Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የማር ምርት በስፋት ወደ አውሮፓ ለመላክ ተዘጋጅቻለሁ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ሐንዳይ መኪኖችን ለመገጣጠም እያሰበ ነው

ታዋቂው አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እየተሳተፈባቸው ያሉት የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች በማብዛት፣ የማር ምርት ወደ አውሮፓ ገበያ በስፋት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በደቡብ ክልል ሸካ አካባቢ እያለማ ባለው የቡና እርሻው ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ማር መሰብሰብ ጀምሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለአገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

በተለይ ጀርመንና ሆላንድን ጨምሮ የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ገበያን ያለመ ሲሆን፣ እስካሁን ለሙከራ ከላካቸው የማር ናሙናዎች ተቀባይነት ማግኘቱንና ተስፋ ሰጪ ምልክቶችን እንዳየበት ኃይሌ ገልጿል፡፡

‹‹በአገራችን ያለው ማር በጥራት ከፍተኛውን ደረጃ የያዘ ነው፡፡ ይህም ደግሞ ለናሙና ከላክናቸው ውስጥ በጀርመንም ሆነ በሆላንድ ያገኘናቸው ደንበኞቻችን በጣም ወደውታል፡፡ አሁን የሚቀረን የእነሱን ደረጃ አሟልቶ በስፋት መላክ ብቻ ነው፤›› ሲል አስረድቷል፡፡

ነገር ግን የማሩ ጥራትና ተወዳጅነት ብቻ ሳይሆን የውጭ አገር ደንበኞች በአስተሻሸግና በማጓጓዝ ላይ ጥብቅ የሆነ መመዘኛ ስላላቸው በስፋት ወደ ውጭ ገበያ ለመግባት እስከ አንድ ዓመት እንደሚፈጅበት ኃይሌ ተናግሯል፡፡ ይሁን እንጂ በዓመት ምን ያህል መጠን ያለው ማር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ እንዳለው ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡

ባለሙያዎችን ወደ ውጭ በመላክ የገበያ ጥናት ማድረጉን የሚገልጸው ኃይሌ፣ በምርት በኩል ምንም ዓይነት እጥረት የማይፈጠርበት መሆኑን፣ የማር ማጣሪያውን ሙሉ በሙሉ ተክሎ ወደ ሥራው ለመግባት ግን የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳጋጠመው ተናግሯል፡፡

በሸካ በሚገኘው የቡና እርሻ ውስጥ ብዛት ያላቸው የንብ ቀፎዎችን በመስቀል ማሩን እየሰበሰበ ሲሆን፣ እስካሁን ሦስት ዓይነት የማር ምርቶችን እያመረተና በአገር ውስጥ ገበያ እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ በ1,500 ሔክተር መሬት ላይ ከተተከለው ቡና ችግኝ ውስጥ፣ በአሁኑ ጊዜ 200 ሔክተር የሚሆነው ለምርት መድረሱንና ውጤቱም ‹‹አርኪ›› ደረጃ ላይ መድረሱን አትሌቱ ጠቁሟል፡፡

በተያያዘ ዜናም አትሌት ኃይሌ በሚቀጥለው ዓመት ታዋቂዎቹን የኮሪያ የሐንዳይ መኪኖች በአገር ውስጥ ለመገጣጠም መስማማቱንና በቅርቡ መሬት ከተረከበ፣ ወደ ፋብሪካ ግንባታ እንደሚገባ ጨምሮ ገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ለቡ አካባቢ መሬት ለማግኘት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ውሳኔ እየተጠባበቀ መሆኑን ጨምሮ አስረድቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች