Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየጦር መሣሪያ ቁጥጥር ሕግ እንዲወጣ ተጠየቀ

የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ሕግ እንዲወጣ ተጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ የግል የፀጥታና የደኅንነት ኩባንያዎች የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ሕግ አለመኖሩ ቁልፍ የሆነ ችግራቸው መሆኑን አስታወቁ፡፡ ከኅዳር 1 እስከ ኅዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተካሄደው ክልላዊ ኮንፈረንስ ላይ እንደተገለጸው፣ የሕጉ መውጣት ለኢንዱስትሪው ዕድገት አስፈላጊ ነው፡፡

የስዊዘርላንድ መንግሥት፣ የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናትና መቀመጫውን ጄኔቭ ያደረገው ዲሲኤኤፍ በጋራ ያዘጋጁት ስብሰባ ዋና ዓላማ የግል የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ላይ የሚደረገው ቁጥጥርና አመራር ላይ ልምድ ልውውጥ ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም ሞንትሮ ሰነድ የተሰኘውና የግል የፀጥታና የደኅንነት ኩባንያዎች እንቅስቃሴ ላይ ሕጋዊ ድንጋጌዎችን፣ እንዲሁም መልካም ተሞክሮዎችን ያቀፈው ሰነድ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ ነበር፡፡

ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ወደ 100 የሚጠጉ የግል የፀጥታና የደኅንነት ኩባንያዎች እንዳሉ የጠቆመ ሲሆን፣ እንቅስቃሴያቸውን የሚገዛ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን ግን እንደ ቁልፍ ተግዳሮት ተለይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/2004 አንቀጽ 6(28) የጥበቃ አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ የግል ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥ ይደነግጋል፡፡ ይሁንና በርካታ ቢሊዮን ብሮችን የሚያንቀሳቅሰው ኢንዱስትሪ የጦር መሣሪያ ቁጥጥርን ጨምሮ ዝርዝር የሕግ ድንጋጌ እንደሚያስፈልገው ታምኖበታል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ በአቶ ሰለሞን ሐሰን የቀረበው ጥናት እንደ ስብሃቱና ልጆቹ የጥበቃ አገልግሎት ያሉ የግል ተቋማት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ ቢሆኑም፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በማደጉ አገልግሎቱ ላይ ፍላጐት እያየለ የመጣው ከ1997 ዓ.ም. በኋላ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ አቶ ሰለሞን በኢንዱስትሪው ውስጥ በባለቤትነት የተሰማሩ አካላት የቀድሞ የፖሊስ መኮንኖች፣ ወታደሮች፣ የግል የደኅንነት ተቋማትን በአማካሪነት ያገለግሉ የነበሩና የቢዝነስ ሰዎች እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ኩባንያዎቹ በጥበቃ፣ በቪአይፒ ጥበቃ፣ በቁጥጥር፣ በትራንስፖርት፣ በመታወቂያ ፍተሻ፣ በካሜራ ክትትል፣ በንብረትና በመሠረተ ልማት ጥበቃ ላይ የተሰማሩ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ዘርፉ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ሲገልጹም የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ የሙያ ደረጃውንና ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን አለመጠበቅ፣ ከመደበኛው ፖሊስ ጋር ያላቸው ግንኙነት የላላ መሆን፣ የሠራተኞቻቸው በቂ ሥልጠና አለማግኘትን ጠቅሰዋል፡፡ እርስ በርስ ያላቸውም ግንኙነት አለ ለማለት የሚቻል እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስም የተቋማቱ እንቅስቃሴ ላይ ክትትል የሚያደርግና አጥቂዎቹን የማይቀጣ መሆኑም ሌላ ችግር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹የፌዴራል ፖሊስ ለዚህ ተግባር የሚውሉ በቂ ሠራተኞች የሉትም፡፡ ወደ 500,000 የሚጠጉ ሠራተኞችን የቀጠረው ዘርፍ ላይ ክትትል የሚያደርጉ 20 ሠራተኞች ብቻ ነው ያሉት፡፡ በሙያው ደረጃዎች ላይ ክትትል አለመደረጉ ጤናማ ያልሆነ ውድድር የጋበዘ ሲሆን፣ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎትም እንዳይሰጥ አድርጓል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ሰለሞን ኢትዮጵያ የሞንትሮ ሰነድን ብታፀድቅ ከእነዚህ ተግዳሮቶች የተወሰኑት እንደሚቀረፉ ተስፋ አድርገዋል፡፡

ከኮንፈረንሱ የጋራ አዘጋጆች አንዱ የሆነው የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም ዳይሬክተር አቶ ኪዳኔ ኪሮስ፣ ጉዳዩ የፖሊሲና የሕግ አውጪዎችን ተገቢ ትኩረት እንዲያገኝ አበክረው እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...