ፓርላማው ያቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ በኮማንድ ፖስቱ ስለተያዙ ተጠርጣሪዎች ብዛትና የተጠረጠሩበትን ወንጀል አስመልክቶ ይፋዊ መግለጫ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚሰጥ ምንጮች ጠቆሙ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በሚቀጥለው ሳምንት የመጀመርያ ቀናት በሚሰጠው መግለጫ አዋጁን በሚተገብረው ኮማንድ ፖስት ዕዝ ሥር ያሉ የፀጥታ አስከባሪዎች ግዳጃቸውን እየተወጡ ያሉት የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች በማስከበር ስለመሆኑ፣ እስካሁን በቁጥጥር ስለዋሉ ተጠርጣሪዎች ብዛትና የተጠረጠሩባቸው ጥፋቶችን የተመለከተ እንደሚሆን ምንጮች ገልጸዋል።
መርማሪ ቦርዱ ተጠሪነቱ ለፓርላማው መሆኑን የጠቁሙት ምንጮች፣ ቦርዱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት ተቋቁሞ ሥራ በጀመረ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋዊ መግለጫ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት አስረድተዋል።
ከላይ ከተገለጹት የቦርዱ ኃላፊነቶች በተጨማሪ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በዜጎች ላይ ኢሰብዓዊ ጉዳት ማድረሱን በምርመራው ካረጋገጠ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በማሳወቅ እንዲስተካከል ሐሳብ መስጠት እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል።
ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙትን በሙሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግም ሕገ መንግሥቱ ለቦርዱ የሰጠው ኃላፊነት እንደሆነ አስረድተዋል።
መርማሪ ቦርዱ በቅርቡ በሞያሌ የተከሰተውን ቀውስና የተወሰደውን ዕርምጃ ለመመርመር ወደ ሥፍራው የልዑካን ቡድን እንደላከ በእሑድ ዕትም መዘገቡ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ባልታወቀ ምክንያት ይህንን ጉዞውን መርማሪ ቦርዱ ለሌላ ጊዜ ማስተላለፉን ምንጮቹ ተናግረዋል።
በቅርቡ የፀጥታ ኃይሎች በተሳሳተ መረጃ ላይ በመመሥረት በኦሮሚያ ክልል በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ በወሰዱት ዕርምጃ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውና ሌሎች 12 ነዋሪዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን ኮማንድ ፖስቱ መግለጹ ይታወሳል። በዚህ ድርጊት የተደናገጡ በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ ወደ ኬንያ መሰደዳቸውን መዘገቡ አይዘነጋም። ወደ ኬንያ የተሰደዱትን ነዋሪዎች ኮማንድ ፖስቱ በመመለስ ላይ ስለመሆኑ ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።
ዕርምጃውን ወስደዋል የተባሉ የፀጥታ አስከባሪ አካላት ትጥቅ ፈትተው በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ኮማንድ ፖስቱ በወቅቱ የገለጸ ሲሆን፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሆኑት እነዚህ ፀጥታ አስከባሪዎች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የተገናኘ ግዳጅ ላይ እንዳልነበሩም በወቅቱ አስታውቆ ነበር።