Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአዲስ አበባ በፌዴራል ቅርፅ በክላስተር በመደራጀት የጋራ አመራር እንዲከተል የቀረበው ሐሳብ ፀደቀ

አዲስ አበባ በፌዴራል ቅርፅ በክላስተር በመደራጀት የጋራ አመራር እንዲከተል የቀረበው ሐሳብ ፀደቀ

ቀን:

– ክላስተሮች በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ኃላፊ ተሾመላቸው

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፌዴራል መንግሥት ቅርፅ በክላስተር ተደራጅቶ የጋራ አመራር ዘይቤ እንዲከተል የቀረበው ሐሳብ ፀደቀ፡፡ ማክሰኞ ጥቅምት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው ድንገተኛና አስቸኳይ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጉባዔ ለ12 ዕጩዎች ሹመት ሰጥቷል፡፡

በከተማው ውስጥ በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ከፍተኛ ግንባታ በማካሄድ ላይ የሚገኙ አራት የመሠረተ ልማት ተቋማት ይዞ የተደራጀው የመሬት አስተዳደርና ኮንስትራክሽን ክላስተር እንዲያስተባብሩ፣ ነባሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ተጨማሪ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡

አቶ አባተ የብአዴን አመራር አባል ሲሆኑ፣ በአቶ ኩማ ደመቅሳ አመራር ወቅት ምክትል ከንቲባ የነበሩት አቶ ከፍያለው አዘዘ ከአገር በመኮብለላቸው ምክንያት ቦታውን እንዲይዙ ተደርጓል፡፡

ከተማው የሚያመነጨውን ሀብት በሚገባ እንዲሰባሰብ የተቋቋመውን የኢኮኖሚ ክላስተር እንዲያስተባብሩ አቶ እርስቱ ይርዳው ተሾመዋል፡፡ አቶ እርስቱ ከዚህ ሥልጣን በተጨማሪ ከአቶ ኩማ የሥልጣን ዘመን ጀምሮ የንግድ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ ለትምህርት ወደ ቻይና በማቅናታቸው፣ የንግድ ቢሮ ኃላፊነት ተደርቦ ተሰጥቷቸዋል፡፡

አቶ እርስቱ ከደኢሕዴን የተወከሉ ሲሆን፣ ከጉራጌ ዞን አስተዳዳሪነት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማኅበራዊ ጉዳይ አስተባባሪነት ባሉ መዋቅሮች ሠርተዋል፡፡

የማኅበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ሆነው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የተሾሙት አቶ ዲላሞ ኦቶሬ ናቸው፡፡ አቶ ዲላሞ በአቶ ኩማ የሥልጣን ዘመን ከደኢሕዴን ተወክለው የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን፣ ከማኅበራዊ ክላስተር በተጨማሪ ይህንኑ ሥልጣናቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ተወስኗል፡፡

የመልካም አስተዳደርና ሪፎርም ክላስተር አስተባባሪ ሆነው የተሾሙት አቶ ይስሐቅ ግርማይ ናቸው፡፡ አቶ ይስሐቅ ከሕወሓት የተወከሉ ሲሆን፣ ከአዲሱ ሹመታቸው በተጨማሪ በአዲስ መልክ የተዋቀረውን የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ እንዲመሩ ተወስኗል፡፡ አቶ ይስሐቅ ቀደም ሲል የከተማው አቅም ግንባታ ቢሮ የሚባለውንና በአሁኑ ወቅት የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ቢሮ ተብሎ የተሰየመውን ይመሩ ነበር፡፡  

ምክር ቤቱ በማክሰኞው ውሎ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ መመራቱ እንዲቆም ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በተለያዩ ተከታታይና ረጅም የመዋቅር ለውጦች ውስጥ አልፎ፣ ከሦስት ዓመት በፊት አሁን የፍትሕ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩት አቶ ጌታቸው አምባዬ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ እንዲመሩት ተሹመው ነበር፡፡

ከአቶ ጌታቸው በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት አቶ ሰለሞን ኃይሌ በዚሁ ምክትል ከንቲባ ማዕረግ ቀጥለው ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማክሰኞው ድንገተኛ ጉባዔው የምክትል ከንቲባን ማዕረግ ከመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አንስቷል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞንን ከቦታቸው የማንሳት ሐሳብ እንደነበረው ምንጮች ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ አቶ ሰለሞንም ቦታውን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ይሁንና ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ እስካሁን ሁነኛ ተሿሚ ባለመገኘቱ አቶ ሰለሞን እንዲቆዩ መደረጉን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

አቶ አባተ በዚህ የማስተካከያ ሹመት ላይ፣ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሹም ሽር እንዳልተደረገ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

ከእነዚህ ሹመቶች በተጨማሪ አቶ ዮሐንስ ምትኩ የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ደስታ ፍፁም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ዮናስ አያሌው የኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ኤልያስ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ጀማል ረዲ የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ፣ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል፡፡ የኃላፊዎቹን ሹመት ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2005 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ የከተማውን ካቢኔ መመሥረቱ ይታወቃል፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ አሁን የተደረገውን ከንቲባ ድሪባ ለምክር ቤት እንዳስረዱት፣ የተካሄደው ሹመትና መዋቅር የማስተካከያ ዕርምጃ ነው፡፡

በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ መጠነ ሰፊ የማስተካከያ ሹም ሽር ተደርጓል ያሉት ከንቲባ ድሪባ፣ በማዕከል ደረጃ በድክመት ለተነሱ አመራሮች ኢሕአዴግ ተመጣጣኝ የቦታ ድልድል ያደርጋል ብለዋል፡፡ ብቃት የነበራቸውና የተነሱ አመራሮች በሌሎች ቦታዎች ተሹመዋል ሲሉ ከንቲባው አስረድተዋል፡፡ በቀጣይነት በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ላይ መጠነ ሰፊ ማስተካከያ ለማካሄድ ጥናት እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...