የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ምክር ቤት ከማክሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ባደረገው ስብሰባ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሊቀመንበር የሆኑትን ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) የግንባሩ ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ፡፡
ምክር ቤቱ የኢሕአዴግ ሦስተኛውን ሊቀመንበር ከመምረጡ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን የሥራ መልቀቂያ በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡ ከሊቀመንበርነት ምርጫ በፊት ምክር ቤቱ የአራቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶችን የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ሪፖርት አዳምጦ ሰፋ ያለ ውይይት አድርጎበታል፡፡
ከምክር ቤቱ አስቀድሞ በተደረገው የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የአራቱን አባል ድርጅቶች ግምገማ በጥልቀት ገምግሞ ከጨረሰ በኋላ፣ ለምክር ቤቱ የሚያቀርበውን የመወያያ ሰነድ መዘጋጀቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተናግረው ነበር፡፡ በወቅቱ በምክር ቤቱ የጠቅላይ ሚኒስትርና የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መልቀቅ የፈጠረውን የአመራር ክፍተት ለመድፈን፣ የአመራር መተካት እንደሚኖር አመላክተው ነበር፡፡
በኢሕአዴግ የተለምዶ አሠራር የፓርቲው ሊቀመንበር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆን ስለሚታወቅ፣ ተመራጩ ሊቀመንበር በፓርላማ እንደሚሰየም ይጠበቃል፡፡