Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ሕገወጥ ንግድ ለአሸባሪዎች የገቢ ምንጭ መሆኑ ተገለጸ

የዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ሕገወጥ ንግድ ለአሸባሪዎች የገቢ ምንጭ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

ከዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ሕገወጥ ንግድና ዝውውር በየዓመቱ እስከ 19 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝበትና ገንዘቡም ለአሸባሪዎችና ለፀረ ሰላም ቡድኖች እንደሚውል የኢንተርፖልንና የኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አኒማል ዌልፌርን ጠቅሰው የሆርን አፍ አፍሪካ ዋይልድ ላይፍ ኢንፎርስመንት ኔትወርክ (ሐዊን HAWEN) ስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አስታወቁ፡፡

ሰብሳቢው አቶ ዳንኤል ጳውሎስ ኔትወርኩን አስመልክቶ ከሪፖርተር ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ፣ በተለይ በናይጄሪያ የሚንቀሳቀሰው ቦኮሃራም አሸባሪ ቡድን፣ ከዝሆን ጥርስና ከአውራሪስ ቀንድ ሽያጭ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኝ ይህም በኢንተርፖል እንደተረጋገጠ ተናግረዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ የሚካሄደውም ሕገወጥ የዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ንግድና ዝውውር አልሸባብን ይደግፋል ተብሎ ከመታሰቡም በተጨማሪ በዱር እንስሳቱ ሕይወት፣ በማኅበረሰቡና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ እጅግ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ፣ የአገራትን ሰላምና ጸጥታ እያወከ ይገኛል ብለዋል፡፡

ስር የሰደደውንና ለአሸባሪዎች የገቢ ምንጭ በመሆንም የሚያገለግለውን ሕገወጥ የእንስሳት ዝውውር ለመግታት በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ የሰባት አገሮች ተወካዮች በ2004 ዓ.ም. ተወያይተው፤ በተለይ በዝሆን፣ በነብርና በፖንጎሊን ላይ ኃይለኛ ተፅዕኖ ያሳደረውን ሕገወጥ የዱር እንስሳት ዝውውር ችግር ለመከላከል “ሆርን ኦፍ አፍሪካ ዋይልድ ላይፍ ኢንፎርስመንት ኔትወርክ” (ሐዊን) መስርተዋል፡፡

ኔትወርኩን በይፋ ሥራ ለማስጀመር የሚረዳ መመሥረቻ ሰነድ የሚያዘጋጅ ስትሪንግ ኮሚቴ የተመሰረተ ሲሆን ሐዊም ይፋ የሚሆነው ሰነዱ በሚኒስትሮች ደረጃ ከተፈረመ በኋላ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሰብሳቢነት፣ ኡጋንዳ በጸሐፊነት ሆነው የሚመሩት ስትሪንግ ኮሚቴ፣ የኔትወርኩን ረቂቅ መመሥረቻ ሰነድ አዘጋጅቷል፣ የኮሚቴውም አባላት ናይሮቢ ኬንያ ተሰብስበው ረቂቁን ገምግመዋል፡፡ አባል አገሮቹ አስተያየታቸውን ለስትሪንግ ኮሚቴው በጽሑፍ እንዲያሳውቁ ረቂቅ ሰነዱ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እንዲደርሳቸውም ተደርጓል፡፡

ሰነዱ ከተላከላቸው አባል አገሮች መካከል ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳና ጅቡቲ አስተያየታቸውን በጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሶማሊያ፣ ሶማሌላንድና ደቡብ ሱዳን አስተያየታቸውን ለመላክ በሂደት ላይ መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡ ለኬንያ የተላከው ሰነድ ግን በኬንያ በኩል እንዳልደረሰ በመገለጹ ዳግም እንደሚላክ፣ ከአገሮቹ አብላጫው ግብረ መልስ ከሰጡና ከፀደቀም፣ ኔትወርኩ በይፋ ሥራ እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡

የሐዊ ሥራ መጀመር፣ ሕገወጥ የዱር እንስሳት ንግድና ዝውውርን በጋራ ለመከላከል፣ መረጃ ለመለዋወጥና የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ አገሮች የዱር እስሳትና ውጤቶቻቸው ሕገወጥ ንግድና ዝውውርን ለመከላከል ተቀናጅተው እንዲሰሩ ሐሳቡን ያመነጨው አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ነው፡፡ ኤምባሲው ይህንኑ ሐሳብ መሠረት ያደረገ ጥሪ ኤርትራን ጨምሮ ለስምንቱም የአካባቢው አገሮች ያስተላለፈ ሲሆን ከኤርትራ በስተቀር ሁሉም ጥሪውን ተቀብለው እየሠሩ መሆኑን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...