Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጫጉላ ሲዘምን

ጫጉላ ሲዘምን

ቀን:

ዶ/ር አግደው ረዲ ትዳር የመሠረቱት ከሐምሳ ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ከሠርጋቸው አንድ ሳምንት በኋላ በሚዜዎቻቸው ታጅበው ለጫጉላ ሽርሽር ወደ አርባ ምንጭ ሄደዋል፡፡ ከባለቤታቸው እንዲሁም የቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር ያሳለፉትን ጊዜ ሲያወሱ በሐሴት ተሞልተው ነው፡፡ በወቅቱ በአነስተኛ ገንዘብ ሶደሬና ላንጋኖም ተጉዘው ነበር፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ የጫጉላ ሽርሽርን ከከተማ ውጪ ማካሄድ እየተለመደ የመጣው ከጣሊያን ወረራ ወዲህ ነው፡፡ ከዛ በፊት ጥንዶች ከተጋቡ በኋላ እንዲተዋወቁና እንዲላመዱ ጊዜ ቢሰጣቸውም፣ ከከተማ አይወጡም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሁኔታዎች ተለውጠው ሙሽሮች ወደ ቻይና፣ ባንኮክ፣ አሜሪካና ሌሎችም አገሮች ሲሄዱ እንደሚስተዋል የሚናገሩት ዶ/ር አግደው፣ በእሳቸው ዘመን የበረውንና ዛሬ ያለውን የጫጉላ ሽርሽር ልዩነት ያስረዳሉ፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጡ ከመጡ ሁነቶች አንዱ የጫጉላ ሽርሽር ነው፡፡ ቀደም ባሉ ጊዜአት በገጠር አካባቢ የጫጉላ ሽርሽር በሙሽሮች የትውልድ ቀዬ ይካሄዳል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ለሙሽሮች መጠነኛ ጎጆ ተዘጋጅቶ ለቀናት ከቤት ሳይወጡ እንዲዝናኑ ይደረጋል፡፡ ከተማ ቀመስ በሚባሉ አካባቢዎች ያሉ ጥንዶች ደግሞ፣ ከከተማ ወጥተው የጫጉላ ሽርሽር ያደርጋሉ፡፡ ተመራጭ ከሆኑ ቦታዎች አንዷ ምፅዋ እንደ ነበረች ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል የጫጉላ ሽርሽር ያልነበራቸው ጥንዶችም ይጠቀሳሉ፡፡

ዛሬ ላይ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው ሰፊ ጊዜ ሰጥተው ከኢትዮጵያ ውጪ የጫጉላ ሽርሽራቸውን የሚያካሂዱ ጥንዶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዱባይ፣ ሞሪሽየስና ታይላንድ ለጫጉላ ሽርሽር ከሚመረጡ አገሮች ጥቂቱ ናቸው፡፡ ልማዱን ከከተሜነት መስፋፋት፣ የገንዘብ አቅም ማደግ፣ አማራጭን የመጠቀም ባህል መዳበርና ሌሎችም ጉዳዮች ጋር የሚያያይዙት አሉ፡፡

ፍጹም ከበደና ባለቤቷ ስለ ጫጉላ ሽርሽራቸው ማሰብ የጀመሩት ከሠርጋቸው በፊት ነበር፡፡ በአስመጪና ላኪ ድርጅት የምትሠራው ፍጹም፣ በሥራዋ ምክንያት በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ወጥታለች፡፡ ከተሞክሮዋ ተነስታ ለጫጉላ ሽርሽር ምቹ አገሮችን ለባለቤቷ ምርጫ አቀረበች፡፡ ዱባይ በርካታ መዝናኛዎች ቢኖሩም ግርግሩ ስለሚበዛ ከከተማ ወጣ ያለ መዝናኛ ወዳለበት ሞምባሳ ለመሄድ ወሰኑ፡፡ ጉዟቸው እንዲሳካም ለወትሮው ከሚያወጡት ወጪ መቆጠብ ጀመሩ፡፡

ሠርጉ ሲቃረብ ሞምባሳ ያሉ መዝናኛዎች ለአዲስ ሙሽሮች የሚያዘጋጁትን የጫጉላ መስተንግዶ ከድረ ገጾቻቸው ተመለከቱ፡፡ የጥንዶች እራት፣ የሙዚቃ ዝግጅትና ሌሎችም የጫጉላ ሽርሽርን የሚያደምቁ መስተንግዶዎች የሚቀርብበትን ሆቴል መርጠው በኢ-ሜይል ቦታ ያዙ፡፡ ከሠርጉ በኋላ በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ቀን ደርሶ ወደ ሞምባሳ አቀኑ፡፡ ሲደርሱ የተሰማቸውን ደስታ ታስታውሳለች፡፡ የባህር ዳርቻ ሽርሽር ቆይታቸውን አይረሴ ካደረጉት አንዱ ነው፡፡

ከሠርግ በኋላ ያሉት ጥቂት ሳምንታት ጥንዶች የአብሮነት ሕይወታቸው ምን እንደሚመስል የሚያስቡበት እንደሆነ ታምናለች፡፡ ከሠርጉ በፊት ስለ ትዳራቸው ያላቸው እሳቤ፣ በዕውን የሚታይበት ወቅት እንደመሆኑም ሁለቱንም በሚያስደስት መልኩ ማለፍ አለበት፡፡ ለጫጉላ ሽርሽራቸው የሚመርጡት ቦታ የሚያዝናናቸው መሆኑ ትዳራቸውን በጥሩ መንፈስ እንዲጀምሩ ይረዳቸዋል፡፡

የጫጉላ ሽርሽርን ከአገር ውጪ ማድረግ እየተለመደ መምጣቱ የከተሜነት መስፋፋትና አዳዲስ ነገሮችን የመሞከር ተነሳሽነት የመኖሩ ውጤት ነው ትላለች፡፡

ፍጹም ከሠርግ በበለጠ ለጫጉላ ሽርሽር ልዩ ቦታ ትሰጣለች፡፡ ‹‹ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ትውስታ የሚፈጠረው በዚያ ወቅት ነው፡፡ ጥንዶች የግድ ከአገር ባይወጡም ከለመዱት አካባቢ በተለየ ስፍራ ቢያሳልፉ ይመረጣል፤›› ትላለች፡፡

ሐሳቧን የምትጋራው ሠራዊት ደረጄ፣ ያገባችው ከአራት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ከሠርጉ ጥቂት ቀናት በኋላ ባለቤቷ ለትምህርት ወደ ታንዛኒያ፣ እሷም ለሥራ ወደ ክፍለ ሀገር ሄዱ፡፡ አፍላ የትዳራቸውን ጊዜ ተለያይተው ከማሳለፋቸው በላይ የጫጉላ ሽርሽር ባለማድረጋቸው ቅሬታ ተሰምቷቸው ነበር፡፡ ከተለያዩ በስድስተኛው ወር  ባለቤቷ ወደ ዛንዚባር እንዲሄዱ ጥሪ አደረገላት፡፡ ያልጠበቀችው ነበርና ደስታዋን መቆጣጠር አልቻለችም፡፡ ሻንጣዋን ሸክፋ ወደ ጫጉላ ሽርሽራቸው አመራች፡፡ ባህር ዳርቻ በሚገኝ ሪዞርት ለጥንዶች በተዘጋጀ ሙሉ መስተንግዶ (ፉል ፓኬጅ) አረፉ፡፡

መስተንግዶው ምግብ፣ መጠጥ፣ ዋና፣ ሳውናና ሌሎች መዝናኛዎችን ያካተተ ነበር፡፡ በዛንዚባር ጠረፍ ላይ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ያሳለፉትን ጊዜ አትዘነጋውም፡፡ ‹‹ባህላቸውና አኗኗራቸው ማራኪ ነው፤›› ትላለች፡፡ የጥንዶችን ስም በእንጨት ላይ የሚቀርጹ፣ የሁለቱንም ስም ቀርጸው ሰጥተዋቸዋል፡፡ ዛሬ እንጨቱን ስትመለከት በትውስታ ወደ ጫጉላ ሽርሽራቸው ትመለሳለች፡፡

በሪዞርቱ ለሦስት ቀን ወደ 30,000 ብር ገደማ አውጥተዋል፡፡ ሠራዊት የጫጉላ ሽርሽርን ከኢትዮጵያ ውጪ ማድረግ የሚጠይቀውን ወጪ ከግምት በማስገባት፣ ጉዳዩን ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ታያይዘዋለች፡፡ ‹‹ጥንዶች ተበድረውም ቢሆን ሠርግ መደገሳቸው አይቀርም፤ የጫጉላ ሽርሽር ግን በፍላጎት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የአቅም ጉዳይ ይወስነዋል፤›› ትላለች፡፡

እሷ እንደምትለው፣ ከፍተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ጉዞው ቢቀልም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ሊፈትን ይችላል፡፡ ገንዘብ ቢኖራቸውም ለጫጉላ ሽርሽር ቦታ የማይሰጡም አይታጡም፡፡ እንደ እሷና ባለቤቷ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ወጪዎችን ቀንሰው በመቆጠብ መሰል ሽርሽሮች ማካሄድ ይችላሉ ትላለች፡፡

የውጪ አገር የጫጉላ ሽርሽር በጣም የተጋነነ ወጪ እንደሚጠይቅ በመገመት ጉዞን ከግምት የማያስገቡ ጥንዶች ቢኖሩም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ መምጣቱን ታምናለች፡፡ ወደ ውጪ የሚሄዱ ሰዎች መበራከታቸውና ተሞክሯቸውን ለማካፈል ቴክኖሎጂው የተመቸ መሆኑ መነሳሳቱን ፈጥሯል ትላለች፡፡

የጫጉላ ሽርሽር የጥንዶችን አቅም የሚያናጋ መሆን የለበትም፡፡ ጥንዶች ስለሚሄዱበት አገር አስቀድመው ቢያጠኑም መልካም ነው፡፡ ለታይታ ሳይሆን ለጥንዶቹ ትርጉም በሚሰጥ ሁናቴ መደረግም አለበት፡፡ ታሪካዊ ወይም ዘመናዊ ቦታዎችን መጎብኘት የሚፈልጉ ጥንዶች ፍላጎታቸውን ማሳካት ወደሚችሉበት አገር ቢጓዙ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሆናል፡፡

አንዳንዶች የጫጉላ ሽርሽርን አዲስ ሕይወት መጀመራቸውን ለማብሰር ሲጠቀሙበት፣ ከትዳር አጋራቸው ጋር የበለጠ ለመቀራረብ የሚገለገሉበት፣ ከሠርግ ግርግር እንደ ዕረፍት የሚወስዱትም አሉ፡፡ ስማቸን አይጠቀስ ያሉ ጥንዶች፣ የጫጉላ ሽርሽራቸውን ከሠርግ ግርግር እንደ ማረፊያ ወስደውታል፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት የነበረው ሠርጋቸው በሁለቱም ወገን ያሉ በርካታ ዘመድ አዝማዶች የተጋበዙበት ነበር፡፡ ከሠርጉ በኋላ የሁለቱም ዘመዶች በየቤታቸው ግብዣ ጠሯቸው፡፡ ጥንዶቹ ግን ከመልሱ በኋላ የተዘጋጁት ጥሪዎች አላስፈላጊ ግርግር ናቸው ብለው ስላመኑ፣ ለጫጉላ ሽርሽር ወደ ዱባይ አቀኑ፡፡ የጥንዶቹ የቅርብ ጓደኛ የሆነ የሙሽራው አንደኛ ሚዜም አብሯቸው ሄዶ ነበር፡፡ በንግድ ምክንያት አገሪቷን ያውቋት ስለነበረ ማረፊያ ለማግኘት አልተቸገሩም፡፡

15 ቀን የወሰደውን የጫጉላ ሽርሽር ዱባይ ከተማ በሚገኝ የእንግዳ ማረፊያና ከከተማ ወጥቶ በሚገኝ ሆቴል አሳልፈዋል፡፡ እንግዳ ማረፊያው ጥንዶቹ ሰፊ የግል ጊዜ ያገኙበት ሲሆን፣ የአዲስ ሙሽሮች ልዩ መስተንግዶ ባለው ሆቴል ደግሞ የጥንዶች እራት፣ ጃኩዚና ሌሎችም አገልግሎቶች አግኝተዋል፡፡

በጥንዶቹ እምነት፣ በአብዛኛው ትልቅ ሠርግ የሚደግሱ ሙሽሮች ለጫጉላ ሽርሽራቸው ብዙ ወጪ አያወጡም፡፡ አሁን አሁን ግን ከሠርግ በበለጠ ለጫጉላ ሽርሽር ገንዘብ ማውጣትን የሚመርጡ ጥንዶች ተበራክተዋል፡፡ ሠርጋቸውና የጫጉላ ሽርሽራቸውን አጣምረው ሚዜዎቻቸውን ይዘው ከኢትዮጵያ የሚወጡ ጥንዶች እንዳሉም ይጠቅሳሉ፡፡

የጫጉላ ሽርሽርን ከኢትዮጵያ ውጪ ማካሄድ ቢለመድም፣ በተቃራኒው ከከተማ በመውጣት ወይም ከተማ ውስጥ ባለ ሆቴል በመቆየት የሚያሳልፉ አሉ፡፡ የአቅም ጉዳይ፣ የግል ፍላጎት፣ ጊዜ ማጣትና ሌሎችም ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ዶ/ር ሶፊያ የሱፍ፣ እንደሷው በሕክምና ሙያ ካለ እጮኛዋ ጋር ትዳር የመሠረተችው በቅርቡ ነው፡፡ ጥንዶቹ የጫጉላ ሽርሽራቸውን ከኢትዮጵያ ውጪ ለማድረግ ቢፈልጉም፣ ከሠርጋቸው በኋላ የነበራቸው የዕረፍት ጊዜ አጭር በመሆኑ አገር ውስጥ ተከናውኗል፡፡ መጀመርያ የሄዱት ወደ ላንጋኖ አፍሪካን ቫኬሽን ክለብ ሲሆን፣ ሁለት ቀናት ቆይተው ደብረዘይት ወደሚገኘው ኩሪፍቱ ሪዞርት ተጓዙ፡፡ የጫጉላ ሽርሽሩ ጋብቻቸውን ከማክበር በተጨማሪ ከሥራ ውጥረትም ያረፉበት ነበር፡፡

በቆይታቸው ለአዲስ ሙሽሮች የተዘጋጀ የጀልባ ጉዞ፣ የጥንዶች እራትና ካምፕ ፋየር አድርገዋል፡፡ መኝታ ክፍላቸውም በልዩ መልኩ ተውቦ ነበር፡፡ ወደ 20,000 ብር ገደማ ያወጡበት የጫጉላ ሽርሽር አንዳቸው ለሌላቸው ጊዜ ሰጥተው ያሳለፉት አስደሳች ወቅት እንደነበር ትናገራለች፡፡

በዶ/ር ሶፊያ እምነት፣ የጫጉላ ሽርሽር በተቻለ መጠን ልዩ ቢሆን ይመጣል፡፡ በጥንዶች መካከል ያለው የሞቀ ስሜት የበለጠ እንዲጠናከርም ወቅቱ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ጥንዶች ከጫጉላ ሽርሽራቸው ባሻገርም በተወሰነ ጊዜ ልዩነት ወደተለያዩ አገሮች እየሄዱ ቢዝናኑ ፍቅራቸው ዘወትር የሞቀ እንዲሆን ይረዳቸዋል ትላለች፡፡

የጫጉላ ሽርሽር ለአዲስ ሙሽሮች የተለየ መስተንግዶ ለሚያዘጋጁ የአገር ውስጥና የውጪ መዝናኛዎች እንዲሁም አስጎብኚዎች ጥሩ የቢዝነስ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በተመሳሳይ የሠርግ ፎቶ አንሺዎችንም ማንሳት ይቻላል፡፡ የሶል ኢሜጅስ ፎቶ ቤት ባለቤት ሰለሞን ቦጋለ፣ አብዛኛውን ጊዜ የሠርግ ፎቶግራፎችን ያነሳል፡፡ ጥንዶች ኢትዮጵያ ውስጥና ውጭም የጫጉላ ሽርሽር ሲያካሂዱ አብሮ እየሄደ ፎቶ ያነሳል፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የጫጉላ ሽርሽራቸውን ከኢትዮጵያ ውጪ የሚያደርጉና ፎቶ አንሺም ይዘው የሚሄዱ ጥንዶች ቁጥር እንደጨመረ ይናገራል፡፡

የጫጉላ ሽርሽራቸውን ከኢትዮጵያ ውጪ ከሚያደርጉ መካከል ሆስተሶችና ዳያስፖራዎች ይገኙበታል ይላል፡፡  ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሀብታሞች ከጫጉላ ሽርሽር በበለጠ ለሠርግ ትኩረት ይሰጣሉ ብሎ ያምናል፡፡ ገንዘብ ያላቸው ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ሲድሩ ውጪ አገር የጫጉላ ሽርሽር እንዲያደርጉ የሚያበረታቱና ወጪውን ሸፍነው የሚልኩም ገጥመውታል፡፡ ጥንዶች ዘወትር የሚያስታውሱት በፎቶና ቪዲዮ የሚቀመጥ ታሪክ እንዲኖራቸው፣ በሠርጉ ወቅት ከቤተሰብ፣ ጓደኞች፣ ዘመዶች ጋር ከሚያሳልፉት ጊዜ ባልተናነሰ ጫጉላ ሽርሽራቸው ልዩ ቦታ ቢሆን ይመረጣል ይላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...