Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበእስር ላይ የሚገኙት የዋልድባ መነኮሳት ማን እንዳሰራቸው ፍርድ ቤትን ጠየቁ

በእስር ላይ የሚገኙት የዋልድባ መነኮሳት ማን እንዳሰራቸው ፍርድ ቤትን ጠየቁ

ቀን:

  • የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች ለመስማት ድጋሚ ቀጠሮ ተሰጠ

በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ሁለት የዋልድባ መነኮሳት፣ ማን እንዳሰራቸው እንዲገለጽላቸው ለፍርድ ቤት ጥያቄ  አቀረቡ፡፡

ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ጥያቄውን ያቀረቡት፣ አባ ገብረ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖትና አባ ገብረየሱስ ኪዳነ ማርያም ናቸው፡፡ መነኮሳቱ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ‹‹ማነው ያሰረን?›› ጥያቄ ላይ እንደተናገሩት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታኅሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ባሰሙት አዋጅ የተከሰሱበት ጉዳይ ቀርቶ እንዲፈቱ ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡ እነሱም እንደተፈቱ እንደሚታወቅ ጠቁመው ያሰራቸው ማን እንደሆነ እንዲገለጽላቸው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ፍርድ ቤቱ እነሱ ያነሱት የመንግሥት ጉዳይ እንጂ ከተከሰሱበት የክስ መዝገብ ጋር ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽ ንግግራቸውን እንዲያቆሙ ሲያደርጋቸው፣ ‹‹ፍርድ ቤትና መንግሥት ይለያያሉ እንዴ?›› የሚል ጥያቄ በማንሳት፣ ‹‹ማን እንዳሰረን ማወቅ አልቻልንም›› ብለዋል፡፡

በዕለቱ ተቀጥረው የነበረው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን ምስክሮች ለመስማት የነበረ ቢሆንም፣ ምስክሮቹ ባለመቅረባቸው ሳይሰሙ ቀርቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች መቅረብ አለመቅረባቸውን ለማረጋገጥ ለዓቃቤ ሕግ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ ምስክሮቹ አልቀረቡም፡፡ ምስክሮቹን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ የተሰጠው ፖሊስ ምላሽ እንዳልሰጠውም ተናግሯል፡፡ ዓቃቤ ሕግ መከታተልና አለመከታተሉን ፍርድ ቤቱ ጠይቆት ‹‹ተከታትያለሁ›› ብሏል፡፡ ምስክሮቹን ስለመለየትና ስላመለየቱም ተጠይቆ፣ የምስክሮቹ ማንነት ተለይቶ ለፖሊስ እንደተሰጠውም ገልጿል፡፡ በመሆኑም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶት፣ ፖሊስ ለምን እንዳላቀረበ እንዲጠየቅና ምስክሮቹን አፈላልጎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት አመልክቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ተከሳሾቹ መነኮሳት አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው በጠበቃቸው አማካይነት በሰጡት ምላሽ፣ መነኮሳቱ የተከሰሱት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ድንጋጌ ተላልፋችኋል ተብለው ስለሆነ የዋስትና መብታቸውን ተከልክለዋል፡፡ ከታሰሩ አንድ ዓመት ከሦስት ወራት ሆኗቸዋል፡፡ የእነሱን ጉዳይ ለየት የሚያደርገው ደግሞ ‹‹የክስ መቃወሚያ የለንም›› በማለታቸው ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን አቅርቦ እንዲያሰማ ብይን ከተሰጠ የቆየ መሆኑን ጠበቃው አቶ አመሐ መኮንን አስረድተዋል፡፡

ሆኖም ዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎቹን በፍጥነት የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም ለፍርድ ቤት እንኳን ምላሽ መስጠት አለመቻሉን፣ በዚህ ምክንያት ፍትሕ እንደሚጓደል፣ መነኮሳቱም እንደሚጎዱ፣ አብረዋቸው ከታሰሩ 35 ተጠርጣሪዎች መካከል የ32 ክስ ዓቃቤ ሕግ እንዲቋረጥ ማድረጉን፣ መነኮሳቱም በአንድ የክስ መዝገብ ተከሰው እያለ ክሳቸው እንዲቀጥል ማድረግ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 ‹‹ዜጎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤›› ከሚለው ድንጋጌ ጋር የሚጣረስ መሆኑንም ጠበቃው አስረድተዋል፡፡

በዚህ ግብታዊ ውሳኔም ተጎጂ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ የመነኮሳቱ ጠበቃ ከላይ የተገለጸውን አስተያየት ሲሰጡ ፍርድ ቤቱ በመሀል አስቁሞ፣ ‹‹ከፍርድ ቤት ውጪ የተወሰነ ውሳኔ ግብታዊ ይሁን አይሁን ከዚህ መዝገብ ጋር አይገናኝም፡፡ በመሆኑም አስተያየቱም የመዝገቡ አካል አይሆንም፡፡ ተገቢም አይደለም፤›› በማለት የመነኮሳቱ ጠበቃ ያቀረቡት አስተያየት ትክክል አለመሆኑን አስታውቋል፡፡

ጠበቃው ቀጥለው በሰጡት አስተያየት ዓቃቤ ሕግ በተደጋጋሚ በፍርድ ቤቱ የተሰጠውን ትዕዛዝ ሊፈጽም እንዳልቻለ አስረድተው፣ ምስክሮቹን ሊያቀርብ ስላልቻለና ለፍርድ ቤቱም የሰጠው አስተያየት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 94 መሠረት አሳማኝ ባለመሆኑ፣ ምስክሮቹ ታልፈው ባቀረበው የሰነድ ማስረጃ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ብይን እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን አስተያየት ከሰማ በኋላ እንደገለጸው፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ምክንያት ተቀባይነት የለውም፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቆች የሰጡት አስተያየት ተገቢ ቢሆንም፣ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ይረዳ ዘንድ አንድ የመጨረሻ ቀጠሮ መስጠት እንዳለበት አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ ለመጨረሻ ጊዜ ምስክሮቹን እንዲያቀርብ ለሚያዝያ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በዕለቱ በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ከሚገኙት ችሎት ማስቻያ አዳራሾች ትልቁና ‹‹ፍትሕ አዳራሽ›› ተብሎ የሚጠራው አዳራሽ በታዳሚዎች ከመሞላቱም በተጨማሪ ከችሎት ውጪ በርካታ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...

አማርኛ ተናጋሪዋ ሮቦት

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም፣ ሚያዝያ 2 ቀን...

ወዘተ

ገና! ከእናቴ ሆድ ሳለሁ፤ ጠላት ሲዝትብኝ ሰምቻለሁ። በዳዴ ዘመኔም፣ በ'ወፌ ቆመችም!'፤ አውዴ ክፉ ነበር...

የአስፕሪን ታሪክ

በቤት ውስጥ የሚገኝ የመድኃኒት መደርደሪያ፣ ምንም ቢሆን፣ እስፕሪንን ሳይጨመር...