Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊምግብ አምራቾች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች አልሚ ምግቦችን እንዲያመርቱ መመርያ ተሰጠ

ምግብ አምራቾች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች አልሚ ምግቦችን እንዲያመርቱ መመርያ ተሰጠ

ቀን:

– ለ350 ሺሕ ሕፃናትና ነፍሰ ጡሮች 40 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሰባት የምግብ ፋብሪካዎች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በአፋጣኝ አልሚ ምግቦች አምርተው እንዲያቀርቡ መመርያ ተሰጠ፡፡ በኤልኒኖ ክስተት በተፈጠረው ድርቅ 350 ሺሕ ሕፃናትና ነፍሰ ጡር እናቶች የአልሚ ምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል፡፡

የምግብ ፋብሪካዎቹ ለተጎጂዎቹ በአፋጣኝ አልሚ ምግቦች እንዲያመርቱ የማስተባበር ኃላፊነት ለኢትዮጵያ ምግብና መጠጥ ልማት ኢንስቲትዩት ተሰጥቷል፡፡ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች አልሚ ምግብ እንዲያቀርቡ ኃላፊነት ከተሰጣቸው መካከል ፋፋ፣ ጤና ምግብ፣ ጋትስ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ ኑሪሽ፣ ዓባይና ፓካና ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች ያመረቱዋቸው አልሚ ምግቦች በብሔራዊ ደረጃ ድርቁን ለመዋጋት ኃላፊነት ለተሰጠው የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ያስረክባሉ፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የአደጋ መከላከልና ዝግጅነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በድርቅ ከተጎዱት 8.2 ሚሊዮን ዜጎች መካከል 350 ሺሕ ሕፃናትና ነፍሰ ጡር እናቶች ለአልሚ ምግብ እጥረት ተዳርገዋል፡፡

የድርቅ ተጎጂዎች ለመታደግ ከሚያስፈልገው 12 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለአልሚ ምግብ ተጎጂዎች 40 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡ አቶ ምትኩ ጨምረው እንደገለጹት፣ የአልሚ ምግቦች አቅርቦት ከአገር ውስጥ በተጨማሪ የዓለም ምግብ ድርጅት ከውጭ በሚያስገባው ጭምር የሚሸፈን ነው፡፡

በተለይ የአገር ውስጥ ምግብ አምራቾች አልሚ ምግቦች እንዲያመርቱ የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ምግብና መጠጥ ልማት ኢንስትቲዩት ለምርት ሒደት ጠቃሚ ናቸው የተባሉ ግብዓቶች ግዥ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በቅርቡም በ52 ሚሊዮን ብር ወጪ ግብዓቶችን ለመግዛት ተዘጋጅቷል፡፡

የአልሚ ምግቦች እጥረት የገጠማቸው ወገኖች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ታውቋል፡፡ ምክንያቱም የሚቲዎሮሎጂ ትንበያዎች እየጠቆሙ እንደሚገኙት፣ እስከ ታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም. ድረስ የኤልኒኖ ክስተቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

በዚህ መሠረት በአሁኑ ወቅት ካሉት የበለጠ ተረጂዎች ዕርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ አቶ ምትኩ የኤልኒኖ ክስተት ተጠናክሮ በመቀጠሉ፣ የድርቅ ተጎጂዎች ቁጥር አሁን ካለው 8.2 ሚሊዮን ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

“ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየተካሄደ ያለው ቅኝት ባለመጠናቀቁ የተረጂዎች ቁጥርን አሁን ላይ መናገር አይቻልም፤” ብለዋል አቶ ምትኩ፡፡

ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በቅርቡ ባወጣው ትንበያ የተረጂዎች ቁጥር እስከ 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል መግለጹ ይታወሳል፡፡

እስከሚቀጥለው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት መጀመሪያ ድረስ አሁን ባለው የተረጂዎች ቁጥር ልክ ዕርዳታ እንደሚከፋፈል ገልጸው፣ ከዚያ በኋላ ግን ከአንድ ሳምንት በኋላ በሚጠናቀቀው ቅኝት ውጤት መሠረት የተለያዩ ዕቅዶች ይወጣሉ ሲሉ አቶ ምትኩ አስረድተዋል፡፡  

በድርቅ ለተጎዱት ወገኖች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ለማድረስ አሜሪካ በዩኤስኤአይዲ በኩል 97 ሚሊዮን ዶላር የለገሰች ሲሆን፣ እንግሊዝ በበኩሏ የ45 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ ማድረጓ ተገልጿል፡፡ ቻይና ደግሞ 163.13 ሚሊዮን ብር ዕርዳታ ለግሳለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...