍል የተረፋት ገንዘብ አልነበረም፡፡ ልምዱ ግን ጠቀማት፡፡ መደበኛ ሥራዋ አድርጋ ለመሥራትም አወጣች አወረደች፡፡ ጉዳዩንም ለወላጅ አባቷ አማከረች፡፡ እሳቸውም ጊዜ ወስዳ እንድታስብበት አሳሰቧት፡፡ ‹‹በባህሪዬ የሆነ ነገር ካሰብኩ ጊዜ አልወስድም፡፡ ወዲያው እተገብረዋለሁ፤›› የምትለው ወጣቷ፣ ለምትሠራበት መሥሪያ ቤት የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገባች፡፡ ውሳኔዋ ብዙዎችን ያስገረመ ቢሆንም ሐሳቧን የሰሙ አበረታትተዋታል፡፡

አንዳንድ ቤት አግኝተው ዕቃ ማጓጓዝ ችግር የሆነባቸው ጓደኞቿ ለሰላም አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ፈቃድ አግኝታ በሰፊው ወደ ገበያው ለመግባት ግን ከባድ ነበር፡፡ ‹‹ዘርፉ የሚታወቅ አይደለም፡፡ በመሆኑም ከምን ዘርፍ እንደሚመደብ ለይቶ የማውጣት ኃላፊነት ነበረብኝ፡፡ ሕግጋቶችን አገላብጫለሁ፡፡ በተጨማሪም በመድህን የዋስትና ሽፋን መካተት ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎቹ የዋስትና ድርጅቶች ጥያቄ ሳቀርብላቸው ይደናገራሉ፡፡ እንመካከርበት በሚልም ይመልሱኛል፤›› ስትል ፈቃድ አውጥቶ ለመንቀሳቀስ ወራት እንደፈጀባት ታስታውሳለች፡፡ በእነዚህ ወራት ግን ይህ ነው የምትለው ቋሚ ገቢ አልነበራትም፡፡ አልፎ አልፎ ዕቃ አዘዋውራ የሚከፈላት ገንዘብ ከቀለብና ከቤት ኪራይ ተርፎ የምትቆጥበው አልነበረም፡፡

የኋላ ኋላ ግን ሁሉም ነገር ተሳክቶላት ከጥቂት ወራት በፊት ሻሎም ሐውስ ኤንድ ኦፊስ ሙቨር የተሰኘ ድርጅቷን ቦሌ ብራስ አካባቢ ከፈተች፡፡ ድርጅቱ ንብረት ከአንዱ ቤት ወደ ሌላ ከማዘዋወር ባሻገር ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ይሰጣል፡፡ የፅዳት፣ ቤትና ቢሮ የማስዋብ፣ መጫንና ማውረድና የቤት ውስጥ ማስዋብ ዲዛይን ድርጅቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ናቸው፡፡

ለምትሰጣቸው አገልግሎት ክፍያውን በተመለከተም እስካሁን ያወጣችው ቋሚ የዋጋ ተመን የለም፡፡ ሒሳብ የምትደራደረውም ቤቱ ካለው ስፋት አንፃር ነው፡፡ በተጨማሪ ልዩ ጥንቃቄ የሚያሻቸውን ዶክመንቶች፣ ካዝናና የመሳሰሉትን ነገሮች ለማዘዋወር ተጨማሪ ክፍያ ትጠይቃለች፡፡ በእስካሁን ቆይታዋ ሥራው ብዙም የተለመደ ባለመሆኑ አገልግሎቱን አምነው የሚጠቀሙ በጣም ጥቂት እንደሆኑ ትናገራለች፡፡ ‹‹ብዙዎቹ ስነግራቸው ሐሳቡን ቢወዱም ለመጠቀም ያቅማማሉ፤›› በማለት ያሰበችውን ያህል መሥራት እንዳልቻለች ትገልጻለች፡፡ ዕቃ ጭና ካንዱ ወደ ሌላው ቤት በምታዘዋውርበት ጊዜም በተለይ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ ‹‹ጫኝና አውራጅ እኛ ነን›› ብለው የሚከራከሯት መኖራቸውም ከሚገጥሟት ችግሮች መካከል ናቸው፡፡

ዋጋው የብዙኃኑን አቅም ያገናዘበ ነው የምትለው ሰላም፣ በእስካሁን ቆይታዋ ከ3,000 ብር እስከ 15,000 ብር ድረስ ተከፍሏት እንደሠራች ትናገራለች፡፡ ‹‹የንብረት ማዘዋወር ሥራ ሕዝቡ እስኪለምደው ዋጋ ያስከፍለኛል፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ በሁለት እግሩ እስኪቆም፣ የሚደግፉትን ሥራዎች ጐን ለጐን እሠራለሁ፡፡ ከቀናት በፊትም ቦሌ አካባቢ ሻይ ቡና መሥራት ጀምሬያለሁ፤›› በማለት ጥረቷን ትገልጻለች፡፡                    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...