Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በሌላ ሥፍራ ማስፈር እንዲቆም መድረክ ጠየቀ

ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በሌላ ሥፍራ ማስፈር እንዲቆም መድረክ ጠየቀ

ቀን:

ለዘመናት ኑሮዋቸውን መሥርተውና ማኅበራዊ ትስስር ፈጥረው ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ተገደው የተፈናቀሉ ዜጎችን መብት በማስከበር መንግሥት ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ማድረግ ሲገባው፣ ተፈናቃዮቹ ወደማያውቋቸው ሩቅ አካባቢዎች ወሰዶ የማስፈር ዕቅድ አንድምታው ለአገሪቱ አንድነትና ለሕዝቡም አብሮነት አደጋ እንዳለው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አስታወቀ፡፡

በተለይም በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል በድንበር ጥያቄ ሰበብ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ካለው አለመስማማት ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ግጭት፣ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በሌሎች ሥፍራዎች መልሰው እንዲቋቋሙ ማድረግ አደጋው ከፍተኛ እንደሆነ መድረክ አስታውቋል፡፡

በየደረጃው በዚህ ጉዳይ እጃቸው ያለበት የፌዴራልና የክልል መንግሥታዊ አካላት በተናጠልም ሆነ በጋራ ተጠያቂዎች እንደሚሆኑና ወደ ሕግ ፊት እንደሚቀርቡ፣ የተፈናቀሉት ዜጎች ደግሞ ቀድሞ ወደነበሩበት ቀዬአቸው እንዲመለሱ ይደረጋል ተብሎ እንደነበር የሚታወስ መሆኑን ጠቁሞ፣ ‹‹ይሁን እንጂ ገዥው ፓርቲና መንግሥት ይኼን የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት ድንጋጌ ለማስከበር ጥረት ሲያደርግ አይታይም፤›› በማለት ፓርቲው ተቋውሞውን አሰምቷል፡፡

ይኼ ዕርምጃ በዚሁ ከቀጠለ ዜጎች በኢትዮጵያዊነት ተከብረው በፈለጉበት ክልል የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እየተጣሰ አገራዊ የአንድነት ግንባታው አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ሥጋቱን የገለጸ ሲሆን፣ ስለሆነም መንግሥት ሕግን በማስከበር የዜጎችን መብት ማስጠበቅና አፈናቃዮችን ወደ ሕግ ፊት በማቅረብ አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት መድረክ አሳስቧል፡፡

ስለሆነም መንግሥት ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውጪ በየክልሉ የተፈናቀሉትን የተሰደዱ ዜጎችን በሌላ አካባቢ አሰፍራለሁ የሚለውን እንቅስቃሴ አቁሞ፣ የደረሰባቸውን በደል ግምት ውስጥ በማስገባት የሚገባቸውን ካሳ ከፍሎ ተፈናቃዮቹን ወደ ነበሩበት ቀዬአቸው መልሶ እንዲያቋቁማቸው፣ በዜጎች ላይ በሰበብ አስባቡ እየተፈጸመ ያለው ሕገወጥ እስራት፣ ማወከብና ግድያ በአስቸኳይ እንዲቆምና በጥፋተኝነት የተጠረጠሩ ዜጎች ጉዳያቸው በሕግ አግባብ እንዲታይ ጥሪ አቅርቧል፡፡

‹‹በአገሪቱ ለተከሰቱ መሠረታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እና መንግሥት ከመድረክና ከሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የውይይትና የድርድር ሒደት በአስቸኳይ እንዲከፍትና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ተካሂዶ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት የሚሆንበት ሁኔታ ይፈጠር፤›› በማለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

መድረክ የአራት ፓርቲዎች ስብስብ ነው፡፡ እነሱም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)፣ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (አረና) እንዲሁም የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...