Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለካቢኔው ሐሰተኛ ሰነድ ቀርቦ በይዞታቸው ላይ ውሳኔ የተላለፈባቸው አቤቱታ አቀረቡ

ለካቢኔው ሐሰተኛ ሰነድ ቀርቦ በይዞታቸው ላይ ውሳኔ የተላለፈባቸው አቤቱታ አቀረቡ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በመልሶ ማልማት ይዞታቸውንና አካባቢያቸውን ለሚለቁና ለሚያለሙ ነዋሪዎች ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፣ ለልማቱ ሲሉ እንደሚለቁ መስማማታቸውን በሚገልጽ ሐሰተኛ ደብዳቤ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው የሚናገሩ ባለይዞታዎች አቤት እያሉ ነው፡፡

ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደር ድረስ ፍትሕ ለማግኘት እየሮጡ መሆናቸውን የሚናገሩት እነዘለቃ በቀለ፣ ፈትያ እስማኤልና ጀማል አብዶ የሚባሉ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 የፌዴራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር መዳረሻ አካባቢ የሚገኙ ባለይዞታዎች ናቸው፡፡ አስተዳደሩ ያወጣውን መመርያ ተከትለው ባላቸው ቅድሚያ የማልማት መብት እንዲያለሙ ጥያቄ ያቀረቡት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሕጋዊ የሆነውን ይዞታቸውን ለማልማት አቅም እንዳላቸው በመግለጽ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመልሶ ማልማት ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ‹‹የአስተዳደሩ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቦርድ የካቲት 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ቦታው ለባለሀብት ተሰጥቷል፤›› የሚል ምላሽ ሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

አቤት ባዮቹ እነሱ የማልማት ጥያቄ ሲያቀርቡ ሊዝ ቦርድ ውሳኔ እንደሰጠ ቢነገራቸውም፣ ቦርዱ በተሰበሰበበት ወቅት ካሉት ዘጠኝ አባላት ከንቲባውን ጨምሮ አምስት አባላት ባለመገኘታቸው ውሳኔው ፈራሽ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለይዞታዎቹ ድጋሚ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት ቦርዱ በሊዝ አዋጅ ተተክቶ የፈረሰ ቢሆንም፣ የመልሶ ማልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት የአስተዳደሩ ሊዝ ቦርድ መፍረሱን ስለማያውቅ የሚሰጣቸው ምላሽ በወቅቱ ካለው ሁኔታ ጋር አልተጣጣመላቸውም፡፡ አቤቱታቸውን ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ቢያቀርቡም፣ ቦታው በአካባቢ ልማት ዕቅድ ተጠንቶ የተከለለ በመሆኑ እንደማያስተናግዳቸው እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል፡፡

ሕግ በሚፈቅድላቸው መንገድ የማልማት መብታቸው እንዲፈቀድላቸው ለከተማው ከንቲባ ታኅሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡ 1,500 ካሬ ሜትር በሆነ ቦታቸው ላይ ለማልማት ክፍለ ከተማውን የፕላን ስምምነት ሲጠይቁ ቦታው ለሌላ ግለሰብ መሰጠቱን፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ደግሞ በለገሀር ጥናት 40 ሔክታር ለመልሶ ማልማት መያዙን በመንገር፣ የተለያዩ ምላሾችን በመስጠት በደል እየደረሰባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በሊዝ ቦርድ ውሳኔ መሠረት ቦታው ለኢንቨስተር እንደተሰጠ የተገለጸላቸው ቢሆንም፣ ሊዝ ቦርድ (የሊዝ አዋጅ በ2004 ዓ.ም. ሲወጣ ፈርሷል) በወቅቱ ከነበሩት ዘጠኝ አባላት ውስጥ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳን ጨምሮ አምስት አባላት ባልተገኙበትና ኮረም ሳይሞላ ተወስኗል መባሉ፣ ምን ያህል በደል እየደረሰባቸው እንደሚገኝ እንደሚያሳይ ለከንቲባ ድሪባ የጻፉት ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

ለከንቲባ ድሪባ ኩማ የጻፉትን ደብዳቤ ተንተርሶ የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኮሚቴ በመዋቀር ባደረገው ጥናት፣ ተበዳዮች እየደረሰባቸው ያለው በደል እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ድምዳሜ ላይ ደርሶ ውሳኔ ለማሰጠት፣ በአጀንዳ ቁጥር 5 ‹‹የእነዘለቃ በቀለ፣ ፈትያ እስማኤል ኢብራሂምና ጀማል አብዶ ጉዳይ›› ተብሎ ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ ውስጥ፣ በአንድ አንቀጽ ተበዳይ ነን የሚሉትና የማልማት አቅም እንዳላቸው እየተከራከሩ የሚገኙት ተበዳዮች ‹‹ልማቱን ማደናቀፍ አንፈልግም፡፡ ጥያቄያችንን አንስተናል፡፡ ልማቱ አይታነቅ፡፡ ሊዝ ቦርድ በወሰነው መሠረት ለኢንቨስተሩ ይወሰንላቸው፤›› ብለው እንደተስማሙና በፊርማቸው ያረጋገጡ በማስመሰል ሐሰተኛ ሰነድ አያይዘው ለአስተዳደሩ ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ባደረገው ስምንተኛው የመሬት ሊዝ ጉዳይ ስብሰባ፣ የቀረበለትን ሐሰተኛ ሰነድ መመርመር ሳያስፈልገው ማፅደቁን ባለይዞታዎቹ አብራርተዋል፡፡ ጉዳዩ ገና ከጅምሩ በተለያዩ ክፍሎች በሚሠሩ ኃላፊዎች እየተደናቀፈባቸው መሆኑን ያስተዋሉት ባለይዞታዎቹ፣ ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዝርዝር መረጃ በማካተት ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ያሳወቁ ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ እስካሁን ምንም እንዳላለ ተናግረዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ነገር የተካሄደው ተበዳዮች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው እየታየ ባለበት ጊዜ መሆኑን ገልጸው፣ ፍርድ ቤቱ ኃላፊዎቹን ጠርቶ ትዕዛዝ መስጠት ሲገባው ዝም ብሎ ይዞ ከርሞ ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ውሳኔ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ክርክራቸው በአስተዳደሩ የተሰጠው ይዞታ ላይ ጥቅም ወይም መብት አለኝ፤›› የሚል በመሆኑ በሚመለከታቸው የአስተዳደሩ አካላት በይግባኝ ተዋረድ በተቀመጠው አግባብ ከሚጠይቁ በቀር፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሊታይ የሚችል አይደለም፤›› በማለት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ፋይሉን መዝጋቱን አሳውቀዋል፡፡ በመሆኑም የደረሰባቸውን የመልካም አስተዳደር በደል መንግሥት ተመልክቶ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ባለይዞታዎቹ ጠይቀዋል፡፡ በደል እየደረሰባቸው የሚገኙት ባለይዞታዎች ያቀረቡትን አቤቱታ በሚመለከት ምላሽ እንዲሰጡበት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት፣ ከተማ ማደስ፣ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤቶችና የከተማ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...