ተዋናይት ወይንሸት በላቸውና ድምፃዊት እናኑ ደጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ካፈራቸው በርካታ አንጋፋ ባለሙያዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሁለቱም ቴአትር ቤቱን የተቀላቀሉት በወጣትነታቸው ሲሆን፣ ከረዥም ዓመታት አገልግሎት በኋላ ጡረታ ወጥተዋል፡፡ በዚህ ሳምንት እየተከበረ ያለውን የቴአትር ቤቱን 60ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአንድ ወቅት ዘወትር ከማይጠፉበት ግቢ ዳግም ተገኝተዋል፡፡ አይረሴ ትውስታዎቻቸውንም አካፍለውናል፡፡
ላስታ ላሊበላ የተወለዱት የ64 ዓመቷ ድምፃዊት ከልጅነታቸው ጀምሮ በትውልድ ቀዬአቸው የታወቁ ዘፋኝ ነበሩ፡፡ እንጨት ሲለቅሙ፣ ሠርጎች ላይም ያንጎራጉራሉ፡፡ በወጣትነታቸው ሙዚቃ ከሚወድ የአገራቸው ልጅ ጋር መገናኘታቸው ሕይወታቸውን ለውጦታል፡፡ ወጣቱ አብረው እየተዘዋወሩ እንዲዘፍኑ ይጠይቃቸዋል፡፡ በወቅቱ ዘፋኝ አዝማሪ እየተባለ ይናቅ ነበር፡፡ እሳቸውም ሰው ምን ይለኛል ብለው ቢፈሩም የሙዚቃ ፍቅራቸው አሸንፏቸው ጥያቄውን ተቀበሉት፡፡
የሰውን አስተያየት በመፍራት ከትውልድ ቀዬአቸው ርቀው መዝፈን ጀመሩ፡፡ በ1967 ዓ.ም. አገር ፍቅር ቴአትር ለመመዝገብ በብሔራዊ ቴአትር በኩል ሲያልፉ ያያቸው አንድ የቴአትር ቤቱ ባለሙያ ጠርቷቸው ጎራ አሉ፡፡ ድምፃዊ መሆን እንደሚፈልጉ ሲነግሩት እንዲፈተኑ ዕድል ሰጣቸው፡፡
ታደለ ታምራት፣ አውላቸው ደጀኔና ሌሎችም ባለሙያዎች ፊት አምባሰልና ባቲን ተጫወቱ፡፡ የሽሽግ ቸኮልና አሰፋ አባተን ዘፈኖችም አቀረቡ፡፡ ከቀናት በኋላ መቀጠር አለመቀጠራቸው እንዲወሰን ሃይማኖት ዓለሙና ፀጋዬ ገብረመድኅን ፊት ቀረቡ፡፡ ሲዘፍኑ ከመድረክ ጀርባ ይመለከቷቸው የነበሩ አልማዝ ኃይሌ፣ አስናቀች ወርቁና ሌሎችም ባለሙያዎች ያበረታቷቸው እንደነበር ያስታውላሉ፡፡ በስተመጨረሻም ብቁ ሆነው ስለተገኙ በ75 ብር ደመወዝ ከተቀጠሩ በኋላ ለ35 ዓመታት በቴአትር ቤቱ ሠርተዋል፡፡
ከአዕምሯቸው የማይጠፋው በ1971 ዓ.ም. የነበው መልሶ ማቋቋም ነው፡፡ መቱ፣ ምፅዋ፣ ኦጋዴን፣ ጅግጅጋ፣ ቀይ ባህርና አሰብ ሥራዎቻቸውን ለማሳየት ከተዘዋወሩባቸው አካባቢዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የወቅቱን ፉከራና ሽለላቸውን ሲያስታውሱ በወኔ ተሞልተው ነው፡፡ ለማ ገብረሕይወት፣ አበበ ተሰማና ሌሎችም የቴአትር ቤቱ አንጋፋ ባለሙያዎች ከሕዝቡ የሚያገኙትን ደማቅ አቀባበል ሲያስታውሱም በሀሴት ይሞላሉ፡፡ ዛሬ በሙያው ውስጥ ባይሆኑም ከሦስቱ ልጆቻቸው አንዷ የሳቸውን ፈለግ መከተሏ ያኮራቸዋል፡፡
እናኑ ቴአትር ቤቱ 60ኛ ዓመቱን ሲያከብር ለመመልከት በመብቃታቸው መደሰታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በ1959 ዓ.ም. ቴአትር ቤቱን ተቀላቅለው ለ33 ዓመት በቴአትር ቤቱ ያገለገሉት ተዋናይቷ ወይንሸትም ሐሳባቸውን ይጋራሉ፡፡ መስተካከል አለባቸው የሚሉትንም አካፍለውናል፡፡
71ኛ ዓመታቸውን የያዙት ተዋናይቷ አሁን ፊልሞችና የቴሌቪዥን ድራማዎች ይሠራሉ፡፡ ቴአትር ቤቱን የተቀላቀሉት በባህላዊ ተወዛዋዥነት ሲሆን፣ ኋላ ወደ ተውኔት ተሸጋግረዋል፡፡ ‹‹የከተማው ባላገር››፣ ‹‹ውድቅት››፣ ‹‹የባላገር ፍቅር›› እና ‹‹ቀዝቃዛ ወላፈን›› ከተወኑባቸው ቴአትሮች ጥቂቱ ናቸው፡፡ ‹‹ለሙያው የነበረን ፍቅር በቃላት አይገለፅም፤ መረዳዳታችንና መዋደዳችንን ሁሌም አስታውሰዋለሁ፤›› ይላሉ፡፡ ባህላዊ ውዝዋዜዎችን ሲያዘጋጁ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ያጠኑ ነበር፡፡ ከባህላዊ ውዝዋዜ ቡድን ጋር በኢትዮጵያ ውስጥና ውጪም ተዘዋውረው ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ተዋናይቷ እንደሚሉት፣ አሁን የባህላዊ ውዝዋዜ ትዕይንቶች እንደቀደመው ጊዜ ጠንካራ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ባህላዊ ውዝዋዜ ከዘመናዊው ሲዋሀድ እንደሚስተዋልና አካሄዱ ተስተካክሎ ቱባ ባህልን ማንፀባረቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በዓሉን አክብሮ መለያየት ሳይሆን ለውጥ የሚያሻቸው ነገሮች ተለይተው ሊሠራባቸው ይገባል፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡
እናኑና ወይንሸት ቴአትር ቤቱ በ60ኛ ዓመቱ ከሚዘክራቸው ባለሙያዎች መካከል ናቸው፡፡ የቴአትር ቤቱን ያለፈ ታሪክ ከማውሳት ጎን ለጎን የወደፊት አቅጣጫዎቹን ለማመላከት ያግዛሉ የተባሉ መርሀ ግብሮች ተካሒደዋል፡፡ በዚህ ተሳታፊ ከሆኑ ውስጥ አሁን በቴአትር ቤቱ በሥራ ላይ ያሉ ባለሙያዎች ሳሙኤል ተስፋዬና ኩስያ ጦሎንጌ ይገኙበታል፡፡
ሳሙኤል ቴአትር ቤቱን ከተቀላቀለ ሦስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ የቴአትር ጥበብ ምዘና፣ እነጻና ሥልጠና ከፍተኛ ባለሙያ ሲሆን፣ የቴአትር ቤቱን 60ኛ ዓመት በማስመልከት ወደ መድረክ የተመለሰው ‹‹ሐምሌት››ን አዘጋጅቷል፡፡ ቴአትር ቤቱ ከተቆረቆረበት ጊዜ ጀምሮ የተሠሩና በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉ አራት ቴአትሮች ተመርጠው ቅንጫቢአቸው ይቀርባል፡፡ ቴአትሮቹ በቴአትር ቤቱ የመጀመርያው ቴአትር ‹‹ዳዊትና ኦርዮን››፣ ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ በደርግ ዘመነ መንግሥት የታየው ‹‹ተሀድሶ››፣ ‹‹ሀምሌት›› እና አሁን እየታየ ያለው ‹‹የቃቄ ውርደወት›› ናቸው፡፡ ቴአትር ቤቱ ያለፈባቸውን ዘመናት የሚያሳዩና አይረሴ ሥራዎች መመረጣቸውን ሳሙኤል ይናገራል፡፡ በዓሉን በማስመልከት በድጋሚ የቀረቡት ሥራዎች ወጣቱን ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሱ እንደሚሆኑም ያምናል፡፡
አሁን የሚሠሩ ቴአትሮችን በርዕሰ ጉዳይ ጥልቀት ከቀደሙት ጋር የሚያነፃፅሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ እሱ በኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ ገናና የነበሩ ቴአትሮች ዳግም መድረክ ማግኘታቸው ለወጣቱ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ይናገራል፡፡ ‹‹ዘመን የማይሽራቸው ተውኔቶች በየጊዜው መታየት አለባቸው፡፡ አዳዲስ ሥራዎች የተሻሉ እንዲሆኑ ያግዛሉ፤›› ይላል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ ብሔራዊ የሚለውን ስያሜ እንደመያዙ ልዩ ልዩ ይዘት ያላቸው ቴአትሮችን ማስተናገድ አለበት፡፡ የቴአትር ቤቱ ሥራዎች የአገሪቱ ኪነ ጥበብ የደረሰበትን ደረጃ በሚያሳይ መጠን እንዲሠሩ በማሳሰብም፣ ቴአትር ቤቱ ታላላቅ ሥራዎች የሚቀርቡበት የልቀት ማዕከል መሆን እንዳለበት ይገልጻል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የቴአትር ቤቱ ባለሙያ ኩስያ ናቸው፡፡ በደቦ፣ በሠርግ፣ በአደንና ሌሎችም ክንውኖች በኮንሶና ደራሼ የሚዘወተሩ ባህላዊ ጨዋታዎችን በማዘጋጀት ይታወቃሉ፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥት ቴአትር ቤቱን ከተቀላቀሉበት ጊዜ ጀምሮ ከ30 በላይ ሥራዎች አሰናድተዋል፡፡
በእሳቸው ጊዜና ከዛም በፊት የነበሩ አንጋፋ ባለሙያዎች የደከሙበትን መድረክ የሚረከበው ትውልድ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደተጣለበት ይናገራሉ፡፡ ቴአትር ቤቱ አገሪቱ ባለፈችባቸው አንኳር ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች የተካፈሉ ባለሙያዎችን አፍርቷል፡፡ እንደ ረሀብና ጦርነት ያሉ፣ በተቃራኒውም አስደሳች ነገሮች ሲከሰቱ ቀድመው የሚገኙትም እኚሁ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ እሳቸውም ‹‹ብሔራዊ ቴአትር በአገሪቱ ታሪክ ጉልህ ድርሻ አለው፤ ኪነ ጥበብ ከሕዝብ ወጥቶ መልሶ ሕዝብን የሚያገለግል መሆኑን ወጣቶች ተገንዝበው ጠንክረው መሥራት አለባቸው፤›› ይላሉ፡፡ በቴአትር ቤቱ የሚዘጋጁ ቴአትሮች፣ ሙዚቃዎችና ሌሎችም የኪነ-ጥበብ ሥራዎች አገሪቷና ሕዝቡ ከሚገኝበት ደረጃ ጋር የተመጣጠኑ መሆን እንደሚገባቸው ገልጸው፣ ‹‹የአገር ዕድገት ሲባል ጥበብንም ያማከለ መሆን አለበት፤›› ይላሉ፡፡
በ1948 ዓ.ም. ሥራውን የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለዓመታት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት በሚል ይጠራ ነበር፡፡ የተገነባው ጣሊያን ሲኒማ ማርኮኒ በሚል ስም መሥራት በጀመረው አዳራሽ ቦታ ነው፡፡ ከቴአትር ቤቱ አስቀድሞ ሥራ በጀመረው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የቴአትርና ሙዚቃ ማስፋፊያ ክፍል የነበሩ ባለሙያዎች ተወዳጅነት አትርፈው፣ የሕዝቡ የቴአትርና ሙዚቃ ፍላጎት ሲያድግ ዘመናዊ አዳራሽ ለመገንባት ዕቅድ ወጣ፡፡
ግንባታው ከተጀመረ በኋላ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ስለደረሰ ሥራው እንዲፋጠን ሆነ፡፡ ቴአትር ቤቱ በተመረቀበት ዕለት የታየው በመኰንን እንዳልካቸው የተጻፈው ‹‹ዳዊትና ኦርዮን›› ሲሆን፣ ላለፉት ስድስት አሠርታት በርካታ ተጠቃሽ ሥራዎች በቴአትር ቤቱ ቀርበዋል፡፡
በእነዚህ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ሲምፖዝየም በቴአትር ቤቱ ተካሒዷል፡፡ በሲምፖዝየሙ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ ጥናቶቹ ቴአትር ቤቱ ከተቆረቆረበት ጊዜ ጀምሮ ባሉ ዘመናት የነበሩ ጥበባዊ ሥራዎችን ዳሰዋል፡፡ የመጀመርያው ‹‹ቴአትር እንደ ትግል መድረክ፤ የብሔራዊ ቴአትር ፈተናና አበርክቶ›› የሚለው የሱራፌል ወንድሙ ጥናት ነው፡፡
ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ ከቴአትር ቤቱ ምስረታ በኋላ ባሉ ዓመታት ንጉሡ ቴአትሮች በመመልከት፣ ሥራዎችን በመተቸትም ይሳተፉ ነበር፡፡ በመጀመርያ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው እንደ ‹‹ማንም ሰው››፣ ‹‹ልደት››፣ ‹‹ሚስጥረ ቅዳሴ››ን የመሰሉ ሥራዎች ይቀርቡ ነበር፡፡ አስከትሎም የአርበኝነት ስሜት ያላቸው ‹‹ቴዎድሮስ››፣ ‹‹አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም›› እና ሌሎችም ተሠርተዋል፡፡
ማኅበረሰቡን ተቺ የሆኑ ቴአትሮች መሠራት የጀመሩት ከ1950ዎቹ ጀምሮ ሲሆን፣ የፀጋዬ ገብረመድህን ቴአትር ቤቱን መቀላቀል ተያይዞ ይነሳል፡፡ ‹‹አወናባጅ ደብተራ››፣ ‹‹ክራር ሲከር›› እና ሌሎችም ሥራዎች የቀረቡበትም ጊዜ ነው፡፡ የቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች በአብዮቱ ወቅቱ የነበራቸውን ሚና እነ ‹‹እናት ዓለም ጠኑ›› እና ‹‹ሀሁ በስድስት ወር›› ቴአትሮችን በማንሳት ጥናቱ ይዳሰሳል፡፡
ሌላው ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሙዚቃ ክፍል ከትናንት እስከ ዛሬ›› የተሰኘው የሠርፀ ፍሬስብሀት ጥናት ነው፡፡ ቴአትር ቤቱ በተቆረቆረበት ጊዜ ከማዘጋጃ ቤት የሄዱት አንጋፋ ሙዚቀኞች ሙሴ ነርሲስ ናርባልዲያን፣ መርአዊ ስጦት፣ ጌታቸው መኩሪያና ሌሎችም መሠረት የጣሉ ናቸው፡፡
የቴአትር ቤቱን ምርቃት የታደሙ በርካታ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ ዘገባቸውን ተከትሎም በርካታ ዓለም አቀፍ ሙዚቀኞች በቴአትር ቤቱ ሙዚቃዎቻቸውን ለማቅረብ ጉጉት ነበራቸው፡፡ ከአሜሪካና ፈረንሳይ የመጡ ዕውቅ ሙዚቀኞች ሥራዎቻቸውን ማቅረብ ከቻሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በ1951 ዓ.ም. የአገረሰብ ሙዚቃ ቡድን ተመሠረተ፡፡ በቴአትር ቤቱ ከቀረቡ ሙዚቃዊ ድራማዎች ‹‹ሀኒባል››ና ‹‹አስቴር›› ይገኙበታል፡፡ የደርግ ዘመን የኪነት ሥራዎች የተነሳሱበት ነው፡፡ ‹‹ወሎ ላሊበላ››፣ ‹‹ጊሽ ዓባይ››ና ‹‹ፋሲለደስ››ን የመሰሉ የኪነት ቡድኖች በቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች የተቋቋሙ ናቸው፡፡ በሙዚቃው ተጠቃሽ የሆኑ እንደ ሐመልማል አባተ፣ በዛወርቅ አስፋው፣ መልካሙ ተበጀና ዓለማየሁ እሸቴን የመሰሉ ድምፃውያንም ከቴአትር ቤቱ ወጥተዋል፡፡
ጥናቱ በኢሕአዴግ ሥርዓት ለማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቶ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን የመዘንጋት ነገር እንደመጣ ያሳያል፡፡ የቴአትር ቤቱን የቀደመ ክብር ለመመለስ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች ቢደረጉም ምን ያህል ተሳክቷል የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡ በጥናቶቹ ብሔራዊ ቴአትር በኪነ ጥበቡ ያለው ቦታና የተሰጠው ክብር ምን ያህል ነው የሚሉ ጥያቄዎችም ተሠንዝረዋል፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡን የቴአትር ቤቱ የቀድሞና የአሁን ባለሙያዎችም ጥያቄዎቹን ያነሳሉ፡፡ የቴአትር ቤቱ ቀጣይ ዓመታት የላቁ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች የሚቀርቡባቸው እንዲሆኑ የሚያሳስብ ክብረ በዓል መሆን እንዳለበትም ያስረዳሉ፡፡