Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅሬክላምና የተለያዩ ማስታወቂያዎች በአዲስ አበባ በ1928 ዓ.ም. በሪኪሊ (Rikli) የተነሳ ፎቶግራፍ

ሬክላምና የተለያዩ ማስታወቂያዎች በአዲስ አበባ በ1928 ዓ.ም. በሪኪሊ (Rikli) የተነሳ ፎቶግራፍ

ቀን:

ጠርጥሪኝ በሆድሽ

ሳላቅሽ ወደድኩሽ

ሳላይሽ አመንኩሽ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንዲህ ያለ አፍቃሪ በዕድሜሽም አይገጥምሽ

‹‹አንድ ቀን ሊያገኘኝ፣ መቻሉ አይቀር ብለሽ››

ጠርጥሪኝ በሆድሽ፡፡

ከታቀደው ይልቅ ያልታቀደው ነገር

በሚያምርበት አገር

ይሻልሻል ሆዴ በሆድሽ መጠርጠር፡፡

ሆድ አይችለው የለው፣ እኔን ታረግዣለሽ

ትወልጂኝ ይሆናል፣ አንድ ቀን ሲቀናሽ

ስሜን ጨክነሽ

‹‹ተጠርጣሪው›› ብለሽ፣ ትሰይሚኛለሽ

ግዴለሽም ውዴ ጠርጥሪኝ በሆድሽ!!

ነቢይ መኰንን፣ ስውር ስፌት፣ 2006 ዓ.ም.

* * *

የዕውቀትን ግርዶሽ አስወግድ

ዕውቀት የህላዌ እንቁ ነች፡፡ በመሆን እግሮች ላይ አሰናካይ ሰንሰለትም ልትሆን ትችላለች፡፡

ብዙውን ጊዜ ብርሃኑን ለማየት የሚሳናቸው እናውቃን የሚሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ከጥንቱም፣ ዕውቀት ከፍተኛዋ መፈተኛ ሆና ኖራለች፡፡

የዕውቅትን መጋረጃ ተርትረህ ጥለህ ራቁቷን እውነት በራቁት ዓይንህ ተመልከት፡፡

የራስህ ዓዕምሮ፣ በህልምህ ቅዱሰ-ቅዱሳን መግቢያ በር ላይ የሚያኖርብህን ተራራ-አካል ደንቃራ ለማለፍ ዝግጁ ከሆንክ፣ ሌሎች ፈተናዎች ሁሉ ይህንኑ ተራራ ለመውጣት የመቆናጠጫ እርከኖች ብቻ ነው የሚሆኑህ፡፡

ያልተኖረ ዕውቀት እንዳልተዳቀለ አበባ ነው፡፡ በክብሩ የፀዴይ ወቅት ብቻ ፈክቶና ተውቦ ይታያል፡፡ የማበቢያ ወቅቱ በሄደ ጊዜ፣ ምንም ቅሪት ሳይተው፣ ረግፎ ይከስማል፡፡ ዕውቀትህን በንፁህና በቅዱስ ምርባር ካባ አልብሰው፡፡ ያኔ ብቻ ነው አዕምሮህ ጥበብን ሊወልድና በዘለዓለማዊነት ዙፋን ላይ ቦታውን ሊያገኝ እሚቻለው፡፡

ዕውቀት የአዕምሮ ዜጋ ነው፤ ጥበብ ግን የነፍስ ነች፡፡ ዕውቀት ኩራዝ ነው፤ ጥበብ ግን ብርሃኑን ነች፡፡ ጥበብ፣ ሁሌም ራሷን በማስፋፋት፣ በመንገዷ እሚገጥሟትን ሌሎች ብርሃኖችም ተቀብላ በማሠራጨት፣ በየኩርባውም በየንጋቱም ይበልጥ እየደመቀች ትሄዳለች እንጂ ከቶም አትጠፋም፡፡

ከጠቢቦች ሁንና ብርሃኑ ከምሥራቅም ይሁን ከምዕራብ፣ ከታናሹም ይሁን ከታላቁ፣ ቢመጣ ሳትዘገይ ያዘው፡፡ አጥብቀህም እቀፈው፡፡

  • ኦ’ታም ፑልቶ፣ የፈላሱ መንገድ፣ 2006 ዓ.ም.

* * *

የሚስጥሮች ጫካ

በአንድ ወቅት በኢታንግ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ ኦቢል ወደሚባለውም ጫካ በመሄድ እንስሳትን ማጥመድ ፈለጉ፡፡ ወጥመዱንም ካዘጋጁ በኋላ በእንስሳቱ መንገድ ላይ አኑረውት በማግስቱ ጠዋት የሆነውን ሊያዩ ሲመለሱ ወጥመዱ አንድ አንበሳ ቢይዝም አንበሳው ወጥመዱን ሰብሮ ማምለጡን አዩ፡፡

በዚህን ጊዜ አንበሳው በጣም ተናዶ ስለነበር በአቅራቢያው ሆኖ ይመለከታቸው ነበር፡፡ ቀስ ብሎ አድፍጦ ከጠበቃቸው በኋላ አጥማጆቹን ያሳድዳቸው ጀመር፡፡ እነሱም ሮጠው ሲያመልጡት አንበሳው ተመልሶ ወደ ጫካው ገባ፡፡

እነርሱም ወደ መንደራቸው በመመለስ ላይ ሳሉ “ይህንን ለማንም አንነግርም፡፡ አንበሳው ስላሸነፈን ሁሉም ይስቁብናል፤” ተባባሉ፡፡

የያዙትንም ዕቃ ሁሉ ቢላዎቻቸውን፣ ጦራቸውንና የውኃ ቅላቸውን ጭምር ጥለው ተመለሱ፡፡

“ፈሪዎች ናቸው ብለው ይሳለቁብናል፤” ተባባሉ፡፡

ነገር ግን ከቤታቸው ሲደርሱ በመንደራቸው ካለና መጠጥ ከሚሰጥበት አንድ ዛፍ ስር ሄዱ፡፡ የሚችሉትንም ያህል ከጠጡ በኋላ አንደኛቸው ብድግ ብሎ “ዛሬ ጠዋት አንበሳ አባሮን ንብረታችን ሁሉ ጠፋብን፤” ብሎ ተናገረ፡፡

ሁለተኛውም የጓደኛውን ትከሻ ነካ አድርጎ “አቁም! እባክህ ይህንን ለማንም አትንገር፤” አለው፡፡ ኦቢልም “መሽቷል፤” አለው፡፡

ይህንንም ያለው ኦቢል ጥቅጥቅ ያለ ጫካና ብዙ ሚስጥሮችን የሚይዝ ነው ለማለት ፈልጎ ነው፡፡ ይህም ማለት በጥል ከተሸነፍክ ሽንፈትህን መደበቅ አለብህ ለማለት ነው፡፡

  • በኦፒው አምዎንግ የተተረከ የጋምቤላ ተረት

*********

አንበጦች እንቅስቃሴያቸውን የሚቆጣጠሩበት የነርቭ ሴል

አንበጦች የሚጓዙት በመንጋ ነው፡፡ “በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ውስጥ 80 ሚሊዮን” አንበጦች አብረው ሊበርሩ ይችላሉ። ያም ሆኖ አንዳቸው ከሌላው ጋር አይጋጩም። ሚስጥሩ ምንድን ነው? ከዓይኖቻቸው በስተ ጀርባ ሎቡላ ጃይንት ሙቭመንት ዲቴክተር ተብሎ የሚጠራ እንቅስቃሴን የሚቆጣጠር የነርቭ ሴል አለ። አንበጦቹ ሊጋጩ ሲቃረቡ እነዚህ ሴሎች ለክንፎቻቸውና ለእግሮቻቸው መልዕክት በማስተላለፍ ፈጣን እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጋሉ። እንዲያውም እርምጃ የሚወስዱበት ፍጥነት ዓይን ከሚርገበገብበት በአምስት እጥፍ ይበልጣል።

የሳይንስ ሊቃውንት የአንበጦችን ዓይንና የነርቭ ሴሎች በመኮረጅ ራዳር ወይም ጨረር የሚጠቀም የተወሳሰበ መሣሪያ ሳያስፈልግ ከፊቱ የመጣበትን ነገር መለየትና መሸሽ የሚችል በኮምፒዩተር የሚመራ ተንቀሳቃሽ ሮቦት መሥራት ችለዋል። ተመራማሪዎች ይህን ቴክኖሎጂ ተሽከርካሪዎችም ላይ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ መሣሪያው ፈጣንና አስተማማኝ ማስጠንቀቂያ ስለሚሰጥ ግጭትን በእጅጉ መቀነስ ያስችላል። በዩናይትድ ኪንግደም የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሺጋንግ ዩዌ “እንደ አንበጣ ካለች አነስተኛ ፍጡር እንኳ ብዙ መማር ይቻላል” ብለዋል።

‹‹ንቁ!›› (2014)

* * *

ኢንዶኔዥያ ከዕፅ ጋር የተያያዙ ወንጀለኞን እስር ቤት በአዞ ልታስጠብቅ ነው

የኢንዶኔዥያ የፀረ አደገኛ ፅዕ ኤጀንሲ፣ ከአደገኛ ዕፅ ጋር በተያያዘ ወንጀል የሚፈጽሙ ግለሰቦች የሚታሰሩበትን እስር ቤት በአዞ ለማስጠበቅ ዕቅድ አቀረበ፡፡

ዘ ቴሌግራፍ እንደዘገበው፣ ኤጀንሲው እስር ቤቱ በባህር ደሴት ላይ እንዲገነባ፣ እስረኞችም በአዞ እንዲጠበቁ ሐሳብ ያቀረበበት ምክንያት፤ ዕፅ አዘዋዋሪዎች እስር ቤት ከገቡ በኋላ እያመለጡ ስላስቸገሩ ነው፡፡ በደሴቱ ላይ የሚገነባው እስር ቤት የሚጠበቀው በአዞዎች በመሆኑ ችግሩን ይቀርፋል ተብሎ ታምኗል፡፡

የኤጀንሲው ዳይሬክተር ቡዲ ዋሲሶ እንደሚሉት፣ እስረኞች አዞዎችን በገንዘብ ደልለው ከእስር ቤት ሊያመልጡ አይችሉም፡፡ በእስር ቤቱ ዙሪያም ኃይለኛ ዝርያ ያላቸው አዞዎችን ከየቦታው አስመጥተው ያራባሉ፡፡

የኢንዶኔዥያው ፕሬዚዳንት ጆኮ ዊዶዶ፣ ዕፅ አዘዋዋሪዎች የሞት ፍርድ ይገባቸዋል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በአገሪቱ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚውም ሆነ አዘዋዋሪው ቁጥር እያደገ በመምጣቱ ነው፡፡

ኢንዶኔዥያ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን በተመለከተ በዓለም ጠንካራ የወንጀል ሕግ ካላቸው አገሮች ትመደባለች፡፡ የዕፅ አዘዋዋሪዎችም እስከ ሞት ፍርድ ድረስ ሊከናነቡ ይችላሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን የኢንዶኔዥያ የእስር ቤት ሥርዓት ጭምር በሙስና በመጨመላለቁ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን መግታት አልተቻለም፡፡ የእስር ቤት ባለሥልጣናት፣ በዕፅ ማዘዋወር ተወንጅለው ከታሰሩት ጋር ያላቸው ግንኙነት እየተደረሰበትም ብዙዎቹ ታስረዋል፡፡ አሁን ላይ የፀረ ዕፅ ኤጀንሲው ያቀረበው እስር ቤትን በአዞ የማስጠበቅ አሠራር ግን መፍትሔ ይዞ ሊመጣ ይችላል ተብሏል፡፡

* * *

የኢራን ፕሬዚዳንት በፈረንሣዩ አቻቸው የቀረበላቸውን የእራት ግብዣ በወይን ጠጅ ምክንያት ሰረዙ

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሃኒ በፈረንሣዩ አቻቸው ፍራንሷ ኦላንዴ በቀረበላቸው የእራት ግብዣ ጥሪ ወይን ጠጅ የሚካተት ከሆነ እንደማይቀበሉ ገለጹ፡፡

ፍራንስ 24 እንደዘገበው፣ የኢራኑ ፕሬዚዳንት ከህዳር 4 እስከ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጣሊያንንና ፈረንሣይን ይጎበኛሉ፡፡ ጣሊያን የመጀመሪያ መዳረሻቸው ሲሆን ለሁለት ቀን ያህል የሚቆዩት ደግሞ በፈረንሣይ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ሮሃኒ በኒውክሊየር ዙሪያ ከአገራቱ መሪዎች ጋር የሚያወያዩ ሲሆን፣ ፖፕ ፍራንሲስን ማግኘትም ሌላው አጀንዳቸው ነው፡፡ ሆኖም በሚዲያዎች ትኩረት አግኝቶ እየተናፈሰ የሚገኘው፣ በኦላንዴ ጋባዥነት በፈረንሣዩ ኤልዜ ቤተ መንግሥት ለሮሃኒ በሚዘጋጅላቸው የእራት ግብዣ የወይን ጠጅ የሚቀርብ ከሆነ፣ ሮሃኒ ግብዣውን የማይቀበሉ መሆናቸው ነው፡፡

በፈረንሣይ ባህል የምግብ ግብዣ በተለይም ምሳና እራት ያለወይን ጠጅ አይሞከርም፡፡ ይህ ደግሞ በሙስሊሙ ባህል የተነቀፈ ነው፡፡

ዘገባው እንደሚያሳየው፣ ኢራን ግብዣው ከመጠጥ የፀዳ እንዲሆን የጠየቀች ሲሆን በፈረንሣዩ ፕሬዚዳንት ጋባዥነት የሚሰናዳው እራት ደግሞ ሃላል (ከአልኮል መጠጥ የፀዳ) ሊሆን አይችልም፡፡

ዘ ጀሩሳሌም ፖስት እንደሚለው፣ ቁርስ ከአልኮል መጠጥ ጋር እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ፣ ሮሃኒ ከአቻቸው ኦላንዴ ጋር ቁርስ አብረው እንዲመገቡም አማራጭ ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ ሆኖም ሮሃኒና ልዑካን ቡድናቸው ‹‹የማይመጥን ግብዣ›› ሲሉ በፈረንሣይ ፕሬዚዳንት የቀረበላቸውን የምግብ ግብዣ ከወዲሁ ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...