– ዓባይና ኢትዮ ባስ ወደ ሥራ ገቡ
በኢትዮጵያ የአገር አቋራጭ የትራንስፖርት ዘርፍ በልዩ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ ከተፈቀደላቸውና አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙ ሦስት የትራንስፖርት ድርጅቶች በተጨማሪ ዓባይና ኢትዮ ባስ የተባሉ ኩባንያዎች ወደ ሥራ ገቡ፡፡ ተጨማሪ 40 ዘመናዊ አውቶቡሶችን ለማስገባት መዘጋጀታቸውም ተገለጸ፡፡
እህትማማች ኩባንያዎች መሆናቸው የተጠቆሙት ሁለቱ ኩባንያዎች ከተቋቋሙ ከአንድ ዓመት በላይ ቢሆናቸውም፣ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎቻቸውን ለማስገባት ባጋጠማቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት እስካሁን ወደ ሥራ ያሰማሯቸው አውቶቡሶች አምስት ናቸው፡፡ ዓባይ ባስ ሦስት፣ ኢትዮ ባስ ደግሞ ሁለት ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን ይዘው ሥራ ማስጀመራቸው ታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓባይ ባስ ስያሜ አገልግሎት ለመስጠት አምስት ተጨማሪ አውቶቡሶች ወደብ የደረሱ ሲሆን፣ እነዚህ አዳዲሶቹ አውቶቡሶችም በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮ ባስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘለቀ በላይ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የአገር አቋራጭ የትራንስፖርት ዘርፍ ልዩ ፈቃድ ተሰጥቷቸው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ሰላም ባስ፣ ስካይ ባስና ሊማሊሞ ባስ ናቸው፡፡
ዓባይና ኢትዮ ባስ የተባሉት እህትማማች ኩባንያዎች ወደ ሥራ የገቡበት ተሽከርካሪ ዩቶንግ የተባለ ዘመናዊ የሕዝብ ማመላለሻ ሲሆን፣ ሃምቢድ ትሬዲንግ በተባለው የዩቶንግ ወኪል በኩል ነው ያስገቡት፡፡
ኢትዮ ባስ በአሥር ባለአክሲዮኖች የተቋቋመ ሲሆን፣ የ100 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ወጪ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ ዓባይ ባስም በተመሳሳይ የ75 ሚሊዮን ብር ካፒታል ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ የሚኝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ዓባይ ባስ የአውቶቡሶችን ቁጥር በ2008 በጀት ዓመት 20 ለማድረስ የወጠነ ሲሆን፣ ኢትዮ ባስም አሁን ያሉትን አውቶቡሶች ጨምሮ በበጀት ዓመቱ የአውቶቡሶችን ቁጥር 30 እንደሚያደርስ ተገልጿል፡፡ ይህን ውጥኑን ዳር የሚደርሰው ግን ያጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲቀረፍላት ብቻ ነው ተብሏል፡፡
ዘመናዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ አሠራሮችን በመተግበር ላይ ናቸው የተባሉት ሁለቱ ኩባንያዎች፣ በአሁኑ ወቅት የቲኬት ሽያጫቸውን በኤሌክትሮኒክ መገበያያ ዘዴ ተግባራዊ እያደረጉ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ በቅርቡም የኦንላይን የቲኬት ሽያጭ ይጀምራሉ ተብሏል፡፡ ከዚህም ሌላ በአዲስ አበባ ውስጥ የአውቶቡስ ተርሚናል ለመገንባት የቦታ ጥያቄ ያቀረቡ መሆኑን ከአቶ ዘለቀ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በአገር አቋራጭ የትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ተጨማሪ ሥራዎችን እንደሚሠሩ የጠቆሙት አቶ ዘለቀ፣ ከዚህም ባሻገር ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያና በሱዳን መንግሥት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ወደ ካርቱም የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ያስችላሉ የተባሉት ተሽከርካሪዎች ‹‹ሌግዥሪ›› በሚባል ደረጃ በትዕዛዝ የተሠሩ ናቸው ተብሏል፡፡ 51 መቀመጫዎችን የያዙት አውቶቡሶች መንገደኞችን በምቾት የሚያጓጉዙና ውስጣዊ ይዞታቸውም ለዚሁ ተብሎ የተሠራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ዘርፍ ለመሰማራት ልዩ የትራንስፖርት አገልግሎት ፈቃድ የሚሰጠውም ከሌሎች ተሽከርካሪዎች የተለየ አገልግሎት ስለሚሰጡ ነው፡፡
ዓባይና ኢትዮ ባስን ጨምሮ በዚህ ዘርፍ ልዩ ፈቃድ የተሰጣቸው ሰላም፣ ስካይና ሊማሊሞ የተባሉት አምስቱ ኩባንያዎች ለአገልግሎት የሚያበቋቸው ተሽከርካሪዎች ተመዝኖ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት እንደሌሎች የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት ሰጪዎች የዋጋ ቁጥጥር የማይደርግባቸውና ራሳቸው በሚያወጡት የዋጋ ተመን የሚሠሩ ናቸው፡፡ ልዩ ፈቃድ ካገኙት ከአምስቱ የአገር አቋራጭ አገልግሎት ሰጪዎች ውጪ ያሉት ግን መንግሥት በሚያወጣው የዋጋ ተመንና ስምሪት መሠረት የሚሠሩ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በልዩ የአገር አቋራጭ የትራንስፖርት ዘርፍ የመጀመርያውን ፈቃድ በማግኘት ወደ ሥራ የገባው ሰላም ባስ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ65 በላይ አውቶቡሶችን በማሰማራት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ስካይ ባስ ደግሞ ከ10 በላይ ተሽከርካሪዎችን የያዘ ሲሆን፣ ሊማሊሞ ባስ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ሦስት ባሶችን ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ነው ተብሏል፡፡
ከሌሎች በተለየ አገልግሎት ይሰጣሉ የተባሉትና የዋጋም ሆነ የስምሪት ግዳጅ ከሌለባቸው አምስቱ ኩባንያዎች ውስጥ ሰላም ባስ ዓባይ ባስና ኢትዮ ባስ ለአገልግሎታቸው የመረጡት ዩቶንግ የተባለውን ተሽከርካሪ ነው፡፡
የቻይው ኩባንያ ዩቶንግ በዘመናዊ የአውቶቡስ ምርቶች ይታወቃል፡፡ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ከ61 ሺሕ በላይ አውቶቡሶችን ለማምረት አቅም ያለው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡