Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አለ በጅምላን ሲያስተዳድር የቆየው ኤቲ ኪራኒ ኮንትራቱን አጠናቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፋይናንስ እጥረት አለ በጅምላ ተልዕኮውን አላሳካም ተብሏል

አለ በጅምላን ላለፉት ሁለት ዓመታት በግማሽ ሲያስተዳድር የቆው ዓለም አቀፉ አማካሪ ድርጅት ኤቲ ኪራኒ ኮንትራቱን ባለፈው ሳምንት አጠናቀቀ፡፡

የአለ በጅምላ የቦርድ ሰብሳቢና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረአብ ባለፈው ዓርብ በተካሄደው የሽኝት ፕሮግራም ላይ በመገኘት፣ አማካሪ ድርጅቱ ላከናወናቸው ተግባራት ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

መንግሥት አለ በጅምላን የመሠረተበት ምክንያት በጅምላ ንግድ ዘርፍ መግባት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምሳሌ ለመሆን እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን በትክክል ማረጋገጥ ከተቻለ አምራቹንም ሸማቹንም በእኩል መጥቀም እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ኤቲ ኪራኒ ባለፉት ሁለት ዓመት በግማሽ አለ በጅምላን በማስተዳደር መሠረቱን የያዘ ድርጅት እንዲሆን እንዳደረገው፣ ወደፊትም በጥሩ ሁኔታ የሚያድግ ድርጅት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ነዋይ አለ በጅምላ መሠረቱን የያዘ ድርጅት ነው ቢሉም፣ የተቋቋመበትን ዋጋ የማረጋጋትና በአምስት ዓመት ውስጥ በመላ አገሪቱ ከ36 በላይ የጅምላ መሸጫ መጋዘኖችን የማስፋፋት ተልዕኮ መወጣት የሚችልበት አቋም ላይ አይደለም፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት አለ በጅምላ የከፈታቸው የጅምላ መሸጫ መጋዘኖች ስድስት ብቻ ናቸው፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአለ በጅምላ ዋና ሥራ አስኪያጅና የንግድ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ኑረዲን መሐመድ፣ አለ በጅምላ የራሱን ኢንቨስትመንት ካፒታል ይዞ ሳይሆን መንግሥት በፈቀደለት ካፒታል መጠን የሚንቀሳቀስ በመሆኑ፣ ዕቅዶቹን ሙሉ በሙሉ ሊያሳካ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

አለ በጅምላ የተሰጠውን አጠቃላይ ተልዕኮ ለመወጣት ቢያንስ የገበያውን ድርሻ 20 በመቶ መያዝ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከገበያው ሁኔታ ጋር የሚጣጣም የኢንቨስትመንት ካፒታል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

አለ በጅምላን ለማቋቋም በተደረገው ጥናት መሠረት በ250 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተመሥርቶ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ካፒታሉ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ኑረዲን፣ ወደ ትግበራ ሲገባ ግን አንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ቀድሞ ሊኖረው ይገባ እንደነበር መገምገም መቻሉን አስረድተዋል፡፡ ይህንንም ሲብራሩ አንድ የአለ በጅምላን መጋዘንን ለመመሥረት 100 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ፣ በመሆኑም ስድስት መጋዘኖች ለማቋቋም 600 ሚሊዮን ብር ማለትም ከድርጅቱ ካፒታል በላይ እንደፈጀ ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህንን ማድረግ የቻልነው 596 ሚሊዮን ብር ከባንክ ተበድረን፣ እንዲሁም ከመንግሥት ያገኘነውን 250 ሚሊዮን ብር ይዘን ብቻ ነው፤›› ብለዋል አቶ ኑረዲን፡፡

ለምሳሌ ያህል አለ በጅምላ አንድ ሊትር ዘይት የሚያቀርበው በ51 ብር ሲሆን፣ ገበያ ላይ ግን ተመሳሳይ ምርት 70 ብር ደርሷል፡፡ በተመሳሳይ ሸኖ ለጋ ቅቤ በ71 ብር በአለ በጅምላ መጋዘኖች ሲሸጥ፣ በገበያ ውስጥ ግን 130 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ አለ በጅምላ ገበያውን ማረጋጋት አልቻለም፡፡

በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት አቶ ኑረዲን፣ ‹‹ይህንን እኛ ብቻ ስላደረግን ገበያውን ማቋቋም አንችልም፡፡ ብዙ ቦታዎች አለ በጅምላን መክፈትና ብዙ ዕቃዎችን በአንድ ጣሪያ መያዝ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት ቀጣይ አማራጭ ብሎ የያዘው አለ በጅምላና ሌሎች የመንግሥት የንግድ ድርጅቶችን ማለትም፣ ኢትፍሩት፣ ጅንአድ፣ የእህል ንግድ ድርጅት የመሳሰሉትን በኮርፖሬሽን አደራጅቶ በአንድ ጥላ ሥር ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ነው ያሉት አቶ ኑረዲን፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ መንግሥት የአለ በጅምላን ኢንቨስትመንት ካፒታል ወደ 500 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የተፈቀደ ካፒታሉን ሁለት ቢሊዮን ብር ሊያደርገው ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በኮርፖሬሽን መደራጀቱ በአንዱ ድርጅት የመሸጫ መደብር የመጠቀም ዕድልን ይሰጣል ብለዋል፡፡

አለ በጅምላን ለሁለት ዓመት ከግማሽ ሲያስተዳድር የቆየው ኤቲ ኪራኒ ኃላፊ ሚስተር ኢማኑኤል ሳቮና ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ፈታኝ ሆኖ ያገኙት የገበያው ተሳታፊዎች ብዛትን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አለ በጅምላ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል በሰው ኃይል ረገድ ሰፊ ሥራ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ ለምሳሌ በመጋዘን አስተዳደር ረገድ ብቁ ባለሙያዎች የሉም ብለው፣ በተጨማሪም የውጭ አቅራቢ ድርጅቶች አለ በጅምላ ላይ እምነት እንዲጥሉ ማድረግ ከባድ እንደነበርና አሁንም ይህ ፈተና ሊቀጥል እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሰጡት ምክንያት ደግሞ በእንደዚህ ዓይነት የጅምላ ንግድ ውስጥ የተሻለ ዋጋ ለማግኘት አለ በጅምላ በሚያነሳው የምርት መጠን መደራደርን ይጠይቃል፡፡ ይህንን በመጠን ከፍተኛ ምርት የማንሳት እምነትን በአቅራቢዎች ላይ መፍጠር ከባድ እንደሆነ፣ ምክንያቱም አለ በጅምላ የሚታወቅ አይደለም ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኤቲ ኪራኒ በኢትዮጵያ ቅርንጫፉን ከፍቶ ሌሎች የማማከር ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ኬቲ ኪራኒ ለሰጠው አገልግሎት የተከፈለውን ለማወቅ አቶ ኑረዲን ቢጠየቁም፣ በመንግሥት የተያዘ ሚስጥር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች