Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣን የነበሩት ተጠርጣሪ ለፓርላማና ለመንግሥት ደብዳቤ ጻፉ

የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣን የነበሩት ተጠርጣሪ ለፓርላማና ለመንግሥት ደብዳቤ ጻፉ

ቀን:

– ከተጠርጣሪው ጋር የተከሰሱት አራት ተጠርጣሪዎች መጥፋታቸው ተገለጸ

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባልና የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ወንድሙ ቢራቱ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው እንዲያደርጉ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ለዕንባ ጠባቂ ተቋም ደብዳቤ ጻፉ፡፡

‹‹የሕገ መንግሥቱ የበላይነትና የኦሮሚያ ክልል የክስና የዳኝነት ሥልጣን ተጥሶ፣ የቀረበብኝን የሙስና ክስ ማንሳትና ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ ሰብዓዊ መብቴን ማስከበር›› በሚል ርዕስ በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹት፣ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የኦሕዴድ ኢሕአዴግ አባል በመሆን በመታገል ላይ ነበሩ፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ምክር ቤት አባልና የክልሉ ካቢኔ አባል በመሆን ለአሥር ዓመታት ማገልገላቸውን ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

በክልሉ ሠራተኛና ባለሥልጣን ሆነው ሲሠሩ የፈጸሙት የሙስና ወንጀል ካለ ጉዳዩን የመመርመርና የመክሰስ ሥልጣን ያለው የክልሉ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሆኖ ሳለ፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መሆኑ ከሥልጣኑና ከሕግ ውጪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እሳቸው በተከሰሱበት ጉዳይ የዳኝነት ሥልጣን ያለው የክልሉ መንግሥት ፍርድ ቤት ቢሆንም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መከሰሳቸውን፣ ይኼም በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና አዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀጽ (7) እና በአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ (7) ሥር በግልጽ መደንገጉንም አቶ ወንደሙ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡ ግለሰብ ምንጊዜም ሊታመን ባይችልም ሕገ መንግሥቱና ተቋማት መከበር እንዳለባቸውና ይኼም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(8) ተደንግጐ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ ጥፋት ካለባቸው እንደሚከሰሱ እንደሚያውቁ የገለጹት አቶ ወንድሙ፣ እየጠየቁ ያለው ሥልጣን ባለው አካል ተከሰው ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት የመዳኘትና ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው መሆኑን በደብዳቤያቸው አስረድተዋል፡፡

አቶ ወንድሙ በክልሉ የፀጥታ ቢሮ የሚሊሺያና የተጠባባቂ ጦር ዘርፍ ኃላፊ ሆነው ከመሥራታቸውም በተጨማሪ፣ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሠራተኛ፣ ምክትል ኃላፊና የቢሮ ኃላፊ፣ እንዲሁም የብድርና ቁጠባ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ሆነው በሚሠሩበት ወቅት የክልሉ ገቢ ሰብሳቢ ጽሕፈት ቤቶችን በኔትወርክ በማያያዝና ተገቢውን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በመዘርጋት፣ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ከፍተኛ ገቢ በማስገኘታቸው ምሥጉን ሠራተኛ ሆነው ተሸላሚ እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከነሐሴ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ አስሮና ከሷቸው የሚገኘው፣ በአሳሳችና ጐጂ የቂም በቀለኞች ሐሰተኛ ጥቆማ መነሻነት መሆኑንም አቶ ወንድሙ የግለሰቦቹን ስም በመጥቀስ ገልጸዋል፡፡

ተከሳሽ አቶ ወንድሙ ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥቆማ በመስጠት እንዲታሰሩ ያደረጉ ሁለት ግለሰቦችንና ለምን ኮሚሽኑን እንዳሳሳቱት በዝርዝር የጠቀሱ ሲሆን፣ ለመንግሥት 19 ዓመታት ሠርተው ያገኙት ገቢ 889,976 ብር ብቻ ተብሎ መጠቀሱን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያ የሠራተኝነት ደመወዛቸውን በ19 ዓመታት ከማባዛት ውጪ በሹመት ያገኙት ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ያልተጨመረበት መሆኑን አክለዋል፡፡

የቀረበባቸው ክስ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1)(2) እንዲሁም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ/122 መሠረት ክሱ እንዲነሳላቸውና ትኩረት እንዲሰጡላቸው ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች፣ ለክልሉ መንግሥት ፕሬዚዳንትና አፈ ጉባዔ፣ ለኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደብዳቤያቸው እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ በግልባጭ የክልሉ መንግሥት ምክር ቤት፣ የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ ኦሕዴድ፣ ኢሕአዴግና የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲያውቁት አድርገዋል፡፡

በሌላ በኩል የአቶ ወንድሙን ክስ እያየው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ከአቶ ወንድሙ ጋር ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸውን ነገር ግን እጃቸው ያልተያዙት አቶ ባህሩ ቢረዳ፣ ሸዋረገድ ቢረዳ፣ እልፍነሽ ቢራቱና ባለቤታቸው ወ/ሮ አሰገደች መንግሥቱን አፈላልጐ ለጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የታዘዘው ኮሚሽኑ እንዳላገኛቸው ገልጿል፡፡ በምርመራም ወቅት አለመገኘታቸውና እስካሁን በክትትል ላይ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ በተገኙ ጊዜ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን በደብዳቤ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም አቶ ወንድሙ የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ፣ አስፈላጊ ሰነዶች በሚታይ ሁኔታ ኮፒ ተደርጐ እንዲሰጣቸው፣ የኮሚሽኑ ምርመራና ክትትል ቡድን ያልተያዙትን ተከታትሎ በመያዝ አስሮ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት፣ የአቶ ወንድሙን የክስ መቃወሚያ ለመስማትና ያልተያዙትን ለመጠባበቅ ለኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...