Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቅርቡ ከእስር የተፈቱ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በቅርቡ ከእስር የተፈቱ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ቀን:

  • ለመታሰራቸው ምክንያት ሕገወጥ ሰንደቅ ዓላማ መጠቀማቸው ነው ተብሏል
  • በባህር ዳር አዲስ ፓርቲ ለማቋቋም የተሰበሰቡ ግለሰቦች ታሰሩ

እሑድ መጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ 11 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡ የመታሰራቸው ዋና ምክንያት ሕጋዊ ያልሆነ ወይም መሀሉ ላይ ያለውን ዓርማ ያልያዘ ልሙጥ ሰንደቅ ዓላማ ሰቅለው በመገኘታቸው መሆኑን ፖሊስ መናገሩ ታውቋል፡፡

ከጀሞ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አንዱ በሆነው የጋዜጠኛ ተመሥገን ደሳለኝ እናት ቤት ተሰባስበው ለዓመታት በእስር ላይ ስለከረሙበትና ስላሳለፉት ጊዜያት እያወጉና ሻይ እየጠጡ ነበሩ የተባሉት እስክንድር ነጋ፣ ተመሥገን ደሳለኝ፣ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን፣ ጦማሪ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ፣ ወ/ሪት ወይንሸት ሞላ (የሰማያዊ ፓርቲ አባል የነበረች)፣ አቶ ይድነቃቸው አዲስ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ አቶ ተፈራ ተስፋዬና አቶ አዲሱ ጌታነህ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ተሰባስበው በተገኙበት ቤት ዓርማ የሌለበት ሰንደቅ ዓላማ ለምን ተጠቀማችሁ ወይም ሰቀላችሁ ተብለው፣ በአካባቢው በሚገኘውና ሙዚቃ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን ሪፖርተር ከታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ለማወቅ ችሏል፡፡ ታሳሪዎቹ በዕለቱ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በአካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ከቆዩ በኋላ ሌሊቱን ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ተወስደው፣ ከሌሎች እስረኞች ጋር ተደባልቀው እንዲያድሩ መደረጉም ታውቋል፡፡ ሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. 11 ታሳሪዎች ለብቻቸው በመለየት የታሰሩ መሆናቸውንና የበላይ ኃላፊ ትዕዛዝ እየተጠበቀ ሳይፈቱ፣ መቆየታቸው ተረጋግጧል፡፡

ታሳሪዎቹን በፖሊስ መምርያው ተገኝተው ያነጋገሯቸው ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን ለሪፖርተር ስለአያያዛቸው እንደገለጹት፣ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው አነጋግረዋቸዋል፡፡ የጣቢያውንም ኃላፊ አነጋግረው እንደተረዱት፣ የተያዙት በኮማንድ ፖስቱ ነው፡፡ እሳቸው እንደገባቸው ኮማንድ ፖስቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የፖሊስ መዋቅርንም እንደሚጠቀም ነው፡፡ በመሆኑም በፖሊስ የተያዙት በጋዜጠኛ ተመሥገን ደሳለኝ መኖሪያ ቤት ታስረው የተፈቱ ግለሰቦችን ‹‹እንኳን ደስ አላችሁ›› ለማለት በተዘጋጀ ዝግጅት ላይ እያሉ ነው፡፡ በዝግጅቱ ላይ ሌሎችም ታስረው የተፈቱ እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ክንፈ ሚካኤል አበበ (አበበ ቀስቶ)፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ ማሙሸት አማረና ሌሎች እንደነበሩ መስማታቸውን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቶ አመሐ በደረሳቸው መረጃ መሠረት በዝግጅቱ ላይ ስብሰባም ሆነ ምንም ዓይነት አጀንዳ አልነበረም፡፡ እንደ ማንኛውም ማኅበራዊ ስብስብ ከመብላት መጠጣትና በእስር ጊዜ የነበራቸውን ልምድ ከመለዋወጥ ባለፈ ሌላ ነገር እንዳልነበረም ከታሳሪዎቹ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ ስብስቡ መሪም ሆነ አጀንዳ እንዳልነበረውና ምንም የተላለፈ መመርያም ሆነ ሌላ ነገር አለመኖሩን አክለዋል፡፡ በአካባቢው ከሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ አንድ አባል መጥቶ ‹‹ለምን ሕጋዊ ያልሆነ ባንዲራ ተጠቀማችሁ?›› በማለት ወደ ጣቢያ እንደተወሰዱ መረዳታቸውን አቶ አመሐ ገልጸዋል፡፡

ታሳሪዎቹ ለፖሊስ በሰጡት ምላሽ ሰንደቅ ዓላማው በቤት ውስጥ የተሰቀለ እንጂ በአደባባይ ላይ እየተጠቀሙበት አለመሆኑንና ላዘጋጁት ማኅበራዊ ግንኙነት ማድመቂያ እንደተጠቀሙበት መግለጻቸውንም እንደነገሯቸው አቶ አመሐ ገልጸዋል፡፡ የክፍለ ከተማውንም ፖሊስ መምርያ ኮማንደርን አነጋግረዋቸው ከዚህ በኋላ ውሳኔው የኮማንድ ፖስቱ መሆኑን፣ ያልተፈቀደ ስብሰባ ማድረጋቸውንና ሕጋዊ ያልሆነ ሰንደቅ ዓላማ ሰቅለው መገኘታቸውን አጣርተው መጨረሳቸውንም ኃላፊው እንደነገሯቸው አስረድተዋል፡፡ በዚህ ላይ ተመሥርቶ ምን እንደሚወሰንባቸው ገና አለመታወቁንም አክለዋል፡፡ በአጠቃላይ ኃላፊነቱ የኮማንድ ፖስቱ መሆኑንም የመምርያ ኃላፊው መግለጻቸውን አቶ አመሐ ጠቁመዋል፡፡ ከእስር የተፈቱትን ግለሰቦች መልሶ ማሰር መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና አገራዊ መግባባት ለመፍጠር እስረኞችን መፍታቱን የሚያደፈርስ ዕርምጃ ይሆናል የሚል ግምት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ በተያዙበት ቦታ ላይ የተገኙት ሰዎች አንድ የሚያደርጋቸው ታስረው መፈታታቸው ካልሆነ በስተቀር፣ በፖለቲካ አመለካከታቸውም ሆነ በሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም የሚያመሳስላቸው ነገር አለ የሚል እምነት እንደሌላቸውም አቶ አመሐ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ተሰባስበው የነበሩ 19 ያህል ሰዎች መታሰራቸው ተጠቁሟል፡፡ ሪፖርተር ከአካባቢው ነዋሪዎች ባገኘው መረጃ መሠረት ቅዳሜ መጋቢት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቶ ጋሻው መርሻ፣ አቶ የሱፍ ኢብራሒም፣ አቶ ተመስገን ተሰማ (ከወሎ ዩኒቨርሲቲ)፣ አቶ በለጠ ሞላ (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)፣ አቶ ሲሳይ አልታሰብ፣ የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ በለጠ ካሳ፣ አቶ ዳንኤል አበባውና አቶ ንጋቱ አስረስ (የአማራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ) እና ሌሎችም መሆናቸው ታውቋል፡፡ ግለሰቦቹ ባህር ዳር የተገኙት የቅድመ ምሥረታ ጉባዔ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ግለሰቦቹ በባህር ዳር ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ውይይታቸውን አጠናቀው ጣና ዳር ራት ለመብላት ተሰባስበው በነበሩበት ወቅት መሆኑም ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...