Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኤጀንሲን ለመቀላቀል ከጫፍ ደረሰች

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ለሙሉ አባልነት የሚያስፈልጋት ገንዘብ ግን አልተሟላም

ለመንግሥትም ሆነ ለግሉ ዘርፍ የጠለፋና የቀጥታ የመድን ሽፋን ይሰጣል በተባለው አፍሪካ ትሬድ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ የአክሲዮን ድርሻ በመያዝ ሙሉ አባል ለመሆን ኢትዮጵያ ከጫፍ መድረሷ ቢነገርም፣ ለአባልነት ከሚጠበቀው 25 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ እስካሁን የ7.5 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ለኤጀንሲው ሊከፈል እንደሚችል ተገለጸ፡፡

መንግሥት የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ አባል ለመሆን የሚያስችለውን የአባልነት ክፍያ በብድር ለማሟላት ከዓለም ባንክ የአጭር ጊዜ ብድር እንዲሰጠው ቢጠይቅም፣ የባንኩ ምላሽ በመዘገይቱ ፊቱን ወደ አፍሪካ ልማት ባንክ ለማዞር መገደዱን የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኃላፊዎች በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክም ቢሆን ከተጠየቀው ገንዘብ ውስጥ 7.5 ሚሊዮን ዶላር ብቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከፈል ብድር በማፅደቁ፣ በዚህ ሒደት የአባልነት ጥያቄው መስተናገድ እንደቻለና ኢትዮጵያ የአፍሪካ ንግድ ኢንሹራንስ ኤጀንሲን ሙሉ አባልነት በሁለት ወራት ውስጥ ለማግኘት መቃረቧን ይፋ አድርጓል፡፡ የተቀረው ገንዘብ የዓለም ባንክ የግሉ ዘርፍ ዋና ተጠሪ በሆነው የዓለም የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍአሲ) በኩል ሊገኝ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበርና የደቡባዊና የምሥራቃዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ዋና ጸሐፊ ኤራስተስ ሞኤንቻ በበኩላቸው፣ የኮሜሳ አባል አገሮች የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ አባል እንዲሆኑ እንደሚጠበቅ ስምምነት በመኖሩ ኢትዮጵያ ወደ ኤጀንሲው አባልነት መምጣቷ ተገቢ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ኤጀንሲው አፍሪካ በዓለም ገበያ ያላትን ዝቅተኛ የንግድና የኢንቨስትመንት ድርሻ ለማስፋፋት የሚያስችል የፋይናንስ ተቋም እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በአፍሪካ የመሠረተ ልማቶችን ለማሟላትና እ.ኤ.አ. በ2063 አፍሪካ ለወጠነችው የልማት አጀንዳ መሳካት ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ለዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሞኤንቻ ገልጸው፣ አፍሪካ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ በዓለም ላይ ያለውን ተዓማኒነትና እንደ ስታንዳርድ ኤንድ ፑር (ኤስኤንድፒ) ያሉ የፋይናንስ አስተማማኝነት ለኪዎች የ‹‹A›› ደረጃን የሰጡት በመሆኑ ለአፍሪካ ትልቅ ተቋም እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ አባል ለመሆን የሚያስችላትን ጥናትና ድርድር ለብዙ ጊዜ ስታካሂድ መቆየቷን ያስታወቀው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር፣ በመጨረሻም የድርድር ሒደቱ ተጠናቆ ሙሉ አባል ለመሆን ወደሚያስችለው ምዕራፍ መደረሱንና በቅርቡም የኤጀንሲውን ሕግጋት ኢትዮጵያ ስለመቀበሏ የሚያረጋገጥ ፊርማ ለመፈረም የሚያስችለው ምዕራፍ ላይ እንደሚትገኝ ተነግሯል፡፡

ይህንን ሒደት በማስመልከት ከመንግሥት ኃላፊዎችና ለግሉ ዘርፍ ጋር የአንድ ቀን ምክክር ያደረጉት የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ ኃላፊዎች፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት ከኤጀንሲው ስለሚያገኙት የመድን ሽፋን ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በዋናነት ለአፍሪካ የግልና የመንግሥት ላኪና አስመጪ ኩባንያዎች የመድን ሽፋን በመስጠት የሚሠራው አፍሪካ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ፣ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትን ለማገዝ መምጣቱን አስታውቋል፡፡ የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጆርጅ ኦ. ኦቲዬኖ እንዳብራሩት፣ የኤጀንሲው መምጣት የአገር ውስጥ የመድንና የባንክ ተቋማትን ለመቀናቀን ሳይሆን ተቋማቱ በማይሠሩባቸው መስኮች ላይ ለመሥራትና ለተቋማቱም ድጋፍ ለመስጠት ነው፡፡

የዩናይትድ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ የኤጀንሲው መምጣት ለኢትዮጵያ በሚሰጠው ጠቀሜታ ላይ እንደሚስማሙበትና ለረጅም ጊዜም እንዲመጣ ሲከራከሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይሁንና የኤጀንሰውን መምጣት ተከትሎ  በአገር ውስጥ ከሚገኙ የፋናንስ ተቋማት ዘንድ ገበያችንን ሊሻማ የመጣ ነው የሚል ቅሬታ ሲስተጋባ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ ባንኮችና የመድን ድርጅቶች የኤጀንሲውን መምጣት የአገሪቱን ሕግ ከመጣስ ጋር ሲያይዙትም እንደሚታይ ተናግረው፣ ሆኖም በአፍሪካ አባል መንግሥታት የተመሠረተው የመድን ተቋም ግን የውጭዎችም ሆኑ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ከዚህ ቀደም ማግኘት ያልቻሏቸውን የቀጥታም ሆነ የጠለፋ ዋስትናዎች በማቅረብ አዳዲስ መስኮች ላይ እንደሚያተኩር አብራርተዋል፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ሕግ የውጭ ኩባንያዎች በዘርፉ እንዳይሰማሩ እንደሚያግድ ይታወቃል፡፡

ዋና ሥራ አስጻሚው ኦቲዬኖ፣ ኤጀንሲው እንደውጭ ተቋም ሳይሆን እንደ አገር አቀፍ ድርጅት የሚያስቆጥረውን ሰውነት ስላገኘበት መንገድ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡ ይኸውም መንግሥት በአጀንሲው ባለድርሻ በመሆኑ ምክንያት እንደውጭ ተቋም መቆጠሩ አብቅቶለታል፡፡ በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ መድን ድርጅት ያሉ የመንግሥት የመድን ድርጅቶች እስከ ሦስት በመቶ ድርሻ ከኤጀንሲው ለመያዝ የሚያስችላቸው ሥርዓት በመፈጠሩ፣ የአገሪቱ የፋይናንስ ሕግ እንዳልተጣሰና የውጭ ኩባንያም ወደ ዘርፉ እንዳልገባ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡  

ኤጀንሲው በኢትዮጵያ ከሚሳተፍባቸው መስኮች መካከል በመንግሥት የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት በንግድ ተቋማትና ኢንቨስተሮች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችንና ኪሳራዎችን ለመሸፈን፣ በጦርነት፣ በግጭትና በሽብር ሥጋቶች ሳቢያ የውጭ ኩባንያዎች የመድን ሽፋን ቢጠይቁ ይህንን ዋስትና በመስጠት ለመሥራት መምጣቱ የተነገረለት የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ፣ በውጭ ምንዛሪ ለውጥ ሳቢያ የሚያጋጥሙ ድንገተኛ ኪሳራዎችንና ጉዳቶችን መሸፈንም ወደ ኢትዮጵያ ከመጣባቸው የሥራ መስኮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡   

ከዚህም ባሻገር ኤጀንሲው ላኪዎች ለገዥዎች በዱቤ በሚልኩበት ጊዜ ገንዘባቸው ሳይከፈላቸው ቢቀር፣ የኮንስትራክሽን ስምምነቶች ተፈጽመው ክፍያ ባይፈጸምና በሌሎችም መስኮች ላይ የመድን ሽፋን እንደሚሰጥ ኤጀንሲው ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን በአገር ውስጥ አዋጭነታቸው የታወቁም ሆነው የፋይናንስ እጥረት ላለባቸው ኩባንያዎች ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭ በመሆን ለባንክና ለመድን ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር በኩል አባልነት በመክፈል ስትቀላቀል በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚፈለገውን የፋይናንስ መጠን በአምስት እጥፍ በመጨመር የጠለፋ ዋስትናውን ወደ ዘጠኝ እጥፍ በመጨመር ተጨማሪ ፋይናንስ እንዲገኝ የሚያስችል ሥራ እንደሚሠራ የኤጀንሲው ከፍተኛ ውል አዋዋይ (አንደርራይተር) ቤንጃሚን ሙጊሻ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም አትዮጵያ አባልነቷን በ7.5 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ብትጀምር ይህ ገንዘብ እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ወይም ብድር እንድታገኝ የሚያስችላትን ሥራ በመሥራትና ለአባዳሪዎችም ዋስትና በመስጠት ኤጀንሲው እንሰሚሠራ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት መስኮች፣ የወጪ ንግድ ዘርፉ ላይ የሚሠሩ የግብርና፣ የማዕድንና ሌሎችም ተቋማትን ለማገዝ እንደሚሠራም ሙጊሻ ገልጸዋል፡፡ 

እ.ኤ.አ. በ2001 በዓለም ባንክ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ የተቋቋመው አፍሪካ ትሬድ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ፣ በአሁኑ ወቅት 180 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ሲኖረው፣ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ለሚገመቱ የንግድና የኢንቨስትመንት ተቋማት የመድን ሽፋን ሰጥቷል፡፡ እስካሁን ያስመዘገበው ጠቅላላ ዓረቦን 17 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ የ3.4 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን የኤጀንሲው መረጃ ይጠቁማል፡፡ እስካሁን አሥር አገሮችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳን፣ ጂቡቲና ሌሎችም አገሮች የአባልነት ጥያቄ አቀርበው ኤንጀሲውን ለመቀላቀል መቃረባቸው ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች