Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳሸን ቢራ ሁለተኛ ፋብሪካውን ያስመርቃል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዳሸን ቢራ በሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ላለፉት ሦስት ዓመታት ከአዲስ አበባ ከተማ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የደብረ ብርሃን ከተማ የገነባው ሁለተኛው ቢራ ፋብሪካ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እሑድ ኅዳር 5 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚመረቅ ፋብሪካው አስታወቀ፡፡

‹‹በደብረ ብርሃን የተገነባው አዲሱ የዳሸን ቢራ ፋብሪካ አጠቃላይ ምርቱን በሦስት እጥፍ ያሳድገዋል፤›› ሲሉ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴቨሊን ሐይንስዋርዝ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ አዲሱ የቢራ ፋብሪካ ምርት ጋር በተያያዘ ፋብሪካው ከዚህ ቀደም ይደርስባቸው ከነበሩ አካባቢዎች በተጨማሪ፣ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍል ለመግባት ማቀዱም ተገልጿል፡፡ ‹‹በተወሰነ መልኩ እስከ አሁን ድረስ ዋነኛ የገበያ ድርሻችን የነበረው የሰሜኑ ክፍል ነበር፡፡ በዚያም ቢሆን የፍላጐቱን ያህል ማቅረብ አልቻልንም ነበር፡፡ አሁን ግን ከሰሜኑ ክፍል በተጨማሪ አዲሱ ፋብሪካ ለአዲስ አበባ ቅርብ እንደመሆኑ መጠን፣ የአዲስ አበባንና የደቡቡን ክፍል ፍላጐት ለማሟላት ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፤›› በማለት ዋና አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ ይህ አዲሱ የቢራ ፋብሪካ በቀጥታ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጐች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጐቹ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡

ዳሸን ቢራ ፋብሪካ በጥረት ኮርፖሬት ሥር ከሚተዳደሩት ድርጅቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2000 ነው የተመሠረተው፡፡ ድርጅቱ እ.ኤ.አ. በ2012 ከድርሻው ላይ 51 በመቶ የሚሆነውን ዱዌት ለተሰኘ የእንግሊዝ ድርጅት ሸጧል፡፡

ጥረት ኮርፖሬት የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ በብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ብአዴን) ሥር የነበሩ ንብረቶችን በማሰባሰብ የተቋቋመ ኢንዶውመንት ነው፡፡

ጥረት ኮርፖሬት በአሁኑ ወቅት ጥቁር ዓባይ ትራንስፖርት ድርጅት፣ ዘለቀ የእርሻ ቁሳቁሶች ማምረቻ፣ ዳሸን ቢራ ፋብሪካ፣ አምባሰል የንግድ ሥራዎች ድርጅት፣ ጣና ኮሙዩኒኬሽንስ፣ በለሳ ሎጂስቲክስና ትራንስፖርትና ጎንደር ብቅል ፋብሪካን በባለቤትነት ያስተዳድራል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች