ሰላም! ሰላም! ይብላኝ ‘ኧረ ለማን ልንገረው?’ እያለ በቫይበር፣ በፌስቡክና በዋትሳፕ በሩቅ ወዳጅ ላበደው ስል ሰነበትኩ። ‘ምን አስባለህ?’ የሚል ካለ መቼም ስማርት ፎን ከመግዛት ቅያሪ ሱሪ በመግዛት ሒደት ውስጥ አልፎ ያልጨረሰ አልሞት ባይ ተጋዳይ መሆን አለበት። እውነት ነዋ። መደብ ሳናበጅ የአጎዛ መአት ከመከመር አንደኛውን በጎቹን ከነነፍሳቸው ማሰንበት ይሻል ነበር እኮ። ሆ! አሁን እስኪ ሬሳውን ለመንካት ስለት ማስገባት ሥራችን በሆነበት በዚህ ጊዜ በግ በነፍሱ አግኝተን ስናባብል ታየኝ። ተውኝማ እናንተ! ጉድ በዛ እያላችሁ ወጥ አታስረግጡኝ እስኪ። ግን እንዲያው በእምዬ ይሁንባችሁ ወጥ እየረገጠ ያስቸገራችሁ ሰው የለም? የእኔ ነገር የሚላስ ጠፍቶ ስለሚረገጥ ወጥ ታወራለህ የሚለኝ እንደማይጠፋ እያወቅኩ ምን እንደሚያስወጠውጠኝ አይገባኝም። ምናልባት የክንብንብ ኑሯችን እያደር ሲንር ግልጽነት ከተጠያቂነት ያድናል የሚሏት ቋንቋ ብቻዋን ግልጽ ሆና ሠርታልኝ ይሆናል። ተሠርተን ሳንጨርስ የሚሠራልን ተፈጥሮ ብዛቱ አለመቆጠሩ። እንዲያው እኮ!
መቼም ያለምክንያት ሰው ይብላኝ እንዳይል ታውቃላችሁ። በእነ አምታታው በከተማ፣ በጠራራ ፀሐይ ገንዘቡን ተበልቶ ወላ ሽማግሌ ወላ ሕግ ያላስመለሱለት ካልሆነ በቀር ማለቴ ነው። ይኼን ስላቸው ለባሻዬ፣ “እህል እንጂ ገንዘብ ይበላል እንዴ?” ብለው ለአገሩ እንግዳ ሆኑብኝ። ይኼኔ ልጃቸው ደለብ ያለ መጽሐፍ እያነበበ ፈንጠር ብሎ ተቀምጦ ነበር። ምን ቢል ጥሩ ነው? “በእህሉ ፈንታ ገንዘቡ ያለ ዋጋ በየቦታው ተዝረክርኮ ሲገኝ ታዲያ ሰው ምን ይብላ?” አይል መሰላችሁ? ባላየ ባልሰማ ባልነበረ ቡና ሳላከትም ወጥቼ ላጥ ስልላችሁ ማኪያቶ 30 ብር እየሸጠ የዋይፋይ ‘ኔትወርኩን’ መሰብሰብ ያቃተው ገጽታ ገንቢ ፎቅ ሥር ቆሜያለሁ። እንጃ ለምን እንደቆምኩ። ምናልባት ከእኔ ከሰውዬው ልጅ እሱ (የብሎኬቱ ልጅ) ከገንቢ ገጽታው ያጋባብኝ ይሆናል ብዬ ይሆናላ። የሚሉንን ቀርቶ የምንለውን አጥርተን ማወቅ ያቃተን ጊዜ ላይ መሆናችንን ረሳችሁት? መቼ ይሆን ግን መርሳት መርሳትን ራሱን የሚረሳው ጎበዝ? እንደ ዘበት የተረሳሳነው በዛን አቦ!
ሆ እላለሁ! ሆ! . . . እዚያ በቁመት ካልሆነ በቀር በውበት ግራር የማያስንቅ ልማታዊ ሕንፃ ሥር ቆሜ። ስልኬን ለካ ያ ‘ዋይፋይ’ ለክፏት ሳትናገር ሳትጋገር ከደጅ እስከ ጓዳዋ ተከፋፍታለች። በነገራችን ላይ የመረብ ዘመን አይመስላችሁም መደፋፈሩን ያናረው? እ? እውነቴን እኮ ነው። እንጃ በስንት ፐርሰንት መሆኑን ግን። ጥያቄዬ እኮ አስተያየት ነው። ታዲያ ወጋችንን የታዳጊ አገሮች የኢኮኖሚስቶች ማኅበር ባናስመስለው ደስ ይለኛል። ደግሞ አንበርብር ምንተስኖት ካድሬ ነው በሉ አሉዋችሁ። ዳሩ መቼ ቀረልኝ። ጢን ጢን ብሎ ስልኬ አስነጠሰችላችሁ። አውጥቼ ሳይ “አፋልጉኝ” ይላል። ‘ማን ምን ጠፍቶት ይሆን?’ አላልኩም። እንዴት እላለሁ? ወገኔ በየአቅጣጫው የጫረው የትስስርና የፍቅር እሳት ጠፍቶበት ዓይኑ በቁጭት ጭስ እያደር እያነሰ እያየሁ እንዴት ብዬ።
ወዲያው ወረድ ብዬ ሳነብ፣ “አገሬ ኢትዮጵያ የዛሬ 24 ዓመት ከቤቷ እንደወጣች አልተመለሰችም። ያለችበትን ያየ ወይም የሰማ ቢጠቁመን ወሮታውን እንከፍላለን፤” ይላል። እውነቴን ነው የምላችሁ ካርቱን አለመሆኔ ጠቀመኝ እንጂ፣ ዓይኔ ለተወሰነ ሰከንድ ከቦታው ተነቅሎ ወጥቶ የምሆነውን ሳጣ ወዳጅና ጠላት ቶምና ጄሪን በገሃድ አገኘሁ ብሎ የቱሪስት መስህብ ሆኘላችሁ እናንተም ዜናውን ትሰሙ ነበር። ለነገሩ መርጠው እየዘገቡ ሀቅ ሀቁን መስማት አልቻልንም እየተባለ ነው። እንግዲህ ማን ቶም ማን ጄሪ ነው የሚለውን የሒሳብ ጨዋታ ትቼላችኋለሁ። መቼም የሹም ሽር፣ የባንክ አካውንት ከማስላት የሰንጠረዥ ጨዋታ ይኼ ይሻላል . . . በበኩሌ። አንዳችን ያንዳችን ግብር ከፋይ ብንሆን ኖሮ ባለቀ ሰዓት ጦር የሚያስንቅ የሠልፍ ትዕይንት በማድረግ ዓለምን ጉድ ይለን ነበር ግን! እንዲያው ለጨዋታ ነው!
የሚገርመኝ ነገር ታዲያ እንዲህ በነበር ብዙ ነገር ጥለን የማለፋችንን ያህል የዕድሜ ጣሪያችን በአርባ ዙሪያ መሽከርከር አልነበረበትም። ባሻዬ አዘውትረው፣ “ሙሴ በአርባ ዓመቱ ለአገልግሎት ሲሰማራ፣ የሠለጠነው ዓለም ከአርባ ዓመቱ በኋላ የቤተሰቡንና የአገሩን አደራ በዕውቀትና በሙላት ተሸክሞ መሮጥ ይጀምራል፣ እኛ እናሸልባለን፤” ይሉኛል። “ምን ያደርጉታል ብለው ነው የአርባ ቀን ዕድላችን ነዋ፤” እያልኩ እኔ ደግሞ ዘመንን በቀን አጣፋላቸዋለሁ። እንዲያው ሌላ ሌላው ቢቀር የማጣፋት ታለንት ቸግሮን አያውቅማ። ልብ አድርጉልኝ ታዲያ። ያቺን ‘አፋልጉኝ’ አረሳኋትም። እንዲህ ያለው ያፋልጉኝ ስላቅ ደግሞ አይመቸኝም። በቃ አይመቸኝም። ስለዚህ ለምን የባሰ አላጣፋቸውም አልኩና “ያለችበትን አውቃለሁ” ብዬ ጻፍኩ። አዳሜ በድብርቱ መጠን በሳቅ እስክተረትረው እየጠበቀ ነው።
“በየት ወዴት አለች?” ጥያቄ ተንጋጋ። እኔም ኮስተር ብዬ፣ “ያለችበትን ስጠቁምና ስታገኙዋት ይህቺን ትመስላለች። የኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤትነት የተመዘገበ ዜጋ የላትም! ዓባይም ግንድ ይዞ መዞሩን እንደቀጠለ ነው፣ ህዳሴ የለም፣ ባቡር የለም፣ ወዘተ፣ ወዘተ” እያልኩ ሳልጨርስ የፍረጃና የስድብ ውርጅብኝ አስተናገድኩ። በካድሬነት ታማሁ ያልኳችሁም ይኼን ጊዜ ነው። ቆይ ግን እኔ ምለው የአገር ካድሬ መሆንም ያስጠቁራል እንዴ? የምሬን እኮ ነው። ይኼ ‘ቫይበርና ፌስቡክ’ በቃ በተቀባባ ማንነት መረብ ለመረብ እያደራጀ አገልግሎቱ ሥራ ለማስፈታት ሆኗል ማለት ነው? የኢትዮ ቻይና የኢኮኖሚና የ‘አይዲዮሎጂ’ ልምድ ልውውጥ ‘እውነተኛ የልማት አጋር ከማኅበራዊ ድረ ገጾች የታቀበ ነው’ ቢለን ምን ልንሆን ነው? እንደፈረደብን ‘ኮሙዩኒዝም ይውደም!’ እያልን በየሰርጡ ፖስት ማድረጋችን ይቀራል ያን ጊዜ። በበኩሌ ኮብልስቶን ሳይሰማኝ ‘ታጥቦ ጭቃ’ ብያለሁ!
እናላችሁ ሥራዬን ትቼ በዚያው ‘ላይክና ኮሜንት’ ሳደርግ ሰዓታት ነጎዱ። ድንገት አንድ ሰው የሌለው ዳያስፖራ፣ “እባካችሁ ከሰላሳ እስከ አርባ ሺሕ ብር የሚከራይ መኖሪያ ቤት ካወቃችሁ አሳውቁኝ፤” ብሎ ስልኩን ቁልጭ አርጎ ጽፎ ለጠፈ። የዛሬ ጊዜ እንጀራ ከቀኝ ይጀምር ከግራ በየት በየት አድርጎ ዞሮ እንደሚቀባ አታውቁትም። “ያልተቀባ ሲጀምር ምኑን ያውቀዋል?” የሚሉኝ ባሻዬ ትዝ አሉኝ። ባሻዬ ደግሞ ሰሞኑን መለኮታዊ ፍቺና እሳቤዎቻቸው ጨምረዋል። ለነገሩ ወደው አይመስለኝም። እንደ እሳቸው ትረካ ከቅዱሱ መጸሐፍ ሌላ የማይዋሽ የማይዘላብድ አዋጅና ራዕይ አጣሁ ስለሚሉ ነው። የእምነት ነፃነትና እኩልነት በተከበረባት አገር ይኼን በተመለከተ ምንም ወግ መቀመር የሚቻል አይመስለኝም። ብቻ ምሁሩ ልጃቸው ይኼን አባባላቸውን ሲሰማ፣ “ለማወቅ አለማወቅን ማመንና መቀበል እንጂ መቀባትን ምን አመጣው?” እያለ ይሟገታቸዋል። አባትና ልጅን እዚህ ተወት እናደርጋቸዋለን።
በበኩሌ ግን አላውቅምን ካለማወቃችን የተነሳ ፖስታ ቤት ሲጠይቁን ፖሊስ ጣቢያ እየጠቆምን ስንቱን ‘ነገር ባይኖርህ ምን አቅለብልቦ አመጣህ’ እያስባልን አስላጭተነው ይሆን እያልኩ አስባለሁ። ይኼን እያሰብኩ ወዲያው ወደ ዳያስፖራው የፌስቡክ ደንበኛዬ ደወልኩ። እጄ ላይ ሁለት ቤቶች ነበሩ። አሳየሁት፣ ሳያገነግን ተስማማ። “ቤቱን ግን በደንብ አይተኸዋል?” አልኩት በችኮላ የወሰነ ስለመሰለኝ ደግሞ ነገ ዞሮ በፌስቡክ ስሜን እንዳያጠፋው ሰግቼ። “ምን ምርጫ አለኝ? ነገ ትመጣለች፣ ቀን የለኝም፤” አለኝ። “ማን ናት?” እንደ ዘበት የወረወርኩት ጥያቄ። “ሚስቴ ናታ። በስንት ጭንቅ ስንት ወጪ አውጥተን የሰው ማህፀን ተከራይተን ልጅ ስናገኝ ሆቴል ላሳርፋት ደግሞ?” አይለኝም?! ደግ የለ ክፉ የለ ዲዳ ሆኜ ዋልኩ። ‘ኖ ኮሜንት!’ ብዬ ፖስት ሳደርግ ላይክ አድርጉልኝ እሺ!
በሉ እንሰነባበት። እንዲያው ነገሩ እንደገረመኝ እዳፈዘዘኝ ሰነበተ። ማንጠግቦሽ በወጣሁ በገባሁ ቁጥር “ምን ሆነሃል አንተ ሰውዬ?” እያለች ታደርቀኛለች። ሰው ሆኖ “ምንም አለመሆን አለ እስኪ?” ማንጠግቦሽ ደግሞ አንዳንዴ። ትክት እያለኝ ቴሌቭዥን እየቀያየርኩ አንድ ፕሮግራም በቅጡ ሳላይ፣ ዜናም ሆነ ዘጋቢ ፊልም እንዳጎረሱኝ እየዋጥኩ ውዬ ከማደሬ፣ ‘ሲኤንኤን’ በአገራችን ቡና ‘ፌመስ’ ስለሆነው ‘ስታርባክስ’ ልዩ ዘገባ ሲያቀርብ አየሁ። ከድብርቴ ነቃ ብዬ ደግሞ ምን ሊሉ ነው? በጀበና ‘ቴክአዌ’ መሸጥ ጀምረው ጀበናንም ወሰዱብን?’ ብዬ ስከታተልላችሁ፣ በተከታተፈ ትርጉም ድርጅቱ የቴክአዌ ዕቃውን ለመጪው ገና ልዩ መስህብ እንዲኖረው ባላስፈላጊ ወጪ እንደተጠበበና ይኼም ጎልቶ መወራቱ ሲተች ሰማሁ። ጆሮዬ ቆመ። ወደ ባሻዬ ልጅ ደውዬ ‘ሲኤንኤን’ አስከፈትኩት። ፈጣሪ ይመስገንና የትርጉም ስህተት አልሠራሁም። ባሻዬ እንዲህ ስል ቢሰሙ መቼም፣ “በፀጋው ጭምር እንጂ በትምህርት ብቻ እግሊዝኛ አይቻልም፤” ይሉ ይሆናል።
ጠቅለል ሳደርገው ታዲያ ‘ሲሪያ ስንቱ የሚበላው የሚጠጣው አጥቶ ጎጆው ፈርሶ ተበትኖ፣ በየቦታው በየአገሩ ድርቅ ረሃቡ መፈጠርን እያስጠላ እያየን እየሰማን እንዴት ለሚወረወር የካርቶን ኩባያ መስህብ ፈጠራ ይወራል? ይታሰባል?’ የሚለው አጨቃጫቂ ርዕስ እኔንና የባሻዬን ልጅ ብዙ ብዙ አስወራን። አስቆዝሞኝ ስያሜ ያጣሁለትን የማህፀን ኪራይ ጉዳይ ሳነሳለት ደግሞ፣ “ይኼ ምን ይገርማል አንበርብር? ሰውን ከነሙሉ አካሉ፣ እምነቱ፣ ስሜቱና ነፍሱ ያለዋጋ ሰው በሰው እየተገዛ ስለአንድ የአካል ክፍል ኪራይ ታወራለህ?” ብሎ ኮረኮመኝ። ሰው መሆን እንደ ዘንድሮ ግራ ገብቶኝ አያውቅም ጎበዝ። አንዱ ሰላሙን አጥቶ አኅጉር በባዶ ሆዱ ያቋርጣል። ሌላው ደሴት ላይ እኮ ቤት የለኝም እያለ ይጨነቃል። እዚያ በውኃ ጥም ወገን ሲያልቅ፣ እዚህ ውስኪ ሲራጭ በግማሽ ሌሊት ዕድሜ ኩላሊትና ጉበት የአጋዥ ያለህ እያሉ ከጥቅም ውጪ ይሆናሉ። የቱ ተነስቶ የቱ ይተዋል እናንተ? በበኩሌ ላይታረቁ በተቃረኑ ተቃርኖዎች ተዝለፍልፌያለሁ። ከዚህ ሁሉ ግን ‹‹ኖ ኮሜንት›› ማለት ሳይሻል አይቀርም፡፡ ደህና ሰንብቱ! መልካም ሰንበት!